ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ናት፡፡ ይህንን ለማደብዘዝና በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሚደክሙ ብዙዎች ናቸው። ይህም የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ ምክንያት ነፃነት መለያዋ የሆነች አገር ድህነት አንገት አስደፍቷት ዓመታትን አሳልፋለች፡፡
እንደ ሰሞኑን ሁሉ ኢትዮጵያን የሚያዳክሙ ድርጊቶችን በመፈፀም አሸባሪዎችን እና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችን በመፍጠርና በማሳደግ ባገኙት አጋጣሚ አገሪቱን ለማዳከም በሚጥሩ የውጪ ጠላቶች ምክንያት ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮቿ እየተናወጠች ከድህነት መውጣት መንታ ልጅን በምጥ የመውለድ ያህል ፈተና ሆኖባት ኖራለች፡፡
እነዚህ የውጪ ጠላቶች ዋነኛ መነሻቸው ጥቁሮች ከነጮች እኩል መሆናቸውን ለዓለም ያሳየች አገር አለች እንዲባል ፈፅሞ አለመፈለጋቸው ነው፡፡ እንኳን መኖር በታሪክ ውስጥ ስሟ እንዲጠቀስ አይሹም፡፡ በቀኝ ገዢ አልገዛም ያለች እና ለጥቁሮች ሁሉ ኩራት የሆነች አገር ስለመኖሯ ማሰብም ሆነ ስለእርሷ መስማት ለአንዳንድ ነጮች የሚፈጥርባቸው የመበለጥ ስሜት የሚናቅ አይደለም፡፡
አፍሪካን በመበዝበዝ ያደጉና በቀጣይም የመበዝበዝ ፍላጎት ያላቸው አገራት በ1888 ዓ.ም እና በ1933 ዓ.ም ለነጭ አልገዛም ብላ በዓለም አደባባይ ትልቅ ታሪክ መሆኑዋን በማውጠንጠን፤ ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎችም ቀኝ ተገዢዎች ስለነፃነት እንዲያስቡና እንዲታገሉ በር እንደከፈተች በማሰላሰል፤ በቀጣይም የኢኮኖሚ ነጻነቷን በራሷ አቅም አጎልብታ፤ የዓለም ገዢነን አስተሳሰብን በራሳቸው ውስጥ የገነቡ አገራትን ትዕዛዝ አልቀበል ትላለች የሚል ስጋት አለባቸው።
ልትሄድበት የቆረጠችበት የብልጽግና መንገድ ለሌሎች አፍሪካውያን አገራት እንደ ቀደመው ዘመን አዲስ ነጻነት / የኢኮኖሚ ነጻነት/ በማጎናጸፍ፤ ራሳቸውን ችለው ከምዕራባውያን ተፅዕኖ ነፃ የሚሆኑበት አስቻይ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ፍርሀትም አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊየን ያላነሰ የህዝብ ቁጥር ለዛውም ከ75 በመቶ ያላነሰ ሊሠራ የሚችል የወጣት ኃይል ያላት መሆኗን ሲያስቡ ይጨነቃሉ፡፡ በዛ ላይ እንደሌሎች አፍሪካ አገራት በነጮች አለመዘረፏ የብዙ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መሆኗን ሲያስቡ ደግሞ የነገ ተስፋዋ፤ ልትፈነጠር የምትችልበት መሰረት ያላት መሆኑ ያሳስባቸዋል፡፡
ነገ እነርሱን የምትገዳደር አገር ልትሆን የምትችልበት ሁኔታ መኖሩን ሲያስቡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዕቅድ ይዘው ሳይታክቱ በትጋት ይሠራሉ፡፡ ለዚህም ልዑዋላዊነቷን አስከብራ እንዳትኖር በውስጥ ክፍፍል እንድትዳከም የማይቧጠጥ የሰማይ ክፍል የማይገፋት ተራራ የለም፡፡
እስካሁን ባይሳካላቸውም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሊገኝ የሚችለውን ምቹ መንገድ በመጠቀም ለዘመናት ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል ለማዳከም ብዙ ሰርተዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ዛሬም ስሟ አልጠፋም፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች፡፡ ነገም ትኖራለች፡፡
ይህን እውነት ያልተረዱ /ተረድተውም አገርን ከራሳቸው በላይ አድርገው የሚያዩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ከውጪ ጠላቶች ጎን በመቆም ቀርቦ በመወያየት ሳይሆን ርቆ ጫካ ገብቶ ጦር በመነቅነቅ ኢትዮጵያውያንን በመፍጀት፤ መንግስትን በማዳከም፤ የውጪ ጠላት መጠቀሚያ በመሆን ኢትዮጵያ ለዘመናት የድህነት ቀንበርን ተሸክማ እንድትኖር ሰርተዋል፤ አሁንም እየሰሩ ነው፡፡
አሁንም የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢትዮጵያን እየኮረኮሙ ለመቅበር የማይጠቀሙት መንገድ የለም፡፡ አንደኛው እና አሁን አሁን በስፋት እየተጠቀሙበት ያለው አገር ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሮ በጎሳ ግጭት ህዝብ እንዲተላለቅ መደላድል መፍጠር ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር ሕዝብ ተማሮ ከመንግስት ጋር እንዲጣላ መሥራት ነው፡፡
አሁንም እንደሚታየው ምዕራባውያን የተለያዩ የዓለም የገንዘብ ተቋማት፣ ገንዘብ አበዳሪዎች እና እርዳታ ሰጪዎች ነን ባዮችን በመጠቀም አሁንም ከድህነት ያልተላቀቀችውን ኢትዮጵያን ቢችሉ ለማፍረስ ባይችሉ ለማዳከም የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ከዚህም ውስጥ ዋነኞቹ ዕርዳታ እና ብድር አለመስጠት፤ በተለያየ መንገድ በኢኮኖሚው ሁኔታ ወይም በዋጋ ግሽበት ሕዝቡ እንዲማረር ማድረግ፤ የአገር ውስጥ አሸባሪ ድርጅቶችን በመደገፍ እና በማበረታታት አገርን ማዳከም ናቸው፡፡
ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በእነዚህ የውጪ ጠላቶች ላይ ነቅተን ልንቆምበት የሚገባ ነው። አንዱ በገንዘብ ተታሎ ሲጮህ አብሮ ከመጮህ ይልቅ ቆም ብሎ ማሰብ ራስን እና አገርን የሚጠቅም ነው ወይ ብሎ ማሰላሰል ያስፈልጋል፡፡
በሃሳብም ሆነ በተግባር አንድ ብሔር በሌላ ብሔር ላይ እንዲነሳ ተሳትፎ ማድረግ የብሔርን ነፃነት ማስከበር ሳይሆን ኢትዮጵያን የማጥፋት ዕቅድ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የውጪ ጠላቶች ደጋፊ መሆን ነው፡፡ እውቀት እና እውነተኛ ብቃት ያለው ማንኛውም ዜጋ ከሚናገረው ብቻ ሳይሆን ከሚያስበው ጀምሮ መነሻው ኢትዮጵያ ጎድላ ሳይሆን ሞልታ ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ ላይ ጠንክሮ መስራት አለበት፡፡
መንግስትን መቃወም፤ የተለየ አቋም መያዝ ወይም ብሔርን የተመለከተ አጀንዳ መያዝ መብት ነው፡፡ ሃጥያት አይደለም፡፡ ነገር ግን የነፃነት ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማጥፋት መተባበር ግን ደማቁን የኢትዮጵያን ቀይ መስመር መጣስ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ዝም ሊል አይገባም፡፡
ለአገራችን ችግሮች አሁን ላይ ዋነኛው መፍትሔ ጦርነት አይደለም፤ የተለየ ሃሳብ ያለው ቀርቦ ጥያቄ ያንሳ፤ ሌላው ህዝብ ደግሞ ሀቀኛ ሆኖ በቅንነት ይስራ፤ ሁሉም ስለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት ይትጋ፤ ያለብሔር ልዩነት ሁሉም ይተባበር፤ ተራ የፖለቲካ ንትርክና አሉባልታ ይቁም፤ ሁሉም ኢትዮጵያ የውጪ ጠላት ያለባት መሆኑን ተረድቶ ይህንን ጠላት ለማሳፈር እና ከድህነት ለመላቀቅ በየሥራ ድርሻው ኃላፊነቱን ይወጣ፤ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ተዓምረኛ ዕድገትን የምታሳይበት ዘመን ሩቅ አይሆንም፡፡ ሰላም !
ፌኔት (ከጠሮ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም