አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ልበ ቀናዎችን ትፈልጋለች:: ልብ ስላችሁ ደረታችን ስር ያለውን ማለቴ አይደለም ቀናውን የሚያይ ልብ እንጂ:: ልብ የርህራሄ ምልክት ነው:: ልብ የእውነትና የፍቅር ማደሪያ ነው:: ልብ ከአእምሮ የላቀ የፍቅር ስፍራ ነው:: ልብ በፍቅር፣ አእምሮ በሀሳብ እስካልተሞሉ ድረስ አገር ታታሪ ነፍሶች አይበቅልባትም:: አእምሮና ልብ ድርና ማግ ናቸው:: ልብ ማፍቀር ሲሳነው አእምሮ ማሰብ ያቆማል:: ልብ ጥላቻን ሲማር አእምሮ ክፉ ሀሳብን ይማራል:: እኛ የልብና የአእምሯችን ጥንስሶች ነን::
በነዚህ ሁለት ኃይሎች ተሠርተን ነው ሰው የሆንነው:: ይህን ሰውነታቸውን ለአገራቸው ገብረው ታረክ የጻፉ አያሌ ነፍሶችም በዙሪያችን አሉ:: በዚያው ልክ ደግሞ ከእውነትና ከሰውነት ሸሽተው ልባቸውን የክፋት ማደሪያ ያደረጉም አይጠፉም:: እኛስ ምን ዓይነት ነን? በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ ምንድነው ያለው? አገራችን የምትፈልገን ነን ወይስ ሌላ ነን? እኒህን ጥያቄዎች ለመጠየቅ ወቅቱ አሁን እንደሆነ ይሰማኛል።
በአእምሯችን ክፉ ሀሳብ፣ እጆቻችን ነውር የሚሠሩ፣ ልባችን ክፉ ምኞት፤ እግሮቻችን ወደ ክፉ የሚሮጡ፣ አንደበቶቻችን መጥፎ የሚናገሩ፣ ከሆነ ገና ተሠርተን አላለቅንም:: ገና ወደ ሰውነታችን አልተመለስንም:: አይደለም ለአገራችን ለራሳችንም ያልበቃን የዋሀን ነን ። ፈርሰን መሠራት ይኖርብናል::
አገር የዜጎች እጅ ሥራ ናት:: አንድ ጥበበኛ ሰዐሊ እውቀቱንና ምናቡን ተጠቅሞ አንድ ውብ ስዕል እንደሚሠራ ሁሉ አገርን ውብ አድርገው የሚሠሩ ዜጎች፤ እኛ ነን:: አገራችንን እንደምንፈልገው አድርገን ለመሥራት መዶሻውም ሚስማሩም እኛው ጋ ነው:: መዶሻና ሚሰማራችን ሀሳብና እውቀት፣ ፍቅርና አንድነት ናቸው:: መዶሻና ሚስማራችን ይቅርታና ወንድማማችነት ናቸው:: መዶሻና ሚስማራችን ትህትናና እግዚአብሔርን መፍራት ናቸው::
ብዙ ዓይነት መዶሻና ሚስማር እያለን በኅብረት የተሻለ ቤት መሥራት ሳናውቅበት ቀርተናል:: አሁን ግን ጊዜው ቤት የመሥራት ነው:: አሁን ጊዜው ለሁላችን የምትበቃን ኢትዮጵያን አምጦ የመውለጃ ነው:: አሁን ጊዜው የመተቃቀፍ ነው:: በመነቋቆር የብቻ ቤት የምንሠራበት ሳይሆን በመነጋገር የጋራ ቤት የምናበጅበት ነው::
ለትውልድ የሚተላለፉ አእምሮና ልብ ያስፈልጉናል፡ እውነት የተጻፈባቸው፣ ፍትህ የደመቀባቸው የሰውነት ብራናዎች ያስፈልጉናል:: ፍቅርን የሚሰብኩ፣ መቻቻልን የሚዘምሩ አንደበቶች ያስፈልጉናል:: ነውርን የሚጸየፉ፣ ጨዋነትን የሚናገሩ አንደበቶች ግድ ይሉናል::
በደልን የማይቆጥሩ ይቅር የሚሉ ልቦች ያሹናል:: በእውቀት የሚራመድ፣ በምክንያት ከፍ የሚል አእምሮ ያስፈልገናል:: ይቅር ለእግዜርን የሚያውቁ አስታራቂ ሽማግሌዎች ማብዛት ይጠበቅብናል::
አገር በአእምሮ ተጠንስሳ፣ በልብ የምትፈጠር፣ በተግባር የምትጸና የሁላችን የቤት ሥራ እንደመሆኗ፤ በዚህ መነሻና መድረሻ ውስጥ አገርን ከነሙሉ ክብሯና፣ ነፃነቷ ጋር የሚፈጥሩልን በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ ያስቀመጥናቸው በጎ መንፈሶች ያስፈልጉናል:: በጎ መንፈስ ሁልጊዜም የበጎ አእምሮና ልብ ነጸብራቅ ነው::
ሰው ለራሱ በጎ ሲሆን በዙሪያው ላሉ ሁሉ በጎ ይሆናል:: በጎ መሆን ማለት ራስን ወዶ ሌሎችን መውደድ ማለት ነው:: በጎ መሆን ማለት ራስን አፍቅሮ ሌሎችን ማፍቀር ማለት ነው:: በጎ መሆን ማለት ራስን አክብሮ ሌሎችን ማክበር ማለት ነው:: በዚህ ሁሉ የጋራ በጎነት ውስጥ አገር ነው የምንፈጥረው:: ትውልድ ነው የምንቀርጸው::
ልብ እንዲወድ፣ እንዲምር፣ ቸርነትን እንዲያደርግ የተፈጠረ ነው:: ልብ ለሌሎች ደስታ እንዲሆን፣ ለሌሎች በረከት እንዲሆን የተሠራ ነው:: በዚያው ልክ ደግሞ በጎ ማሰብና በጎ ማድረግ ተስኗቸው ራሳቸውን በመርዘኛ ሀሳብ መርዘው ሰውነታቸውን አውሬ ያደረጉ አሉ:: ሰው ፍቅርን ካልተማረ በራሱ ላይም በሌሎች ላይም አውሬ መሆን ይችላል::
ሰው አውሬ ሲሆን ጥፋቱ ብዙ ነው:: ሰው አውሬ ሲሆን ፍቅር ምን እንደሆነ አያውቅም:: ኃይሉ ጥላቻና በቀል ይሆናል:: ማሸነፊያው እልህና ማንአለብኝነት ይሆናል:: ሰው አውሬ ሲሆን ሌሎችን ለማሸነፍ የሚሮጠው በኃይልና በጉልበቱ ይሆናል:: ሰው አውሬ ሲሆን እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ውስጥ ይቆማል:: እኛ ምርጫችንን ነን:: እኛ ራሳችንን ያደረግነውን ነን:: በሀሳባችንና በድርጊታችን አውሬም ሰውም መሆን ይቻለናል::
አሁን አገራችንን እያሰቃየናት ያለው በልባችን ውስጥ ያጨቅናቸው ክፉ ሀሳቦች ናቸው ነው:: በመልካም ልብ ፍቅርን አውርተን፣ ፍቅርን ተናግረን ሰው መሆን ለምን ተሳነን? በክፉ ሀሳባችን ራሳችንን አውሬ ለማድረግ ሳይሆን ለማፍቀር ነው የተፈጠርነው:: በዙሪያችን ያሉትን ለማቀፍ ነው ሰው የሆንነው:: በፍቅር ጽዋ እንሙላ፤ በእውነት ጸጋ እንትረፍረፍ::
የአገር ስቃይ የትውልድ ስቃይ ነው:: የአገር ስቃይ የዜጎች ስቃይ ነው:: አገራችን ኢትዮጵያ ለነፍሳቸው ኩነኔን፣ ለልባቸው ሀጢዐትን፣ ለሰውነታቸው አረመኔነትን ባስተማሩ ነፍሶች ብዙ ዋጋ ከፍላለች። ለእኛ ግን ፍቅራችን ያለው መቻቻል ውስጥ ነው:: ደም ባልነኩ፣ ጥላቻ ባላስነወራቸው ጸዐዳ ጣቶቻችን ልቦቻችን ላይ ወንድማማችነትን እንጻፍ::
ይሄ የታሪክ ድርሳን በልጆቻችን እየተገለጠ ሲነበብ የት ቦታ ምን እየሠራን እንደነበር አስረጂ ይሆናል:: ምን ያክል ጥያቄ፣ ምንም ያክል ቅሬታ ቢኖርብንም በፍቅር መድረክ ላይ በመልካም አንደበት መነጋገር እንችላለን:: ልቦቻችንን ለፍቅር እንግለጥ:: ለአንድነት እንክፈት::
የተገለጡ ልቦች….
የተገለጡ ልቦች..ክፉ ሀሳቦችን፣ ክፉ ምኞቶችን፣ ክፉ ተግባራትን ማንበርከኪያ ጥበቦች ናቸው:: የተገለጡ ልቦች ክፉ ሰውነትን፣ እኩይ ስብዕናዎችን መርቻ መንገዶች ናቸው:: አገራችን ከትናንት እስከዛሬ በዚህ ግልጽ ማንነት ጠላቶቿን ስታንበረክክ ኖራለች፤ አሁንም በነዚሁ መንገዶች ታሸንፋለች::
ነፍሶች ስውር ሀቃቸውን የሚገልጡት በአገር ነው፣ ልብ የነፃነት ድሉን የሚቀዳጀው ከወገኑ አጠገብ ሲቆም ነው:: ያለ አገርና ሕዝብ ሰውነት ምንም ነው:: ይሄ ሊገባን ይገባል:: የልብ መገለጥ ለአገር ጥሪ፣ ለወገን መከራ ምላሽ መስጠት ነው::
ልብ ስለ አገር ሲያዜም ደስ፤ ቀልብ በእናት አገር ላይ ሲያርፍ ደስ ይላል:: የሁሉም የሰው ልጅ የነፍሱ ማረፊያ አገርና ሕዝብ ነው:: በበጎ ሀሳባችን ተገልጠን ሰላም ላጣችው አገራችን ሰላም እንሁናት:: የተገለጡ ልቦች ነውር አያውቁም፣ ለወገን የተገለጡ ልቦች ፍትህ አያጓድሉም::
ለኢትዮጵያ መገለጥ ስቃይዋን መሰቃየት፣ ችግሯን መቸገር ነው:: ለኢትዮጵያ መሰቃየት በደስታዋ መደሰት፣ በትንሳኤዋ እልልታ ማሰማት ነው:: ዳር ቆሞ ማጨብጨብ፣ ወደነፈሰበት መንፈስ ለኢትዮጵያ መገለጥ አይደለም:: ለአገር በመኖር ውስጥ ያለውን ክብር፣ ለወገን በመቆም ውስጥ ያለውን ፍሰሀ ልባችንን ገልጠን እንመልከት:: በምንም የማይገኙ ትላልቅ ደስታዎች በዚህ እውነታ ውስጥ የተደበቁ ናቸው::
በምንም የማይተኩ የነፍስ ፈንጠዝያዎች በልብ መገለጥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው:: የአገር መገለጥ የትውልድ መገለጥ ነው:: የአገር መነሳት የእኔና የእናንተ ብርሃናዊ ነገ ነው:: ይሄ ሁሉ እንዲሆን ግን ከሁሉ በፊት እኛ ስለአገራችን ልቦቻችንን መግለጥ ይኖርብናል:: ስለኢትዮጵያ ክፉ አላይም፣ ክፉ አልሰማም፣ ክፉም አልናገርም ስንል ልባችንን በክፉዎች ላይ ማጽናት ይኖርብናል::
አገር ስትታመም ስትስቃ የሚታመሙትና የሚሰቃዩት ሕዝቦቿ ናቸው:: እኛ የአገር ደስታ ማረፊያዎች ነን:: መገፋፋት ያበላሸውን ኢትዮጵያዊነት ማደስ ይኖርብናል:: ጥላቻ የመረዘውን ታሪካችንን ማስተው:: እኛ ለአገራችን ስር ግንድና ቅርንጫፎች ነን:: አገራችንን ዋርካ የምናደርጋት እኛ ነን::
የምዕራባውያኑን የተንኮል ሩጫ ጥሰን፣ የብሔር ካባ የለበሰ ፖለቲካችንን አስተካክለን፣ ወንድማማችነትን አግንነን፣ በተባበረ ክንድ የጋራ ቤታችንን መሥራት ይኖርብናል:: ስለ አገራችን ልባችንን እንግለጥና በአገራችን በኩል ለራሳችን እንኑር:: ለአገር መልፋት ለራስ መልፋት ነውና:: ለአገር መድከም ለራስ መድከም ነውና::
ለአገራችን የምንሰስተው አንዳች ነገር ሊኖር አይገባም:: ራስን ለአገር እንደመስጠት ያለ ስጦታ የለም:: አገር አርነት የምትወጣው ራሳችንን ስንሰጥ ነው:: ራሳችንን ሰስተን የምንፈጥረው አገርና ሕዝብ የለም:: በሀሳብና በምክክር እስካልተወጣነው ድረስ የአገራችን አሁናዊ ችግር ዳር ቆመን የምንወጣው አይደለም:: ልብን ለአገር መግለጥ ያስፈልጋል::
ራሳችንን ለአገራችን እንስጥ …ራስን ለአገር መስጠት ራስን ከባዕድ አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት ነው:: አሁናዊ ችግሮቻችን እልባት የሚያገኙት ራሳችንን ለውይይትና ለአንድነት ስንገልጥ ነው:: የተገለጠ ልብ የአንድነት ክንድ ነው:: የተገለጠ ልብ አገሬን ለማንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ወኔ የነቀነቀው ነው:: ልባችንን በመግለጥ መርህ ወደፊት ልንሄድ ይገባል::
ከመቼውም ጊዜ በላይ ልባችንን የምንገልጥበት ጊዜ ላይ ነን:: ከገንዘባችን፣ ከእውቀታችን፣ ከጊዜአችን ለአገራችን የምናዋጣበት ጊዜ ላይ ነን:: ያለንን ሁሉ እየሰጠን አገራችንን ወደ ፊት የምናራምድበት ሰሞን ላይ ነን:: አላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሰራዊት በአንድ ልብ የምንቆምበት የፈተና ጊዜ ላይ ነን:: በእኛ የአንድነት ግፊት ከፊታችን ያለውን ዳገት ሰላምን ምርኩዝ አድርገን እንሻገር::
ጦርና ጎራዴ ሳንመዝ በተከፈተ ልብ ብቻ ወደረኞቻችንን መርታት እንችላለን:: አገራችንን የምናፈቅር ከሆነ ልባችንን እንክፈትላት:: የመለያየት ጉድፋችንን እያጸዳን ከሰላም ውጪ ምንም አማራጭ እንዳይኖረን ሆነን እንኑር:: ሕዝባችን በሚፈልገን ቦታ ላይ ሁሉ እንገኝ:: ኢትዮጵያ በምትፈልገን ስፍራ ላይ ሁሉ መቆም ግዴታችን ነው:: በዚህ የአብሮነት መንፈስ ውስጥ የምትፈጠረውን ኢትዮጵያ ሁላችንም እንናፍቅ::
ትላልቅ አገራት በትላልቅ ሀሳብ የተፈጠሩ ናቸው:: ዘመናዊና ስልጡን ሕዝቦች በዘመናዊና ተራማጅ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ናቸው:: እኚህ ሁሉ ስፍራቸው ክፍት አእምሮና ልብ ነው:: ክፍት አእምሮና ልብ የዘመናዊነት መፈጠሪያ ቦታ ነው::
ሰው ሌሎችን ለመፍጠር ከመሞከሩ በፊት መጀመሪያ ራሱን በበጎ ሀሳብ መፍጠር አለበት:: ራሳችንን በበጎ ሀሳብ መፍጠር ከቻልን በጎ ቤተሰብ፣ በጎ ጓደኛ መፍጠር አያቅተንም:: በጎ ቤተሰብ ደግሞ የበጎ ማህበረሰብ መነሻ ነው:: በጎ ማህበረሰብ ደግሞ አገር ነው:: በአሁኑ ሰዓት አገራችን የሚያስፈልጋት በጎ ሀሳብ ብቻ ነው:: የበጎ ሀሳብ መብቀያ ማሳ ደግሞ በጎ ልብ ነው:: በበጎ ልብ አገራችንን እናብቀል ! አበቃሁ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/ 2015 ዓ.ም