የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢፌዴሪ መንግሥትና በአሸባሪው ትህነግ መካከል በደቡብ አፍሪካ ለቀናት ያህል የተደረገውን የሰላም ንግግር መቋጫ አስመልክተው በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ በአካባቢው ስላለው የልማት እንቅስቃሴን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት የሰላም ንግግር እና ስምምነቱን አስመልክተው ያስተላለፉትን መልዕክት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ የቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የአርባ ምንጭ ልዩ አምባሳደር፤ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ክቡር አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ የጋሞ ሸበላ፤ የተከበራችሁ የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች፤ ሚኒስትሮች ፤ ከንቲባዎች፤ እዚህ ስፍራ የተገኛችሁ እንግዶች በሙሉ፤ አካል ብቻ ሳይሆን አይን ማጥገብ ብቻ ሳይሆን፤ ለመንፈስ እረፍት ወደምትሰጠው ውቧ ገነቷ አርባ ምንጭ እንኳን በሰላም መጣችሁ።
ብዙ ቦታ ለአካል እረፍት ይሰጣል፤ አርባ ምንጭ ጬንቻ ግን ለመንፈስም እረፍት ይሰጣል። እነ ኃይሌ የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአርባ ምንጭ አፕል፣ የአርባ ምንጭ ወተት፣ የአርባ ምንጭ የእጅ ጥበብ የሆነው ሸማ ብለው ለዘመናት ሲናገሩ ነበር፤ ዛሬ ልነግራቸው የምፈለገው ግን የአርባ ምንጭ ጣዕም ያለው የሰላም መንፈስም ይጨመርበት። ትናንት ወደ ጬንቻ ሄደን ነበር፤ በጬንቻ ወተትና አፕል በየጓሮው የሚታይበት፤ ደጋግ አርሶ አደሮች ያሉበት ኢትዮጵያዊነት ኩራት የመሆን ተምሳሌት የሆነበትን ስፍራ ለማየት ዕድል አግኝቻለሁ።
ጬንቻ፣ አርባ ምንጭ፣ ሳውላ፣ ሶዶ፣ ዳውሮ፣ ጂንካ፣ ጂማ፣ ኢትዮጵያ በጋራ የምንቆምባትን ምድር የሰጠን ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን። ከጥቂት አመታት በፊት በምዕራብ ኢትዮጵያ የንግድ፣ የፈጠራ የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ወደ ሆነችው ወልቂጤ ከተማ የመሄድና የመጎብኘት ዕድል ነበረኝ።
የወልቂጤ ሕዝብ ዛሬ በአርባ ምንጭ እንደምናየው በከፍተኛ ደስታ እና የሰላም መንፈስ ተቀብሎን እዛው እያለን የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ ነበር የሰማነው። እንደ ጉራጌ ሕዝብ ሰላም ወዳድ፣ ሥራ ወዳድ፣ አርቆ አሳቢና በኢትዮጵያዊነቱ ፅኑ አቋም ያለው የአርባ ምንጭ ሕዝብ ከልቡ ደግነትና ቸርነት የተነሳ እዚህ እያለን የኢትዮጵያ የሰሜን ጦርነት የሚያበቃበት ሰላም ትናንት ተነገረ።
እኛ ሰላም የምንወድ ሕዝቦች፤ እኛ ሰላምን የምንሻ ሕዝቦች፤ እጅግ በምንወዳት ገነት በሆነችው የፍቅር ከተማ ውስጥ የሰማነው ዜና ሁልጊዜ የማይረሳ በመሆኑ ጋሞዎች እንኳን ደስ አላችሁ።
ዛሬ እዚህ የተገኘነው ለሁለት መሠረታዊ አላማ ቢሆንም፤ ሦስተኛ ጉዳይ ተጨምሯል። አንደኛው የጋሞ፣ የጎፋ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የሀዲያ፣ የከምባታ የዚህ አካባቢ ሕዝቦች በሙሉ ኢትዮጵያ ስትደፈር፤ የኢትዮጵያ ልጆች በግፍ ሲገደሉ፤ ‹ይህንን ለመስማት ለማየት ዝግጁ አይደለንም› ብላችሁ በፈቃድ በደስታ በልጆቻችሁ ደምና ሕይወት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማፅናት ትልቅ ዋጋ ስለከፈላችሁ ሁሉም አመራሮች ‹እናመሰግናችኋለን› ለማለት ነው ። ሁለተኛው ፕሮግራማችን ከዚህ ፕሮግራም በኋላ የሚጀመር ስለሆነ እሱን እዚህ አልገልፀውም። ሦስተኛው ግን ትናንት የሰማችሁት፤ የሰማነው የሰላም ድርድር ጉዳይ ቀደም ብዬ ካነሳሁት አላማዎች የሚያንሰ ስላልሆነ በተወሰነ ደረጃ ነካ አድርጌ ለማለፍ እወዳለሁ።
እንደምታስታወሱት፤ የዛሬ ሁለት አመት ባልተገባ መንገድ ከወንድሞቻችን እጅግ አሳዛኝ ጥቃት ተሰንዝሮብን ነበር። የኢትዮጵያ ወንድና ሴት ልጆች በገዛ ወንደሞቻቸው ባልተገባ ሁኔታ በተኙበት ታርደው፣ ተገድለው፣ ተገፍተው ነበር።
ያ ሁኔታ ሁላችንንም ያስቆጣ በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት አንደራደርም፤ ቢሮ ተቀምጠን መምራት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ክብር ከተመጣ የጥይት አረር በግንባራችን ለመቀበልና ሉአላዊነታችንን ለማስከበር ዝግጁ መሆናችንን ለመላው የኢትየጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ያሳየንበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።
ነገር ግን፣ እንኳን እርስ በርስ በወንድማማቾች መካከል ቀርቶ በማንኛውም አገር መካከል ቢሆን የሚወደድ፣ የሚናፈቅ፣ የሚፈለግ ነገር አይደለም፡፡ ጦርነት የሰው ሕይወት ይቀጥፋል፤ እጅ እግር ያሳጥራል፤ ንብረት ያወድማል፤ ጥላቻን ያበዛል፡፡ ከዚህ የተነሳ ለፈጣሪ ምስጋና መስጠት የሚገባው ሕዝብ የእርግማን ምንጭ ይሆናል፡፡ ጦርነትን እኛ አብዝተን እንጠላለን፡፡ እኛ የምንፈልገው ሰላምና ብልጽግና ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ በነበረው የሰላም ድርድር ጀግኖች የጋሞ ልጆች፣ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች በመሬት ላይ ያስገኙትን ታሪካዊ ድል ዳግም የሚያስረግጥ የሰላም ድል ማግኘት ተችሏል። ከተገኙ ዋና ዋና ድሎች መካከል አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም የሚለው በሁለቱም ወገን ተቀባይነትን አግኝቷል። ለኢትዮጵያ አንድነት የሞቱ የቆሰሉ፣ ባልተገባ ሁኔታ የወደቁ ጀግኖች እንኳን ደስ ያላቸው፤ ሕልማቸው እውን ሆኗል፡፡
ሁለተኛ፣ በሰለጠነው ዓለም እንደ ጋሞ ባሉ ሽማግሌዎች ስር ያደግ ሕዝብና አገር ነገር በምክክርና በንግግር እንደሚጨረስ ስለሚያወቅ በአንድ አገር ውስጥ ከአንድ መከላከያ በላይ አያስፈልግም የሚለው ጉዳይም ከስምምነት ተደርሷል።
ሦስተኛ ሕጋዊ እና ሕጋዊነትን ማስፈን ለአንድ አገር ህልውና መሠረት ስለሆነ የራሳችንን ሕግ የማናከብር ማሻሻል ሲኖርብንም በሕግ አግባብ የማናደርግ ከሆነ ተቋማዊነት አገር የሚለው ቁመና ስለሚሸረሸር ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተደረገው ምርጫ በሕጋዊ ምርጫ መተካት አለበት የሚለውም በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አግኝቷል። ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውና አከራካሪ የሆኑ ቦታዎች ዳግም የሰው ልጅን ሕይወት ሳይጠይቁ በሰላም፣ በድርድርና በአገሪቱ ሕግ መሠረት ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ በሁለቱም ወገኖች ከስምምነት ተደርሷል።
ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ድርድር ኢትዮጵያ መቶ በመቶ ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል። ታዲያ የጋሞ ጀግኖች ጀግንነት ማለት ማሸነፍ ብቻ አይደለም። ጀግንነት ማለት ከድል በኋላ ደግነት ማለት ነው። ከድል በኋላ ይቅር ማለት ነው። እኛ ጀግኖች ብቻ ሳንሆን ፈጣሪን የምንፈራ የምናከበር ሰዎች ስለሆንን ያገኘነውን የሰላም ዕድል በታላቅ ክብር የምንቀበል እና በሙሉ ልብ ይቅር ብለን የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም በመመለስ የልመናን ጣጣ ለማፍረስ ስለምንፈልግ እጅግ የምወዳችሁ የጋሞ ሕዝቦች እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የምትገኙ ዜጎች የተገኘው የሰላም እድል ለኢትዮጵያ ታላቅ እድል ስለሆነ ብዙ እጃቸውን ያስገቡ ጠላቶቻችሁ ያፈሩበት ስለሆነ፤ በሙሉ ልብ ትግራይን፣ የትግራይ ሕዝብን ለመገንባትና ወደ ቀደመው ወደ አገሩ ስሜት ለመመለስ አብረን እንድንቆም በታላቅ ትህትና እጠይቃችኋለሁ።
የአማራ ጀግና፣ የአፋር ጀግና፣ የኦሮሞ ጀግና፣ የሱማሌ ጀግና፣ የደቡብ ምዕራብ ጀግና፣ የደቡብ ጀግና ጀግንነታችን የሚረጋገጠው ካለን አካፍለን በትግራይ የተጎዱ ወገኖቻችንን ማጉረስ ስንችል ነው። ካለን አካፍለን በማጉረስ ፍቅር በመስጠት ኢትዮጵያዊነት የሚሻል፣ ኢትዮጵያዊነት የላቀ፣ ኢትዮጵያዊነት ምስጢርና ጥበብ መሆኑን እርስ በእርሳችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተጨማሪ ትምህርት መስጠት ስለሚኖርብን እናንተ ያሸነፋችሁ ጀግኖች ልባችሁን ከፍታችሁ ወደኋላ ሳተመለከቱ ኢትዮጵያን ለመገንባትና አንድነቷን ለመጠበቅ ያላችሁን በመስጠት በጉልበት በማገዝ፣ ፍቅር በማጋራት፣ ክፉ ከመናገር በመቆጠብ፣ ደጋግ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች እንድትሆኑ በታላቅ ትህትና ደግሜ ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ።
ለአገር አንድነት ሕይወት ከከፈልን፣ ለአገር አንድነት ደማችንን ካፈሰስን፣ አጥንታችንን ከከሰከስን፣ ለሰላምና ለአንድነት ላባችንን ብናፈስ፣ ከኪሳችን ብናወጣ ፀጋ በረከት እንጂ ጉድለት ስለማይሆን ኢትዮጵያውያን ልባችሁ ይስፋ፤ ወደኋላ አትመልከቱ። ሰላማችን ወደኋላ እንዳይመለሰ በፀሎታችሁ፣ በሀሳባችሁ፣ በድርጊታችሁ ከእኛ ጋር በመቆም ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጠና ኢትዮጵያ እፎይ እንደትል የበኩላችሁን ሚና እንድትጫወቱ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።
ለትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ ትግራይ አገራችን ሕዝቡም ሕዝባችን ነው ስንል መቆየታችን ይታወቃል። ብዙ ያልተገባ መቆሳሰል፣ ያልተገባ መደማማት፣ ያልተገባ ጉዳት በእያንዳንዳችን ደርሷል፡፡ ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ ደርሷል። የመጨረሻው መልዕክቴ፣ ለትግራይ ሕዝብ ነበር፤ የትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ ሕዝባችን ምድሩም ምድራችን እንደሆነ ስንገልፅ ቆይተናል፡፡
ተጠቃ ብለን ስናስብ በትግራይ ምድር የልጅነት ወራታችንን ያጠፋንና ትግራይን የተከላከልን መሆናችንን ታሪክ ይመሰክራል። ዛሬም ያ ልባችን በቦታው ላይ ነው ያለው፡፡ ለመላው የትግራይ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አላስፈላጊ ጦርነት፣ አላስፈላጊ ጉዳት፣ አላስፈላጊ ኢትዮጵያን አጋልጦ የመስጠት ሂደት በዚህ ይብቃ።
ብዙ መከፈል የማይገባው ዋጋ ተከፍሏል፤ ብዙ ደም ፈስሷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ኢትዮጵያን የዓለም ሚዲያዎች የሚያውቁም የማያውቁም ትልቁም ትንሹም በከፍተኛ ደረጃ አንጓጠዋታል፤ አሳንሰዋታል፤ ይብቃ። ብዙ ጊዜ ከሰላም ድርድር በኋላ ሸፍጦች፣ ተንኮሎች፣ ደባዎች ይታያሉ። የተከበርከው የትግራይ ሕዝብ እኛ ልባችንን ከፍተን ሰላም ለማምጣት ዝግጁ ስለሆንን ይህንን የገባነውን ቃል ለመጠበቅ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን የበኩልህን ሚና እንድትወጣ ተንኮል፣ ክፋት፣ ሸር እዚህ ጋር እንዲበቃ ጥቂቶች እየሸረቡ ኢትዮጵያውያንን ዳግም አደጋ ውስጥና ጦርነት ውስጥ እንዳያስገቡ ሕዝባዊ ኢትዮጵያዊና ዜግነታዊ ሚናችሁን እንደትወጡ ለትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በታላቅ ትህትና አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያውያን ተጣልተዋል፤ ይገዳደላሉ፤ ገንዘብ ብናቀብል፣ ሚዲያ ብናቀብል፣ የጦር መሣሪያ ብናቀብል ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብላችሁ ብዙ የተጋችሁ የቅርብና የሩቅ አገራት ኢትዮጵያ የማትፈርስ፣ የፀናች፣ የምትበለፅግ የአፍሪካ ፈርጥና ኩራት ስለሆነች እኛ ኢትዮጵያውያን እያለን ኢትዮጵያን ማፍረስም፣ ማሳነስም፣ በቅኝ መግዛትም የማይታሰብ ስለሆነ ስላወጣችሁት ወጪ፣ ስለድካማችሁ ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ ልላችሁ እወዳለሁ።
በዚህ ጭንቅ ጊዜ ኢትዮጵያን አንጥልም ብለው እጅግ ጥቂት አገራት ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አንድ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ሆነው በመከራ፣ በችግር፣ በጫና፣ ከእኛ ጋር መቆማቸው ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ያካፈሉን፣ ጓዳችንን ያበሱ፣ የጓዳችንን መጉደል አይተው የሞሉ፣ ጥቂትም ቢሆኑ አስደማሚ ወዳጆች እንዳሉን ያየንበት ጊዜ ስለሆነ ለነሱ ኢትዮጵያ ታሪክ የምትሠራ፤ ታሪክ የማትረሳ አገር ስለሆነች ብድራታችሁን የምትከፍል መሆኑንና ታላቅ ምስጋና እንዳላት ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።
አንተ የተከበርክ፣ ለሕይወትህ የማትሳሳ፣ ሁለት ዓመት ሙሉ በብርድ፣ በዝናብ፣ በየጫካው የተኛህ፣ አንተ
የኢትዮጵያ ኩራት፣ የአገር መከላከያ፣ አንተ የኢትዮጵያ ወኔ፣ አንተ የኢትዮጵያዊነት ምልክት፣ አንተ የጀግንነት ምልክት፣ በአንተ ድካም፣ በአንተ መቁሰል፣ በአንተ ሕይወት ኢትዮጵያ ዳግም ቆማ በክብር መናገር ስለቻለች መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ያለንን ታላቅ አክብሮትና ፍቅር ካለንበት በመቆም እንድናሰማ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ። አመስግናለሁ።
ሰው ይፈጠራል፤ ይኖራል፤ ይሞታል፡፡ ጀግና ግን ይፈጠራል፤ ለልጆቹ አገር ያፀናል፤ እሱ መስዋዕት ይሆናልና እናንተ ጀግኖች ሞታችሁ ሞት አይደለም የደማችሁ መፍሰሰም የደም መፍሰስ አይደለም የኢትዮጵያ መፅናት ነውና እንወዳችኋለን፡፡ እናክብራችኋለን፡፡ ክብር ምስጋና ለተሰውት ሰማዕታት እንዲሆን የተቀራችሁ ጀግኖች ክብር እንዲሰማችሁ ለመግለፅ እወዳለሁ።
የጋሞ ሽማግሌዎች ሲመርቁ ‹እንደሚታጨድ ሳር ሳይሆን እንደሚበቅለው ሳር ያለመልምህ› ይላሉ። ኢትዮጵያ እንደሚታጨደው ሳር ሳይሆን እንደሚበቅለው ሳር የምትለምልም፣ የምትበለፅግ የአፍሪካ ኩራት የሆነች፣ የሁላችን መታፈሪያ የሆነች፣ ብርቅዬ አገር፣ ለዚህች አገር አገልጋይ መሆን ሳይሆን ዜጋ መሆንም ትልቅ ክብር ነውና የሚሰማኝን ክብርና ፍቅር ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።
በመጨረሻም ከእኛ የተለየ የፖለቲካ እሳቤ ያላችሁ ግለሰቦች፣ ቡድኖች በተከበረው የጋሞ ሕዝብ ፊት ጥሪ ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ። እንኳን በአንድ አገር በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ብዙ የማያግባቡ ጉዳዮች አሉ። እንከራከር፤ እንነጋገር፤ እንወያይ፤ ግን የኢትዮጵያን ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፈን የምንሸጥ ባንዳዎች አንሁን። ከባለፈው እንማር፤ ብልፅግና የተመረጠው ሕጋዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻዬን መንግሥት ካልሆንኩ፤ ብቻዬን ኢትዮጵያን ካልገዛሁ የሚል እብሪት፣ ትዕቢት ያለበት መንግሥት አይደለም።
በመጀመርነው አካታች ክርክርና ወይይት ሁላችንም እንሳተፍ። ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሀሳብ እናምጣ። ሕዝባችንን እናወያይና ዳግም መገዳደል፤ ዳግም መሰዳደብ የሌለባት፤ የምትበለፅግ፤ ሰላማዊት ኢትዮጵያን በጋራ እንድንገነባ በታላቅ ትህትና ጥሪ ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያውያን መሰዳደብ፣ መገዳደል፣ መገፋፋት ይብቃን። ሴት፣ ወንድ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ አፋር፣ ሱማሌ ሳንል ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ ሳንል እንደ አንድ ሰው በመካከላችን ያለውን ልዩነት አክብረን ኢትዮጵያን እንድንገነባ፣ እንድናበለፅግ አደራ እያልኩ የኢትዮጵያዊነትን ሽታ፣ የኢትዮጵያዊነትን ጣእም ማወቅ የፈለጋችሁ ወደ ጬንቻ እንድትመጡ እጋብዛችኋለሁ።
ይህች ታይታ የማትጠገብ፣ በየቀኑ ምስጢር የሆነች፣ የፈጣሪ ድንቅ ሥራ ተሰጥቶን አደራ መቀበል የማንችል ሕዝቦች እንዳንሆን ልብ እንግዛ፤ ስሜታችንን እንቆጣጠር፤ እንደማመጥ፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለአንደነት፣ ስለብልፅግና ብቻ የምንናገር ይሁን። ከአፋችን፣ ከአንደበታችን የማይረባ ነገር፣ ስድብ ቋንቋ አይውጣ፡፡ ግድየላችሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፈርጥ ትሆናለች፡፡ እንደማመጥ፤ እንከባበር፤ በጋራ እንቁም። በዚህ ውይይት ውስጥ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ማንኛውም ሀሳብ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ማንኛውም ሀሳብ ከመጣ ብልፅግና በሁሉም መስክ ዝግጁ መሆኑን በተከበረው በጋሞ ሕዝብ ፊት ቃል ልገባላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ቡና፣ ግሪን ሌጋሲ ስንል ቆይተናል፡፡ ዛሬ በምድረገነቷ አርባ ምንጭ የሌማት ቱርፋት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወጅበት አዲስ የልማት ዘመቻ በጋራ የምንጀምርበት ስለሆነ አርባ ምንጮች እንኳን ደስ አላችሁ። ለምን አርባ ምንጭን ፈለጋችሁ ከተባለ ልማቱ የሚታይበት፣ ፀሎቱ የሚሰማበት፣ ለምለምና ምድረ ገነት ስለሆነ ነው። ጋሞዎች ስለፍቅራችሁ፣ ስላሳያችሁን ትህትና፣ ስለልጆቻችሁ መስዋእትነት፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ታከብራችኋለች።
እኔም ልጃችሁ ወንድማችሁ እጅግ አድርጌ አመስግናችኋለሁ። ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለአፍሪካ! ሰላምና ብልፅግና ለመላው ዓለም ይሁን። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር። ፈጣሪ ኢትዮጵያና ልጆቿን ይባርክ። አመስግናለሁ።
አስምረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም