ኢትዮጵያ ከኖረችባቸው ከ3ሺ በላይ ዓመታት አብዛኞቹን በጦርነት እንዳሳለፈች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በእነዚህ የጦርነት ዓመታትም ኢትዮጵያ ከነበረችበት የገናናነት ታሪክ ፍጹም ወደ ሆነ ድህነትና ኋላ ቀርነት አዘቅዝቃለች። በዓለም ላይ ግዙፍ የነበሩት የአክሱምና የዛግዌ ስልጣኔዎች በተከታታይ ጦርነቶች ላሽቀው ከገናናነት ወደ ቁልቁለት ለማሽቆልቆ ተገዳለች ።
ያለፉት 50 ዓመታትን እንኳን ብንመለከት ኢትዮጵያ ሦስት ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን አካሂዳለች። ለ17 ዓመታት በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከመርገፋቸውም በላይ ሀገሪቱ በድርቅና በስደት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ማሟሻ ሆናለች። ጦርነቱ በፈጠረው አሉታዊ ገጽታ ምክንያት የኢትዮጵያ ስም በየትኛውም የዓለም ዳርቻ ከርሃብና ከችግር ጋር እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።
እውነታው በመዝገበ ቃላት ጭምር ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከርሃብ ጋር አብሮ እንዲነሳ አድርጓል። በዚህም ምክንያት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀና ብለው እንዳይሄዱ፤ በሙሉ አፋቸውም ስለ ሀገራቸው እንዳይናገሩ አድርጓቸዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ይህንን አስከፊ ገጽታ ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች የሚፈለገውን ውጤት እያስገኙ አይደለም ።
ከ17 ዓመታቱ ጦርነት ካበቃ ጥቂት ዓመታት በኋላም የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሀገሪቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት ዳግም እንድትገብር አስገድዷታል ። በአፍሪካ እጅግ ዘግናኝና ኋላ ቀር በተባለለት በዚሁ ጦርነት ሀገሪቱ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሀብት ለመገበርም ተገዳለች ።
ይህ የጦርነት አዙሪት ቀጥሎ ፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ጦርነት ሌላኛው የኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ሆኗል ። ጦርነቱ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ቀስፏል ፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብና የሀገር ሀብት አውድሟል ። የሀገር ውስጥ ስደት እና መፈናቀል አስከትሏል ።የሀገሪቱን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ አጉድፏል።
በትናንቶቹም ሆነ በዛሬው የእርስ በእርስ ጦርነቶቻችን እንደሀገር ለልማት የሚሆነንን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ከማሳጣት ባለፈ ያገኘነው ምንም አይነት ጥቅም የለም። ይህንኑ በመገንዘብም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያካሂዱት የነበረውን ጦርነት ለማቆምና ሀገሪቱንም ወደ ተረጋጋ ሰላም ለመመለስ ታሪካዊ የሆነ ስምምነት አድርገዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በደቡብ አፍሪካ/ፕሪቶርያ ከተማ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ታሪክ ጽፈዋል። አስራ ሁለት አንቀጽ ያለው የሰላም ስምምነት በማውጣት ሰላምን አውጀዋል። ስምምነቱ ለዘመናት መፍትሔን በጠብመንጃ ለማምጣት ሲኬድበት የነበረውን ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሰበረና ስልጡን የሆነ አካሄድን ለሀገራችን ያስተዋወቀ ነው።
ኢትዮጵያውያን በጦርነት ጀግና ብንሆንም ሁሉንም ነገር በነፍጥ ብቻ እንፈታለን የሚል ዘመናትን የተሻገረ አስተሳሰብ ስናራምድ ቆይተናል። በጦርነት አንዱ ድል አድራጊ ሌላው ድል ተደራጊ፤አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እስካልሆነ ድረስ ጥማችንን አንቆርጥም። የፈለገውን ያህል የሰው ሕይወት ቢጠፋ፤ንብረት ቢወድም፤ዜጎች ቢራቡ ፤ቢሰደዱና ቢፈናቀሉ ጦርነት በአንዱ ድል አድራጊነት እስካልተደመደመ ድረስ ማባሪያ፤መቋጫ የለውም።
ከጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ቀናት የተካሄደውን የሰላም ውይይት ብዙዎች በዚህ መልኩ ይጠናቀቃል ብለው አልገመቱም ነበር። በተለይም በአሸናፊነትና ተሸናፊነት እሳቤ ውስጥ ሲሽከረከር የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ ዓውድ የሚያውቁ ሰዎች የሰላም ውይይቱ ያለስምምነት እንደሚጠናቀቅ ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።
እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ዓለምን ባስደመመ ሁኔታ ፤በሰላም ስምምነት ተቋጭቷል። በዚህም በጦርነት ሲንገላታ የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እፎይ ብሏል። ለቀጣይ ሀገራዊ ፖለቲካው በአዲስ መንገድ የሚሄድበትን ጅማሬ አብስሯል። ከሀገር ከዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት “ወሳኝ ቀዳሚ እርምጃ” ነው ሲሉ አወድሰውታል።
በአፍሪካ ኅብረት በኩል የተደረሰው ስምምነት የበርካቶችን ሕይወትና ኑሮን ያወደመውን ጦርነት ለማስቆም ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው ። “ኢትዮጵያውያን እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት የወሰዱትን ቆራጥ እርምጃ” እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ በውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ በሆኑት ጆሴፍ ቦሬል በኩል ፤በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ሲዋጉ የቆዩት ወገኖች ግጭት ለማቆም በመስማማታቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ጎረቤታችን ኬንያ የሰላም ስምምነቱን በቀድሞ ፕሬዚዳንቷ እሁሩ ኬንያታ አማካኝነት ወደ ውጤት እንዲደርስ አበክራ ሰርታለች። ለተገኘውም ውጤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬንያታ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበርም በውይይቱ የተሳተፉ አካላት ሲገልጹ ተሰምተዋል።
እሁሩ ኬንያታ ካደረጉት አስተዋጽዖ በተጨማሪ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ፣ በተገኘው ውጤት መደሰታቸውን ገልጸዋል። ኬንያ በቀጣይ የኢትዮጵያን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያውያን ይህ ስምምነት የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው ለአገራቸው አዲስ የሰላምና የብልጽግና ምዕራፍ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የእርቅ ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል። በተመሳሳይም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ለተደረሰው ስምምነት አሜሪካ ያላትን ድጋፍ ገለጸች።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ሁለት ዓመት የሞላውን ጦርነት ለማስቆም መስማማታቸውና የተጀመረውን የሰላም ሂደት ለማጠናከር ንግግራቸውን ለመቀጠል እንዲሁም ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ በመወሰናቸው የአሜሪካ መንግሥት አድናቆቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረቡትን ምስጋና አድንቆ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና ለልማት ያላቸውን ፍላጎት አሜሪካ እንደምትደግፍ ገልጿል።
በአጠቃላይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ግምትና አድናቆት የተሰጠው የሰላም ውይይት ለኢትዮጵያ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል። አንደኛውና የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ አሸናፊዎች እንዲሆኑ አድርጓል። ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸውና ለዜጎቻቸው አሳቢዎችና ተቆርቋሪዎች መሆናቸውን አረጋግጧል። ድሉም የመላ ኢትዮጵያውያን ድል እንደሆነና አሸናፊዋም ኢትዮጵያ መሆኗን አስረግጦ አልፏል።
ከዚህ ባሻገርም በዋነኝነት ለሁለት ዓመታት ያህል በጦርነት ስር ለነበሩት የትግራይ፤ የአማራና አፋር አካባቢዎች እፎይታን ማምጣቱ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በርካታ ዜጎች ረግፈዋል፤ ተርበዋል፤ ታርዘዋል፤ ብሎም በርካታ የሰብዓዊ ጥሰት ደርሶባቸዋል። ለስደትና መፈናቀልም ተዳርገዋል።
የሰላም ስምምነቱ የእነዚህን ዜጎች ሕይወት ከመታደጉም ባሻገር የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደርጋል። ከተረጂነት ተላቀው እራሳቸውን እንዲችሉ በር ይከፍታል። ከጦርነት ስነ ልቦና ተላቀው ወደ ተረጋጋ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ያስችላል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን እንደገና ለመመለስና ዜጎች ወደ ተለመደ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ያደርጋል። ለሁለት ዓመታት ያህል በተካሄደው ጦርነት የጤናና የትምህርት መሠረተ ልማቶች፤ ባንኮች፤ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል። ዜጎች በእነዚህ መሠረተ ልማቶች እጥረት ምክንያት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴቸው ተስተጓጉሏል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተዛንፈዋል።
የሰላም ስምምነቱ እነዚህን መሠረተ ልማቶች መልሰው እንዲጠገኑ እና ከነበሩበትም በተሻለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ በር ይከፍታል። ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው፤ ነጋዴዎች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ያስችላል። የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች በተሟላ መልኩ እንዲተገበሩና ዕድገቱም ሁለንተናዊ እንዲሆን ዕድል ይፈጥራል።
ጦርነት ልዩነትን የሚያሰፋ፤ጠላትነትን የሚፈጠርና ጥላቻን የሚያነግስ ነው።ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ዜጎች በጦርነት ምክንያት የተሳሰሩበት ገመድ ሊላላ ብሎም ሊበጠስ ይችላል። የሰላም ስምምነቱ በጦርነቱ ምክንያት ተፈጥሮ የቆየውን የሕዝቦች መራራቅ መልሶ ለመቀጠልና ኢትዮጵያዊነት ቦታውን እንዲይዝ ያደርጋል። የሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር መልሶ እንዲጠናከር በር ይከፍታል።በቀልና ቁርሾን ይሽራል። ጠላትን ያሳፍራል፤ወዳጅን ያኮራል።
ጦርነት የሀገርን ገጽታ ያበላሻል። የውጭ ጣልቃ ገብነትንም ያበረታታል። ስለዚህም ሰላም ውይይቱ በውጤት መጠናቀቁ ላለፉት ሁለት ዓመታት ጎድፎ የነበረውን የኢትዮጵያ ገጽታ መልሶ እንዲታደስ ያደርጋል። በዚህም ሸሽተው የቆዩ የውጭ ኢንቨስተሮች መልሰው ወደ ኢትዮጵያ እንዲያማትሩና ኢኮኖሚውም እንዲነቃቃ ያደርጋል። በሰላም ዕጦት ምክንያት ፊታቸውን አዙረው የነበሩ ቱሪስቶችም መልሰው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ዕድል ይሰጣል።
በኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት በርካታ የውጭ ተዋንያን የተሳተፉበትና በዚያው መጠን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፉ ጣልቃ ገብነቶች የተስተዋሉበት ነበር። በነበረው ጣልቃ ገብነትም በርካታ የዲፕሎማሲ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያን አጋጥመዋታል። እነዚህ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችና የዲፕሎማሲ መዛነፎች የሀገሪቱን ገጽታ ከመጉዳታቸውም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኗቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የሰላም ስምምነቱ በረጅሙ የሚዘረጉ እጆችን በአሉበት ለመከላከል ከማስቻሉም በላይ የተዛነፈውን ዲፕሎማሲ አካሄድም ለማስተካከል ይረዳል። ለኢትዮጵያ የልማት ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትም በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ከስምምነቱ በኋላ በዓለም ገንዘብ ድርጅት በኩል የታየውም ተነሳሺነት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
በፕሪቶርያ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ፋይዳው ከኢትዮጵያ የዘለለ ነው።ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የስበት ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ኢትዮጵያ ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ የሚፈጠሩ ጉዳዮች ምሥራቅ አፍሪካን በበጎም ሆነ በክፉ መንካቱ አይቀሬ ነው። ያለ ኢትዮጵያ ሰላም የምሥራቅ አፍሪካን ሰላም ማሰብ ዘበት ነው።
ስለሆነም የሰላም ስምምነቱ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ወደ ተረጋጋ ዓውድ በመመለስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። የብዙዎችን ሀገራት ቀልብ የሚስበውና የዓለም ኃያላን ሀገራት የትኩረት ማዕከል የሆነውን የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር አካባቢን እንቅስቃሴን ሰላማዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የማይተካ ሚና ይጫወታል።
አፍሪካውያን ለዘመናት ሲታገሉለት የኖሩትን የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ውጤት ማምጣት እንደሚችል በጥሩ ምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል ነው። አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የፕሪቶርያው ስምምነት ዋቢ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግር ሊፈታ የሚችለው በአፍሪካዊ መፍትሔ ብቻ ነው በሚል በቁርጠኝነት ስትንቀሳቀስ የቆየችና ለዚህም በርካታ መስዋዕትነቶችን የከፈለች ሀገር ነች። የአፍሪካ ሀገራት ከገቡባቸው ችግሮችም ለማላቀቅ በየቦታው በመገኘት የመፍትሔ አካል ለመሆን የምትጥር ሀገር ነች። ችግሮች በራሷ ውስጥ ሲከሰቱም ሊፈቱ የሚችሉት በአፍሪካዊ ዕሳቤ ነው በማለት መፍትሔ ስትፈልግ የቆየች ሀገር ነች። ይህ ዘመናትን የተሻገረ አስተሳሰብ ዛሬም መለያዋ ሆኖ ዘልቋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታትም በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተከሰተው ጦርነት ሊፈታ የሚችለው በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ብቻ ነው ብላ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። በርካታ የውጭ ኃይላትም ይህንን የፓን አፍሪካን ዕሳቤ በመቃወም በሀገሪቱ ላይ በርካታ ተጽዕኖዎችንና ማስፈራሪያዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሆኖም ኢትዮጵያ ለእነዚህ ማስፈራሪያዎች እጅ ሳትሰጥ እስከ መጨረሻው ተጉዛ ለችግሮቿ አፍሪካዊ መፍትሔ አግኝታለች።
በአጠቃላይ የሰላም ውይይቱ በሰላም መጠናቀቅ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። ዜጎች የሰላም አየር ለመተንፈስ ከመቻላቸውም በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸና ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም