ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ያጣችበትን የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት እያሰበች ትገኛለች:: የመታሰቢያ ዝግጅቱም ለ100 ቀናት ያህል ይቆያል ተብሏል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ባለፈው ዕሁድ ኪጋሊ ከተማ በሚገኘው የዘር ጭፍጨፋው ሰለባዎች መታሰቢያ ማዕከል (The Kigali Genocide Memorial Centre) ተገኝተው ለ100 ቀናት ያህል የሚቆየው የመታሰቢያ ዝግጅት መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ የፍርሐትና የብስጭት ጊዜያት በተስፋና በዓላማ እንደተተኩ ተናግረዋል፡፡ “ሩዋንዳውያን እርስ በእርሳቸው እንዲጠፋፉ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ሩዋንዳ የትናንቱን ስህተት በፍጹም አትደግመውም፤ ይህ መቼውንም ቢሆን የማይዛነፍ ዓላማችን ነው” ብለዋል፡፡
በዕሁዱ ዝግጅት ላይ ከታደሙ መሪዎች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ሩዋንዳውያን የዘር ጭፍጨፋውን በይቅርታ በመሻገር ያሳዩት የዕድገት ግስጋሴ ለመላው ዓለም አርአያ የሆነ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ጂያን ክላውድ ጀንከር በበኩላቸው፤ ነገን የተሻለ ማድረግ የሚቻለው በታሪክ አጋጣሚ የተፈፀሙ መልካም ያልሆኑ ድርጊቶችን በማስታወስ በይቅርታ በመሻገር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዕሁድ ዕለት ኪጋሊ ከተማ በሚገኘው የዘር ጭፍጨፋው ሰለባዎች መታሰቢያ ማዕከል በነበረው ዝግጅት ላይ የአገራትንና የዓለም አቀፍ ተቋማትን መሪዎች ጨምሮ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በማዕከሉ ከነበረው ዝግጅት በተጨማሪ ከአገሪቱ ፓርላማ እስከ አማሆሮ ስታዲየም ድረስ የመታሰቢያ የእግር ጉዞ ተከናውኗል፡፡
በኪጋሊ ከተማ የሚገኘው የዘር ጭፍጨፋው ሰለባዎች መታሰቢያ ማዕከል 250 ሺህ የሚሆኑ የጥቃቱ ሰላባዎች አፅም ያረፈበት ቦታ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2017 ከ96 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ተጎብኝቷል፡፡ ለ100 ቀናት ያህል ይቆያል የተባለው የመታሰቢያ ዝግጅት፤ እ.ኤ.አ ከሚያዝያ መጀመሪያ እስከ ሐምሌ አጋማሽ 1994 ለሦስት ወራት ከግማሽ ያህል የቆየውን አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ በተለያዩ ዝግጅቶች የመዘከር ዓላማ እንዳለው ተገልጿል፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 6 ቀን 1994 በጊዜው የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ጁቬናል ሃብያሪማናንና የቡሩንዲውን አቻቸውን ሲፕሬን ንታርያሚራን የያዘ አውሮፕላን ተመትቶ ሁለቱን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ በአውሮፕላኑ ውስጥ የተሳፈሩት ሁሉም ሰዎች አለቁ፡፡ ፕሬዚዳንት ሃብያሪማና የሁቱ ጎሳ ተወላጅ መሆናቸው በወቅቱ ስልጣን ይዘው የነበሩት ሁቱዎች ለረጅም ዓመታት በሩዋንዳ የመንግሥትን ስልጣን ይዘው በቆዩት ቱትሲዎች ተበድለናል ከሚለው እሳቤ ጋር ተደምሮ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲዘምቱ አደረጋቸው፡፡ በ100 ቀናት የማጥቃት እንቅስቃሴም ከ800 ሺህ በላይ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ተገደሉ፡፡
በወቅቱ የመንግሥት ስልጣን በተነጠቁት ቱትሲዎች እና ስልጣን በጨበጡት ሁቱዎች መካከል የእርስ በእርስ ጦርነት እየተደረገ ነበር:: የሁቱ ፖለቲከኞች ለአውሮፕላኑ አደጋ “የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር” (Rwandan Patriotic Front – RPF) በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀስ የነበረውና በአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ይመራ የነበረውን ቱትሲ መራሹን የአማጺያን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ የካጋሜው “የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር” በበኩሉ “ሁለቱን ፕሬዚዳንቶች የያዘው አውሮፕላን ተመትቶ እንዲወድቅ የተደረገው የሁቱ ፖለቲከኞች ባቀነባበሩት ሴራ ሲሆን፤ አደጋውም ሁቱዎች ቱትሲዎችን ለመጨፍጨፍ ቀድመው ያዘጋጁት ምክንያት ነው” በማለት ዛሬም ድረስ ይሞግታል፡፡ የአደጋውን ምክንያቶች ለማጣራት የተካሄዱ ምርመራዎችም ሁለቱን ፕሬዚዳንቶች የያዘውን አውሮፕላን መትተው የጣሉት እነማን እንደሆኑና ከድርጊቱ ጀርባም የትኛው ወገን እንደነበረ መለየት አልቻሉም፡፡
800 ሺህ ዜጎቿን በአስከፊው የዘር ጭፍጨፋ ያጣችው ሩዋንዳ አስቀያሚው ድርጊት የጣለባትን ጠባሳ ተሻግራ በልማትና በዕድገት ለሌሎች የዓለም አገራት ተምሳሌት መሆኗ በተደጋጋሚ አስመስግኗታል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በአንተነህ ቸሬ