ያለንበት ወቅት መጸው ይባላል፤ መጸው የመኸር ሰብል የሚያፈራበት፣ ሰብሉ ታጭዶ፣ ተወቅቶ፣ ፍሬው ደግሞ ከገለባው መለየት የሚጀመርበት ነው። ፍሬው ከገለባው የሚለየው ደግሞ በንፋስ አማካይነት ነው። መጸው የንፋስ ጊዜ መሆኑም ለዚህ ይጠቅማል። በዚህ ወቅት ንፋሱ የደረሰውን ሰብል ማሳ ላይ እያለ ሲያዘናፍለው ይታያል፤ የተሰበሰበው አዝመራ እየተወቃ በመንሽ እየተንገዋለለ በላይዳ እየተደረገ ለንፋስ ወደ ላይ ይሰጣል። በዚህም እህሉ ከገለባው ይለያል።
የታጨደው ሰብልም ተወቅቶ በከብቶች ተበራይቶ ፍሬው ከገለባው እንዲለይም ያግዛል። ገበሬዎች ፍሬውን በጎተራ ይሞሉታል። ገለባው አብዛኛው ለከብቶች ለዓመቱ መኖ እንዲሆን በተወሰነ ቦታ ይከምሩታል፤ አንዳንዶች ለቤት መምረጊያ ጭቃ እንደ ጭድ ይጠቀሙበታል፤ የተቀረውን ደግሞ እናቶች ጠራርገው ማገዶ ያደርጉታል። መጸው ፍሬው ከገለባ የሚለይበት የተስፋ የደስታ ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱ ጦርነቶች፤ የሰው ሕይወት ሲቀጠፍ፣ ሀብት ንብረት ሲዘረፍ፣ አካል ሲጎድል ነበር። በዚህም እናቶች ልጆቻቸውን ለጦርነት ገብረዋል ፤ሰላማዊ ሰዎች ከፊሎቹ ደማቸው ሲፈስ ፤ገሚሶቹ እንባቸውን አፍሰዋል።
ሰሞኑን በፕሪቶሪያ የተደረገው ውይይት ሕውሓት ከመንግሥት ጋር በመስማማት ግጭቱን ለማብረድ፤ ጦሩን ለማውረድ መስማማታቸው ይህን አይነቱን ቀውስ ለማስወገድ እና ልማትን ለማሳለጥ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
ይህም እንባቸውን ሲያዘሩ የነበሩ እናቶችና አባቶች በከንቱ ሲፈስ የነበረ እንባቸው እንደሚታበስ አንድ የምሥራች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከላይ መጸው የተስፋ ወቅት ነው እንዳልነው ሁሉ ቀጣዩ ጊዜ ጥላቻና ሽኩቻን መቃቃርን አስወግደን እርቅና ፍቅርን የምንመሠርትበት የተስፋ የደስታ ፍሬያማ ወቅት እንዲሆን ስምምነቱ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ያለንበት የመጸው ወቅት ከገለባው ግጭትና ሽብር የተላቀቅንበት ነው። ከላይ እንደጠቀስነው በመጸው ነፋስ፤ ፍሬው ከገለባው ይለያል። ፍሬው ወደ ጎተራ ሲከተት፤ ከገለባው የተወሰነው በንፋስ ሲወሰድ የተወሰነው በሌላ አገልግሎት ይቀመጣል። በሀገራችን የደረሰውን ጥፋት ንፋስ እንደወሰደው ገለባ መመልከት ይቻላል፤ ጥፋቱ ንፋስ እንደወሰደው ገለባ ብን ብሎ እየሄደ ነው፤ እየተወገደ ነው። የንግግሩ ፍሬ የሆነው ስምምነት ሀገር እያረጋጋ ነው። ሀገርና ሕዝብን ጤናና ሕልውና ሲያናጋ የነበረው የጥፋት ደመና ሲወጣ፣ የልማትና የሰላም ደመና ሲያንዣብብ እያየን ነው።
የጥፋት መና፤ መናኛ፣ ከንቱ ማለት ነው። በጦርነት ፍሬና ልማት አይገኝም፤ የጦርነት ትሩፋት ካለ፤ ሞትና ውድመት ነው። ግጭት ገለባ ሆኖ በየቦታው ተበተነ ወደቀ ብንል ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።
ከላይ እንደገለጽነው የሀገራችንን ሕልውና ለማናጋት ከጀርባው ሆነው በጦርና በብር ሲደግፉ የነበሩ ሁሉ በኢትዮጵያውያን የማዕበል ንፋስ አንገታቸውን ደፍተዋል። ከጎን ሆነው የውክልና ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትም እና በወንድሞች መካከል ደም ያፋሰሱት አፍረዋል።
በጦርነቱ ተመድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ታዳጊ ሀገሮችን እየገፉ ያደጉ ሀገሮችን እየደገፉ ዕድሜያቸውን የሚገፉ መሆናቸውን ታዝበንበታል። ጦርነቱ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከአፍሪካም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ሀገሮች አለመኖራቸው የአፍሪካ መብት እየተረገጠ እንደሚኖር ያየንበት ነው።
የሰላም ስምምነቱ መፈጸሙ ያሳዘናቸውም አሉ። በየዓመቱ ይህቺን ሀገር ለመበታተን የሚያወጡት ወጪና ድካማቸውን ሁሉ ስናስበው ፈረንጆች ዜሮ ሰም ጌም እንደሚሉት ፤በሀገራችን ‹‹ዘጠኝ ገዝቶ ዘጠኝ መሸጥ ትርፉ ዘጥ ዘጥ ›› እንደሚባው ብሂል ሆኖባቸዋል።
ከጀርባ ሆነው ወንድም ከወንድሙ እንዲተላለቅ ብዙ ሞከሩ ፤እርቅ በመፈጸሙ ግን ክፋታቸውና ልፋታቸው ሁሉ ከንቱ መሆኑን በተግባር አይተውበታል። በዚህ እርቅ ሕዝባችን ጊዜያዊ ቅሬታዎችን ወደ ጎን ትቶ፤ ሀገሩን ከፊት አድርጎ መተባበሩን፣ መደመሩን በተግባር አሳይቷል። በዚህም ውጤት አስገኝቷል።
ኢትዮጵያም የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ በሚል በያዘችው ጽኑ አቋም ድል ተገኝቷል፤ የአፍሪካ ኅብረት በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ንግግር እንዲደረግ ያደረገው ጥረት ተሳክቷል፤ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ማለት ይሄው ነው፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጭን በመከተል ስታደርግ የቆየችው ጥረት የደቡብ አፍሪካው ውይይት በስምምነት እንዲቋጭ የበኩሏን ሚና በመጫወት የአፍሪካ ኅብረት ክብርና ዝና እንዲጎላ አድርጋለች። ዲፕሎማሲያዊ ድልን ተጎናጽፋለች።
ሕወሓትም ጦሩን ለማውረድ፣ ታጣቂዎቹም ትጥቅ እንዲፈቱ፣ የጦር መሣሪያዎቹን ለማስረከብ፣ በትግራይ ከሕገ መንግሥቱና ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ ያካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ፣ በክልሉ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ውጪ ከውጪ ሀገር መንግሥታትና ተቋማት ጋር ግንኙነት ላለማድረግ፣ ፌዴራል መንግሥቱን የሚቃወሙ አካላት ድጋፍ ላለማድረግ በአፍሪካውያን እና በሌሎች ታዛቢዎች ፊት ስምምነቱን ገልጿል።
ጦርነት ለሰው ልጆች እልቂት፣ ለአካል እና ስነልቦና ጉዳት የሚዳርግ፤ ለንብረት ውድመት ለምጣኔ ሀብት ድቀት ምክንያት ነው። በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱት ጦርነቶች ወንድም ከወንድሙ ያለቀበት ነው። ወንድም ወንድሙን ቢገድል የሚያገኘው እረፍት፣ ትሩፋት እና ፍሬ አይኖርም።
ለሰላም የሚደረግ ድርድርና ውይይት ግን ፍሬ ነው። ሕውሓት ለሰላም ዝግጁ ሆኖ መፈረሙ፤ የትግራይ እና አካባቢው ወገኖቻችን ከእልቂት ከስጋት ይድናሉ። በዚህ ስምምነት ፍሬ ልናፈራበት እንደምንችል ሰሞኑን በናይሮቢ የመንግሥትና የሕውሓት ጦር አዛዦች በጠረጴዛ ዙሪያ እያደረጉ ያሉት ውይይት ማሳያ ነው።
ይህም የሰላምን ፍሬ በሰለጠነ ጎዳና በውይይት ለማስገኘት ያስችላል። ውይይቱ ለሰላም የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል። በዚህ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ እና ኢትዮጵያውያን ሁሉ አትራፊዎችና አሸናፊዎች ናቸው። ሲጀመር ገለባ ፍሬ የወጣለት ሣር ወይም ቅጠል ነው። ፍሬ የሌለው ሣር ደግሞ ፍሬ አልባ ወይም ገለባ ነው። ከላይ ፍሬ አልባ ገለባ ስንል ፍሬ ያለው ገለባ አለ ለማለት እንዳልሆነ ይሰመርልን።
ዜጎች በማወቅም ባለማወቅም የነበራቸውን ዕኩይ አመለካከት የማጥራት ሥራ በዋነኛነት መወጣት ያለባቸው የመንግሥት አካላት ከሚዲያው ጋር ተባብረው በመሥራት ነው። የስነልቦና ምሑራን የሃይማኖት አባቶች ዜጋው የተዘራበትን ጥላቻ ለማስወገድ ሕዝቡን በማስተማር ይቅርታን እንዲላበስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት የዜጎች ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ የአካል ጉዳት፣ ሥነ ልቦናዊ ቀውስና የንብረት ውድመትን አስከትሏል። በኢትዮጵያ በሕጋዊ፣ በፖለቲካዊና በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት የነበረበት አለመግባባት ብዙ ጥፋት አድርሷል። ይህም ህጽበተ አዕምሮን ይፈልጋል። የህፅበተ አዕምሮው ሥራው በጥንቃቄ በዘላቂነት ከተካሔደ፤ ቀጣይ ጥላቻና ሽኩቻን፣ ቂም በቀልን ለመንቀል መተባበርና መረዳዳትን ለመትከል፤ ሰላምን ለመዝራት ይረዳል።
የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከወገኑ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የመሠረተ ልማት ዝርጋዎችን መልሶ በመጠገንና መልሶ በመገንባት መብራት፣ ስልክ ፣ባንክ፣ የሕክምና ተቋማት አገልግሎት መስጠት የጀመሩባቸው ቦታዎች አሉ። ሰላም በመስፈኑ ጅማሮ በሀዘኔታና ኡኡታ የቆየው ሕዝብ ወደ ደስታና እልልታ እየተሸጋገረ ነው። የልማት ደመና ሲመጣ የጥፋት ደመና ሲገፈፍ በተስፋ እያየ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ከአሁኑ የመብራት አገልግሎት እየቀረበለት ይገኛል። በሁለት ዓመት ጨለማና ጦርነት ውስጥ የነበረው ሕዝብ ተስፋን እያየ ነው። መጻፉም ‹‹ ሕዝብ ዘይነብር ዲበ ጽልመት ርዕየ ብርሃን›› ማለት (በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ብርሃን አየ) እንደሚለው መብራትና የመሠረተ ልማት እየተዘረጋለት ተስፋን እያየ ይገኛል።
ትምህርትና ወጣቶች ተለያይተው ነበር፤ ሕክምና ተቋማት ወድመዋል፣ ባንኮች ሥራ የሚሠሩበት ሰላም አልነበረም። አሁን ግን በጦር ለተከፋው ሕዝብ የመጸው ተስፋ እያካፋ የሰላምን ፍሬ ሊያጣጥም የሚችልበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ሕዝቡ ከሽኩቻና ከጥላቻ ርቆ በሰከነ መንፈስ ስለ ራሱና ስለ ሀገሩ ማሰብ ይጀምራል።ይህ ደግሞ የፍጻሜው ጅማሬ ነው።
ይቤ ከደጃች .ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም