አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ ናት። ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን የቡድኑ ወዳጅና ደጋፊ ከሆኑ አገራት ጋር ጭምር ግልጽ የሆነ ጦርነት ውስጥ ነች። ይሄን እውነት ለማወቅ ጠቢብ መሆን አይጠበቅብንም። የምናየው የምንሰማው ሁሉ አገራችን በዓለም አቀፍ ጦርነት ውስጥ እንዳለች የሚመሰክር ነው። በዚህም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍ ባለ የአገር ውስጥና የውጪ ጫናዎች ውስጥ ነበረች።
በጫናዎች ውስጥ እንደአገር ብዙ ዋጋ ከፍለናል። በህልውናው ለመጣበት ድርድር የማያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመወገን በብዙ ጫና ሰልፍ የወጡበትን ጠላቶቹን አሳፍሯል። ዛሬ ላይም ቢሆን በተመሳሳይ መንገድ እለ አገሩ ዘብ በመቆም የጠላቶቹን ሕልም እያከሸፈ ይገኛል።
ከአገር ውስጥ አሸባራው ሕወሓትና ሸኔ ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጋር በመሆን፣ ከውጪ ደግሞ ታሪካዊ ጠላቶቻችንንና ከአካባቢው ያልተገባ ጥቅም የሚፈልጉ ኃይሎች በመናበብ በጫና ሊያንበረክኩን ረጅም ርቀት ሄደዋል። ግልጽ ጦርነት አውጀው በአደባባይ ተገዳድረውናል።
በዓለም አቀፍ የመገናኝ ብዙሀን የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻችን ከማካሄድ ጀምሮ እስከ ማእቀብ የደረሱ ማእቀቦችን ጥለውብናል። በተቀጣሪ አክቲቪስቶችን የበሬ ወለድ ዘገባዎች አገራዊ እውነታችን በማጠልሸት ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን ነገር እንዳይረዳ በትጋት ሰርተዋል። ሁሉም ግን እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። በዚህ ሁሉ ዘመቻ ለኢትዮጵያ የሚያስቡ፣ እውነታችንን ተረድተው ከጎናችን የቆሙ አገራት የሉም ማለት አይደለም፤ ነበሩ ።
ሕወሓት እንደ ነፃ አውጪ ድርጅት በደደቢት በርሀ በሰይጣናዊ ሀሳብ የተወለደ ነው። ይህ ቡድን ለአገርና ህዝብ መልካም ነገር ይሰራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ እየተሰቃየንበት ያለው በዚህ ቡድን ሀሳብና የፖለቲካ ፍልስፍና ነው።
ቡድኑ ገና ከውልደቱ ጀምሮ ብቻውን ሆና አያውቅም። ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ ውልደቱ ድረስ በብዙ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ሀይሎች ሲደገፍ የኖረና አሁንም እየተደገፈ ያለ ሀይል ነው። አቅም ትምክህቶቹም እነዚህ ሀይሎች ናቸው። ከነዚህ ሀይሎች ውጪ ህይወት የለውም። ዛሬ ላይም ተፈጥሯዊ ሞቱን ከመሞት ይልቅ በነዚህ ሀይሎች ህይወቱን ለመዝራት የሚያደርገው ጥረት የዚህ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ከትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን የመጣው በነዚህ ሀይሎች ትከሻ ላይ ታዝሎ ነው። ለ ሀያ ሰባት አመታት ስልጣን ላይ የቆየውም በነዚህ ሀይሎች ድጋፍ ነበር። ከስልጣን ከተባረረች ማግስትም ወደ ስልጣን በሀይል ለመመለስ የሄደበት የጥፋት መንገድ በነሱው ታምኖ ነው።
ያለፉት ሁለት የጦርነት አመታት በስተጀርባ የእነዚህ ሀይሎች ፍላጎት ለማስፈጸም በአሸባሪው/ ባንዳ ሕውሓት በኩል የተካሄደ ነው። አላማውም በራሷዋ የምትተማመንና ለሌሎች ጥቁር አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ምሳሌ የምትሆን አገር ተፈጥራ ላለማየት ነው። ለዚህም ሀገሪቱን ባልተገባ መንገድ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ማሳያ ነው።
አገሪቱ ባለፉት ሁለት አመታት ታይቶና ተሰምቶ በማያቅ ሁኔታ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኩል ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ ተሞክረዋል አብዛኞቹ ስብሰባዎች ለአሸባሪው ሕወሓት አጋርነትን የመግለጽ ያህል እስኪመስሉ ድረስ ትዝብትን ፈጥረው አልፈዋል።
አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ምድር ሁሉንም አይነት ግፍ ፈጽሟል። የትም መቼም በማንም ላይ ያልደረሱ ሰብዐዊ ግፎችን በገዛ አገሩና ወገኑ ላይ አድርሷል። ዓለም አቀፉን የጦርነት ህግ በጣሰ መልኩ ሁሉንም አይነት ግፍ ሰርቷል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ቡድኑ በአደባባይ በትምክህት ለፈፀማቸው ግፎች የጠየቀው ሆነ ለህግ ይቅረብ ያለው አካል የለም። ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ለሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ነን የሚሉ አገራት ሳይቀር ዝምታን እና አይቶ አለማየትን መርጠዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ለስልጣን ጥማቱ ሲል በየትኛውም ሀይል ከመጋለብ ወደ ኋላ የሚል አይደለም። ከውልደቱ ጀምሮ ያለው ታሪኩ በዚህ ባህሪው የተሞላ ነው። ከታሪካዊ ጠላቶቻችን አንስቶ በየወቅቱ በአገራችን፣ በህዝባችን ጥቅምና ፍላጎት ላይ ለተነሱ ጠላቶቻችን ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህም አገርን አስከ ማፍረስ የደረሰ የባንዳነት ተልእኮ ፈጽሟል።
የለውጡ መንግስት ሆነ በለውጡ አስተዳደር ስር ያለው መላው ህዝባችን ለቡድኑ ማንነትና ከማንነቱ ለሚመነጨው ሴራ እንግዳ አይደለም። ከዚህ የተነሳም ቡድኑን አምርሮ እየተዋጋ ይገኛል። ቀጣይ እጣ ፈንታው አገር ከዚህ ቡድን የባንዳነት ተልእኮ ነጻ ስትሆን እንደሆነም ከትናንትና እና ከዛሬ ታሪኩ በሚገባ ተረድቷል። ለዚህ አስረጅ የሚፈልግበት የመረጃ ክፍተት የለበትም።
ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻችው ከመቼውም ጊዜ በላይ ለችግሮቻችው መፍትሄ እንደሆኑ የተረዱበት ወቅት አሁን ነው። የችግሮቻችን ዋነኛ ባለቤት ያውቃሉ፤ መፍትሄውም ምን እንደሆነ ይረዳል። በዚህ ጉዳይ የውጪውን ዓለም እርዳታ አይፈልጉም። ከፈለጉም የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ እንጂ የችግሩ አቅም እንዲሆኑ አይደለም።
አሸባሪውን ሕወሓት ለራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም እየጋለቡ ያሉ ሀይሎች ቡድኑን ዳግም ወደ ስልጣን ህልማቸውን እውን ለማድረግ እየሄዱበት ያለው የሴራ መንገድ እንደ አገር ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ብዙ ሊሆን ይችላል እንጂ ከተነሳንለት የለውጥ አላማና ግብ የሚያደናቅፈን አይደለም።
በዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ጦርነት እና ጫና እንደ አገር እስከ ሙሉ ክብሯ የመቆየቷ ነገር የዚህ ተጨባጭ እውነታ ማሳያ ነው። ይህ ጦርነት እና ጫና በሌላ አፍሪካዊ አገር ሆኖ ቢሆን ኖሮ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት አያቅትም። በተመሳሳይ ጦርነትና ጫና የፈራረሱ አገራትን ቀደም ሲል የነበራቸውን አገራት ቁመና ማሰብ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በርግጥም የጽናት ምልክት መሆኑን ማረጋገጫ ነው።
እኛ ለእውነት ስለቆምን የቆምንለት እውነት ደግፎናል። ለእውነት መቆማችን መከራዎቻችንን ችለን እንድንጸና አድርጎናል። ወደፊትም ለሚፈጠርብን የክፉዎች ሀሳብ እንደማንወድቅ ይሄ ማረጋገጫችን ነው። በአንድነት በመቆም ድል ያደረግናቸው በርካታ ታሪኮች አሉን። ዛሬም ይህንን አለም አቀፍ ጦርነት እና ጫና በአንድነት የመከትንበት ታሪካችን የማንነታችን ተጨማሪ መገለጫ ሆኖ በትውልዶች መካከል የሚታወስ ይሆናል።
እንደ ቀደመው ትውልድ በአሁኑ ሰዐት ሀገራችንን ከግፈኞች ለመጠበቅ ከራሳችን በቀር ልንተማመንበት የሚያስችል አንዳች ነገር የለንም። መተማመኛችን አንድነታችንና የምንሞትላት አገር እንዳለችን ማሰብ ብቻ ነው። መተማመኛችን የህዝባችን የአገር ፍቅር ስሜትና የአትንኩኝ ባይነት የታሪክ ገድል ነው። መተማመኛችን ኢትዮጵያን የሚሉ ልቦች ናቸው። መተማመኛችን አገሬን ለባዕድ አሳልፌ አልሰጥም የሚሉ መልካም ሀሳቦች ናቸው። መተማመኛችን በአባቶቻችን መንፈስ በወንድማማችነት መቆማችን ነው። እንደ አገርም ሆነ እንደ መንግስት መተማመኛችን ይሄ ብቻ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ለሶስተኛ ጊዜ በከፈተብን ጦርነት የመሳሪያ፣ የሎጅስቲክስና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ የሚሰጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎችን እንደጀመረው አፍ ማስያዝ/ማሳፈር የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም የታሪክና የሞራል ግዴታም አለበት።
በዚህ ዘመን እንደቀደሙት ዘመናት ለጀመርነው ለውጥ ተግዳሮት በመሆን ዓለም አቀፍ አደባባዮችን የሞሉት የአሜሪካ አስተዳደር /የባይደን አስተዳደር / እና የአውሮፓ ህብረት አባል የሆኑ አንዳንድ አገራት ናቸው። እነዚህ አገራት ለኢትዮጵያ እውነት ለመወገን አቅም የማጣታቸው እውነታ ለማንም የሚሰወር አይደል። ከቻሉ አሸባሪውን ቡድን ወደ ስልጣን ማምጣት ፍላጎታቸውን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጫን ነው።
የጦርነቱ መጀመር ሰሞን አንቶኒዮ ጉተሬዝ እንዲህ ብለው ነበር ‹ጦርነት ለሕወሓት ያደገበት ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባይዋጋ ነው የሚሻለው› ብለው ነበር። ይሄ ንግግር በየትኛውም መመዘኛ አለም አቀፍ ተቋም ከሚመራ ግለሰብ የሚጠበቅ አልነበረም። የተነገረው ግን በአጋጣሚ አልነበረወም፤ ንግግሩ ለአሸባሪው ብድን የቱን ያህል የጥፋት ትምክህት እንደሆነው ማሰብ አይከብድም።
ከሰሞኑ ደግሞ እኚሁ ግለሰብ ‹ተደራደሩና ጠመንጃችሁን አስቀምጡ የሚለው ነገር ትልቅ ነገር አይደለም ትልቁ ቁም ነገር የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ድንበር ይውጣ የሚለው ነው። ሲሉ ተደምጠዋል።
ከውጪው አለም እንዲህ አይነት መልዕክት ያላቸውን ብዙ ንግግሮች መጥቀስ ይቻላል። ሀሳብን ያነሳሁበት አሜሪካ፤ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ሆኑ እነሱ የሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት የቱን ያህል ኢትዮጵያን በተመለከተ እየሄዱበት ያለው መንገድ የተሳሳተና የተዛባ መሆኑን ለማሳየት ነው።
አላማቸው ከተሳካላቸው አሸባሪውን ሕወሓት በመደገፍ ወደ ስልጣን ማምጣትና እንደፈለጉ አሻንጉሊት መንግስት በመፍጠር ለዘመናት እየሄዱበት ያለውን መንገድ በኢትዮጵያ እውን ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ለህዝባችን ምን ማለት ሊሆን እንዲችል ነጋሪ የሚሻ አይሆንም ።
እንደ አገር ወደ ለውጥ የመጣነው ከዚህ አለም አቀፍ እውነታ እራሳችንን በመታደግ የራሳችንን እጣ ፈንታ በራሳችን ለመወሰን ነው። ለዚህ ደግሞ በቂ መነቃቃትና ዝግጅት አለን። በጫናና በማዋከብ የሚፈጠር ምንም ነገር አይኖርም። የተረከብናት አገር በብዙ መስዋእትነት የተፈጠረችና ከትውልድ ወደ ትውልድ ስትሸጋገር የኖረች ነች።
ትውልዱ የገባበት እልህ አስጨራሽ ትግል የአገርን ህልውና ለማስጠበቅና የህዝባችንን የመልማት መሻት እውን ለማድረግ ነው ። ትግሉ በልጆቿ ሀሳብ፣ እውነት እና ታሪክ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠርና ለጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ለመሆን ነው።
ለዚህም ይህን መሰረታዊ ጥያቄ ሁሉም ዜጋ ሊጠይቅ ይገባል፤ አሸባሪው ሕወሓት በባንዳነት አገር ለማፍረስ እስከ ሲኦል ለመውረድ ከራሱ ጋር መማማሉ የአደባባይ ሚስትር ነው፤ እኛስ አገራችንን ለመታደግ እስከየት ድረስ ተጉዘናል፤ ለመጓዝስ ወስነናል?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015