የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገር ውስጥ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ክሪስጀን ኒልሰን ስልጣናቸውን ለቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ እጅግ አወዛጋቢ የሆኑትን የፕሬዚዳንቱን የኢምግሬሽን ፖሊሲዎችና ሕግጋት በበላይነት ሲመሩና ሲቆጣጠሩ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ የሚኒስትሯ ኃላፊነት መልቀቅ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢምግሬሽን ፖሊሲዎችንና ሕግጋትን የበለጠ ጥብቅ ለማድረግ የጀመሩት ጉዞ አካል ነው ተብሏል፡፡ አንድ ስማቸው ያልተገለጸ ባለስልጣን እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ የደቡባዊ ድንበር በኩል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ያበሳጫቸው ትራምፕ ሚኒስትሯ ስልጣናቸውን እንዲለቅቁ ጠይቀዋቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደተለመደው በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ሚኒስትር ኒልሰን ከኃላፊነቷ ለቅቃለች፡፡ ለእስከአሁኑ አገልግሎቷ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ” ብለዋል፡፡ የአሜሪካ የጉምሩክና የድንበር ቁጥጥር ኮሚሽነር ኬቪን ማካሌናንም ኒልሰንን ይተካሉ ተብሏል፡፡
ክሪስጀን ኒልሰን የፕሬዚዳንት ትራምፕ የአገር ውስጥ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው በቆዩባቸው 18 ወራት ሕፃናትን ከወላጆቻቸው ይለያያል በተባለው አወዛጋቢ ፖሊሲ ምክንያት ስማቸው ሲብጠለጠል ቆይቷል፡፡ ስልጣናቸውን እንዲለቅቁም ከመብት ተሟጋች ቡድኖችና ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ተደጋጋሚ ጫና ሲደረግባቸው ነበር፡፡
የመንግሥትን ሹመቶች በተመለከተ ትንተናዎችን የሚያቀርበውና “ሪቮልቪንግ ዶር ፕሮጀክት” (Revolving Door Project) በመባል የሚታወቀው ተቋም መስራችና ዳይሬክተር ጄፍ ሃውዘር፤ ሚኒስትሯ ከስልጣን የለቀቁት በፕሬዚዳንት ትራምፕ ጫና እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፕሬዚዳንቱ እንደተለመደው ያልተረጋጋ የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጡ በመሆናቸው ሚኒስትሯ ኃላፊነታቸውን እንዲለቅቁ ጫና አድርገውባቸዋል፡፡
የሚኒስትሯ ውሳኔ የተሰማው ፕሬዚዳንቱና ሚኒስትሯ በጋራ በመሆን አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ ጉብኝት ካደረጉ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸውና ጥገኝነት ለጠየቁ የሌሎች አገራት ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት “አሜሪካ ሙሉ ስለሆነች ሌሎች ዜጎችን ማስተናገድ አትችልም” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም ኮንግረሱና ማዕከላዊ መንግሥቱ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ስደተኞች ለመግታት የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድ ካልቻሉ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር እንደሚዘጉት ዝተዋል። ይህም ሚኒስትሯ ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡
በጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ መምህርና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ቢል ሽናይደር፤ የኒልሰን ከስልጣን መልቀቅ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን የኢምግሬሽን ፖሊሲዎችንና ሕግጋትን የበለጠ ጥብቅ ለማድረግ የጀመሩት ጉዞ አካል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ደጋፊዎቻቸውን ማስቀየም ስለማይፈልጉና በአሁኑ ወቅት ያለው የሕገ ወጥ ስደት ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከነበረበት ወቅት የከፋ በመሆኑ የአሜሪካን የኢምግሬሽን ፖሊሲዎችንና ሕግጋትን የበለጠ ጥብቅ በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያመኑበትን ዕርምጃ መውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ሚኒስትሯ ከኃላፊነት መነሳት እንዳለባት ያምናሉ” ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ ሚኒስትሯ ተጨማሪ የጥገኝት ጥያቄዎችን እንዳይቀበሉ ፕሬዚዳንቱ ይወተውቷቸው እንደነበር፤ እንዲሁም፤ ፕሬዚዳንቱ የሚያቀርቡላቸውን ሃሳቦች ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ስለመቅረታቸውም ሽናይደር ይጠቁማሉ፡፡
የ46 ዓመቷ ክሪስጀን ኒልሰን እ.ኤ.አ ከታኅሳሥ 2017 ጀምሮ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገር ውስጥ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ፕሬዚዳንቱ በሴትየዋ ብቃት ላይ ተደጋገሚ ትችት ሲሰነዝሩ ቢቆዩም ኒልሰን ግን ለፕሬዚዳንቱ ታማኝ ሰው ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል፤ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ወር በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ እገነባዋለሁ ብለው ላይ ታች ለሚሉለት ግንብ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ያስችላል የተባለ ብሄራዊ አዋጅ ሲያውጁ ኒልሰን ድጋፋቸውን አልነፈጓቸውም፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለስለጣኖቻቸው ከኃላፊነታቸው ለቅቀዋል፤ ተሰናብተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰንን ጨምሮ ከዋይት ሐውስ (The White House) እንዲሁም ከሌሎች መስሪያ ቤቶች የለቀቁትና የተሰናበቱት የሥራ ኃላፊዎች ጉዳይ የፕሬዚዳንቱ አስተዳደር በየጊዜው መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህ ረገድ፤ ቶም ፕራይስ ከጤናና ሰብዓዊ አገልግሎት ሚኒስትርነት፤ ጀምስ ኮሜይ ከፌደራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተርነት፤ ኒኪ ሃሌይ ከመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደርነት፤ ኤድዋርድ ስኮት ፕሩይት ከአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ዳይሬክተርነት፤ ሌተናል ጀኔራል ኸርበርት ሬይሞንድ ማክማስተር ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪነት፤ አንድሪው ማካቤ ከፌደራል ምርመራ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተርነት፤ ስቲቭ ባነን ከስትራቴጂ አማካሪነት፤ ሌተናል ጀኔራል ማይክል ፍሊን ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪነት፤ ሬይንስ ፒየርበስ ከዋይት ሐውስ ዋና አዛዥነት፤ ሳሊ የትስ ከጊዜያዊ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግነት፤ አንቶኒ ስካራሙቺ ከዋይት ሐውስ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርነት፤ ሾን ስፓይሰር ከዋይት ሐውስ የፕሬስ አታሼነት፤ እንዲሁም ጌሪ ኮህን ከምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አማካሪነት ለቅቀዋል፤ ተሰናብተዋል፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪም ኃላፊነታቸውን የለቀቁና የተሰናበቱ ሌሎች በርካታ ሰዎች እንዳሉ የመገናኛ ብዙኃን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ባለፈው ጥቅምት በተካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ፤ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ (Republican Party) በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በዴሞክራቶች ብልጫ ተወስዶበታል፡፡ ይህም ፕሬዚዳንቱ ውሳኔዎችን እንደፈለጉ እንዲያሳልፉ ዕድል አይሰጣቸውም፡፡ የአስተዳደራቸው መለያ የሚመስለው የከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ስንብት በዚህ ላይ ሲጨመርበት ደግሞ እ.ኤ.አ በ2020 በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ስኬታማ ላይሆኑ እንደሚችሉ ግምቶች እየተሰጡ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በአንተነህ ቸሬ