ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በፖለቲካ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስኮች በችግር ውስጥ ትገኛለች። ችግሩ ያልነካው ወይንም የማይነካው ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ አይኖርም። ችግሩ የሁላችንም መሆኑ ደግሞ ለመፍትሔውም የሁላችንም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው። በመንግሥት በኩል ለነገዋ ነጻና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ይበጃል ተብሎ የታመነበት ሁሉ ከፖሊሲ እስከ መመሪያ እየወጣና እየተተገበረ ይገኛል።
የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ግን ከላይ እንደጠቀስኩት በፖሊሲና በመመሪያ በመንግሥት እንቅስቃሴ ብቻ የሚቀረፍ እንደማይሆን ያሳለፍናቸው ዓመታት አሳይተውናል። ዛሬ ወያኔና በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎቹ በጦር አውድማ አልሳካ ያላቸውን እኩይ ዓላማ በሽብርና በኢኮኖሚ አሻጥር ለማሳካት እየተንደፋደፉ ይገኛሉ።
የዚህ ሥራቸው የመጨረሻ ግብ ሕዝብ በየመንደሩ በሚፈጸሙ ወንጀሎች፤ የሽብር ሥራዎችና የኑሮ ውድነት ተማሮ በመንግሥት ላይ እንዲዘምት፤ ያንንም ተከትሎ በሀገሪቱ ቀውስና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው። እኛ ደግሞ ከሽብሩም ከኑሮ ውድነቱም ከወንጀሉም ጀርባ በዘላቂነት ሊያጠፉን ያሰፈሰፉ ጠላቶች እንዳደሉን በመገንዘብ ሳንማረር ከመንግሥት ጎን በመቆም ልንታገላቸው ይገባል። በተለይም ንጹሐንን በግፍ እየገደሉ እያፈናቀሉ ራሳቸው የዚህ ብሔር ፤ የዚህ ጎሳ ወገን ተጨፈጨፈ አለቀ ሲሉን እኛ «ኢትዮጵያዊ ሞተ» ብለን ራሳቸውን አንገት ልናስደፋቸው ይገባል።
በሌላ በኩል የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃንና መንግሥታት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ እጃችንን ካልጠነቆልን እያሉ ይገኛሉ። ወያኔ በጦርነቱ የበላይነት ያሳየ ሲመስላቸው ጉድጓዳቸው ውስጥ የሚሸሸጉት የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ፍላጎት ያናወዛቸው ሀገሮች መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደማያስደፍር ሲገባቸው ዳግም ከተሸሸጉበት ብቅ ይሉና በሁሉም ሚዲያዎቻቸው ፕሮፖጋንዳቸውን ያጧጡፉታል።
የውሸት ዜናዎችን እየፈበረኩ በቀን በቀን ይለቃሉ። ሰላም በሚፈልግና በዲፕሎማሲያዊ ምክክር መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ደጅ መጥናታቸውን ያበዙታል። አንዳንዴ ምክር አለፍ ሲልም ማስፈራሪያ ንግግራቸውን ሳያቋርጡ ያደርሱናል። በጥቂት ወዳጅ ሀገሮች ፍትሐዊ የሕሊና ፍርድ በፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ከሸፈባቸው እንጂ ኢትዮጵያን ዳግም እንዳትጠገን አድርገው የማፍረስ ሕልማቸውን ለማሳካት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።
ይህንን ሙከራቸውን ወደፊትም የሚያቆሙት አይመስልም። በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ ድምፅ እንዳይኖራት፣ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እንድትገባ እና ሌሎች ሀገሪቱን ያንበረክካል ያሉትን ሙከራዎች በሙሉ ተግባራዊ ሲያደርጉ እየተመለከትን ነው። ይህ ቀጥተኛ የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በሕዝቡ አንድነት፣ በመከላከያ ደጀንነትና በወዳጅ ሀገራት ትብብር እንደማይሳካ በተደጋጋሚ እየታየ ይገኛል።
አሁንም ቢሆን መላው የኢትዮጵያ ዜጎች ይህን በሚገባ በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት የአሸባሪውን ወያኔ ሀገር የማፍረስ ቅዠት ለማክሸፍ የሚያደርገውን ርብርብ በሙሉ ኃይል ልንደግፍ ይገባል ። የመከላከያ ሠራዊት የሚወስደውን እርምጃ በሞራል፣ በጉልበት አለፍ ሲልም በኢኮኖሚ መደገፍና ድሉን ማፍጠን የሕዝቡ ኃላፊነት ነው።
አሸባሪው ትሕነግ በጦር ግንባር ከሚያደርገው ወረራ ባሻገር የምጣኔ ሃብቱን ለማሽመድመድ በርካታ ሴራዎችን በድብቅ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ደጋፊዎቹ ጋር በማበር እየሠራ መሆኑ እሙን ነው። ይህንን ተከታትሎ ማክሸፍና ድሉን ሁለንተናዊ ማድረግ ያሻል። ይህን ሥራ መንግሥት ብቻውን ሊያከናውነው እንደማይችል እርግጥ ነው።
ለዚህም ማኅበረሰቡ የምጣኔያዊ አሻጥር ውስጥ የሚገቡ አካላትን በማጋለጥና እግር በእግር በመከታተል መጠቆም አለበት። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከውጭና ከውስጥ ለመገዳደር የሚሞክሩ ጠላቶችን በቀላሉ መርታት ይቻላል። በተጨማሪ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ከርቀት የሚያደርጉትን የሳይበር ጦርነት መመከት ከኅብረተሰቡ የሚጠበቅ ነው። በተለይ ለፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ ባለመስጠት፤ አለፍ ሲልም ሴራውን በማጋለጥ ሂደት ላይ መሳተፍ ያስፈልጋል።
ወያኔም ሆነ ምዕራባውያን የሚዘምቱብን ከማእቀብ ጀምሮ እኛን ለማንበርከክና አንገት ለማስደፋት የተመቻቸውን ያዋጣናል የሚሉትን በሙሉ በማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ሀገራችንንና ሕዝቧን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እንዲያልፉ ማድረጉ አይቀርም። በዚህም ከሞራል ጀምሮ ከሚደርሰው ጉዳት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተቋዳሽ ከመሆን ባሻገር የከፋው ነገር ሲፈጠርም በእሳቱም መለብለቡ አይቀሬ ነው።
በእሳቱ ብርሃንና ሙቀት የሚጠቀሙትና የሚደሰቱት የቅርብ ጠላቶቻችንና አንዳንድ አውሮፓውያን ብቻ ናቸው። ይህንን ግን ወያኔዎችና አባሪዎቻቸው በቅጡ የተረዱት አይመስልም። በመሆኑም እነዚህን ጠላቶቻችንን ከመንግሥት ጎን በመቆም የምንታገለው ማንንም ለማስደሰት አልያም የተለየ ጥቅም ለማግኘት ብለን ሳይሆን ራሳችንን፤ ሀገራችንንና ትውልድ ለመታደግ መሆኑን ማመን አለብን።
እንደዚህ አይነት ተደራራቢ ቀውሶች በማንኛውም ግዜ በየትኛውም ሀገር ሊከሰቱ ይችላሉ። ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ተከስተውም አይተናል። የኛን ለየት የሚያደርገው ግን ለሁሉም ችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያቱ የሀገራችን ጠላቶች ተላላኪ የሆነው ወያኔ መሆኑ ነው።
የወያኔ ባለስልጣናት ዛሬም ሞት አፋፍ ላይ ሆነው ገና በጨቅላነታቸው የሄዱበትን መንገድ በስተእርጅናም ተያይዘውታል። የት እንደሚያደርሳቸው የሚያውቀው ግን ዲያቢሎስ ብቻ ይመስለኛል። የትግራይ ምድር በወያኔ ተንኳሽነት እስካሁን ካሳለፋቸውም ሆነ ወደፊት ከሚያሳልፋቸው ጦርነቶች ውድ ልጆቹን ከመገበርና ሕዝቡን በስቃይ ከማቆየት ውጪ ምንም ጥቅም ሊያገኝ አይችልም።
የትግራይ ሕዝብ ከመቼውም ግዜ በላይ ዛሬ በትልቅ የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቋል። የወያኔ ሥራ ደግሞ እየፈጠረ ያለው ጥላቻ በጦር ሜዳ ውሎ ብቻ ሳይሆን የትግራይንም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ እህት ወንድሞቹ ጋር ደም የሚያቃባና የሚያቀያይም ነው። እዚህ ላይ በቀሪው ቦታ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምላሽ ሊሆን የሚገባው ወያኔንና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ ማየት ነው።
ትግራይ ታሸንፋለች የሚለው የወያኔ ድንፋታ መነሻው ይህ ካልሆነ «ትግራይ በቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሸንፋ ትዋጣለች» በሚል እሳቤ ለትግራይ ሕዝብ እየተነገረው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሰምተናል። እውነታው ግን በወያኔ መደምሰስ ኢትዮጵያ የምታሸንፈው ለትግራይ ሕዝብ የድል የነጻነትና የዲሞክራሲ ሻማ በማብራት ነው።
በመሠረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ሁሉም በየዘመናቱ በአስተዳዳሪዎች በርካታ ችግሮች እንደደረሰባቸው ይታወቃል። ይህ ማለት ግን አንዳንድ ብሔርና ጎሳ ተኮር ፖለቲከኞች እንደሚያራግቡት በኢትዮጵያ በሕዝብ ላይ የዘመተ ሕዝብ ኖሮ አያውቅም። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በቅርቡ እንደተናገሩት የሰሜኑ ጦርነት እንዲጠናቀቅና ኢትዮጵያና እኛ ሕዝቦቿ ሰላም እንድናገኝ በያለንበት የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል እላለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015