ለአንድ ሀገር ሕልውና ሆነ ለዜጎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ሰላም ዋነኛው ጉዳይ ነው። ከዚህ የተነሳም ሀገራትና መንግሥታት ስለሰላም አበክረው ይሠራሉ። በውጤቱም ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማትን ያጸናሉ ።
ይህንን ሀገራዊ እውነታ ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማላበስ፤ ከዚያም በላይ ከሁከትና ከግጭት ነጻ የሆነች ዓለም ለመፍጠር ለዚህ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከመመሥረት ጀምሮ ሰላምንና የሰላም ጉዳይን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ በስፋት እየተሠራ ነው ።
ዓለም በቀደሙት ዘመናት ከጦርነትና ከግጭት ከሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ውጪ ያተረፈችው አንዳች ነገር ባለመኖሩና ካለመደማመጥ እና ካልተገባ የአስተሳሰብ መሠረት የሚፈጠሩ ውድመቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ አቅሞችንም ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ውጤቱ የታሰበውን ያህል ባይሆንም ዓለም ከቀደሙት ዘመናት የጦርነትና የግጭት ታሪኮች በመማር ስለ ሰላም የምታዜማቸው ዜማዎች አሁን ላይ በብዙ ተግዳሮቶች/ፈተናዎች ውስጥ ቢወድቁም የሰላም ድምጾች መሰማታቸውን አላቆሙም።
ዛሬም ስለሰላም የሚያዜሙ ድምጾች አሉ፤ ዛሬም ከጦርነትና ከግጭት ከሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ውጪ የሚገኝ አንዳች ትሩፋት የለም የሚሉ ድምጾች አሉ፤ ዛሬም በጦርነትና በግጭት የሚገነባ ነገ እንደሌለ አበክረው የሚናገሩ ድምጾች አሉ።
በተለይም እንደኛ ባሉ ዛሬን አሸንፈው ለመውጣት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ያሉ ሀገራትና ሕዝቦች በጦርነትና በግጭት ነገዎቻቸውን ከማጨለምና ትውልዶችን ተስፋ ቢስ ከማድረግ ባለፈ የሚያገኙት አንዳች ጠቀሜታ/ፋይዳ ሊኖር አይችልም ።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ከውጪ ኃይሎች ጋር ካደረግናቸው የነጻነትና የሉዓላዊነት ጦርነቶች ውጪ በእርስ በርስ ጦርነት የከፈልነው ዋጋ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያበቃ አይደለም። እንደ ሕዝብ ከአቅማችንና ከፈቃዳችን በላይ ዋጋ ከፍለናል ።
ባለፉት የአጼዎች ዘመን ለአጼዎች ስምና ክብር እንደ ሀገር የከፈልነው ዋጋ አሁን ላላቸው ሀገራችን አሁናዊ እውነታ ትልቁ ምክንያት እንደሆነ ለማሰብ የሚከብድ አይደለም፤ ከዚህ የሚከፋው ግን እውነታው በዛሬው ሀገራዊ የፖለቲካ/ ኢኮኖሚ አስተሳሰባችን ላይ ያጠላው ጥላ ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦች የወለዱት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የግራና ቀኝ መንገደኝ ሆነው ሳይገጣጠሙ ቀርተዋል። ይህም ሀገርን እንደ ሀገር፤ ሕዝባችንን እንደ ሕዝብ ከፍያለ ዋጋ አስከፍለውታል።
ሕዝባችን በብዙ ተስፋ የሚያምጣቸው የለውጥ ምጦች በዚህ የትናንት ጥላ እየተጨናገፉበት፤ ነገዎቹን በአግባቡ መሥራት የሚችልበትን ተስፋና ከዚህ የሚመነጭ ራዕይ አይቶ በሙሉ ልብና ቁርጠኝነት መሄድ ሳይችል ቀርቷል።
ከሁሉም የሚያሳዝነው ከትናንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፤ ከሚኖርበት ማኅበረሰብ መማር ያልቻለው አንዳንድ ጽንፈኛ የትግራይ ዲያስፖራ ጉዳይ ነው። ስለ ሰላም ትልቅ ቦታ የሚሰጥ፤ በዚህም ሀገሩን ሀገር አድርጎ ጥገኝነት በሰጠው ማኅበረሰብ መሀል ሰላምን ተቃውሞ አደባባይ ካልሞላሁ የማለቱ እውነታ ነው።
የትግራይ ዲያስፖራ ትናንት በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አደባባዮች ”የሰላም ሐዋርያ” ሆኖ ሲጮህ፤ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በአስቸኳይ ሰላም ይውረድ፤ ለዚህ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጊዜ መስጠት የለበትም ሲል ተሰምቷል ።
ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ከመፈለግ ይመስል የነበረው የዲያስፖራው የአደባባይ ጩኸት፤ በሁለቱ አካላት መካከል የሰላም ስምምነት በተፈረመ ማግስት መልኩን ቀይሮ የሰላም ስምምነት ለምን አስፈለገ፤ ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት ነው የሚሻለው ወደሚል ፍጹም የተቃረነ ጩኸት ተለውጧል።
በርግጥ ይህ ማኅበረሰብ የጦርነትን አስከፊነት ማሰብና መረዳት የሚያስችል ሰብዓዊ ማንነት አይኖረውም ብሎ ማሰብ ቀላል ሊሆን አይችልም፤ የትግራይን ምድር የደም ምድር/አኬልዳማ ያደረጉ ጦርነቶች የቱን ያህል የትግራይን ሕዝብ ዋጋ እንዳስከፈሉት የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በነጻነት ስም ለ17 ዓመታት በተደረገው ጦርነት ከስድስት አስርት ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶች ለሞት ተዳርገዋል፤ በመቶ ሺዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል/ይህ ለአደባባይ የበቃ መረጃን ብቻ ያካተተ ነው። በዚህም በማኅበረሰቡ ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ጫና ለመናገርና ለመጻፍ የሚከብድ አይደለም።
በኢትዮ-ኤርትራም ጦርነትም ቢሆን ክልሉ የጦርነቱ አውድማ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በርግጠኝነት ከክልሉ ነዋሪዎች ይህን ያህል ቁጥር ያለው ነዋሪ ሞተ የሚል መረጃ ባይኖርም፤ ክልሉ የጦርነቱ አውድማ በመሆኑ ብቻ የትግራይን ሕዝብ ሊያስከፍል የሚችለው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ስነልቦናዊ ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በተፈጠረው ግጭትም በአንድም ይሁን በሌላ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የግጭቱ ሰለባ ሆኗል። ለዚህ ሕዝብ ከሰላም ይልቅ ጦርነት መመኘት፤ ይህንንም በየአደባባዩ ያለ ሀፍረት ይዞ መጮህ የጤንነት አይመስልም።
በአንድ በኩል የትግራይ ሕዝብ ወገኔ ነው፤ ከኔ በላይ ሊቆረቆርለት የሚችል የለም የሚለው ይህ የትግራይ ዲያስፖራ፤ በሌላ በኩል የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም መልኩ ከጦርነት ሊወጣ አይገባም፤ ልጆቹን፣ ጥሪቱንና ተስፋውን ለጦርነት መማገድ አለበት እያለ ነው።
ዛሬ ላይ ለትግራይ ሕዝብ ጦርነትን የሚመኝለት ይህ ዲያስፖራ፤ ከሀገር እንዴትና ለምን እንደወጣ፤ ከሀገር ውጪም እንዴት እንደሚኖር ማስታወስ ይጠበቅበታል። ባህር ተሻግሮ በብዙ መከራና ስቃይ አሁን ያለበት ሀገር እየኖረ ያለው ምን ተስፋ አድርጎ እንደሆነ በአግባቡ ሊያስተውል ይገባል ።
ይህ ዲያስፖራ ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት ከመመኘቱ በፊት፤ ቀናትን አሸንፎ ከሀገር የተሰደደበትም ሕልሙን እውን ለማድረግ በቀን የቱን ያህል ሰዓት እንደሚሠራ፤ በዚህ እንኳን ሕልሙን ምን ያህል መግፋት እንደቻለ በአግባቡ ማጤን ይጠበቅበታል።
የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ነገ ላይ ሕልም ያለው ሕዝብ ነው፤ ይህ ሕልሙ በየትኛውም ሁኔታ በጦርነት እውን ሊሆኑ እንደማይችል ከትናንት ታሪኩ ለመረዳት አቅም የሚያጥረውም ሕዝብ አይደለም። ዛሬ ላይም እየሆነ ያለው ይሄው ነው። በሰላም ነገዎቹን የመፍጠር ቁርጠኝነት ነው።
ለዚህ ደግሞ ስለጦርነት እንደ አዲስ የሚሰብከው፤ የሚጮኸለት ኃይል አይፈልግም፤ ከትናንትም ከዛሬም ሕይወቱ በቂ ልምድ አለው። አሁን የሚፈልገው ሰላምና ልማትን የሚሰብከው ሐዋሪያ ነው። ወደ ነገ የተስፋው ዓለም የሚያሻግረውም መንገድ ይሄው ነው!
ከመርደቂዮስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም