ዛሬ ስለ እኛና ስለዛኛው ትውልድ እናወራለን። ለመሆኑ ያኛው ትውልድ ማነው? ያኛው ትውልድ ከዚህኛው ትውልድ በምን ይለያል? ያኛው ትውልድ ኢትዮጵያን የሰራ የኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ ነው። እኛን ያቆመን፣ ለእኛ ታሪክና ነጻነትን የሰጠ ባለማዕረግ ትውልድ ነው። ያኛው ትውልድ በሚደነቅ ባህል፣ በሚደነቅ አብሮነት የምትደነቅ ሀገር የሰራ የእውቀትና የጥበብ ባለቤት ነው።
በደሙ ሀገር ያቆመ፣ በአጥንቱ የነጻነት ቤት የሰራ እርሱ ነው..ያኛው ትውልድ። ያኛው ትውልድ በእኔና በእናንተ ልብ ውስጥ ታሪክ ያስቀመጠ፣ ስርዓት ያበጀ የማንነታችን ዋልታና ማገር ነው። ዛሬ ብቻ አይደለም፣ ነገ ብቻ አይደለም፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እስካሉ ድረስ ሁሌም የሚታወስ የሀገርና ህዝብ የትውልድም ጌጥ ነው።
ያኛው ትውልድ ከዓለም በፊት ገኖ፣ ከፍጥረት በፊት ሰልጥኖ እኔና እናንተን በጥበብና በስልጣኔ ከፊት ያስቀደመ ባለውለታ ትውልድ ነው። እርሱ በማይጠፋና በማይደበዝዝ እውነት ለዛሬ ማንነታችን ምሰሶ ነው። ከአጥንቱ ወጋግራ ከደሙ እያጠቀሰ ሀገር የሰራ፣ ህዝብ የፈጠረ ባላደራ ትውልድ ነው።
ከላቦቱ ኩሬ ከወዙ እያጠቀሰ እኔና እናንተን ያበጀ፣ ለእኔና ለእናንተ ታሪክና ትውፊት የተወ የሚደነቅ ትውልድ ነው። እኔነትን ሽሮ እኛነትን ያጸደቀ፣ ብሔርተኝነትን ተጸይፎ ኢትዮጵያዊነትን የተከለ አራዳ ትውልድ ነው። በአንድነትና በአብሮነት የተደነቀ የእያንዳንዳችን የኩራት ምንጭ ነው።
ያኛው ትውልድ በብሄርና በሃይማኖት መለያየትን ሳያውቅ በአንድ ታላቅ ስም በኢትዮጵያዊነት የቆመ፣ በሀገሩና በርስቱ ለመጡበት ቀልድ የማያውቅ ደግ አዛኝ ፈርሃ እግዚአብሔር ውስጡ ያደረበት ትውልድ ነበር። ያኛው ትውልድ በብዙ ነገሯ የምትደነቀውን የኩራት፣ የጽናት፣ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን ሀገረ ኢትዮጵያ የሰጠን ባለውለታችን ነው።
እየተራበ ያጠገበን፣ እየተጠማ ከወይን የጣፈጠ የላቡን ወዝ እንጥፍጣፊ ታላቅ ሀገርና ህዝብ የሰጠን እርሱ ነው። ሳይማር ለዘመናዊው ዓለም መደነቂያ የሆነ ስልጣኔን የሰጠን፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ተንግርት የሆኑ አክሱምና ላሊበላን የፈለፈሉ እጆች ባለቤት ነው። ሳይለብስና ሳያጌጥ ኩታና ካባ ያለበሰን፣ ከአንደበቱ ነውር የማይወጣ፣ ከእሱ በፊት በነበሩ በአባቶቹ ህግና ስርዓት ወጥቶ የሚገባ ትውልድ ነው።
ከዓለም በፊት፣ ከሰው ልጅ በፊት፣ ከስልጣኔ በፊት ራሱን በህግና ስርዓት የሚያስተዳድር በኩረ ጥበብ ባለቤት ነበር። ዛሬ ላይ እንደ ሀገር የምንኮራባቸው፣ እንደሀገር ያቆሙን፣ እንደታሪክ ቀና ያልንባቸው እንቁዎቻችን የነሱ የጥበብ ውጤቶች ናቸው። ዛሬ ላይ በዓለም ላይ የታወቅንባቸው፣ በዓለም ላይ ታላቅ የሆንባቸው ትውፊቶቻችን የዛኛው ትውልድ የአብራክ ክፋዮች ናቸው።
ዛሬ ላይ ነጻና ኩሩ፣ ጽኑና አይበገሬ ሆነን በአፍሪካና በዓለም ላይ ከፍ ያልነው በነሱ ነው። ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ባለታሪክ፣ እንደ ህዝብ ባለማዕረግ ሆነን የቆምንው በነዛ ትጉ ነፍሶች ነው። ዛሬ ላይ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነትና የቀና ማለት ፋና ወጊዎች ሆነን የምንታየው በእርሱ ነው..በዛኛው ትውልድ…በአባቶቻችን።
እኛስ የዛሬዎቹ ምን አይነቶች ነን? እኛ የዛሬዎቹ እንደ አባቶቻችን የሆነ ምንም ነገር የለንም። እስካሁን ድረስ ያኛው ትውልድ በሰጠን እውነት ላይ የቆምን ነን። ለራሳችንም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ የሚሆን አዲስ እውነት፣ አዲስ ታሪክ አዲስ ሀገር እየሰራን አይደለም።
አይደለም አዲስ ታሪክ ልንጽፍ ቀርቶ አባቶቻችን በነፍሳቸው ተወራርደው የሰጡንን እውነት እንኳን ውሸት ነው እያልን ነው። አይደለም አዲስ ታሪክ ልንጽፍ ቀርቶ ያኛውን ትውልድ በላቡ ወዝ ሞቶና ተጎሳቁሎ የጻፈልንን የምንወቅስ ወቃሽ ትውልድ ወጥቶናል። አይደለም አዲስ ሀገር ልንፈጥር ቀርቶ በብሔር ስም የአባቶቻችንን የነጻነትና የአደራ ምድር ለማፍረስ መዶሻ እያነሳን ነው።
ተምረን እንዳልተማርን አውቀን እንዳላወቀ መሆን መገለጫችን ሆኗል። ድሮነትን ተጸይፈን “አራዳ” ነን ባይ “ፋራዎች” ሆነን እየኖርን ነው። ነፍሳችንን ያለመለመ የዛኛው ትውልድ አሻራ መልካችን ላይ የለም። ምናችንም አባቶቻችንን አይመስልም። ተምረናል ግን አናውቅም። ሰልጥነናል ግን እንደ መሀይም ነን።
ስልጡን ዘመን ላይ ነን ግን ኋላ ቀሮች ነን። የአባቶቻችን ልጆች ነን ግን እንደ አባቶቻችን አይደለንም። በስርዓት በኢትዮጵያዊያን ወግና ባህል ያደግን ነን ግን ባለጌዎች ነን። ከዓለም በፊት ጠቢብ ነበርን ግን ምንም የለንም። አባቶቻችን ፈጣሪን የሚፈሩ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ሩህሩህ ነበሩ እኛ ግን ጨካኝ ወጥቶናል። ፈጣሪን አንፈራም። ፍቅርን ገለን ቀብረንዋል። አንድነትን ትተን መለያየትን የሙጥኝ ብለናል።
አባቶቻችን እንዲህ አልነበሩም..እነሱ የእውነት ሰው ነበሩ። እነሱ የእውነት ዜጋ ነበሩ። በሞታቸው እኔና እናንተን ፈጥረዋል። በጉስቁልናቸው ኢትዮጵያ የምትባል የነጻነት ምድር መስርተዋል። በሞታቸው ለጥቁሮች ሁሉ ተስፋ የሆነችን አንዲት ድንቅ ሀገርን ሰርተዋል። በአንድነታቸው ዓለምን ያስደነቀ ጀብድ ሰርተዋል። እኛ ግን ምናችንም እነሱን አይመስልም።
ከህግና ስርዓታቸው አፈንግጠን እርስ በእርስ መገፋፋትን ስልጣኔ አድርገነዋል። ከእውነታቸው ሸሽተን ነውረኛ ሆነናል። አደራቸውን ከማክበር ይልቅ አደራ በል መሆንን መርጠናል። ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሔርተኝነትን መርጠናል። ጀግንነትና፣ ሀገር ወዳድነታቸውን አልተላበስንም። ፍቅራቸውን፣ አንድነታቸውን፣ መተሳሰባቸውን አቀዝቅዘናል።
አብሮ መብላት፣ አብሮ መጠጣት ኋላቀር እስኪመስለን ድረስ የብቻ ሕይወትን የሙጥኝ ብለናል። ብዙዎች የሞቱላትን ሀገር እየተውን መሰደድ፣ የራስን ንቆ የባዕድ ሀገርን ማድነቅ ባህሪያችን ሆኗል። ከባህላችን ርቀን፣ ከማንነታችን ሸሽተን ሌላ ባዕድ ማንነትን ተላብሰናል። ታላቅ ሀገርና ህዝብ እንፈጥር ዘንድ እንደ አባቶቻችን መሆን አለብን። የአባቶቻችንን አይነት አእምሮና ልብ የእኛ ማድረግ ግድ ይለናል። አርነት ያወጣንን የአባቶቻችንን መንፈስ ፈልጎ ማግኘት ግድ ይለናል። ያኛውን ትውልድ ማወቅና መረዳት አለብን። ምክንያቱም ያኛው ትውልድ የታሪካችን፣ የባህላችን፣ የማንነታችን መብቀያ ለም መሬት ነውና።
ያኛው ትውልድ ጌጣችን ነው። አልቦ አሸክታባችን። የኔና የእናንተ ነፍስ ያጌጠችው በዚያ ትውልድ ጌጠኛ አልቦ ነው። የተሰፋነው፣ ሰው የሆነው በዚያ ትውልድ መልከኛ መርፌና ክር ነው። ያኛው ትውልድ ኩታና ቡሉኮ፣ እጀ ጠባብ፣ በርኖስ ኩታ፣ ተነፋነፍና አስኬማ ለብሶ ራሱን ሆኖ ራሱን መስሎ ነበር ታሪክ ያቆየልን እኛ የዛሬዎቹ የራሳችንን ንቀን ዘመናዊነት እየመሰለን የአውሮፓን ቀዳዳና ጨምዳዳ ድሪቶ እየሰበሰብን ራሳችንን እያጣን እንገኛለን።
ያኛው ትውልድ በባዶ እግሩ እየሄደ ለእኛ ጫማ ሰጥቶናል። የድሮዎቹ ደህና ዋልክ፣ ደህና ዋልሽ በማለት ከወገባቸው በማጎንበስ፣ ባርኔጣቸውን በማውለቅ ነበር በታላቅ ፍቅርና አክብሮት ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹት። እኛ የዛሬዎቹ የአባቶቻችንን ሰላምታ ቀይረን…ምኑንም በማናውቀው ፈረንጅኛ ሀይና — ፒስ እየተባባልን ባህልና ወግ እንበርዛለን።
የድሮዎቹ ነውር ያውቁ ነበር..የድሮዎቹ ለፈጣሪ የተመቹ ነበሩ። የድሮዎቹ ተከብረው የሚፈሩ፣ ተወደው የሚከበሩ ነበሩ። የአሁኖቹ ነውር የማናውቅ ፈጣሪ የት እንዳለ የረሳን ግራ ገብቶን ግራ የምናጋባ ትውልድ ሆነናል። የድሮዎቹ እየፈተሉና ሸማ እየሰሩ፣ እየፎከሩና እየተመሰጋገኑ አንተ ትብስ አንተ በሚል ሀበሻዊ ወግና ስርዓት ተወልደው ያደጉ እንዲህም ነበሩ። እኛ የዛሬዎቹ መገፋፋትና እኔነትን የሙጥኝ ብለን ስር በሰደደ ትችትና ነቀፋ መኖርን የመረጥን ነን። ይቅርታና ፍቅር ስፍራቸው የት እንደሆነ አናውቀውም። ትዕግስትና በጎነት በእኛ ልብ ውስጥ ከሞቱ ቆይተዋል።
የድሮዎቹ ታሪክ እያጠኑ በአንድ ልብ፣ በአንድ መንፈስ ለጋራ ጥቅም ሲለፉ እኛ የዛሬዎቹ ግን በማንችስተርና በአርሴናል መከራችንን እናያለን። በማያገባን እየገባን፣ በሚያገባን ዝምታን እየመረጥን ለራሳችንም ለሀገርም ሳንሆን መሀል መንገድ ላይ የቀረን ሞልተናል። በታሪክ፣ በባህል በማይመስሉን ሀገራት ተጽእኖ ስር ወድቀን በምንም የማናገኘውን ድንቅ ኢትዮያዊነታችንን እያጣን ነው። የራሳችንን ጀግኖች ቸል ብለን በመሲና ሮናልዶ እየተወራረድን፣ በወለምታቸው እየታመምን፣ በሀዘናቸው እያዘንን እየተደባደብንና እየተፈነካከትንላቸው የቆምን ነን።
ዓድዋ ምንድነው? ስንባል ግራ የሚገባን፣ የአርበኞች ቀን መች እንደሚከበር ስንጠየቅ ቁጥር የሚምታታብን እኛ እኮ የከሰርን ትውልዶች ነን። ቫላንታይን ዴይና፣ ክሬዚ ዴይ መቼና ለስንተኛ ጊዜ እንደሚከበር ጠንቅቀን የምናውቅ፣ የሰማዕታትን ቀን ስንጠየቅ ግን የምንደናገር፣ አፕሪል ዘፉል መቼና የት፣ በማን እንደተጀመረ ስንጠየቅ በብዙ ማስረጃ የምንናገር ግን ደግሞ አቡነ ጴጥሮስ ማን እንደሆኑ ስንጠየቅ ግን ግራ የሚገባን እኛ እኮ ስልጡን አላዋቂዎች ነን።
የአውሮፓን ስልጣኔ፣ የኢሲያን ጓዳ ጎድጓዳ ስናውቅ የራሳችንን የረሳን፣ አጼ ምኒልክንና አብዲሳ አጋን የረሳን፣ ዘርዐይ ደረስንና ባሻ አውዓሎም የዘነጋን..በአባቶቻችን ሞት ቆመን ለገዳዮቻችን ነጭ የምናጎበድድ እኛ እኮ ብኩኖች ነን። እኛና የድሮዎቹ የተለያየን መልኮች ነን።
እንበረታ..እንጀግን ዘንድ የአባቶቻችን ሀቅ በነፍሳችን ላይ መብቀል አለበት። ድሮነትን መውረስ አለብን። ዓድዋን የፈጠረውን፣ በካራማራና በአንባላጌ ያሸበረቀውን የአንድነት ሸማ መልበስ አለብን። ድሮነት በእያንዳንዳችን ነፍስና ስጋ ላይ መዘራት አለበት። እውቀት ባልገባው፣ ስርዓት ባልጎበኘው ነፍስና ስጋችን ላይ የአባቶቻችንን ሀቅ ከትበን እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስንል በኩራት መናገር መልመድ አለብን።
እኛ ማንም የማይቀይረን የአባቶቻችን ልጆች ነን። እኛ ማንም የማይለውጠን የአባቶቻችን መልኮች ነን። እኛ ከራሳችን ውጭ የማንም የማንሆን የራሳችን ሰዎች ነን። ይሄንን እውነት ተረድተን እንደ አባቶቻችን ማሰብና፣ እንደ እነሱ መሆን ይጠበቅብናል። በየትኛውም መስፈርት ብንለካው የነሱ ሀሳብ፣ የእነሱ ህልም ከእኛ ሀሳብና ህልም በእጅጉ የተሻለ ነው። ዓድዋን የፈጠረው የነሱ የአንድነት መንፈስ ነው። ኢትዮጵያን የሰራው የእነሱ ፍቅርና ወንድማማችነት ነው።
እኛም በዛሬ ሕይወታችን ላይ ያለውን ድህነት፣ ያለውን ኋላቀርነት፣ ያለውን መጠላላት እናሸንፍ ዘንድ እንደ አባቶቻችን ያለ የጋራ መንፈስ ያስፈልገናል። ሀገራችንን ከድህነት፣ ህዝባችንን ከኋላቀርነት፣ እኛንም፣ ትውልዱንም ከወረረን የባዕድ አስተሳሰብ ነጻ እናወጣ ዘንድ ነጻ የሚያወጣን የአባቶቻችን የመቻል ትከሻ ያስፈልገናል። በቃ እነሱን መምሰል አለብን። ከዛሬ በኋላ በሚመጣው አዲሱ ቀናችን ላይ የአባቶቻችን ልጆች በመሆን ታሪክ መስራት አለብን።
ይሄኛው ትውልድ ያኛውን ትውልድ መምሰል አለበት። በእውቀት፣ በትህትና፣ በማጎንበስ መምሰል አለበት። በአስተሳሰብ፣ በመረዳት ያኛውን ትውልድ መምሰል አለበት። በመቻቻል፣ በመረዳዳት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት አባቶቹን መሆን አለበት። በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በትዕግስት የአባቶቹን ሰውነት መውረስ አለበት። አሁን ያለው የፖለቲካ ችግር፣ የኑሮ ውድነት እልባት የሚያገኘው ያጠለቅነውን የንቀት ጭንብል አውልቀን የአባቶቻችንን የመቻቻል ካባ ስንደርብ ነው።
ከዚህ ውጭ ወደፊት የመራመጃ አቋራጭ መንገድ የለንም። ከፍታችን ያለው በተውነውና በተጸየፍነው እኛነታችን ውስጥ ነው። ይሄኛው ትውልድ በጊዜው ላይ ጀግና መሆን ይጠበቅበታል። የሚመጣው ትውልድ ራሱን ፈልጎ የሚያገኘው በእኛ ውስጥ ነውና ለአዲሱ ትውልድ የሚሆን ኢትዮጵያዊ ሰውነት ያስፈልገናል።
ይሄ ሰውነት የሚገኘው ደግሞ በፍቅርና በእውነት ውስጥ ነው። በይቅርታና በመቻቻል ውስጥ ነው። በመነጋገርና በመስማማት ውስጥ ነው። ይሄ ሰውነት የሚገኘው እንደ አባቶቻችን የሆነ ልብ፣ የሆነ ነፍስ፣ የሆነ አእምሮ ሲኖረን ነው። ይሄ ሰውነት የሚገኘው እንደዛኛው ትውልድ እግዚአብሔርን ስንፈራ፣ ነውር ስናውቅ ነው። በጋራ ሀሳብ ሀገር ለመፍጠር በስርዓት የበቀልንባቸው የአባቶቻችን ነፍስ ግድ ይሉናል። በእኛ ውስጥ እነሱን እንፈልግ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም