የኢፌዴሪ መንግስት በመንግስት ይዞታ የሚገኙ አንዳንድ ኩባንያዎች ወደ ግል ባለሀብት በሙሉ ወይም በከፊል ለማዞር ወስኖ እየሠራ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ ድርጅቶችንና የኃይል ማመንጨት፣ የመንገድ ግንባታ እና ሌሎች ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዞር የሚያስችለውን ጥናት የሚያካሂድ ቦርድ ማቋቋሙም ይታወሳል፡፡
እንደ መንገድና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ያሉ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች ከግል ባለሀብቱ ጋር በአጋርነት ለመስጠት የሚያስችለውን አሰራር በአዋጅ ቁጥር 1076/2010 አጽድቆ ወደ ስራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ የተቋቋመው ቦርድም ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የመንገድና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመለየት ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ ወደ ስራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
መንግስት “ለመንግስትና የግል አጋርነት” ክፍት የሚያደርጋቸው መስኮች የሚጠይቁትን እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ካፒታል ያለው ባለሀብት በሀገር ውስጥ የለም፡፡ ስለሆነም የውጭ ባለሀብት መጋበዙ ተገቢ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት መንግስት የግል ባለሀብቶችን በመሰረተ ልማት አቅርቦት ግንባታ ለማሳተፍ የጀመረው እንቅስቃሴ ተገቢና ወቅቱ የሚያስገድደው ቢሆንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያሳስባሉ። ምክንያቱ ደግሞ ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ነው፡፡
በተለይ ለውጭ ባለሀብቶች የሚሰጡ ፕሮጀክቶች በመንግስትም ሆነ በሀገር ባለሀብት መከናወን ያልቻሉና ልምድ ያልተያዘባቸው ሊሆኑ ይገባል። ኢትዮጵያውያን ከዘርፉ ተቀብለው የሚያስቀሩት የእውቀትና የቴክኒካል ብቃት እንዲኖር በስምምነት ውስጥ የሚካተት አስገዳጅ ሁኔታም መኖር አለበት።
ለምሳሌም ያህል የውጭዎቹ ባለሀብቶች ሶስት መንገድ ከገነቡ አራተኛውን በሀገር ውስጥ አቅም መገንባት የሚያስችል የእውቀት ሽግግር ማድረግና ልምድን ማዳበር ይጠበቃል። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ እየጠበቅን በሌለን አቅም ለውጭ ባለሀብቶች እየከፈልን በማሰራት የምንቀጥል ከሆነ ኢኮኖሚውን ማቀጨጭ ይሆናል። ስለዚህ አጋርነቱ ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኝ ተደርጎ መቀረጽ አለበት፡፡
ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት መንግስት ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ውል ሲፈጽም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በየዘርፉ የሚማሩ ተማሪዎችና ከፕሮጀክቶቹ ጋር የሚገናኙ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች መረጃ የሚያገኙበትን ህጋዊ ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። ፕሮጀክቶችን የሚከታተሉ አካላትም ለቁጥጥር ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባልተናነሰ የእውቀት ሽግግሩ በተገቢው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡
የአብዛኛዎቹ የእስያ ሀገራት እድገት የተመሰረተው በመኮረጅና ልምድና ተሞክሮን በፍጥነት በማስፋፋት ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን ከዚህ በፊት ይህን ዓይነት ልምድ እንደነበረ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ።
ለምሳሌ የአትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያውያን ሲዛወር በወቅቱ ብቃት ያላቸው ሰራተኞች ስለነበሩ ከአስተዳደር እስከ ቴክኒካል ስራዎች በሀገር ውስጥ በመተካት ሳይንገራጭ ማስቀጠል ተችሏል። አሁንም ቢሆን የውጭ ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር በአጋርነት እየሰሩ ቆይተው በሆነ አጋጣሚ ከሀገር ቢወጡ የእውቀት ሽግግሩ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡
እውቀት ብቻውን ግን በቂ አይደለም የስራ ዲሲፕሊኑንም መውረስ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ በቀጣይ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በመንግስትና በሀገር ውስጥ ባለሀብት ለማከናወን አቅምን መገንባት ያስችላል፡፡ ስለሆነም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት በተለይ ደግሞ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር የሚደረገው አጋርነት ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት መስጠት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ