ስንሰቃይበት ከከረምነው የጦርነት ዜና (መርዶ) መለስ ካልን ሁለተኛ ሳምንታችን ነው። መርዶና ሰቆቃው መንግሥትና ሕወሓት ጦርነቱን ለማቆም በመስማማታቸው ዜና (በቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የተመራው፣ ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) የተካሄደውና የተደረሰበት የተኩስ ማቆምና የሰላም ስምምነት) መተካቱም እንደዚሁ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። (የሕወሓት ጦር እንዴት ትጥቅ መፍታት እንዳለበት የሚመክረው) ሁለተኛው ዙር ውይይትም በኬኒያ እየተካሄደ ነው ፤ ከዛም ቸር ቸሩን እየጠበቅን ነው።
ጉዳዩ ለብዙዎቻችን ግልፅ ነው ፣ በተለይ ከትኩስነቱ አኳያ፣ ወደ ግጭት አፈታት ማኅበረ-ባህላዊ እሴታችንና ስላለንበት ሁኔታ ጥቂት እንበል። ስንልም ከፈረሱ አፍ እንዲሉ፣ ከሚመለከታቸው ቢሆን ይመረጣልና አንድ ያለፈውን ዓመት ሁነት እንመልከት።
በዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት አዘጋጅነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት “ግጭቶችን እንዴት በሠላም መፍታት እንችላለን?” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምክክር ተካሂዶ እንደ ነበር ይታወሳል (አምና፣ ጁን 2021)።
በምክክሩ ወቅትም፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች “ባህላዊ የዕርቅና የግጭት አፈታት ዘዴ እሴቶችን ዋጋ ዝቅ አድርገን ማየታችን ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር ትልቅ ድርሻ አለው” ማለታቸውም አይዘነጋም። እርግጥና እውነት ነው፤ ማንነታችንን ሳይቀር ዝቅ አድርገን ተመልክተናል። ያም ውድ ዋጋ አስከፍሎናል። ውድ ዋጋ መክፈሉ እስካሁን ቆሟል ማለት ባይቻልም።
በምክክር መድረኩ የተገኙትና በድርጅቱ አማካሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የቀደምት ሃይማኖት ተቀባይና ጠባቂ፣ እንዲሁም የውብ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗን፤ ኢትዮጵያ እስካዛሬ ድረስ በሰላም የቆየችው ግጭት ሳይፈጠር ቀርቶ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ግጭቶቻቸውን በባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተጠቅመው መፍታት ስለቻሉ መሆኑን፤ ኢትዮጵያውያን አሁን ለገጠሙን አለመግባባቶች በየሃይማኖታችንና ባህላችን መሰረት ተወይይተን መፍታት እንደምንችል፤ እነዚህን እሴችንም ልናከብራቸውና ልንጠቀምባቸው የሚገባ መሆኑን …
መናገራቸው … ለአደባባይ በቅቶ ሰምተናል፤ አይተናልም።
ሌላው የሼህ ሙሐመድ ኑር አወል መልዕክት ነው፣ እሳቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ያኔ የእስልምና ሃይማኖት ወደ ሐበሻ ምድር መግባት ሲጀምር፣ ጥንት ኢትዮጵያውያን በውብ እንግዳ ተቀባይነት ባህላቸው መሠረት ሃይማኖታቸውን ሳይሆን ሰው መሆናቸውን ተረድተው ከነብዩ ሙሐመድ የመጡ እንግዶችን ተቀብለው ያስተናገዱ መሆናቸውን፤ እነዚህን ብንጠቀምባቸውና ብናስቀጥላቸው በሀገራችን ሰላምንና መዋደድን ለማምጣት ያሉን ሃይማኖቶችና ባህላዊ እሴቶቻችን ከበቂ በላይ እንደሆኑ ተናግረው ነበር።
አባ ገዳ ካላ ገዛኸኝ ወ/ዳዊት በበኩላቸው፣ ይቅርታ ከሌለ፣ ቂም በቀልነት ካልተተወ ሰላም እንደማይረጋገጥ ገልጸው፣ ሰላምን ማምጣት ካስፈለገ ቂም በቀለኝነትን መተው እና ለግጭት የሚዳርጉ ታሪኮችን ከማጉላት ይልቅ አንድና ሊያስተሳስሩን የሚችሉ እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባ፤ እንዲሁም፣ ሀገራችን ግጭትን ለመፍታት ድንቅ ባህላዊ ዘዴዎችን የመሠረቱ፤ የመሠረቱ ብቻም ሳይሆን ተጠቅመውባቸው እስካሁን በሰላም ኖረውባቸዋል፤ አሁንም ቢሆን መፍትሔው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓታችንን ብቻ በመጠቀም መፍታት የሚቻል መሆኑን፤ ነገር ግን ዛሬ ላይ ለእነዚህ እሴቶቻችን የምንሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የእርቅና የግጭት ባህሎቻችን ሰላምን ለማምጣት ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ተረድተን ልንጠቀምባቸውና ለመጪው ትውልድም ልናስተላልፋቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። ሌሎችም እንዲሁ።
አርትስ ቲቪ (የባህልና ቱሪዝም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ) ያነጋገራቸውና “ባህላዊ ግጭት አፈታት” በሚል ርዕስ የቀረበው ፕሮግራምም ይህንኑ የሚጋራ ሲሆን አጠቃላይ መደምደሚያውም ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ልናተኩር የሚገባ መሆኑ ላይ ነው።
አዎ፣ ኢትዮጵያ ምንም የሚጎድላት ነገር የለም። የማንነት ጉዳይ ስለ ሆነ ሳይሆን ስለ እውነት ለመናገር ሁሉ ነገር ሞልቷታል። በተለይም ግጭትን ከነሰንኮፉ ነቅሎ የሚጥል ለየት ያለ ባህላዊ ዘዴ(ዎች) አሏት ፣ ለዚህ ይህ ጸሐፊ በሀላባ ቁሊቶ ተገኝቶ በሴራ ባህላዊ ግጭት አፈታት የዳኝነት ሥርዓት ላይ የሠራ በመሆኑ ዘዴው ለዚህ እየተነጋገርንበት ላለነው ጉዳይ ራሱን የቻለ ማረጋገጫ ወይም አንዱ ማሳያ ነው ፤ በሌሎችም እንደዚሁ መሆኑን መገንዘብ፤ እንደ አንድ የአፍሪካ አካልም ጉዳዩን ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” ከሚለው አህጉራዊ አስተሳሰብ ጋር በማገናኘት ሰፋ ባለ መልኩ መረዳት ይቻላል።
ሕወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ- ፕሪቶሪያ ባለፈው ሳምንት ያደረጉትን ፀብ የማብረድና ተኩስ የማቆም ተግባርንም እዚሁ ላይ አንስቶ ከአስቀያሚ ፀብ ወደ ፍፁም ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ እንደምንችልም ምልክት ሰጥቷል።
የእኛ፣ የኢትዮጵያውያን ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶች ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም። ከላይ የኃይማኖት አባቶቹ ”ባህላዊ የዕርቅና የግጭት አፈታት ዘዴ እሴቶችን ዋጋ ዝቅ አድርገን ማየታችን …” ካልጎዳን በስተቀር አያት ቅድመ አያቶቻችን ቆጥረው ያስረከቡን እሴቶች እንኳን ለእኛ ለሌላውም የሚተርፉ ናቸው።
የዛሬው ጽሑፍ ዓላማ እሴቶቻችንን ማስተዋወቅ ሳይሆን ተጣልቶ የመታረቅና ሀገርን ያህል ነገር ለባዳ አሳልፎ ያለመስጠት ታሪካችን ያለና የነበረ መሆኑን ለማመላከት ነው። (እዚህ ላይ ከበርካታ ጥናቶች አንዱን እንኳን መጥቀስ ቢያስፈልግ የአብዱልፈታህ አብደላህ (2010)ን ”የኢትዮጵያ የሀገር በቀል የአስተዳደር፣ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቶች ማውጫ፤ ቅፅ 1” መጠቆም ይቻላል።)
እርግጥ ነው ማንም ስህተት ይሰራል። በሠራው ስህተትና በፈፀመው ተገቢ ያልሆነ ተግባር ደግሞ ይወገዛል። ይሁንና፣ ዛሬ ደግሞ ወደ ሰላም ተመልሻለሁ ቢል ለምን ተመለስክ ልንለው አይገባም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በየትም ይሁን በየት ሀገርና ሕዝብ የሚፈልጉትና እንደ ሰማይ የራቃቸው መሠረታዊ ጉዳይ ሰላም በመሆኑ ነው።
እዚህ ላይ በደማቁ ሊሰመርበት የሚገባውና ይህም ጽሑፍ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልዕክት “አይታረቁም” የሚለው ሚዛን በደፋበት ዓለም ሌላ ዙር ጦርነት የማስጀመሪያ ፊሽካውን ፊርርርር…. ሊያደርግ በተዘጋጁበት — ፊሽካውን ወደ ውስጥ እንዲነፋው ማድረጋቸውና ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ ማሳየታቸው ነውና ይህ እሴታችን ሊቀጥል ይገባል።
ሰላም ለኢትዮጵያ!!!
(MaR) ግርማ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም