‹‹ እባብ ተንኮሉን አይቶ እግር ነሳው›› አሉ፡፡ እንዲያው ይህን ተንኮሌን አይቶ ድሃ አደረገኝ እንጂ እኔ ሀብታም ብሆን ኖሮ ለማስታወቂያ አምስት ሳንቲም አልከፍልም ነበር፡፡ የምር ግን በማስታወቂያ ስለተነገረ የሚገዛ ምርት አለ? እኔ ዕቃ ስገዛ ከሳሙና ጀምሮ ማስታወቂያ አይቼ አይደለም፤ ባይሆን እንኳን ከዚህ በፊት የተጠቀመበት ሰው ካለ ስለዚያ ምርት የሚያወሩትን ሰምቼ ነው፡፡ ምርትም ሆነ አገልግሎት በማስታወቂያ ሲነገር ‹‹ይሄን ነገርማ መግዛት አለብኝ›› ብዬ አላውቅም፡፡ ይሄ የኔ ባህሪ ነው፤ ምናልባት ማስታወቂያ ላይ በሚሰማው ጥራትና ጥንካሬ የሚገዛም ይኖር ይሆናል፡፡
የሌሎች ማስታወቂያዎች ነገር ይቅርብንና እስኪ ስለ አልኮል ማስታወቂያዎች እንተዛዘብ፡፡ በእርግጥ ብዙ ተብሎላቸዋል፡፡ የሰሞኑን ለየት የሚያደርገው ግን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ድረ ገጻቸው የለቀቁት የአልኮል ማስታወቂያን አስመልክቶ የወጣው ደንብ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ መነጋሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ልብ ብላችሁ ከሆነ ይሄ ነገር በማህራዊ ገጾች መነጋገሪያ ሲሆን አንድ እንኳን ‹‹ለምን ይሄ ህግ ወጣ?›› ብሎ የተቃወመ አላጋጠመኝም፤ ቆይ ግን ሰው በአልኮል ማስታወቂያዎች ይህን ያህል ተማሮ ነበር ማለት ነው?
በእርግጥ በወጣው ደንብ ላይ አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑልኝ ነገሮች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው ከአልኮል ማስታወቂያዎች ውስጥ አብዛኞቹ የቢራ መጠጦች ናቸው፡፡ እነዚህ የቢራ መጠጦች ደግሞ የአልኮል መጠናቸው ከአምስት በመቶ በላይ አይደለም፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እንዳሉት ግን የአልኮል መጠጥ አምራቾች፣ አስገቢዎችና አከፋፋዮች በስፖርት ማዘወተሪያ ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህዝብ በዓላትና በዓውደ ርዕይ ቦታዎች የአልኮል መጠኑ ከ10 በመቶ በላይ ማስታወቂያ እንዳይሠራ ነው፡፡
የቦታዎቹ ነገር በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤ የአልኮል መጠኗ ነገር ግን ምቹ አይደለችም፡፡ ክቡር ሚኒስትር ይሄን ነገር እንደገና ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ማለት እኮ እነ ቢራ በተጠቀሱት ቦታዎች መተዋወቅ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ የሆነውስ ሆነና ግን ከ10 በመቶ በላይ የአልኮል መጠን ያለው መጠጥ ምን ይሆን? ይሄ ነገር የሀበሻ አረቄ ትሆን እንዴ? ለነገሩ አረቄ በፋብሪካ ስትጠመቅ ዘሮቿ ብዙ ብዙ ይሆናሉ። እነሱን አለማየትም አንዱ እፎይታ ሊሆን ይችላል።
ቆይ እስኪ የሚኒስትሩን መመሪያ እንቋጨው! ሚኒስትሩ ቀጥለው ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡፡ «የአልኮል መጠኑ ከ10 በመቶ በታች የሆነ የትኛውም የአልኮል ማስታወቂያ ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ እስከ ንጋት 12፡00 መተላለፍ ይችላል›› ይቺኛዋ ጥሩ መመሪያ ናት፡፡ ከምሽት ሦስት ሰዓት በኋላ ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ስለሚተኙ ቢያንስ ይሻላል፡፡ በዚችኛዋ ሰዓት ነበር አረቄን ማስተዋወቅ! እንዲያው ቢያንስ ቢያንስ ይቺን ግጥም እንኳን ቢለቋት።
«አረቄ ጠጥቶ አረቄ ነው ሽታው
ይታመማል እንጂ ሰው እንደ በሽታው!»
አይ የገጠር ልጅ ነገር! ይቺን አረቄ ደጋገምኳት አይደል? ታዲያ ምን ይደረግ እኔ በአካባቢዬ የማውቀው የአልኮል መጠጥ አረቄ ብቻ ነበር፤ አሁን ባልጠጣው እንኳን ባለፍኩበት ጎዳና ሁሉ በትልቅ ባነር፣ በገባሁበት ካፌ ሁሉ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ ባለፍኩበት ጎዳና ሁሉ በየግሮሰሪው የመጠጥ ዓይነት አያለሁ፡፡ የአረቄን ነገር አረቄ ያነሳዋልና የአካባቢያችን አረቄ ጠጪዎች የሚቀኟት ይቺ ቅኔ ትዝ አለችኝ፡፡
«ታረቂው እባክሽ ታረቂው
ተይ አታስጨንቂው»
በገጠርኛ ዘዬ ‹‹ታረቂው›› የሚለውን ‹‹ከአረቄው›› ብለን እንተረጉመዋለን(የትኛው ነው ትክክል ሌላ ጥያቄ ነው)፤ እናም አረቄ ቅጅልኝ ማለት ሲፈልጉ ‹‹እባክሽ ታረቄው›› እያሉ ያንጎራጉራሉ፡፡ የቅኔዋ ሰም ይሁን ወርቅ ባላውቅም ሁለተኛው ትርጉም እርቅ አድርጊለት ለማለት ነው፡፡
ከአረቄ ወሬ ወጥተናል (ኡኡቴ! አልሸሹም ዞር አሉ)፤ ከአረቄ ወሬ ወጥቶ ወደ ቢራ መሄድ ምን ይሆን ልዩነቱ? የሆነውስ ሆነና የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ ገደብ ይደረግለት መባሉ ጥቅሙ ለማን ይሆን? እንደኔ እንደኔ የአልኮል ማስታወቂያ ጭራሹንም ቢከለከል ራሱ ጥቅሙ ለባለቤቶች ነው፡፡ በቃ ወጪ ይቀንሳሉ፡፡ ማስታወቂያው በመቅረቱ ምንም የሚጎልባቸው ነገር የለም፡፡ ማስታወቂያ ቀረና ይሄ ህዝብ መጠጣት ሊያቆም? በፍጹም አይታሰብም! እንኳን የማስታወቂያው መከልከል መጠጣት ቢከለከል ራሱ አይተወውም፡፡
በነገራችን ላይ የመጠጥ ፋብሪካዎች የተለያዩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ስፖንሰር የሚያደርጉት እዚያ ላይ በመተዋወቁ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ብቻ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነትን እንደመወጣትም ይቆጥሩታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፋብሪካዎች ድጋፍ ባያደርጉ ያ ፕሮግራም ወደ ህዝብ ሊደርስ አይችልም፡፡ ዋናው ነገር ያ የሚተላለፈው ፕሮግራም ይዘት ነው፡፡ ህብረተሰቡን የሚያስተምር፣ ታሪክና ባህልን የሚያስተዋወቅ ፕሮግራም ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞችን የሚደግፉ የታወቁ የቢራ ፋብሪካዎችም አሉ፡፡
እነዚህ ድጋፍ የሚያደርጉ የቢራ ፋብሪካዎች ህብረሰተሰቡን እያገለገሉ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው፡፡ አስታውሳለሁ 2009 ዓ.ም ሄኒከን ቢራ ፍብሪካ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ የቅሬታ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ ስለፋብሪከው በተሠራው ዘገባ ላይ ቅሬታውን ሲገልጽ የተለያየ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጾ ነበር፡፡ ያ ማለት ስፖንሰር ከሚያደርጋቸው የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በተጨማሪ የተጎዱ ወገኖችንም ይደግፍ ነበር ማለት ነው፡፡
እኔ ራሱ ማስታወቂያ ሠራሁላቸው እኮ! ይህን ማለት የተገደድኩበት ምክንያት ስፖንሰር የሚሆኑት ማስታወቂያውን ሰምቶ ተጨማሪ ጠጪ እናገኛለን ብለው ስለማይሆን ነው፡፡ እናም ይሄ የማስታወቂያ ደንብ ቢጸድቅና ቢተገበር በፍጹም እነዚህ የመጠጥ ፋብሪካዎች አይጎዱም (እንዲያውም ተገላገሉ)፡፡ እኛም ተገላገልን! የእኛ ግልግል ደግሞ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ያለውን ቅጥ ያጣ ጩኸት መገላገል ነው፡፡ እንደ መጥጥ እና ኮንዶም ማስታወቂያ የሚያሳቅቀኝ የለም፡፡ ወዲያውኑ አቀራረቡ ተቀየረ እንጂ አንድ በሬዲዮ የሚተላለፍ የኮንዶም ማስታወቂያ ነበር፡፡ ገና ሲጀምር ብቻዬን ሆኜ አፍራለሁ፡፡ የህዝብ ትራንስፖስር ውስጥ የሰማው ሁሉ ግማሹ ይናደድ ነበር፤ ግማሹም ይስቅ ነበር፤ ግማሹም አፍሮ እንዳልሰማ ሆኖ የሚያሳልፈው ነበር፤ በቃ ፖርኖግራፊ እንደማሳየት በሉት!
የአልኮል ማስታወቂዎችም እንደዚሁ ነው፤ ከሰው ጋር ሆኖ ለማየት የሚያሳፍር፡፡ ምንም እንኳን በማስታወቂያ ውስጥ ግነት ስለሚበዛ የሰዋሰውም ሆነ የተጠይቅ ህግ ባይጠበቅም አንዳንድ ጊዜ የማይሆን ነገር ሁሉ ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ ሽማግሌ የተጣላ ሲያስታርቅ፤ ሰካራም ሲመክር እንጂ ሽማግሌ አልኮል ሲያስተዋውቅ የሌለ ነገር ነው፡፡ በሴቶች የሚተዋወቀው የአልኮል መጠጥም መስመሩን የሳተ ነው፡፡ በመጠጥ የሚታወቅ ወንድ እንጂ ሴት አይደለችም፤ ሴት መጠጥን ስትጠላ ነው በገሃዱ ኑሯችን የምናውቀው፡፡ በየአደባባዮች ላይ የተሰቀሉ የመጠጥ ባነሮች ግን የተራቆተች ሴት መጠጥ ጨብጣ ነው፡፡ የሚጠጡ ሴቶች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡
ለማንኛውም የዚህ የማስታወቂያ ደንብ መውጣት ማንንም ስለማይጎዳ ተግባራዊ ይደረግልን!
ዋለልኝ አየለ