ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ በአርባ ምንጭ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ እያሉ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ “… አሁንም ለሰላም ላባችንን ብናፈስስ፣ በጦርነት የወደሙብንን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ካለን ላይ ብናዋጣ እናተርፋለን እንጂ አንጎዳም :: በሙሉ ልብ ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ ለመገንባት ወደቀደመው የአገር ስሜት ለመመለስ አብረን እንድንቆም በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ ፤ …” ብለዋል ::
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ማለትም ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በኋላ ጀግናው የመከላካያ ሠራዊት ትግራይን መሉ በሙሉ በተቆጣጠረበትና ጊዜያዊ አስተዳደር በተቋቋመበት ለክልሉ መልሶ ማቋቋም ቀድመው የደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነበሩ :: ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጸሐፋቸው ሽያጭ 200 ሺ ብር ከአንድ ወር ደሞዛቸው ጋር እንዲሁም ሦስት ቦቲ መኪናዎችን ለንጹህ መጠጥ ውሃ ማመላለሻ ለግሰዋል ::
የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ለመልሶ ግንባታ ከ100 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል :: የኦሮሚያ ፣ የጋምቤላ ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 282 ሚሊዮን ብር መቐሌ በመገኘት በመለገስ አለኝታነቸውን አረጋግጠዋል: የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተለይ ለትምህርት ዘርፉ መልሶ ግንባታ 320 ሚሊዮን ብር በጀት አዙሮ እየሰራ ነበር::
ከዚያ በፊት የአፋርና ሌሎች ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የተለያዩ ተቋማት ለትግራይ ሕዝብ የገንዘብና የተለያዩ የዕለት ደራሽ ድጋፎችን አድርገዋል :: የፌደራል መንግሥት ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወገኖች እርዳታ ያቀረበ ሲሆን ዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የጩኸታቸውን ያህል ባይሆንም መጠነኛ ድጋፍ ማድረጋቸው አይረሳም ::
ይህ አኩሪ የተቀናጀ ርብርብ ዜጎችን ከርሀብና ከጠኔ ከመታደጉ ባሻገር የትግራይ ሕዝብ በክፉ ቀኑ የሚደርስለት አለኝታ መንግሥትና ወገን እንዳለው ያረጋገጠ ነበር:: እጣ ፈንታውና መጻኢ እድሉ ከኢትዮጵያ ጋር መሆኑንም ያስመሰከረ ሰናይ ተግባር ነበር:: ጥምር ኃይሉ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎችም ሆነ በቀጣይ ሕዝቡን አቅርቦ ማወያየትና የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎኑ እንዳለ ማሳየትም ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው::
ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ ንግግር በሰላም ለመቋጨት ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነቱ አውደ ውጊያ ግን ለጊዜውም ቢሆን እንደ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ በውሸት ትርክታችንን ተነጥቀናል :: ይህ ንጥቂያ የትግራዋይን ልብም እንዳያሳጣን በችግሩና በመከራው ከጎኑ መሆናችንን ደግመን ደጋግመን ማረጋገጥ አለብን :: የትግራዋይን አእምሮና ልቦና በፍቅር ፣ ያለንን በማካፈል በማጽናናትና ፍቅር በመስጠት መማረክ ይጠበቅብናል ::
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ መሪነት ከመጡበት ሰዓት አንስቶ በትግራይ ክልል ይህ ቀውስ እንዳይቀሰቀስ ሕወሓትን ለማግባባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም :: ያላደረጉት ጥረት የለም :: እውነት ለመናገር የሰላምን ውድ ዋጋ እንደ አሳቸው አበክሮ የተረዳ አልነበረም:: ከባዕለ ሲመታቸው የፓርላማ የመጀመሪያ ንግግር እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ድረስ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም ::
በዚሁ ቀን ምሽት ከዛን ጊዜው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር በስልክ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ስለተያዙ እቅዶች ከተወያዩ በኋላ አዲሱን የብር ኖት ለማድረስና አሮጌውን ብር ለማምጣት ሁለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ምሽት መቀሌ አርፈው ነበር::
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለሰላም ካላቸው ቁርጠኝነትና ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በውትድርና ሕይወታቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ፤ ጓደኞቻቸውንና ወንድማቸውን ስለነጠቃቸው ፤ ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ ምን ያህል እምሽክ ድቅቅ እንደሚያደርግና እንደሚያወድም አበክረው ስለተገነዘቡና ፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ይበቃዋል በሚል እምነትና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች የድሀን ልጅ የእሳት ራት ያደርጋሉ እንጂ እነሱ አይዋጉም በማለት ለትግራይም ሆነ ለሌሎች ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ እስከ መጨረሻው ሰዓት ሆደ ሰፊነትንና ትዕግስትን መርጠዋል ::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት መች በዚህ ያበቃል :: አይደለም ጦርነትን ተራ ግጭት እንኳ ለመከላከል ሲሉ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረው የነበሩ ተቃዋሚዎችንና አክቲቪስቶችን ከዛሬ ነገ ይለወጣሉ ፣ ይመከራሉ ፣ ይዘከራሉ ሲሉ በሆደ ሰፊነትና አንዳንድ ጊዜም አይተው እንዳላዩ በማለፋቸው መንግሥታቸው እንደደካማ በመታየቱ በአውሮፕላንና በአውቶብስ የገባው ኦነግ ሳይቀር “ ማን የማንን ትጥቅ ያስፈታል !? “ እስከሚል እብሪት ደርሶ ነበር ::
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገሪቱን ከጠብ መንጃ አዙሪት ለማውጣትና ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች ያልሄዱበትን የሆደ ሰፊነትና ቁጭ ብሎ የመነጋገር መንገድ በመምረጣቸው በልኩ እውቅና ሊሰጣቸውና አብዛኛው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ሲገባ መንግሥታቸው በልፍስፍስነት ከመወቀሱ ባሻገር ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ደጋፊያቸውና ተከታያቸው ብዥታና ድንጋሬ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል::
የሀገራችንን ፖለቲካና ታሪክ እንደ አዲስ የሚበይን ፤ የሀገሪቱን ህልውና በጽኑ መሰረት ላይ የሚያኖር እና መጻኢ እድሏን ወገግ የሚያደርገው ይህ የሰላም ድል የተመዘገበው በእሳቸው ፣ በደጀኑ ሕዝብና በየደረጃው ያለው ወታደራዊና ሲቪል አመራር የተንሰላሰለና የተቀናጀ ብልህ አመራር በመስጠቱ መሬት ላይ በተቀዳጀነው ወታደራዊ ድል ነው:: የዓለም ታሪክ እንደሚያስታውሰን ጦርነትና የቀውስ ጊዜ የሀገራት መሪዎች ተቀባይነት የሚወሰነው ጦሩነቱ በመሩበት ስልትና ባስመዘገቡት ድልና ቀውሱን በፈቱበት አግባብ ነው ::
ከዚህ አንጻር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ ሠራዊቱ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ አድናቆት እያተረፉ ነው :: የትግራዋይን ልብና አእምሮ በሰላምና በፍቅር ለመማረክ ደግሞ በዚያ ሰሞን ከአርባ ምንጭ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥሪ አድርገዋል :: ክልሎችም ሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ከትግራይ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ በማድረግና በማግባባት የትግራይን ሕዝብ ልብ ለመማረክ የተለመደ ጥረታቸውን ጀምረዋል ::
ፈጣሪ ከብልቶቻችን ሁሉ ያስቀደመው ልባችንን ነው:: እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሁሉ እንድ የሕግ አዋቂ ፈጣሪን ሊፈትነው ፤ “ መምህር ሆይ ፥ ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው:: “ ፈጣሪም በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ማቴዎስ 22 ÷ 37 – 38 ላይ እንዲህ ሲል ይመልስለታል ፤ “ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ :: ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት :: “
በዚህ ታላቅና ቀዳሚ ትዕዛዝ እየሱስ ክርስቶስ ከነፍስም ሆነ ከአሳብ በፊት ልብን እንዳስቀደም እንረዳለን:: የ32ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የፍራንክሊን ዴሎን ሮዝቬልት ባለቤትና ቀዳማይ እመቤት ኤሌንኖር ሮዝቬልት፤ ሮዝቬልትን ጨምሮ የበርካታ ፕሬዝዳንቶች አማካሪና ሊቅ የነበረውን በርናንድ በሩክ ፤ “ አእምሮየና ልቤ በሃሳብ ቢለያዩ ማንኛውን ልከተል !? “ ስትል ትጠይቀዋለች ፣ እሱም ያለምንም ማወላወል ፣ “ ልብሽን ተከተይ “ ሲል ይመልስላታል ::
እነዚህ መንፈሳዊና ዓለማዊ ዋቢዎች ልብ በሰው ልጅ ዘንድ ያለውን ከፍ ያለ ስፍራ ያሳያል:: እኛም የትግራዋይንም ሆነ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑትን የአማራና የአፋር ሕዝቦችን ለማከም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል :: ሸኔም የብዙዎችን ልብ በኀዘን ሰብሯልና ተመሳሳይ ርብርብ ይጠይቃል ::
በዲፕሎማሲው መልክዓ ከ30 ዓመታት ወዲህ ብቅ እንዳለ የሚነገርለት የመማረክ ወይም የማግባባት ጥረት (የሶፍት ፓወር) መንግሥታት እንዴት በሌሎች ሀገራት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ለመረዳት የማይተካ ሚና እንዳለው መስከረም መግቢያ ላይ ለንባብ የበቃው “ ፎሪን ፖሊሲ “ መጽሔት ያትታል :: አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ጆሴፍ ኔይ ፤ ሶፍት ፓወር አንድ ሀገር በምትከተለው የፖለቲካ ሥርዓት ፤ ፖሊሲ ፣ እሴቶች እንዲሁም በሲቭል ማህበረሰቧና በባህሏ አማካኝነት ሀገራትን የመማረክና የመሳብ ዲፕሎማሲያዊ ሀቲት ነው ::
የሕዝቦችን አእምሮና ልብ በመማረክ (አትራክሽን) ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ አይነት ነው :: ሀርድ ዲፕሎማሴ ከዚህ በተቃራኒው ወታደራዊ ኃይልንና ጉልበትን የሚጠቀም ነው :: አሜሪካ የሳዳምን በማስከተል የታሊባንን አገዛዞች በጦር ሜዳ ማንበርከክ ብትችልም ፤ የኢራቃውያንንና የአፍጋኒስታውያንን ልብና አእምሮ መማረክ ላይ ባለመስራቱ ተልኮውን ሙሉ በሙሉ ሊያሳካና ግቡን ሊመታ አልቻለም ::
ሶፍት ፓወር ምን ያህል ወሳኝ ሚና እንዳለው ከዚህ መረዳት ይቻላል :: የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፣ እሴቶች ፣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ፣ የሰላም ጓድ ፣ ዩኤስኤይድ ፣ ሆሊውድ ፣ የትምህርት ተቋማት ሙዚቃው ፣ ወዘተረፈ የሀገራትን ልብና አእምሮ መማረኪያ የሶፍት ፓወር አካል ናቸው ::
እንደ መውጫ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጀመሪያውን የወይራ ዝንጣፊ ሀገር እየተመለከተና እያዳመጠ በግልፅ ለሕወሓት የላኩት በመጋቢት 24 ቀን ፣ 2010 ዓ.ም የበዓለ ሲመት ንግግራቸው ነበር :: የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ እናቶች ፣ ክብርት ሙፈሪያት እያለቀሱ እግሩ ስር ወድቀው ለምነው ነበር :: ከዚያ በኋላም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለሰላም ፣ እርቅና አካታችነት ያላነሱበት ጊዜ አልነበረም ::
ይህ ጽኑ አቋማቸው እሳቸውንም ፓርቲያቸውንም ውድ ዋጋ አስከፍሏል:: ለውጡ ግለቱን ጠብቆ እንዳይሄድ ተፅዕኖ እስከማሳደርና ለሴራ ፖለቲካ እንዲጋለጥ በር እስከመክፈት ደርሶ ነበር:: የአስቸኳኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በዚያ ሰሞን ይፋ ባደረገው ሰነድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ክልሉ በልማትና በሰላም ላይ እንዲያተኩር በተደጋጋሚ መክረዋል:: ዘክረዋል ::
የለውጥ ኃይሉም የሕግ የበላይነትንና ሕልውና ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የትግራይን ሕዝብ ልብና አእምሮ መማረክ የሚችሉ ስልቶችን ነድፎ በስፋት መንቀሳቀሱ አይዘነጋም :: ይህ የትግራዋይን ልብ በፍቅር የማሸነፍ እና በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምም ሆነ የሥነ ልቦና ህክምና ታላቅ ኃላፊነት ስለሆነ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም :: ስላልሆነ ዜጎችና የግል ድርጅቶች ከዳር እስከ ዳር በሙላት ሊቀላቀሉት ይገባል ::
ሁላችንም ለሰላም ስምምነቱ መሳካት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም