የአገራችን መንግሥትና የሕወሓት እርቅ በደቡብ አፍሪካ ተፈራረሙ ተብሎ ሲነገርና ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ዜና ሲሆን እንደብዙ ኢትዮጵያውያን ግራ ተጋባሁ።ምን እንደሆነ የማላውቀውም ስሜት ተሰማኝ። ምክንያቱም ከሁለት ሶስት ቀናት በፊት ከምዕራባውያን ማስፈራሪያና ፍራቻን የሚያጭሩ የሚመስሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ስለተመለከትኩ ነው። እንዴት ሁሉም ጉዳይ እንዲህ በስምምነት አለቀ ብዬም አሰብኩና ተገረምኩ። እናም ልዑሉንና ገናናውን አምላኬን የማይቻለውን ስላስቻለ እንዲሁም በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደገናም ጣልቃ ስለገባ ከቤተሰቤ ጋር ተንበርክከን አመሰገንነው አወደስነውም።
ለወትሮው በእንዲህ ያለ ሁኔታ የቅርብ ወዳጆቼ ጋር ደውዬ ደስታዬን የማካፍል ቢሆንም በዚህ ጊዜ ግን ለራሴም ለመረዳትና በጥያቄ የተሞላውን አእምሮዬን ለማሳመን ጊዜ ወሰድኩ። በዚያ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ግን መቆየት ያላስቻላት ጓደኛዬ ደወለችልኝና “ሰማሽ አይደል? ቅዱስ እግዚአብሔር ይመስገን! ልዑሉ አምላካችን ይመስገን!” ከማለቷ የደስታ ሲቃ ሲያንሰቀስቃት ስሰማ ደነገጥኩ።
እውነት ነው ደዋይዋ ጓደኛዬ የትግራይ ክልል ተወላጅ ናት። የቤተሰቧን በተለይ የወንድም የእህቷን ወሬ ከሰማች ሁለት ዓመት ሊሞላት ምንም አልቀራትም። ያስለቀሳት፣ የደስታ ሲቃ ያስያዛት፣ ተስፋም የሰጣት ከዚህ በላይም የሆነ ምክንያቷ ምን እንደሆነ አስታወስኩ። እየተገረምኩ አናግሬያት ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፈችውን ውጣ ውረድና መከራ አስታውሼ እኔም በሀዘንና በለቅሶ እንዲሁም በአዲስ ምስጋናና ተስፋ ተሞላሁ። ይህቺው ጉደኛዬ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ጦርነቱ እንደተጀመረና መንግሥት መቀሌን እንደተቆጣጠረ እንደማንኛውም ሰው እረፍት ተሰምቷትና ተስፋ አድርጋም ነበር። ነገር ግን የስጋ ነገር ነውና ሁሉም ቤተሰቧ ሰላም መሆኑን ለመስማት በጉጉት ከዚያ የሚመጣ ወሬ ትጠብቅ ነበር። እውነትም ሆኖ ራያ አካባቢ ያሉት ወንድሞቿም ሆኑ ሄዋነ ያለችው እህቷ ሰላም መሆናቸውን መስማታችን እረፍት ሰጠን።
መቀሌ አካባቢ ወንድም እና እህት ቢኖራትም በጊዜው በዚያ አካባቢ ጦርነት ስላልነበረ እጅግም አልሰጋችም ነበር። ከእርሷ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በትግራይ የተለያዩ ቦታዎች ዘመዶቿን ተዋውቄ፤ በተለያየ ጊዜ አስተናግደውኝ ስለሸኙኝ እኔም እረፍት አገኘሁ። በተለይ መኾኔ የሚባለው ቦታ ሄደን ከአስር በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቿ ሊያገኟት ከገጠር መጥተው ሲጨዋወቱ፤ እኔ መካከላቸው ካለሁ እኔም ጨዋታቸው እንዲገባኝ ወዲያውኑ ቋንቋቸውን ወደአማርኛ ይቀይሩት እንደነበር አስታውሳለሁ። እንግዳ ተቀባይነታቸው ኢትዮጵያዊ ፍቅራቸው ይማርከኝም ነበር። በወቅቱ አንዳንዶቹ አማርኛ መናገር የማይችሉ መሆናቸውን ስረዳና እንዲጫወቱ ብዬ ከአጠገባቸው ዞር ስል እንደገና በቋንቋቸው ማውራት ይጀምራሉ። እኔም “እባካችሁ በሚመቻችሁ ቋንቋ አውሩ፣ ደሞኮ ትግሪኛን ለመስማት ቀላል ነው፣ አማርኛ ማለት ነው” ስላቸው “ከመቼ ወዲህ ነው ቋንቋውን የማይናገር እንግዳ እያለ እርሱን ቁጭ አድርገን በቋንቋችን የምናወራው?” ይሄ አይደረግም ሲሉ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ የነገሩኝን በፍጹም አልረሳውም። ከዚህ ደግነትና ፍቅራቸው የተነሳ ደህንነታቸውን መስማቴ እረፍት ሰጠኝ። ድግሜም ልዑል አምላኬን አመሰገንኩ።
ነገር ግን በሳምንቱ አካባቢ መቀሌ ይኖር የነበረ በግል ሥራ የሚተዳደር ወንድሟ በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ማረፉን ተረዳች!! ይህ ወንድሟ እንደልጇ ያሳደገችው ሲሆን የግል ድርጅቷን በኃላፊነት የሚመራ ነው። እኔም በተለያየ ጊዜ ትግራይ ስንሄድ ያገኘሁት ሲሆን በተለይ ጓደኛዬ ከዘመዶቿ ጋር ስትጫወት እኔና እርሱ ወጣ ብለን በየከተማው አንዳንድ ቦታዎች ያስጐበኘኝና ታሪክም ያጫውተኝ ስለነበር በብዙ እንቀራረብ ነበር፤ ቀልድና ጨዋታ የሚወድ ስለሆነ በተለያዩ ነገሮች ስደናበር ሙድ ይዞ ስቆ ያስቅብኝ ነበር። ጓደኛዬ ሀዘኗ እጅግ ከባድ በመሆኑ የሆነውን ማመን አቃታት!! መቀሌ በተረጋጋችበት ወቅት ከቤቱ ወጥቶ ትልቅ እህቱ ቤት እየሄደ ነው ተኩሱ ከየት እንደሆነ ያልታወቀ ጥይት ነው የመታው።
ከሁሉ የሚገርመው ሀዘንተኞች እርማቸውን ሊያወጡና ሊያጽናኗት ሲመጡና የእልህ ንግግር ሲናገሩ እርሷ “የሞተው አንድ ኢትዮጵያዊ ነው ከዚህም ከዚያም ወንድም ወንድሙን ገድሏል፤ ተቆሳስለናል ተጎዳድተናልም እኔ ብቻ ሳልሆን የኢትዮጵያ እናትና እህት ታልቅስ” ብላ ትመልስላቸው ነበር። የምታዝነው ምክንያት በሌለው፣ በማያስፈልገው ጦርነት እንጂ ʻየወንድሜ ገዳይ እከሌ ነውʼ አትልም ነበር። በርግጥ ከዚህ ማንነቷ የተነሳ በዘመናት ውስጥ ብዙ ወዳጆች በዙሪያዋ ቢኖሩም፤ በዚህ ሁኔታዋ ግን ሰው ሁሉ እጅግ ተደነቀ። እውነቷን ነው እንዴ ብሎ በመጠራጠርም ማመን ያልቻለውም ብዙ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ለቅሶ ሊደርሱና ከጎኗ መሆናቸውን ሊያሳዩ መጥተው “ልናጽናናሽ መጥተን አጽናንተሽ መለስሽን” ብለዋታል።
ይህች ጓደኛዬ ጠንካራ የቢዝነስ ሰው ከመሆኗም በላይ አንባቢ፣ አሳቢ፣ ለኅብረተሰብ መልሶ በመስጠት የምታምን፣ ለውጥ የምትናፍቅ፣ ተስፋ የምታደርግ፣ በነገር ሁሉ መልካሙን ማየት የምትመርጥ ናት። ከአጭር ጊዜ ግለሰባዊ ጥቅም ይልቅ የረጅም ጊዜና የኅብረተሰብ ጥቅም የሚያማልላትም ናት። በሀገራችን ለውጥ መጥቶ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት የሚል ሀሣብ ሲያፈልቁ የድርጅቷን ሠራተኞች ሰብስባና ምሳ ጋብዛ አዲስ ተስፋና አዲስ ጅማሬ እንዳለ አብሥራ ከሥራው በተጨማሪ በግል የራሱን ፈጠራ ይዞ የሚመጣን ሠራተኛ በፋይናንስ እንደምታግዝ ቃል ገብታለች። ለቃሏ የተገዛች ስለሆነችም ቃሏን በተግባር አውላለች።
ሀገራዊውን ለውጥ በሙሉ ልቧ ተቀብላና ወደውስጧ አስርጻ ሠራተኛውም በአዲስ ተስፋ በግል ሕይወቱ፣ በሥራው እንዲሁም ለሀገሩ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ እንዲበረታ አሳሰበች። በአስተሳሰብ ላይ በተለይ ወጣቱ ላይ መስራት ይገባል በሚል ʻሀልዮተ ዓምባʼ የሚል ስብስብ ፈጥራ ወጣቱ በመነጋገር ችግርን በውይይት መፍታት፣ እንዲሁም ሃገራችን ካለችበት የሞራል ዝቅጠት እንዴት መውጣት ትችላለች በሚል በትምህርት ጥራት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በየሳምንቱ ተገናኝቶ ሃሣብ የሚያነሳ፣ የሚወያይ፣ የሚከራከርና የሚጽፍ ቡድን መሠረተች።
ይህ ስብስብ ኮሮና መጥቶ እስኪቀዛቀዝ ድረስ ለሁለት ዓመት አካባቢ በስኬት ዘለቀ። ጦርነቱ ለሁለተኛ ዙር በተጀመረ ሰሞን ተጠርጣሪዎች በጥቆማ ይታሠሩ ነበርና እርሷም ከቤቷ ተወሰደች። ማንነቷን የምናውቅ ሰዎች ልባችን ቢደማምና ሁኔታው ለርሷና ለቤተሰቧ አስደንጋጭ ቢሆንም፤ የጠቆመባት ሰው ሀሰተኛና ለውጡን መደገፏና ተስፋ ማድረጓ ያላስደሰተው የድርጅቷ ሠራተኛ መሆኑን ማመን ከብዷት ነበር።
ነገር ግን ከወንጀል ነጻ መሆኗ ተረጋግጦ ከ20 ቀን እስር በኋላ ስትወጣ ሊያጽናኗት የሚመጡ ወዳጅ ዘመዶቿ በመኪናዋ ቁልፍ መያዣ ላይ ያለውንና ሰው በዶ/ር ዐቢይ ፍቅር ሲናውዝ እርሷም የገዛችውን የርሱን ፎቶ አሁንም ይዛ መታየቷን ማመን አልቻሉም። “አሁንም? እንዲህ ትላለች እንዴ እና እርሷንስ ይበላት” ለሚለው አስተያየታቸው የምትሰጠው መልስ መንግሥት ምን አደረገኝ? ይህ ሁሉ ጉዳት አላስፈላጊው ጦርነት ያመጣብን ችግር ነው እንጂ ነበር መልሷ። ሰው ናትና ስትታሰር እንዴት ቂም አትይዝም? እንዴት አትማረርም? እንዴት አይከፋትም? እውነትም ለማመን የሚከብድ ነው። ነገር ግን እርሷ ማሰብና ማመዛዘን የምትችል፣ ላመነችበት የምትቆም፣ ነገርን ከራሷ አንጻር ብቻ የማታይ በሳልና ሩቅ አሳቢ ሰው ናትና የሆነው ይሄው ነው።
ይህም እንዳይበቃ ያው የጠቆመባት ሰው በሥራ ቦታዋ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎች እየላከ ይህንና ያንን ማስረጃ እያስጠየቀም ስቅሏን አሳይቷል። በዚህም የተነሳ ከጭንቀትዋ የተነሳ ጤናዋን ማጣት ጀመረች። ዳግም እንዳያሳስራት በመስጋትም በፍርሃት ራደች። ስለሆነም የዛሬ ሰላሳ ዓመት አገሯ ላይ ለመስራት ጓዝዋን ጠቅልላ የመጣች፣ አገሯ ውስጥ ብዙ ደክማ የተሳካላት ሴት፣ ከአገሯ እንደገና ለመሰደድ ተገደደች። ጦርነት ጣጣውና ጉዳቱ ብዙ ነውና ለዚህ ነው ይህ የሰላም ስምምነት ከፖለቲከኞች ፍላጐት በላይ ነው በሚል ይህን ሃሳብ ለማካፈል የፈለግሁት።
በተከሰተው ጦርነት በየጦር ቀጣናው ያሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ያሉ ወገኖችም በእጅጉ ውድ ዋጋ ከፍለዋል። ሕይወታቸውን፣ ጤናቸውን፣ ሥራቸውን፣ ቤተሰባቸውን ያጡ ብዙ ናቸው። ለረጅም ዘመን ያፈሩት ጥሪት ከእጃቸው በኖ የጠፋባቸውና ሕይወት እጅግ ፈታኝ የሆነችባቸውንም ቤት ይቁጠረው። ለዚህ ነው ይህ የሰላም ውል ሲፈረም እኔን ጨምሮ ብዙዎች እጅግ የተደነቁትና በእፎይታ ያነቡት።
ለሁለት ዓመት የናፈቁትን ሰላማዊ ታናሽ ወንድማቸው መቃብር ላይ ሄደው እርማቸውን ለማውጣት ከመፈለግ፣ የአዛውንት እህት፣ ወንድም፣ እናት አባትን ትከሻ አቅፎ ለመሳም ከመጓጓት፣ በረሃብና በጦርነት የተጐዱትን ወገኖች ለመደጐም ከመፈለግ የተነሳ። ከዚህም አልፎ ዘመናቸውን በሙሉ የደከሙበትን ሥራ በሰላም ለማስቀጠል ከመፈለግ፣ በወንድማማችነትና በመተማመን እንደወትሮው ከሌላው ሕዝብ ጋር በሰላም ለመኖር፣ ዳግም ውሾን ያነሳ ብሎ ምህረት አድርጐ የሰላም ኑሮን ለመኖር ከመፈለግ የተነሳ።
ሩቅ ሆኖ ለሚያጋግል የጦርነቱ ነበልባል አይፈጀውምና ስቃዩን ሊገነዘበው ፈጽሞ አይችልም። በጦርነቱ ውስጥ ለነበረ ግን ወላፈኑ የማቃጠል ጥግን በደንብ ያውቀዋልና ስለሰላም መሻቱ እጅጉን ግዙፍና የተለየ ነው። ከጦርነት ብዙ ተጎድተናልና ሰላማችንን አታቃሉብን፣ አታወሳስቡብን፣ ለኛ ልዩ ትኩረት የምንሰጠውና አንገብጋቢ ጉዳያችን ነውና!
በፍሬሕይወት ተሰማ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም