አንዳንድ ምእራባውያን ሀገራት የአሸባሪው የትህነግ እስትንፋስ እንዳይቋረጥ የእርቅና ድርድር ድራማ ከመሥራታቸው በፊት ፌደራል መንግሥቱ ከልቡ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ብርቱ ጥረት አድርጓል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሰላም አምባሳደር እናቶች መቀሌ ድረስ በመሄድ ስለሰላም እንባ እያነቡ ተማጽነዋል። ሌላው ቀርቶ መንግሥት የአሸባሪው ትህነግ አባላት ስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ስለፈጸሙት ወንጀል እና ስለዘረፉት ሀብት ተጠያቂ ሳይሆኑ በሰላም ብቻ እንዲኖሩ እድል ሰጥቷቸዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሰላማዊ ውይይትና ድርድር የማድረግ ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ እነዚህን ወርቃማ ሀገር በቀል እድሎች አሻፈረኝ ብሎ በባዕዳን መዳኘት ባልፈለገ ነበር። ለነገሩ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከሀገሩ ሸምጋዮች ይልቅ ባእዳን ላይ ተስፋ የጣለው እስትንፋስ ዘርተው ወደ ዙፋኑ እንዲመልሱት በማሰብ ነው።
ቡድኑ እና ሀገራቱ የእከክልኝ ልከክልህ ቃልኪዳን የተግባቡት ወያኔ የደርግ መንግሥትን ለመጣል የትጥቅ ትግል ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ነው። በወቅቱ የደርግ መንግሥት የሶሻሊስት ርዕዮተዓለም ተከታይ ሆኖ የአሜሪካ ባላንጣ ከሆነችው ሶቬየትህብረት ጋር በመወዳጀት የማርክሲስት ሌኒንስት ቲዎሪዎችን በኢትዮጵያ ለመተግበር መሞከሩ ምእራቡን አለም በተለይም አሜሪካንን አስቀይሟታል።
ሀገራቱ /በተለይም አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጓጓችለትን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን በእጇ ማስገባት ህልሟ ስለነበር ዛሬ ጀርባዋን የሰጠችውን ሸአቢያን ጨምሮ ለወያኔ ታጣቂዎችና እና በሲያድባሬ ለሚመራው የሶማሊያ መንግሥት ድጋፍ እያደረገች የደርግ መንግሥትን አስወግዳ የእርሷን ፍላጎት የሚያስፈጽም ተላላኪ መንግሥት ለማቋቋም ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ወግናለች።
እንዳሰበችውም የተለያዩ አሻጥሮችን በመሥራት የደርግ መንግሥትን አስወግዳ ጉዳይ የሚያስፈጽምላትን የማፊያ ቡድን ወደ ስልጣን በማምጣት ጥቅሟን እያረጋገጠችና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንዲኖራት የምትፈልገውን የበላይነት የምታረጋግጥበትን ተስፋ አንግባ የመቀመጥ እድል አግኝታ ነበር።
ይሁንና በአስራ ሰባት ዓመት የወያኔ አገዛዝ ጫንቃው የቆሰለው የኢትዮጵያ ህዝብ የወሮ በላውን ሥርዓት ከትከሻው ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል በአዲስ መንግሥት አዲስ የለውጥ ምእራፍ ሲጀምር በአንጻሩ አሜሪካ ያስቀመጠችው አሻንጉሊት መንግሥት በትረ ስልጣኑን መነጠቁን ተከትሎ ጥቅሟ ሲከስምና ተስፋዋ ሲጨልም እጇን ሰብስባ መቀመጥ አልፈለገችም። ብዙኋኑን ትታ በጣት ከሚቆጠሩ ወንበዴዎች ጋር የማሸርፈገዷምስጢርም ይሄው ነው።
ወትሮም የፀረ ሽብር ህግ አውጥታ በአሸባሪነት የፈረጃቻቸውን ቡድኖችና ግለሰቦች ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ተኝታ የማታድረው አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውን ቡድን እንደ እንቁላል ስትንከባከበው ሲታይ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ያላት የጥቅም ትስስር እና ቃልኪዳን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መገመት አይከብድም።
የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች በሞኖፖል የያዙትን ስልጣን መልቀቃቸውን ሲያረጋግጡና መቀሌ ላይ ተሰባስበው ተመልሰው ወደ ስልጣን የሚመጡበትን ሴራ ሲዶልቱ አሜሪካን አጋራቸውና ምስጢረኛቸው አድርገው ነው። መቀሌ ቁጭ ብለው ከተላላኪዎቻቸውና ከጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጋር እየተመሳጠሩ በመላ ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉት በአሜሪካና የአሜሪካን ዓላማ በሚያራምዱ ምእራባውያን አይዟችሁ ባይነት ነው።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከስልጣን የተወገደው የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃው ላይ የተጫነበትን የጭቆና ፣ የብዝበዛና የዘረኝነት ቀንበር አሸንቀንጥሮ ለመጣል በማሰብ እንጂ ይህን ያህል የአሜሪካና የቡድኑን ጥቅማዊ ተስስር ተረድቶ አልነበረም። አሁን ግን አሜሪካና ምእራባውያኑ ለአሸባሪው ብድን የመወገናቸው ምስጢር ቁልጭ ብሎ ታይቶታል።
ቡድኑ ከተጠያቂነት ለማምለጥ እና በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ ለመሸጎጥ ሲል ‹‹ትግራዋይ ጠል አስተዳደር በመስፈኑ ተገፍተናል›› የሚል ፕሮፓጋንዳ እየነዛ በአንድ በኩል ፌደራል መንግሥቱ አቅም እንዳይኖረው በሁሉም ዘርፍ የማዳከምና ሀገር እንዳይረጋጋ የማድረግ ሥራ ሲሠራ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ህዝብን በተለይም ወጣቱን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እየጋተ የሚቃጣብህን ጥቃት ትመክታለህ በሚል እየደለለ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥ አሜሪካና አጋሮቿ በይፋም በህቡእም ይደግፉት እንደነበር ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ቡድኑ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ በእንቢተኝነት ምርጫ ሲያካሂድ፤ የሰሜን እዝ ወታደር ላይ ጥቃት ሲፈጽም፤ በአማራና በአፋር ክልል በንጹኋን ዜጎች ላይ ሰቆቃ ሲያደርስ፤ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሰ ህጻናትን እያስታጠቀ ለጦርነት ሲያሰልፍ ፤ ተወንጫፊ ሮኬቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት እና ሰላማዊ ሰው ወደሚኖርባቸው ትልልቅ ከተሞች ሲተኩስ፣ የእርዳታ እህል ጭነው የገቡ ተሸከርካሪዎችን ለወታደራዊ አገልግሎት ሲያውል፣ የእርዳታ መጋዘኖችን ሲዘርፍ፣ የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማቶችን ሲያወድም የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን የእርሱን ዓላማ የሚያራምዱ ምዕራባውያን ትንፍሽ ማለት አልፈለጉም። እንደውም አሸባሪው ትህነግ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶችን እያደረገ ወደ አማራና አፋር ክልል ሲያስፋፋ ምእራባውያኑ እያንቆለጳጰሱና እያጀገኑ ያወሩለታል።
የትህነግ አመራሮች በሁለተኛው ዙር ወረራቸው ገና የደቡብ ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ደሴን ሲቆጣጠሩ የተናገሩትን እናስታውስ፤ ጀነራል ጻድቃን ‹‹ጦርነቱን ጨርሰናል፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው? መደራደር አያስፈልገንም፤ እያሉ ሲመጻደቁ ሰምተናቸዋል›› አሁንም እኮ መንግሥት ጦርነቱን ጨርሶታል ለምን ከወንበዴ ጋር መደራደር ይፈልጋል የሚል አይጠፋም።
ትህነግ ወሰኑን እያሰፋ ወደመሃል ሲገሰግስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ይሁን ምእራባውያንባለበት እንዲቆምና ድርድር እንዲያደርግ ጫና ሲፈጥሩ አልታየም። እንደውም እንደቢቢሲ፣ አልጀዚራና ሲኤን ኤንን የመሳሰሉት ሚዲያዎቻቸው ትህነግ በመቀሌ ከተማ አቅራቢያ ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በቪዲዮ እያሳዩ ልክ የአዲስ አበባ ከተማ በትህነግ ታጣቂዎች በከበባ ውስጥ እንዳለች በመግለጽ ህዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ ይጥሩ ነበር።
ዜጎቻቸው አዲስ አበባ ከተማን ለቅቀው እንዲወጡ በተለያዩ ጊዜያት ማሳሰቢያ ይሰጡ እንደነበር የምናስታውሰው ነው። ይህም ብቻ አይደለም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ጥገኝነት የሚፈልጉ ከሆነ ሊያሰጠጓቸው እንደሚችሉ ጭምር የማግባባት ሥራዎችን ይሠሩ እንደነበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አንደበት የሰማነው እውነታ ነው።
የእነርሱ ምኞት በህዝብ የተመረጠውን እና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሊሰጣቸው የማይችለውን መንግሥት ከስልጣን አውርዶ ጥቅማቸውን የሚያረጋግጥላቸውን የትህነግ አሸባሪ ቡድን ወደ ስልጣን ማምጣት ስለሆነ ቡድኑን በተለያየ መንገድ ቢደግፉት ሊገርመን አይገባም።
ጦርነቱን ተከትሎ በሁለቱም ወገን በኩል የሚደርሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የሀገር ጉዳትነው በሚል መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ትንሽ ርምጃውን ገታ ሲያደርግ አሸባሪው ትህነግ በበኩሉ የጦርነት ነጋሪቱን እየጎሰመ፣ ዘገሩን እየሰበቀ፣ ሰላማዊ ሰዎችን እየጨፈጨፈና መሰረተ ልማቶችን እያወደመ ወሰኑን አስፍቶ መቆሚያዬ አራትኪሎ ነው ሲል ምእራባውያኑም ሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያበረታቱታል እንጂ አያወግዙትም።
አሸባሪው ትህነግ ድል የቀናው ሲመስለው እንደአንበሳ እያገሳ ዓለምን ያናውጣል፤ ያኔ ወዳጆቹ ጮቤ እየረገጡ ገድሉን ያወሩለታል፤ የሚደፈሩት ህጻናትና ወይዛዝርት፣ በግፍ የሚጨፈጨፉት ንጽኋን ጉዳይ ምናቸውም አይደለም። እነርሱ ህልማቸው አሻባሪውን የትህነግ ቡድን ወደ መንበረ ስልጣኑ መልሰው በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላቸውን ጥቅም ማስከበር ነው።
መንግሥት ርምጃውን ጠንከር ሲያደርግና በመረጡት ቋንቋ እያነጋገረ ሕግ የማስከበር ርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ ጦረኛ ነኝ፣ ማንም አይደፍረኝም ፣ አንበሳነኝ ሲል የነበረው የወንበዴዎች ስብስብ ወዲያው ድመት ሆኖ እናገኘዋለን። የአሳዳሪዋን እግር እየላሰች ቁራሽ እንደምትለምን ድመት ሚያው… ሚያው… እያለ የጣረሞትና የድረሱልኝ ደምጽ ያሰማል። ይህን ጊዜ ወዳጆቹ ነፍሱ ከመውጣቷ በፊት ሊያድኑት ይሯሯጣሉ። አሁን በእርቅ ስም እያደረጉ ያለውም ይህንን ነው። እርቅ ፣ድርድር ፣ ሰላማዊ ውይይት የሚታያቸው መንግሥት በአሸባሪው ትህነግ ላይ የሚወስደው ርምጃ ሲበረታና የትግራይ ህዝብ በተለይም የትግራይ እናቶች እፎይ የሚሉበት ጊዜ ሲቃረብ ነው።
ለአሸባሪው የትህነግ ቡድን የችግሮች ሁሉ መውጫ መንገድ ጦርነትን ነው። ጦርነትን ልዩ መገለጫው /ብራንዱ / አድርጎ ወጣቱን እያነሳሳ ሲፈልግም እያስገደደ ወደ እሳት በመማገድ በርካታ ወላጆችን የወላድ መካን አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያውያን በተለይም የትግራይ እናቶች ዘላቂ ሰላም የሚወርድላቸው ደቡብ አፍሪካ ላይ በተጀመረው ድርድር ቡድኑ ትጥቅ መፍታት ሲችል ፤ የቡድኑ አመራሮችም በትግራ ህዝብ ሆነ በማላው ህዝባችን ላይ ለፈጸሙት መንጀል ለፍርድ ሲቀርቡ ነው ። ድል ለመከላከያ ሠራዊታችን።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015