የታሪክና የጊዜ ሂደት የሰውን ልጅ ከኢንተርኔት (በይነ-መረብ) ውጭ ሆኖ መኖር እጅግ አስቸጋሪ፣ ምናልባትም የማይቻል፣ የሆነበት ዘመን ላይ አድርሶታል። ዓለምን ያለኢንተርኔት ለማሰብ፣ ትውስታንና ግንዛቤን ወደ መጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ የዝግመተ-ለውጥ ደረጃዎች በመመለስና በማሰላሰል ማሰብ ሳይሻል አይቀርም።
‹‹የቴክኖሎጂ ዘመን›› የሚባለው የአሁኑ ጊዜ፤ የረቀቀውን ሰው ሠራሽ የልኅቀት ቴክኖሎጂ (Artificial Intelligence) በመጠቀም የሰውን ኑሮ ቀላል ያደረጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኝበት ወቅት ነው ሀገራትም መጭውን ጊዜ በማሰብ ቴክኖሎጂን እንደዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በመያዝ ምጣኔ ሀብታቸውን በቴክኖሎጂ የሚታገዝ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ ነው።
በአሁኑ ወቅት ቀልጣፋና ውጤታማ የሥራ እንቅስቃሴን ከኢንተርኔት ነጥሎ ማሰብ አይቻልም ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ተግባቦቶችና ግብይቶች መሰረታቸውን በኢንተርኔት ላይ አድርገዋል ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከፈጣንና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ብቻም ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጭ የሆነው የዓለም ሕዝብ ቁጥር የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን ከቻለው ጋር የሚስተካከል እንደሆነ የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ጉባኤ መረጃዎች ያሳያሉ።
ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የዓለምን እንቅስቃሴ በተቆጣጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገትን ከቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት ውጭ ማሰብ የሚቻል አይሆንም ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለማችን ቁንጮ የሆኑት ልዕለ ኃያላን ሀገራት የቴክኖሎጂ ዘርፋቸው እጅግ የተራቀቀ ነው የቴክኖሎጂ ፈጠራና ስርጭት ደግሞ ያለኢንተርኔት መሰረተ ልማት አቅርቦት አይታሰብም በተለይ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴያቸውን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ባሸጋገሩ ሀገራት የዜጎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ያለኢንተርኔት የሚታሰብ አይሆንም በእነዚህ ሀገራት የዜጎች ተግባቦት፣ ግብይትም ሆነ የስራ ግንኙነት ኢንተርኔትን መሰረት ያደረገ ነው።
ዘመኑ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በየጊዜው ይፋ የሚሆኑበት የታሪክ ምዕራፍ በመሆኑ፣ ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ተያያዥ የሆኑ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም ይስተዋላሉ በየጊዜው ይፋ የሚደረጉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰዎችን ሕይወት ቀላል ለማድረግ ሚናቸው የላቀ ቢሆንም፣ ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር የሚፈጠሩት ችግሮች ደግሞ ቀላል የማይባሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ያሳርፋሉ ስለሆነም የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች የሚያስገኟቸውን እድሎች በሚገባ ለመጠቀም እና ቴክኖሎጂ ወለድ ችግሮች የሚፈጥሯቸውን ጫናዎች ለመቀነስና ለማስወገድ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መፍጠር ይገባል ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢንተርኔት አስተዳደርን (Internet Governance) በሚገባ መምራት ያስፈልጋል።
የኢንተርኔት አስተዳደር ከኢንተርኔት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች የመምራት ተግባር ሲሆን፣ በቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ኢንተርኔት ተኮር በሆነው የሰዎች አለታዊ እንቅስቃሴ መብዛት ምክንያት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረትና ክትትል የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኗል።
የኢንተርኔት አስተዳደር በአሁኑ ወቅት የዓለም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በሚያደርጓቸው ጥረቶች ትልቅ ትኩረት እየሰጧቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከሆነው ከሳይበር ደህንነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው የሳይበር ዘርፍ ሀገራት የቴክኖሎጂ የበላይነታቸውን ለማሳየት ጭምር የሚጠቀሙበት መሳሪያ ከሆነ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ተቆጥረዋል በፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥ የገቡ ሀገራት አንዱ የፍልሚያ ግንባራቸው የሳይበሩ ዘርፍ ሲሆን መመልከት እየተለመደ ነው ሀገራት በሳይበር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ልቆ በመገኘት በሌሎች ሀገራት ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር እልህ አስጨራሽ ፉክክር በማድረግ ላይ ናቸዉ።
የሳይበር ምኅዳር ዓለም አቀፍ ሉላዊነት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ከሳይበር ምኅዳር ውጭ መሆን የማይታሰብ ሆኗል ያለ ሳይበር አቅም እንደሀገርም ሆነ እንደተቋም ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ ይቅርና ህልውናን ማስጠበቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል በአጠቃላይ ውጤታማ የሳይበር ቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ያላረጋገጠና የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት ያላስጠበቀ ሀገር ሉዓላዊነቱንና ብሔራዊ ጥቅሙን ማስጠበቅ የማይችልበት ወቅት ላይ ተደርሷል።
የኢንተርኔት አስተዳደርን ለመምራትና ለማቀናጀት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ በየዓመቱ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ (Global Internet Governance Forum/IGF) ነው ጉባኤው እ.አ.አ በ2006 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ የተለያዩ ተሳታፊዎችንና ባለድርሻ አካላትን ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ከበይነ-መረብ አስተዳደር ጋር በተያያዙ ፖሊስዎች ላይ ውይይት የሚካሄድበት መድረክ ነው መድረኩ ውሳኔ አመንጪና ሰጪ ለሆኑት ለግሉ ዘርፍና ለመንግስት የመረጃና የፖሊስ ሀሳብ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ጉባኤው ከተለያዩ ሀገራትና ዘርፎች የተውጣጡ ተወካዮች ስለበይነ መረብ ዘርፍ እድሎችና ፈተናዎች የሚወያዩበት፣ መረጃ የሚለዋወጡበትና ልምድ የሚቀስሙበት እንዲሁም የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መድረክም ነው።
ጉባኤው የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ደህንነትንና አስተማማኝነትን የሚያመቻቹ የፖሊስ ጉዳዮችን ያነሳል፤ በታዳጊ ሀገራት ያለው የበይነ መረብ መሰረተ ልማት እንዲሻሻል፣ ባለድርሻ አካላት በበይነ መረብ አስተዳደር ላይ ያላቸው ሚና የተቀናጀ እንዲሆንና ለበይነ መረብ አስተዳደር የአቅም ግንባታ ግብአቶችንና ምክረ ሃሳቦችንም ያቀርባል።
በይነ-መረብ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ ከሀሰተኛ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ጉዳቶችም አሉት ጉባኤውም እነዚህን ጉዳዮች በሕግና በሌሎች ማዕቀፎች መፍትሄ እንዲያገኙ ምክረ ሃሳቦች ይመላከቱበታል።
17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት (በይነ መረብ) አስተዳደር ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሕዳር 19 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ኢትዮጵያ 17ኛውን ይህን ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለውጦችንና እድገቶችን እያስመዘገበች በመሆኑ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፀድቆ ወደ ስራ በመግባቱ፣ የተለያዩ የማሻሻያዎች የተደረጉበት የቴሌኮም ዘርፍ ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት በመደረጉ እና የቴሌኮምና የበይነ-መረብ ተደራሽነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ በመሆኑ እንደሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ 56 ሚሊየን ገደማ የሞባይል እና ከ20 ሚሊዮን በላይ የበይነመረብ አገልግሎት ተጠቃሚ ዜጎች መኖራቸውም ለጉባኤው አዘጋጅነት እንዳገዛትም ተገልጿል ጉባኤው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት የማዘጋጀት ልምዷን ለዓለም ከምታሳይባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
በ17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ጉባኤ ላይ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ2000 እስከ 2500 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል ጉባኤው ከሚመክርባቸው ጉዳዮች መካከል ከበይነ- መረብ ግንኙነት ውጪ የሆኑ ህዝቦችን ማገናኘትና ሰብዓዊ መብትን መጠበቅና ሰዎችን ከጥቃት መከላከል፤ ዳታን በአግባቡ ማስተዳደርና የግል ዳታ ጥበቃ፤ የተቆራረጠ የኢንትርኔት አገልግሎትን መቅረፍ፤ የኢንተርኔት ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ጥበቃ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስፈን እንዲሁም የመጪው ጊዜ ቴክኖሎጂዎች የሆኑትና እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ያሉ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ።
የዘንድሮውን ጉባኤ የማስተናገድ ኃላፊነትን 16ኛውን ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ካስተናገደችው ከፖላንድ የተረከበችው ኢትዮጵያ፣ ጉባኤውን በብቃት ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ተገልጿል ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ ለዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባዔ መሰረት ይጥላል የተባለውና ባለፈው ሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም የተካሄደው የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ ነው፡፡
‹‹ኢንተርኔት ለአካታች ልማት›› በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ጉባኤው ስለበይነመረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች እንዲሁም ተመጣጣኝ እና ትርጉም ስላለው የበይነመረብ ተደራሽነት መክሯል 17ኛውን ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ፤ በጉባኤው ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች ሁሉን አቀፍ፣ ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተናበቡና ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑ የተገለፀውም በዚሁ ብሔራዊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ ላይ እንደነበር ይታወሳል
ኢትዮጵያ 17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት ከኢንተርኔት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያሉባቸው ችግሮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁም እና ለፖሊስ አውጪዎች መነሻ ሀሳብ የሚገኝበት እንዲሆን እንደሚሰራ በመጠቆም፣ የአፍሪካ ሀገራት በጉባኤው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርባለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሴክሬታሪያት የኢትዮጵያን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ዝግጅት አድንቋል ሴክሬታሪያቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና ከኢትዮጵያ የበይነ መረብ አስተዳደር አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር የመከረ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ጉባኤውን ለማስተናገድ ላከናወነችው ተግባር አድናቆቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን በማስተናገዷ ታገኛቸዋለች ተብለው ከሚጠበቁት ጥቅሞች መካከል የሀገሪቱን መልካም ገጽታ፣ እድገትና አቅም ማስተዋወቅ፤ ሀገሪቱ የጀመረችውን የቴሌኮም ሪፎርም ኢንዲሁም በዘርፉ ያሉ ውጤቶችን ለሌሎች ሀገራት ማሳየት፤ ከተለያዩ ሃገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት እና የልማት አጋሮች ጋር ትስስር መፍጠር፤ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚሉት ይገኙበታል።
ከአዲሱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊስ ዓላማዎች መካከል አንዱ ምቹ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር እንዲፈጠር የሚያስችሉ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን መዘርጋት ነው ይህ ዓላማ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከበይነ መረብ አስተዳደር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው ይህም የፖሊስው ውጤታማነት በበይነ መረብ አስተዳደር ብቃት እንደሚመዘን ማሳያ ይሆናል።
በሌላ በኩል ከአስር ዓመቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል የዘርፉን ውጤታማነት ለማጎልበት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡት ግብዓቶችና አቅጣጫዎች መካከል የኢንተርኔት አቅርቦትና አስተዳደር ስራ አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል በዚህ ዘመን በተቋምም ሆነ በሀገር ደረጃ በኢንተርኔት አስተዳደርና ደህንነት ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን ካልተቻለ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህልውናም ከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚገባም አያጠራጥርም ስለሆነም አቅርቦቱም ሆነ አስተዳደሩ አስተማማኝና ውጤታማ የሆነ የኢንተርኔት መሰረተ ልማት እውን በማድረግ ሀገራዊ የልማት እቅዱን ለማሳካት ጥረት ማድረግ ይገባል ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/ 2015 ዓ.ም