በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችውና በሜድትራንያን ባህር ጫፍ የምትገኝ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ እ.ኤ.አ በ2011 ለአራት አስርት ዓመታት ካስተዳደሯት የሙዓመር ጋዳፊ መሪነት ከተፋታች በኋላ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በማጣቷ ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት አስከፊ ጊዜያትን አሳልፋለች።
በተለይ ከ2014 ወዲህ በፖለቲከኞች አቋም መለያየት ማዕከላዊ መንግሥት አጥታ ለሁለት በመሰንጠቅ መቀመጫቸውን ትሪፖሊ ባደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ ሲራጅን፤ በምስራቅ ቡድን መሪ ጄኔራል ከሊፋ ሃፍጣር አስተዳደር ስር ወድቃለች። ይህ እንደመሆኑም ከአመራሮቹ ጎን በተሰለፉ ታጣቂ ኃይሎች፤ በጎሳ፣ በከተማና በቀበሌ በተደራጁ አንጃዎች ስትዋከብ ሠላምና ዜጎቿንም ስትነጠቅ ቆይታለች።
በተለይ የአልቃይዳና የአይ ኤስ አይ ኤስ መፈልፍያ ሌላ ሳይሆን መነሻው ከሊቢያ ነው፤ ከአፍሪካ ምድር በገፍ የሚፈልሱ ስደተኞችን ለማስቆም የሊቢያን ሠላም ግድ ይላል» የሚሉት አውሮፓውያንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሁለቱን ባላንጦች ለማስታረቅ ብዙ ደክመዋል።
6 ነጥብ 4 ሚሊየን ህዝብ በሚኖርባት ሊቢያ የሠላም አየር እንዲነፍስ ሁለቱን ባላንጦች ከቀደመ ደም አፋሳሽ ትግላቸው በማለዘቡ ሂደት በተለይ አውሮፓውያኑ ብዙ ደክመዋል። የፈረንሳይና የጣሊያንና ሚና ደግሞ ከሁሉ ገዝፎ ይታያል። ሁለቱ አገራት በተለይ ባሳለፈነው ዓመትም በሊቢያ ሠላም ጫና ፈጣሪና መፍትሄ አምጪ ለመሆን የዲፐሎማሲ ፍልሚያቸውን አጧጡፈውት ተስተውለዋል።
ምንም እንኳን ውጤታማነቱ ከመድረክ ስምምነት መሸጋገርን ባይችልም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁለቱን ባላንጦች ፓሪስ ላይ ፊት ለፊት ማገናኘት ችለዋል። ጣሊያንም በበኩሏ ፓሌርሞ ላይ ጉባኤ በማሰናዳት ሁለቱን አንጃዎች ፊት ለፊት አደራድራለች።
ይሁንና ሁለቱን አውሮፓውያን ጨምሮ ሌሎችም ለሊቢያ ሠላም የሚታትሩ አካላት እንደ ግል ፍላጎትና ምኞታቸው በሚጓዙበት መንገድ የየቅል መሆኑ የሚነሳ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ሰፊ ትንታኔው ያሰፈረው የፋይናንሺያል ታይምሱ አንደሪው ኢንግላንድ እንደሚለውም፤ ፈረንሳይና ጣሊያንን ጨምሮ ለሊቢያ ሠላም የሚታትሩት አገራትና ተቋማት የየግል እርምጃ የትሪፖሊን ዜጎች ለአስከፊው ሞት፤ ስደትና ረሃብ አገሪቱንም ከመፈራረስ መታደግ እንዳይችል ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ይታያል።
ምንም እንኳን የደህንነት ሁኔታዋ ይህ ነው በሚባል መልኩ በቅጡ ባይታወቅና ፖለቲካ ጡዘቱ ፍቱን መፍትሄ ባያገኝም ቀደም ሲል የነበረው እጅግ እስከፊና አስፈሪ ቀውስ አሁን ላይ ጋብ ብሏል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል።
ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው አስከፊ ጦርነት እልቂት በተቃራኒው አሁን ላይ ሁለት ጎራ መድበው ሲፋለሙ የነበሩ አንጃዎችም ቀልብ ወደ መግዛቱ መጥተዋል። ይህም በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት በማስፈን ህዝቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲመራ ለማድረግ በጦርነት በምትታመሰው ሊቢያ ጭላንጭል ተስፋ እንዳላት ብዙዎች እንዲያምኑ ምክንያት እስከ መሆን ተሻግሯል።
ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ይህ ነው ብሎ ስለ ሊቢያ ሠላም አፍን ሞልቶ መናገር አስችጋሪ ሆኗል። ሁለቱ አንጃዎች በፓሪሱ ጉባኤ በአገሪቱ ምርጫው እስኪካሄድ ሠላም ለማስፈን የየበኩላቸው ኃላፊነት ለመወጣት ቃላቸው ቢሰጡም አሁን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተቃረነ ነው።
መቀመጫቸውን ትሪፖሊ ባደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ ሲራጅን በምስራቅ ቡድን መሪ ጄኔራል ኮማንደር ከሊፋ ሃፍጣር መካካል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክሩ አሁንም ቢሆን መቋጫውን አላገኘም። መሪዎቹ የሚራመዱበት አጀንዳ የየቅል መሆን የትሪፖሊን ሠላም ከሰባት ዓመታት በኋላ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ብዙ ርቀት እንዳትጓዝ እየተገዳደረው ይገኛል።
ይህም ሆኖ ለሊቢያ ሠላም ደከመኝ ሰለቸኝ የማይለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ሁለቱን አንጃዎች ዳግም ወደ ጠረጴዛ የሚመልስ ጉባኤ ማሰናዳቱ ታውቋል። በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ግሃሳን ሳለሜ ዋቢ በማድረግ በርካታ መገናኛ ብዙኃኑ ባወጡት መረጃም፤ ጉባኤው ከቀናት በኋላ እንደሚካሄድ ታውቋል። በጉባኤውም 120 እስክ 150 የልዑካን ቡድን እንደሚገኙና የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ከማቅረብ ጀምሮ የፕሬዚዳንቱን የፓርላማ ምርጫም ቀነ ቀጠሮ ይወስንበታል ተብሎ ተጠብቋል።
በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ግሃሳን ሳለሜ የጉባኤ መካሄድ ብቻም ሳይሆን ድምር ውጤቱ ስኬታማ መሆን ከሁሉ በላይ እጅጉን አስፈላጊ ነው» ያሉ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነና ነገሮች በተቃራኒው ከተጓዙ ግን አገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ በማሸጋገር ባለፈ ከመበታተን ማዳን እንደማይቻል አስገንዝበዋል።
የአፍሪካውያን አጀንዳ በአፍሪካውያን ሊቃለል የግድ ስለመሆኑ አጥብቀው ያምናሉ የሚላቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ሙሃመትም ከቀናት በፊት መቀመጫቸውን ትሪፖሊ ካደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ ሲራጅን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ሁለቱ መሪዎች በትሪፖሊ በነበራቸው ቆይታ በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ እንዲሁም የሠላምና የፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም ስለ ቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
ሊቀመንበሩ የሊቢያውያን ችግር በራሳቸው መፈታት እንዳለበትና የውጭ ጣልቃ ገብነትም ቀውሱን ከማባባስና ከማወሳሰብ በዘለለ ምንም አይነት መፍትሄን ይዞ እንደማይመጣ አፅዕኖት መስጠታቸው የተመላከተ ሲሆን፤ ተቋማቸውም ሁለቱን አንጃዎች ያሳተፈ የብሔራዊ መግባባት ጉባኤን ለማሳናዳት ፍላጎት እንዳለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለማቅረባቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ ሲራጅም የኮሚሽነሩን ጥያቄ በደስታ መቀበላቸው የታወቀ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች ቢኖሩም ምቾት አይነሳኝም ማለታቸውም ይህን ለሙሳ ፋቂ ማሳወቃቸው የሚድ ኢስት ዘገባ አስነብቧል።
ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከቀናት በፊት በቱኒዚያ በተካሄደው በዐረብ ሊግ ጉባኤ ላይ በታደሙት ወቅት የሊቢያንን ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ሠላም ለመቀላቀል ሕብረቱ የሚያዘጋጀው ጉባኤም ከሦስት ወር በኋላ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል። በአዲስ አበባ ለማሰናዳት የተወጠነው ጉባኤ ለአገሬው መልካም አጋጣሚ መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ አንጃዎችም ለወደፊቷ ሊቢያ ዕጣ ፈንታ ሊያስጨንቃቸው እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተውታል።
በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያለው ቀውስ ዜጎችን በሚያሰቃይበትና አገራትና ተቋማት ይህ መቋጫ ያገኝ ዘንድ ከመማፀን ባለፈ መድረክ አዘጋጅተው ተፋላሚ ኃይሎቹን ለድርድር በሚማፀኑበት በዚህ ወቅት ተስፋ አስቆራጭ ሁነቶች መታየት ጀምረዋል።
በተለይ በጄነራል የካሊፍ ሃፍታር ቡድን በምስራቅ በኩል አገሪቱን በኃይል የመቆጣጠሩ አቅም መዳበር በተለይ መዲናዋ ትሪፖሊን የመቆጣጠር አቅም ማጎልበት ስለ ነገን ዋስትና ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል። መሰል ሁነቶችን ተከትሎ ትላንት በተካሄደው ግጭት የ21 ዜጎች ህይወት መነጠቁን የቢቢሲ ዘገባ አስነብቧል። ይህን ያስተዋሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፋይዝ ሲራጅ፤ አማፂያኑ ከውይይት ይልቅ በኃይል በማመንና መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተማዋን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየታተሩ ናቸው ሲሉ ኮንነዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖንፒዮም ሁለቱ አንጃዎች በአፋጣኝ የርዕስ በርዕስ ሽኩቻቸውን በማቋረጥ ለውይይት እንዲዘጋጁ አሳስበዋል። አንዳንድ አገራት ደግሞ ከዛሬ ነገ ሲጠብቁት የነበረው የሊቢያ ሠላም ተስፋ አስቆርጧቸው ዜጎችና አምባሳደሮቻቸውን ከአገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ እስከ ማሳለፍ ተሻግረዋል። ህንድና አሜሪካን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት የወሰኑ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳያሸጋግረው ተሰግቷል።
በርካቶች አሁን ላይ በአገሪቱ ምርጫ ማካሄድ እንዲሁም የኢኮኖሚና የደህንነት መዋቅሩ ማሻሻል አለበት ይህም ሳይውል ሳያድር መፈፀም ይኖርብታል የሚለውን አፅዕኖት ቢሰጡትም ከሁሉ በላይ ግን የሊቢያ ሠላም ማጣት በርካታ ዜጎችን በማሰቃያት ላይ ስለመሆኑና የሚያስገንዝቡ ተበራክተዋል።
በዚህ ረገድ ሰፊ ዘገባው ያስነበበው ዥንዋም በአሁን ወቅት በሊቢያ በሚስተዋለው ቀውስ የዜጎች ህይወት አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱንና ሳይውል ሳያዳር አፋጣኝ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ መጠየቁን፤
ዩ ኤን ኤች ሲ አር ዋቢ በማድረግ አትቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በታምራት ተስፋዬ