(ክፍል አንድ)
ትዝብተ ሰብእ፤
በሰዋዊ የባህርያችን ትዝብት እንንደርደር። መራር ነገር ወደ ሆድ፣ ወደ ልብም ሆነ ወደ ስሜት ዘልቆ ለመግባት በእጅጉ ይገዳደራል። የልብንና የስሜትን ተግዳሮት ጉዳይ ወደ ኋላ ግድም ስለምንመለስበት ለጊዜው ወደ ሆድ ውስጥ የሚገባ መራራ ነገር ምላሳችንን ገና መንካት ሲጀመር የሚገጥመውን ፈተና በተመለከተ አንድ ግልጽ ማሳያ አስታውሰን ወደ ሌሎቹ ጉዳዮች እናመራለን።
የሰው ልጅ ወደ ሆድ ውስጥ የሚገባን መራር ነገር ለማጣፈጥ በፈጠረው ዘዴ እየተጠቀመ “መራራ ጠላቱን” ማሸነፍ ከጀመረ ዘመናት አስቆጥሯል። እንደ መተሬ ወይንም እንቆቆ የመረረ ባህላዊ መድኃኒት በሌሎች ሀገራት ባህል ውስጥ ይኑር አይኑር እርግጡን ለማወቅ ጥልቅ ምርምር ይጠይቃል። አይኖርም ለማለቱ ድፍረት ባይኖረንም የሀገራችንን ያህል በቁም እንደሚያንዘፈዝፉት እንቆቆና መተሬ ብርታት ይኑራቸው አይኑራቸው ለመገመት ይከብዳል።
ብልሁ የሀገሬ ሰው መተሬን የመሰለ መራር የባህል መድኃኒት “እየተቄለ” ወደ ሆድ እንዲዘልቅ የፈጠረው ጥበብ አጃኢብ ያሰኛል። እንኳን ሲቀምሱት ቀርቶ ስሙን ሲጠሩት ምሬቱ በስሜት የሚያንገሸግሸው መተሬ የሚወሰደው በሙዝ ወይንም ቤት ባፈራው ፈጠራ (ብዙ ጊዜ ገንፎ) እየተጠቀለለ ነው። ከዚያማ ምን ይጠየቃል ለቅጽበት ምላስን አጣፍቶ ወደ ሆድ የወረደው መተሬ እንክብል ተልዕኮውን አጠናቆ ከጥገኛ ትላትል የሚፈውሰው በሚያስደንቅ ፍጥነት ነው።
እንደሚመስለን ይህንን ባህላዊ ዘዴ መነሻ ያደረጉ የዘመናዊ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መራራ ኪኒኒዎች (ታብሌቶች) ምሬታቸው ሳይታወቅ እንዲዋጡ ለማድረግ ከምላስ እስኪወርዱ ድረስ ስኳር በመቀባት (Sugar Coated Tablets) ባህላዊውን ዘዴ በዘመናዊ ጥበብ ሳይተኩት አልቀረም::
“ሰማይ ተቀደደ ቢሉት፤ ሽማግሌ ይሰፋዋል አሉት”፤
ይህ ባህላዊና ዘመናዊ የምሬት ማለሳለሻና ማጣፈጫ ዘዴ እንደ መንደርደሪያ ሊጠቀስ የተፈለገበት ዋና ምክንያት ለሰላምና ይቅርታ ጥሩ የማሳያ አብነት ስለመሰለን ነው። የሰው ልጅ ለተለያዩ የፍቅር መገለጫዎች እጁን የሚሰጠው ቢግደረደርም ሳይዘገይ ነው። በውስጡ የተዳፈነውን ድፍረት፣ ወኔ፣ ጀግንነትም ሆነ ሌሎች አወንታዊ ስሜቶች ለክፉም ይሁን ለደግ ለመግለጽ ስሜቱ ቅርብ ነው። ግፋ ቢል መቆስቆሻው ፉከራ፣ ቀረርቶ፣ ወይንም “ጨክን” ይሉት አይነት ስሜት ማነሻሻዎች በቂና ከበቂ በላይ ናቸው።
ለይቅርታና ለሰላምስ? አንባቢው መልስ ለመስጠት የሚቸገር አይመስለንም። ሰላምና ዕርቅን ለማስፈን የሰው ልብ ምን ያህል በምሬት እንደሚሞላ በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል። ሰላምን አሜን ብሎ አክብሮ ዝቅ ለማለት ጭንቅ ጥብብ ያደርጋል፣ ያስምጣል፣ ስሜት በውስጥ ማንነታችን ይፋጫል፣ ይጋጫል፣ ይታወካል። በተለይማ ይቅር ተብሎ ሰላም እስኪወርድ ድረስ ያለው የምጥ ጣር ከወላድ እናት ምጥ ቢስተካከል እንጂ የሚያንስ አይሆንም። እኮ ስለምን ይሆን የሰው ልጅ “አጥፍቻለሁ” እና “ለሰላም እጆቼን ዘርግቼ ይቅርታውን ተቀብያለሁ!” ለማለት የሚቸገረው?
ለሰላምና ለዕርቅ የሚደረጉ የሽምግልና ድርድሮችና ውጣ ውረዶች በመተሬ መጠቅለያ ሙዝ ወይንም በስኳር ቅብ ኪኒኒዎች የሚመሰሉትም ስለዚሁ ነው። ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) የተደረሰበት ስምምነት ውጤቱ ለአሥር ቀናት ሲዘገይ በጉጉትና በልብ መንጠልጠል እንዲጠበቅ ምክንያት የሆነው በተለይም በሕወሓት በኩል ይኼው ሰዋዊ ባህርይ ትንቅንቅ ስለገጠመው ይመስለናል።
ኢትዮጵያ በዚህ ንግግር ገና ከጅማሬው ልቧን ለሰላም ክፍት አድርጋ በመዘጋጀት “መቶ በመቶ” ለማሸነፍ የበቃችው ከላይ የተጠቀሰው መሰል ሕዝባዊ የዕለት ተዕለት ባህሏና የከበረው ታሪኳ ብዙ ስላስተማራት እንደሆነ ለማመን አይከብድም።
በሁለቱ አካላት መካከል የተደረሰበት የሰላም ንግግር እንዲቋጭ የኢትዮጵያ መንግሥት ልቡን ያሰፋው በሀገሪቱ ላይ የተፈጸመው ግፍ ቀላል ስለነበር፣ የፈሰሰው የንጹሐን ደም ስለተዘነጋ፣ የተፈናቀሉና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ የደረሰባቸው ዜጎች እምባ ስለታበሰ ወይንም የወደሙት ንብረቶችና ሀብቶች በቀላሉ ስለታዩ አይደለም። በፍጹም። እነዚህ በደሎች ለዛሬውም ሆነ ለመጻኢው ትውልድ ጠባሳቸው በቀላሉ ይሽራል ተብሎ ስለታመነበትም አይደለም።
ይልቁንስ የመሪዎቻችን የማስተዋል ጥበብ፣ የአማካሪ ወዳጆቻችን የከበረ ቃልና የመላው ሕዝብ ኢትዮጵያ ጸሎት፣ መሻትና ጉጉት ዋናው መግፍኤ ምክንያት ስለሆነ ነው። የፈሰሰን ደም የሚያደርቀው፣ የቆሰለን ስሜት የሚፈውሰው በጦርነት በማሸነፍ በሚገኝ ድል ብቻ ሳይሆን ዋናው መደላድል “እርቀ ሰላም” በማዕከላዊነት ሲሰፍን ብቻ ነው።
በአንጻሩ የወዲያኛው ቡድን ቤተኞች የሆኑ “የዲያስፖራ ምን ግዴዎች” የሰላም ንግግሩ “በሰላም” መቋጨቱ እያንገበገባቸው የሚኖርባቸውን ባዕዳን ሀገራት የሚያምሱት፣ አደባባዮችን የሚያውኩት፤ አውራ ጎዳናዎችን የሚዘጉትና የየሀገሩ የመንግሥታዊ ተቋማት ባለስልጣናት በሰላም ተግባራቸውን እንዳይከውኑ በጨረባ ጩኸት እያወኩ ሰላም የሚነሱት በርግጠኝነት “ሕዝባችን” እያሉ በአንደበታቸው ብቻ ለሚያንቆለጳጵሱት የትግራይ ሕዝብ ተጨንቀው ሳይሆን “የሰላም ንግግሩ መቋጨት” የእነርሱን እኩይ ዓላማ ተርትሮ እርቃናቸውን እንዳያጋልጣቸው ፈርተው ጭምር ነው። በጦርነቱ የሚፈሰው የንጹሐን ደምና የሚወድመው የሀገርና የዜጎች ሀብት ግድ ያልሰጣቸው “ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ እንደሚውሉት የኮምፒውተር ጌም” የሕዝባችን ሞትና መፈናቀል ስለቀለለባቸው ጭምር ነው።
በአንድ ሀገር ዕርቀ ሰላም የሚሰፍነው አስተዳዳሪው መንግሥት በሚወስዳቸው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ የልብ ስፋት ብቻም አይደለም። ዜጎችም ልባቸው ሊሰፋ፣ መንፈሳቸው ተረጋግቶ በምሕረትና በይቅርታ ዝግጁ ሲሆኑም ነው። በተለይም ለመቶ ፐርሰንት ጥቂት ፊሪ የሆነው ሕዝቧ በአንድም ሆነ በሌላ የእምነትና የሃይማኖት ቤተሰብ አባል ነው በሚባልበት ሀገርና በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት “ይቅርታና ሰላም” እንደ ክረምት ዝናብ በሚዥጎደጎድባት ኢትዮጵያ ምሬትን ሳይሆን ምሕረትን ማስቀደም ችግር ባልሆነ ነበር።
በደልን ይቅር መባባልና ከሰላም ጋር መስማማት ለውስጥ ስሜት ፈውስን፣ ለሀገር በረከትና እረፍትን፣ በፈጣሪም ዘንድ በእጅጉ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም። ችግሩ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” እብሪትና የልብ ድንዳኔ እንደ ጭንጫ ጠንክሮ እልኸኛ ስለሚያደርግ ብቻ ነው። ከወዲያኛው ወገን የሚደመጠው “ዲያስፖራዊ የቁራ ጩኸት” ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን ይሄው አፍቅሮተ ራስና ከእኛ ወዲያ ለአሳር ልክፍት ነው።
ይህ ጸሐፊ ስለ እርቀ ሰላም ሲያስብ ሁሌም ፈጥኖ ወደ አዕምሮው የሚመጣና በብዙ አጋጣሚዎች የሚጠቅሰው አንድ ታሪክ ይታወሰዋል። ታሪኩ ልቦለድ ሳይሆን በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በሀዲያ ዞን፣ በሶሮ ወረዳ በኦሞሽራ ቀበሌ የተፈጸመ ነው። ስማቸው የሚጠቀሰው ባለታሪኮችም እውነተኞቹ የድርጊቱ ፈጻሚዎች መሆናቸውን ማረጋገጫ እንሰጣለን። ወደ ትረካው እንዝለቅ።
አቶ ለቴቦ አርበጮ የሚባሉ አንድ አባት ዕድሜዋ ሰባት ዓመት የሆናት መካሜ የምትባል ሴት ልጅ ነበራቸው። በሆነ አጋጣሚ በተፈጠረ ሁኔታ አቶ ለቴቦ ከሚጎራበታቸው አንድ ቤተሰብ ጋር የከረረ ፀብ ውስጥ ገብተው ነበር። ይህንን ፀባቸውን በእርቀ ሰላም ለመፍታት የሚያስችል ሙከራም በሁለቱ ጎረቤታማቾች መካከል ሳይፈጸም ቀናት ነጉደዋል። ሁለቱም ቤተሰቦች በየቤታቸው አንዱ የሌላውን በደል እየተረከ ሲያወራ ውሎ የሚያድረውም የየቤቱ ሕጻናትና ወጣት ልጆቻቸው ባሉበት ስብስብ መካከል ነበር። ይህ በቁጭትና በእልህ ሲወራ የኖረው ቂምና ቁርሾ ከአዋቂዎቹ ይልቅ በታዳጊ ልጆቹ ዘንድ እጅግ ምሬትን መፍጠሩን ታላላቆቹ ልብ ሊሉ አልቻሉም።
አንድ ዕለት ከጠበኞቹ ቤተሰቦች መካከል የአንደኛቸው ታዳጊ የአሥራ ሁለት ዓመቱ ማቴዎስ ቤተሰቦቹ ሲያወሩ በሰማው ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ ስላቄመ ሌላኛውን ቤተሰብ ለመበቀል ልቡ ለክፋት ድርጊት መነሳሳት ጀመረ። ስለሆነም የአቶ ለቴቦን ቤተሰብ ለመበቀል በማሰብ ትኩረቱን በሰባት ዓመቷ መካሜ ላይ ማድረግን ተያያዘው። እንዴት ይህቺን ታዳጊ ገድሎ የቤተሰቡን ቂም እንደሚፈውስም ማሰላሰል ጀመረ። አሰላስሎ ብቻም አልተወም እንዴትና መቼ ዕቅዱን ለመተግበር እንደሚችልም ራሱን ዝግጁ አደረገ።
በአንድ ክፉ ዕለት መካሜ ከብቶች እየነዳች ወደ ወንዝ ስትወርድ ማቴዎስ ከበስተኋላዋ እየተከተላት እንደነበር አልጠረጠረችም። ማቴዎስ ድንገት እመር ብሎ እጅና እግሮቿን ጠፍሮ ካሰረ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ ገደላት። አስከሬኗ እንዳይገኝም በአካባቢው በሚገኝ ወንዝ በቦረቦረው ጉድጓድ ውስጥ ጣላት።
ድርጊቱ እንደተሰማ የአቶ ለቴቦ ቤተሰብ በሀዘን ተመትቶ እርር ኩምትር አለ። በአካባቢው እረኞች ጥቆማ የተገኘውን የመካሜን አስከሬን አንስተው በባህላቸው መሠረት የቀብሯን ሥነ ሥርዓት ቢፈጽሙም መሪሩ ሀዘናቸው ከልባቸው ሊወጣ ከቶውንም አልቻለም ነበር። ምሥጢሩ ውሎ ያደረው ለጥቂት ቀናት ብቻ ስለነበር ገዳዩ ማቴዎስ መሆኑ ተረጋገጠ።
ጉዳዩ በቸልታ ሊታለፍ የሚገባው ስላልነበር የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች በእርቀ ሰላም ለመፍታት ምክክር ጀመሩ። የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች በሽማግሌዎቹ ፊት ቀርበው በሞቀው ጉርብትናቸው መካከል የገባው ነፋስ ምክንያቱ ምን እንደነበረ በዝርዝር አስረዱ። ይህ ለረጅም ጊዜ ሳይፈታ የቆየው የሁለቱ ጎረቤታማቾች ቂምና ቁርሾ ጉዳዩ ጭርሱኑ በማይመለከታት ታዳጊ ንጹሕ ደም መደምደሙ የባሰ ቁርሾውን ሊያባብስ እንደሚችል የተረዱት ሽማግሌዎች “በደም ማድረቂያው ዘዴ” ጉዳይ ላይ አብዝተው መወያየት ቀጠሉ።
በቀሉ መቀጠል ስለማይገባው ሽማግሌዎቹ በአቶ ለቴቦ ላይ እንደ እሬት የሚመር፣ እንደ መርግ የሚከብድ ውሳኔ በማሳለፍ በተግባር እንዲፈጽሙ ግድ አሏቸው። “ከፊተኛው የኋለኛው” እንዲሉ ለሰላም ሲባል መከራ በተሸከመው ቤተሰብ ጫንቃ ላይ ሌላ ቋጥኝ ጫኑባቸው።
በውሳኔው መሠረትም አቶ ለቴቦ የልጃቸውን የመካሜን ገዳይ ማቴዎስን ልክ ለሟች ልጃቸው እንደሚያደርጉት ለቀናት አቅፈውት እንዲያድሩ ተበየነባቸው። ደመኛውን ወጣት ልክ እንደ ወለዱት ልጅ የፍቅር ጠረን እየሰጡ አቅፎ በመተኛት የተፈጸመው የባህላዊው እርቀ ሰላም እጅግ የሚከብድ ቢሆንም የሁለቱን ቤተሰብ ጉርብትናና መልካም ወዳኝነት “በይቅር ለእግዚሃር” አጠናከረው እንጂ ከነቂማቸው እንዲኖሩ አላደረጋቸውም። የመፈዋወስ መድኃኒት ሆናቸው እንጂ ቁርሾውን እያመነዠጉ እንዲኖሩም አላደረጋቸውም። እስከ ደም ማፍሰስ የተፈጸመን ድርጊት በእርቀ ሰላም ለመፍታት ይህ ታሪክ ሁነኛ ማስተማሪያ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያም በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ያሸነፈችው በተመሳሳይ ውሳኔ እንጂ ፖለቲካውና ዲፕሎማሲው ብቻ በተጫወቱት የአሸናፊነት ሚና አይደልም። በፍጹም። ታላቋ ኢትዮጵያ “ዕርቅ ደም ያድርቅ” ብላ ግፍ የፈጸመባትን ቡድን ለማቀፍ የጨከነችው ባህሏም ታሪኳም የከበረ ስለሆነ ነው። ይህ ልበ ሰፊነቷና አሸናፊነቷ ለአህጉረ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለግዙፏ ዓለማችንም ታላቅ ትምህርት እንደሚሆን ይታመናል። “ዕርቅ ደም ያድርቅ” ይሏ እንዲህ ነው። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም