ክፍል ሁለት
“ሰላምን ግዛት እንጂ አትሽጣት!” ይህ አገላለጽ በብዙ ሀገራት ቋንቋ ውስጥ የተለመደ ብሂል ነው፡፡ ዓለማችን በሰላም ውላ እንዳታድር ብዙ የሚያባንኗትን ፈተናዎች እንደተጋፈጠች ዘመኗን በመፍጀት ላይ ትገኛለች፡፡ በብብቷ አቅፋ የያዘቻቸው ልጆቿም የፈተናዋ ተጋሪ መሆናቸው ግድ ስለሆነ ውጤቱን እየተጎነጩ ያለው ከአንድ የጋራ ጽዋ ነው፡፡ ብዙዎች ሰላምን የግል ሀብትና ዕሴት ከማድረግ ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች በደራ የጥፋትና የክፋት ገበያ ላይ ለሽያጭ እያቀረቡ ሲያስማሙ እየተስተዋለ ነው፡፡ የአብዛኞቹ ሀገራት ታሪክና የአምባገነኖች የየዕለቱ ዜና መዋዕል ይህንኑ እውነታ እያሳየን ስለሆነ በዝርዝር ዘልቆ መተንተኑ እጅግም ላያስፈልግ ይችላል፡፡
“ፀረ ሰላምነት የሚጀምረው ከአንድ ግለሰብ ነው” የሚለው ዘወትራዊ አገላለጽ በሁሉም ዘንድ በአሜንታ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ባይገመትም እውነትነት እንዳለው ግን መካድ አይቻልም፡፡ ለሰላም ተጻራሪነት የግለሰብ ድርሻ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ከሆነ ዘንዳ የሰላም ሐዋርያ ለመሆንም የግለሰቦች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የአንድ ሰው ሰላማዊነት የሚጀምረው ከራስ ጋር የሚደረግን ጠብና እልህ በራስ ሽምግልና ማረቅ ሲቻል ነው፡፡ ከራሱ ጋር የታራቀ ግለሰብ ደግሞ በቅርቡ ካለው ሰው ጋር ለመታረቅ አይከብደውም፡፡
እርቅ ከራስና ከሌሎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋርም መታረቅን ግድ ይሏል፡፡ ከራስ ጋር፣ ከሌሎችና ከተፈጥሮ ጋር ለመታረቅ ልቡ ገር የሆነ ሰው ከፈጣሪ ሃሳብ ጋር ለመስማማት አይከብደውም፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በማለት ማረጋገጫውን የሰጠን፡፡
ግለሰብ የሰላም ሐዋርያ ሲሆን በዙሪያው ያሉት የቅርቦቹ ወይንም የእኔ የሚለው ማሕበራዊ ክበብ/ቡድን ፈለጉን መከተላቸው አይቀርም፡፡ አንድ ቡድን ሰላማዊ ሆነ ማለት ማሕበረሰቡ ሰላማዊ ሆነ ማለት ነው፡፡ ማሕበረሰብ የሰላም መገለጫ ከሆነ ደግሞ የሕብረተሰብ የሰላም አድማስ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ እንጂማ ሰላም የሚጀምረው ከላይ ወደ ታች ወይንም ከስብስብ ወደ ግለሰብ እንዳልሆነ በብዙ ማሳያዎች ማመላከቱ አይገድም፡፡
በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ አብርቶ “የሰው ያለህ!” እያለ በገበያ መካከል የተንከራተተው ዐይነ ሥውሩ አቴናዊው ፈላስፋ ዲዮጋን በድርጊቱ ለማስተላለፍ የፈለገው ቁምነገር “አንድ የሰላም መሪ” ተገኘ ማለት ሕብረተሰብን መፈወስም ሆነ መታደግ ቀላል ነው የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጎ ይመስላል፡፡ ደግሞም እውነት ነው፡፡
ጆን ጋርድነር የተባሉ እውቅ አሜሪካዊ ደራሲ በውጤታማ የአመራር ዘይቤ ዙሪያ በጻፉት አንድ መጽሐፍ ውስጥ ከላይ የተጠቀሰውን የአንድ ግለሰብ ተጽእኖ ፈጣሪነት የገለጹት እንደሚከተለው
ነበር፡፡ “ዛሬ የምናውቃት ታላቋ አሜሪካ ከ200 ዓመታት በፊት በሀገር ደረጃ ስትታወቅ የሕዝቧ ብዛት ሦስት ሚሊዮን ብቻ ነበር፡፡ ከእነዚያ ሦስት ሚሊዮን ሕዝቦቿ መካከል ስድስት ታላላቅ መሪዎች ነበሯት፡፡ አነርሱም ዋሽንግተን፣ አደምስ፣ ጄፈርሰን፣ ፍራንክሊን፣ ማድሰንና ሃሚልተን ነበሩ፡፡ ”
“ዛሬ የሕዝቧ ቁጥር ከ240 ሚሊዮን ልቆ ‹ታላቅ ነኝ ብላ ራሷን ስትሸጥ በምትውለው አሜሪካ› ሰማኒያ እጥፍ ዝነኛ የሰላም ደቀመዛሙርት መሪዎች ሊኖሯት ሲገባ ያለመታደል ሆኖ የጥንቶቹን ያህል ስድስት ያህል ተጠቃሽ የሰላም ሐዋርያት መሪዎችን ለማግኘት አልታደልንም፡፡ ” በማለት ሀገራቸውን ሞግተዋል፡፡ ደራሲ ጆን ጋርድነር በቁጭት ለማስተላለፍ የሞከሩት መልዕክት የአሜሪካውያን መሻት ብቻ ሳይሆን የብዙ ሀገራትና ሕዝቦችን የጋራ ጉጉት ጭምር ነው፡፡
አባባሉን ከራሳችን ሀገር ወቅታዊ ዐውድ ጋር አዛምደን እንየው፡፡ በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል የተለኮሰው የጦርነት እሳት ምን ያህል የንጹሐንን ሕይወት እንዳስገበረ፣ ምን ያህል ሀብት እንዳወደመብንና በማሕበራዊ ተራክቧችን የፈጠራቸው ሳንካዎች ገና በሚገባ ተጠንተው ስላላለቁ ከድምዳሜ ላይ ለመድረስ አልተቻለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ጠለቅ ብሎ ቢጠና የጥፋት ሃሳቡ ጥንስስ በመጀመሪያ የተብላላው በአንድ ግለሰብ አእምሮ እንጂ የቡድን ጭንቅላት የፈጠረው እንዳልሆነ ለማመን አይከብድም፡፡
የጀግንነት ዋና መለያው “ሰላም ወዳድነት”
ነው፡፡ ለሰላም አሜን ብሎ የሚገዛ ጀግና ሁሌም ጦርነትን እንደፈራ ነው፡፡ የፍርሃቱ መንስኤ በጦርነቱ አሸንፋለሁ ብሎ በመስጋት ሳይሆን በአረር ፉጨት መካከል የሚፈጸመው ጥፋትና ውድመት ሰብዓዊነቱን እየፈተነ ስለሚሞግተው ነው፡፡ ሰላም ወዳድ ጀግና የማንም ዜጋ ደም እንዲፈስ ያለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን የሰላም ዘብ ጭምር ነው፡፡ አንድ ሰው ሰላም ወዳድ ስለመሆኑ በበርካታ ማሳያዎች ሊገለጽ ይችላል፡፡
ከብዙ መገለጫዎች መካከል ዋነኛው ከራስ ሁኔታ ባሻገር ስለ ሰላም ሲባል ዝቅ ማለትን መድፈር በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ “በእንዲህና በእንደዚያ መስፈርቶች ሲመዘን እኔ የተሻልኩ ነኝ” ከማለት ይልቅ ራስን ዝቅ አድርጎ “ሰላምን” ከፍ በማድረግ የሰላም ሐዋርያ መሆን ከሁሉም ልቆ የሚውለበለብ የምስክርነት ሰንደቅ ነው፡፡ የሚከተለው የጸሐፊው አንድ የግል ገጠመኝ ከላይ የተዘረዘሩትን እውነታዎች ይበልጥ ሊያጎላ ይችላል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የአሜሪካዋን 50ኛ ግዛት (ስቴት) የሆነችውን ሐዋይን ለመጎብኘት እ.ኤ.አ. በታህሳስ 1996 ዓ.ም ዕድል ገጥሞት
ነበር፡፡ ይህቺ ክፍለ ግዛት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለመስማትም ሆነ ለመተረክ እጅግ የሚዘገንን ጭፍጨፋና እልቂት ተፈጽሞባት እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ያንን እጅግ አሰቃቂ ታሪክ ለተከታታዮቹ ትውልዶች ትምህርት እንዲሆን በማሰብ ፊልሞቻቸው፣ የጥበብ ሥራዎቻቸውና ሙዚዬሞቻቸው ሳይቀሩ በሚያስደንቅ አደረጃጀት ታሪኩን በመተረክ ላይ ናቸው፡፡
ያንን የከፋ ጥቁር የታሪክ ክስተት እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት (እ.ኤ.አ ከ1939 – 1945) እንደ ሰደድ እሳት ዓለማችንን እያንገበገበ ባለበት አንድ ዕለት (እሁድ ዲሴምበር 1941) የሐዋይ ሕዝብ እንደተለመደው ወደ ጉዳዩና ወደየቤተ እምነቶቹ ሊሰማራ ዝግጅት ላይ በነበረበት ሰዓት ድንገት ሳይታሰብ ብዛታቸው 353 የሆኑ የጃፓን የጦር አውሮፕላኖች አከታትለው እየበረሩ በመሄድ ያቺን የደሴቶች ስብስብ ክፍለ ግዛት በአውዳሚ ቦንብ እምሽክ አድርገው አነደዷት፡፡ ሰውም እንስሳትም ሆነ የባሕር ኃይል ወታደራዊ ምድቦችና መኖሪያ ቤቶች በአንድ ቅጽበት ወደ አመድነት እንደተለወጡ ታሪኩ በዝርዝር ተጽፏል፡፡
በሐዋይ ክፍለ ግዛት ውስጥ ሞት ዱታ ነኝ ብሎ ነገሠ፡፡ አካላቸው ጎድሎና እንዳልነበሩ የሆኑ ሰለባዎች በጣር ድምጽ እዬዬ እያሉ ቢቃትቱም የሚያደምጣቸውና የሚረዳቸው አለሁ ባይ ሊደርስላቸው ስላልቻለ የስቃያቸው ጩኸትና ሰቆቃ ዋጋ አልነበረውም፡፡
በአጭሩ ሐዋይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቁርስ ሆና በግፈኞች መንጋጋ ታኘከች ማለቱ ይቀላል፡፡
“የዕንቁ ወደብ” (Pearl Harbor) በመባል የሚታወቀው የባሕር ኃይል መደብ ከእነ ሠራዊቱ፣ የሠራዊቱ ቤተሰቦችና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መርከቦችና አውሮፕላኖች እንዳለ የዶግ አመድ ሆኑ፡፡ በግፍ የተጨፈጨፉት የባህር ኃይሉ አባላትና የሲቪሎች አጠቃላይ ቁጥር 2,335 ሲሆን የቆሰሉት ደግሞ 1,143 ነበሩ፡፡
ይህ ጥቃት ያንገበገባቸው አሜሪካኖቹ ለበቀል የወሰኑት ጊዜ ሲደርስ ከታላላቆቹ የጃፓን ከተሞች ሁለቱን ሄሮሽማንና ናጋሳኪን በዚያው ዓመት ኦገስት 6 እና 9 በሁለት የአቶሚክ ቦንቦች አጋዩአቸው፡፡ በበቀል ድርጊቱ ያለቁት ጃፓናውያን ሲቪሎችና ወታደሮች ቁጥር በሂሮሽማ 140,000 በናጋሳኪ ደግሞ 74,000
ተገምቷል፡፡ ከተሞቹ ወደ ፍርስራሽነት መለወጣቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመቶ ሺህዎች የሚገመቱት ዜጎችም ቁስለኞችና አካለ ጎዶሎዎች ሆነዋል፡፡
የእነዚህ ሁለት ሀገራት ጠላትነት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም የቂሙና የጥላቻው ቁርሾ ዛሬም ድረስ ተፈውሶ አብቅቶለታል ለማለት
ያዳግታል፡፡ በተለይም በጃፓን ከተሞች ላይ በዘነበው የአቶሚክ ቦንብ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ በሚወለዱ ሕጻናት ላይ ተጽእኖው ጎልቶ እንደሚታይ ተደጋግሞ ይገለጻል፡፡
ይህንን የታሪክ ዳራ መነሻ በማድረግ እነሆ ይህ ጸሐፊ የግል ገጠመኙን እንደሚከተለው ለአንባቢያን ያጋራል፡፡ ጸሐፊው እ.ኤ.አ በ1996 ሐዋይ ክፍለ ግዛት በተገኘበት ወራት ክፍለ ግዛቷ የቦንቡ መዓት የዘነበባትንና የአስከፊውን ዕልቂት 55ኛ ዓመት በመዘከር ላይ ተጠምዳ ነበር፡፡ ጸሐፊው በዚያ ምድር የተገኘው ከ23 ሀገራት ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር በአመራር ጥበብ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለመውሰድ
ነበር፡፡ ከሥልጠናው ጎን ለጎንም የተዘጋጀው የጉብኝትና የባህል ልውውጥ እጅግ የተዋጣለት ነበር፡፡
ከአሰልጣኞቻችን መካከል አንዱ ዝነኛና ታዋቂ የነበሩት ፕሮፌሰር ጃፓናዊው አሬጋ
ነበሩ፡፡ የፕሮግራሙ መክፈቻ ሊጀመር የታሰበው በሐዋይ የባህል ቡድኖች የመድረክ ላይ ትርዒት ስለነበር የጥበብ ሥራቸውን ሊያቀርቡ የተዘጋጁት ባለሙያዎች በባሕላዊ ልብሳቸውና ጌጣጌጦቻቸው እንደተዋቡ በመድረኩ ላይ ወግ ባለው ሥርዓት ተዘጋጅተው ተቀምጠው ነበር፡፡ ከኦፊሴላዊ ትውውቅ በኋላ የባሕል ትርዒት አቅራቢዎቹ መሪ ከወንበራቸው ከፍ ብለው የሚከተለውን ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡
“የተከበራችሁ እንግዶች! እንኳን በሰላም ወደ ውቢቷ የሐዋይ ግዛት በሰላም መጣችሁ፡፡ እኔ ስሜ እከሌ ይባላል፡፡ የትርዒት አቅራቢዎቹን ወክዬ እንኳን ወደ ግዛታችን በሰላም መጣችሁ የምለው “አሎሃ! በማለት ነው፡፡ ጥቂት ስለ ራሴ ላስተዋውቃችሁ፡፡ እኔ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የአየር ኃይል አባል ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ አባል በሆንኩበት የጦር ክፍል ላይ አሰቃቂውን የጃፓኖች ቅጣት ከተቀበሉት አንዱ ነኝ፡፡ እንደምታዩኝ በዘነበብን ቦንብ ምክንያት ከፊል ሰውነቴ ሽባ ሆኖ በሥጋዬ ውስጥ የማይድን ካንሰር ተሸክሜያለሁ፡፡ ሐኪሞች በአጭር ጊዜ እንደምሞት ቢያረጋግጡልኝም በእግዚአብሔር ፍቅርና ቸርነት ዛሬን ደርሻለሁ፡፡
የሞቴ ቀን ሳይደርስ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ እናንተን መሰል ዜጎች ጋር በመተዋወቃችን በግሌ ኩራት ይሰማኛል፡፡ እነዚህ የምታዩአቸው ጎልማሶችና ወጣቶችም የእኔን ስሜት እንደሚጋሩ አምናለሁ፡፡ ላስታዋውቃችሁና ትርዒታችንን እንጀምር” ብለው ፊታቸውን ወደ ትርዒት አቅራቢዎቹ ዞር ከማድረጋቸው እኛ ጃፓናዊ ፕሮፌሰር ከተቀመጡበት ወንበር እመር ብለው በመነሳት መድረኩ ላይ ወጥተው በአዛውንቱ እግር ላይ ተደፉ፡፡
እግራቸው ላይ ተጠምጥመውም “ስላፈሰስነው ደም ጃፓንን ማሩ! ንጹሐንን በመጨፍጨፋችን በድለናችኋልና ማሩን! ለፈጸምንባችሁ የግፍ ዓይነት ሁሉ ጃፓንን ማሩ!” እያሉ ለደቂቆች ያህል እየተንሰቀሰቁ እግራቸውን በእምባቸው አበሱ፡፡ እንደምንም እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ከመድረኩ ወርደው ወደ እያንዳንዱ የፕሮግራሙ ተሳታፊ እግር ላይ እየተደፉ ናይጄውያን፣ ኢትዮጵውያን፣ ብራዚላውያን፣ አውስትራሊያውያን ፣ጃፓንን ማሩ! …እናንተን የበደልነው በኢኮኖሚያችን በመታበይ ነው፡፡ ” ዝርዝር ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ በአጭሩ አዳራሹ በእንባ ታጠበ ማለቱ ይቀላል፡፡
ከዚህ ገጠመኝ አንባቢው ምን ትምህርት ያገኛል? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ከአንድም ሰው ሆነ ከቡድን የሚደመጥ የሰላምና የይቅርታ ቃል በዳይንም ሆነ ተበዳይን በእኩልነት ይፈውሳል፡፡ ደም የሚደርቀው ልብንና መንፈስን ለሰላምና ለይቅርታ በማስገዛት
ነው፡፡ እርግጥ ነው በዳይ ተበዳይን መካስ የነበረና ያለ ስለመሆኑ ባሕልም ሆነ ሕግ ግድ ይለናል፡፡ ከካሳውና ከደም ዋጋው በፊት መቅደም የሚኖርበት ግን ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ምድርም እየተፈጸመ ያለው ይኸው ነው፡፡ በክፍል አንድ ጽሑፌ በደልን ይቅር ለማለት እንደምን እንደሚከብድ ለማሳየት
ሞክሬያለሁ፡፡ መጠቃት ውስጥን እንደ ሻህላ እንደሚያመነዥግ የደረሰበት ሁሉ
ያውቀዋል፡፡ የፈሰሰን ደም “በጥቁር ደም” ለመበቀል መሞከር ትርፉ በማይወጡት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ እንደመኖር ይቆጠራል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የፈሰሰው ደምና የወደመው ንብረትና ሀብት፣ የደረሰው የሥነ ልቦና ቀውስና መከራ ምናልባትም ሸክሙ በቀላሉ ሊራገፍ እንደማይችል ይገመት ይሆናል፡፡
እውነት ነው! የመንፈስና የስሜት ስብራት በፋሻ ታስሮም ሆነ በጄሶ ታጅሎ እንደሚድነው የአጥንት ስብራት ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ከልብ ይቅር መባባል ከሰፈነና አሸናፊውና ተሸናፊው እጃቸውን ለሰላም ከዘረጉና ዝቅ ብለው ከተቀባበሉ “ዕርቅ ደም ያደርቃል”፣ ይቅርታም የውስጥ ቁስልን ይፈውሳል፡፡ ከይቅርታ በኋላ የሚፈጸመው ተጨማሪ ሂደት በራሱ የአካሄድ ወንዝ እየፈሰሰ ፈውሱ ፈጥኖ እንዲለመልም ያግዛል፡፡
ሰላም ይሁን፡፡
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም