በሰሜኑ ክፍል የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት በመጨረሻ በሠላማዊ መንገድ በድርድር እልባት አግኝቷል። የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን ሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም አስጠብቆ ጉዳዩን ለመቋጨት ችሏል። ከዳር ሆነው የኢትዮጵያን እንደ አንባሻ መቆራረስ በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ሃይሎች ህልማቸው ከሽፏል። በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩት ዜጎች በመጨረሻም እፎይታ ያገኛሉ። እርዳታ የሚሹት የሰብአዊ ድጋፍ ያለምንም እንከን እንዲደርሳቸው የተደረሰው ስምምነት የሚያግዝ ነው።
በሂደት ሁኔታዎች ሲረግቡና ስምምነቱ ተፈፃሚ ሲሆን ደግሞ ሁሉም ዜጎች በሠላም ከመንቀሳቀስ አልፈው ስነልቦናዊ እረፍትን ያገኛሉ ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፣ የመንግስት ሰራተኛው ወደ ቢሮው፣ ገበሬው ወደማሳው፣ ተማሪውም ወደ ትምህርት ቤቱ ይገባል። በዚህ ውስጥ ማንም አሸናፊ ማንም ደግሞ ተሸናፊ አይኖርም።
በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች። የህሊና እረፍት አጥተው በጦርነት እገታ ውስጥ የቆዩ ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች አሸናፊ ይሆናሉ። የሚሰሩ እጆች ነፃ ይወጣሉ። በተደረሰው የሠላም ስምምነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያሸንፋል። ያለማንም ጣልቃ ገብነት አፍሪካ ውስጥ የሚከሰቱ ጦርነቶች በንግግርና በድርድር እንደሚቋጩ ትልቅ ማሳያ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ ወገን ብቻ ሳይሆን አፍሪካ ታሸንፋለች።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን እውነት በልቦና ውስጥ ሊያስቀምጠው ይገባል። የተደረሰውን የሠላም ስምምነት አስመልክቶ በማህበራዊ ድረገፆች የተለያዩ የሃሰት መረጃዎች እየተነዙ ነው። ምክንያቱ ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው። የአገሪቱ መረጋጋትና ፊቷን ወደ ልማት ማሸጋገር የማይዋጥላቸው ቡድኖች ስምምነት ባደረጉት አካላትና በህዝቦች ውስጥ ልዩነት የሚፈጥሩ መልእክቶችን እያሰራጩ ነው። በሰላም ስምምነቱ አሸናፊና ተሸናፊ አካላትን ለመፍጠር እየታገሉ ይገኛሉ። ይህንን ማክሸፍ ያስፈልጋል።
በጦርነቱ ወቅት ህዝቦች ጦር አልሰበቁም። እርስ በእርስም የፈጠሩት ግጭት የለም። ይልቁኑ ወደሚያምኑት አምላክ በመፀለይ ሠላም እንዲወርድና መረጋጋት እንዲሰፍን ሰርተዋል። ህዝብ ባልተጋጨበት ሁኔታ “የሠላም ድርድሩ በዚህኛው አካል አሸናፊነት ተደመደመ” የሚል መልእክት ማሰራጨት እና ለዳግም ግጭት ግፊት መስራት አዋጪ አይደለም።
ዜጎችም ለዚህን መሰል ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ሊሰጥ አይገባም። በጥቅሉ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተደረሰው ስምምነት ሁሉንም አካላት አሸናፊ የሚያደርግ እንደሆነ ሊታመንበት ይገባል። በእውነትም በአግባቡ ከተጠቀምንበት ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት ነው።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ትብብር የተደረሰውን ስምምነት አስመልክቶ እጅግ በርካታ አወዛጋቢ መረጃዎች የኢትዮጵያን ሠላም በማይፈልጉ አካላት እየተሰራጨ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ አንዱ የተዛባና ከእውነት የራቀ የስምምነት አንቀፆችን የያዘ ሰነድ ይገኝበታል። ይህን መሰል መረጃ ምንጩ ከማይታወቅ አካል በመውሰድና በማሰራጨት ዜጎችን ማወናበድ የቱንም አይነት ሴራ ሊያሳካ አይችልም። ለጊዜው ግርታን የሚፈጥር ቢሆንም ቀስ እያለ የሚጠራ ይሆናል።
አሁን የኢትዮጵያ መንግስት በስምምነት ሰነዱ መሰረት ቀጣይ መርሃ ግብሮችን ተከትሎ የሚተገበረውን እርምጃ ይፋ እስኪያደርግ ድረስ ሁሉም ዜጎች ግርታ ውስጥ ሳይገቡ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ይህ ሲሆን ከአላስፈላጊ መወናበድ ያድናል። ምንጩ የማይታወቅ መረጃን ማጥራትም እንዲሁ የዜጎች ኃላፊነት ነው። በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚፅፉ አንዳንድ አካላት ውሉን የሳተ ትንታኔ ውስጥ ገብተው ህልማቸውን ለማሳካት ከላይ እታች እያሉ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለእነዚህ አካላት ጆሮ መስጠት አይኖርበትም።
አንዳንዶች ደግሞ ፍጹም በሆነ ድንዳኔ የሠላም ስምምነቱን አደባባይ ወጥተው በመቃወም፣ሀገርና ህዝብ ከጦርነት የሚያተርፈው አንዳች ነገር ያለ ይመስል እየጮሁ ይገኛሉ። ከጦርነቱ አካባቢ ርቀው ሁሉ ነገር ሠላም በሆነበት ምድር እያሰሙት ያለው ድምፅ በሀገርና በህዝብ ላይ በአደባባይ ሞት የማወጅ ሟርት እንደሆነ ለማስተዋል ስክነት አላገኙም።
በአክቲቪስት ስም የሚያካሂዷቸው አደናጋሪ ዘመቻዎች በቀደመው ዘመን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈሉን ሁሉ አሁንም ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍሉን መጠንቀቅም ተገቢ ነው። ከዚህም በላይ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለደረሰው ችግር እንደ ማህበረሰብ የጀመርነው የብሽሽቅ ፖለቲካ አንዱ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም።
ሃያ ሰባት አመት ይዘነው የመጣነው የብሽሽቅ ፖለቲካና አላስፈላጊ የሆነ ፉክክር በማህበራዊ ሚድያው እየታገዘ የብዙ ችግር ምንጭ ሆኗል። እነዚሁ ሰዎች ዛሬ ለሠላም ስምምነቱ አቃቂር በማውጣት ሕዝቡን ለማሳሳት ረጅም መንገድ እየሄዱ ነው።
ስምምነቱ ሀገርን ከገባችበት አጣብቂኝ በማውጣት ሀገርን እንደ ሀገር መላው ህዝባችንን እንደ ህዝብ አሸናፊ ያደረገ ፣ በዚህም ዘላቂ ሠላም በማምጣት የጀመርነውን ልማት ከፍ ወዳለ ደረጃ አሳድገን ሀገርን በብልጽግና አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለመግለጽ የጀመርነውን ጥረት ወደ ተግባር ለመለወጥ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።
ይህን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ለሀገራችን በጎ ሃሳብ የሌላቸውን ግለሰቦች ፣ቡድኖችና ተቋማት ሀገር የማፍረስ ሴራ ልናከሽፍ ፤ ለዚህ የሚሆን ልበ ሰፊነት፣ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ልንላበስ ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም