መልካም ነገር በመዝራት ያማረ ፍሬ እንደሚገኝ ሁሉ፤ መጥፎ ዘር መዝራትም ከግለሰብ እስከ በማህበረሰብ ብሎም በአገር ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ የትየለሌ ነው። ዘር መዝራት ስንል ታዲያ በጥሬ ቃሉ ትርጉም የምናገኘው የግብርና ሥራን አልያም ተክል መትከል ሳይሆን በሕይወት ዘመናችን የምናደርገው ማንኛውንም እንቅስቃሴ ይመለከታል።
በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን መንገዳችን ቀና ከሆነ ያማረ ፍሬን እናፈራለን፤ በተቃራኒው ደግሞ መንገዳችን ያልተገባና ጤናማ ካልሆነ ውጤቱ ረብ የለሽ ይሆንና በዘራነው መጥፎ ዘር ትውልዱ መከራ እንዲያጭድ ምክንያት እንሆናለን። እኛም በዘራነው የጥፋት ዘር ዋጋ መክፈላችን የማይቀር ነው።
ዛሬም በአገራችን እየሆነ ያለው ይሄው ነው። የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች የስልጣን ጥማት እና የከፋ እራስ ወዳድ የተነሳ አገርና ህዝብ በብዙ መከራ እየተፈተነ ይገኛል። እየከፈለ ያለውም ዋጋም የትየለሌ ሆኗል።
ቡድኑ ባለፉት 27 ዓመታት በምድሪቷ የዘራው ክፉ የዘረኝነት ዘር መከራ ሆኖ እየታጨደ ነው። ከመከራም በላይ የጋንግሪን ቁስል ሆኖ እየገዘገዘን ነው። ይህ መርዝ ታዲያ መልሶ እንዳይበቅል ከስሩ መንቀል ለነገ የምናሳድረው የቤት ስራችን አይደለም።
ቡድኑ ‹‹ጦርነት የገበጣ ጨዋታችን ነው›› በማለት በእብሪትና በማን አለብኝነት የለኮሰው እሳት እሞትለታለሁ እያለ ከሚያስጨርሰው የትግራይ ህዝብ ባለፈ በመላው አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽን ፈጥሯል።
ነገ ሁለተኛ አመቱን በሚያስቆጥረው የሰሜኑ ጦርነት በአሸባሪው ትህነግ እብሪት ተለኩሶ ዛሬም ድረስ እሳቱ አገርና ህዝብን እየለበለበ ይገኛል። ቡድኑ በለኮሰው በዚህ እሳት የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ሕዝብ አላስፈላጊ ዋጋ ለመክፈል ተገዷል።
እየተከፈለ ባለውም ዋጋ መላው ኢትዮጵያዊ ውስጡ ቆስሏል፤ ታሟል። ህዝቡ ከዚህ ህመሟ ማገገም እንዲቻል መንግሥት የሰላም አማራጮችን በተደጋጋሚ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል። ይሁንና መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመግፋት ለሶስተኛ ጊዜ የተጀመረው ጦርነት በምንም መንገድ ቢሆን መቋጫ ሊበጅለት እንደሚገባው በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
መቋጫው እየተናፈቀ ያለው ይኸው የሰሜኑ ጦርነት በጊዜ ሊቋጭ ያልቻለው ቡድኑ የትግራይን ህዝቡ መያዣ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ቡድኑ ይህንኑ እውነታ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በተለያየ መንገድ ሲገልጽ መስማት የተለመደ ነው።
ይህንንም አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱ በተጀመረበት በ2013 ዓ.ም መገባደጃ ላይ አገር እያፈረሱ ያሉትን ጥቂት ግለሰቦች ከትግራይ ሕዝብ ነጥሎ ለማውጣት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት እንደሆነ ገልጸዋል። በወቅቱም “አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን። አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን” በማለት ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ብልሃት፣ ጥንቃቄና ጊዜ የሚፈልግ ነው። እርግጥ ነው ቡድኑ አገር ከማተራመስ እስከ ማፍረስ የሚዘልቅ አጀንዳውን ለማስቀጠል የትግራይ ህዝብን መያዣ አድርጎ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ደግሞ ጦርነቱን ፈታኝና ውስብስብ ማድረጉ አይቀሪ ነው።
ያም ቢሆን ታዲያ አረም ያው አረም ነውና የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መነቀሉ የግድ ነው። ሲነቀልም መልሶ እንዳይበቅል ከስሩ መንቀል ሁነኛ መፍትሔ ከመሆኑም በላይ ‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል›› የሚለው ተረት እንዳይደረስ በማያዳግም መልኩ ምንጩን ማድረቅ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያን የገጠማት ጠላት የውጭ ወራሪ ሳይሆን የስልጣን ጥማት ያናወዘውና የገዛ አገሩን ለማፍረስ የተዘጋጀ ነቀርሳ ባንዳ ነው። ይህን የአገርና የህዝብ ነቀርሳ የሆነን ቡድን መልሶ እንዳይበቅል አድርጎ የመንቀሉ እውነታ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሚቀር አይደለም ።
‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ ዛሬ የትግራይ ህዝብን መያዣ አድርጎ እየነገደ ያለው ይህ ቡድን ጉም ሆኖ የሚተንበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም። ለዚህም ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለአንዲት ኢትዮጵያ መቆማቸው ብቻ በቂ ነው።
ቡድኑ የትግራይን ህዝቡ መያዣ አድርጎ የጀመረውን ጦርነት ለዘለቄታው በማስቆም ወደ ጀመርነው የልማትና የብልጽግና ጎዳና በሙሉ አቅማችን ለመመለስ ህዝብ በአንድ ልብ ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል። ኢትዮጵያን እየተፈተነች ያለችው በምታውቃቸው የውስጥ ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን በብዙ አደባባይ በሙሉ ጠላቶች ነው። ለዚህ ደግሞ በአንድነት መቆም የግድ ነው።
ጦርነቱ የቱንም ያህል እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እህሉን ከገለባ የመለየት ሥራ ጊዜ ወስዷል። በአውደ ግንባር ያለው እውነታም የጦርነቱን የመቋጫ ጊዜ የሚያሳብቅ ከሆነም ውሎ አድሯል፤ ለዚህም ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን የአላማ ጽናት እና ሕዝባዊነት ከፍ ብሎ የሚታይ ነው።
ሠራዊቱ ድንጋይ ተንተርሶ፣ ጤዛ ልሶና ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ እየከፈለ ባለው መስዋእትነት አገርና ህዝብን አንገት ከመድፋት አውጥቷል፤ የጠላቶቻችንም ሟርቱ ከንቱ እንዲሆን አድርጓል። ለዚህም ከፍ ያለ ክብር ይገባዋል።
በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ግዞት ውስጥ ወድቆ ረሃብ የጠናበት የትግራይ ህዝብም ዛሬ ነጻ እየወጣ መሆኑ ዕለታዊ ዜና መሆን የቻለው በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደም ነውና ዳግም ክብር ይገባቸዋል።
ከድል ዜናው ባሻገርም የትግራይ ህዝብ በቡድኑ ከገባበት የሰቆቃ ሕይወት ነጻ እንዲወጣ መንግስትና መላው ህዝብ በርካታ የቤት ሥራዎች አሉባቸው። ቡድኑ በአገሪቷ ካደረሰው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በበለጠ በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰውን የስነ ልቦና ስብራት በቶሎ ማገገም እንዲችል የኢትዮጵያውያን ርብርብና ትብብር ለነገ የሚባል አይደለም።
በጦርነቱ የመጨረሻው ምእራፍ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እየበረታ የመምጣቱ አውነታ፤ ለቡድኑ ሕይወት ለመስጠት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ዘመቻ መሆኑን በመገንዘብ አንድነታችንን በማጠናከር ዘመቻውን ለመቀልበስ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015