በለንደን እምብርት ላይ በተገነባው የእንግሊዙ የዜና ማሰራጫ BBC ዋና መስሪያ ቤት መግቢያ ደጃፍ ላይ በእጁ ሲጋራ የያዘ የጆርጅ ኦርዌል የነሐስ ሀውልት በግርማ ቆሟል። ከግርጌው ጥቅሱ ሰፍሯል። «ነፃነት ሌላ ምንም አይደለም። ሰዎች መስማት የማይፈልጉትን የመናገር መብት ነው» ይለናል። እኔም በዛሬ መጣጥፌ መስማት የማትፈልጉትን ነገር የመናገር መብቴን ተጠቅሜ ልነግራችሁ ነው።
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሽብርተኛው ትህነግ ጥቂት ገዢዎች ለድርድር እንደወጡ በዚያው እንዲቀሩ የሚመኙ ምኞቶችን በስፋት ሲዘዋወሩ ተመለከትሁ። አንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎችና ዩቲውበሮች ደግሞ ከደርግና ከትህነግ ጋር በጂሚ ካርተር አደራዳሪነት ለንደን ላይ ከተደረገ የይስሙላ የመጨረሻ ድርድር ጋር እያነጻጸሩ የደቡብ አፍሪካውን መንገድ የማራሚያ መንገድ አድርጎ እስከማየት ከመድረስ ባሻገር ታሪክ ራሱን ደገመ እስከማለት ደርሰዋል።
ንጽጽሩ ከመነሻው ዘመነ ጓዴነት የሚጎድለውና ለአቅመ ሙግት ስለማይበቃ እዚህ ላይ ልለፈው። ይህ በምኞት ላይ ያነጻጸረ ምኞት እንዳይበርደው የእኔን ልደርብለት። መቼስ ምኞት አይከለከል አይደል፤ የእኔ ምኞት ለሀገሬ ፦ በሕግ ተይዘው የነፈጉንን ፍትሕ አግኝተው፤ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የሀገራዊ ምክክሩ አካል ሆነው፤ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ሰቆቃ የፈጸሙበትን ሕዝብ እና ደጋግመው ከጀርባ የወጓትን እናት ሀገር ይቅርታ ጠይቀው፤ ለእነዚህ እኩያን ተግባራት በማጣቀሻነት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጥቋቁር መጽሐፎቻቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጉ፤ «በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን፣» እንዲሉ ነው።
ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ አመራሮቹ እንደወጡ ቢቀሩ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን መዋቅራዊና ተቋማዊ አድርገው በትግራዋይም ሆነ በሌላ ማህበረሰብ የዘሩት ጥላቻ፣ ልዩነት፣ ሀሰተኛ ትርክት፣ ኩርንችትና አሚካላ አብሯቸው አይወጣም። አይሰደድም። እነሱ እንደወጡ ከቀሩ እዳው ገብስ ነው የሚለው ሀሳብ ውሃ አያነሳም፤ የሽብርተኛው ትህነግ ክፉ መንፈስና አመለካከት ከገዢዎቹ አልፎ በማህበረሰብም በትውልድ የተጋባ መሆኑን በውል ካለመረዳትና መገንዘብ የተቀነቀነ ገራገርና የዋህ ሀሳብ አድርጌ ነው የወሰድሁት።
አይደለም በጣት የሚቆጠሩ ገዢዎች በየደረጃው እስከ ጎጥ ያሉ የ1ለ5 ጠርናፊዎች ሳይቀሩ በሆነ ተአምር ብን ብለው ከትግራይና ከመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መልክዓና አየር ቢጠፉ ክፉ ሀሳቡና የተሳሳተ ትርክቱ ላልተወሰነ ጊዜ አብሮን እንደሚኖር ያለምንም ማቅማማትና ማወላወል ተቀብለን፤ ለወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድሉ የሚጠበቅብንን እልህ አስጨራሽ ትግል የምናፈሰውን ሀብት፣ ጉልበትና ጊዜ ያህል፤ የሽብርተኛውን ክፉ መንፈስና የተሳሳተ አመለካከት ከአብዛኛው ትግራዋይ አስተሳሰብ ለማስጣል እንደሚያስፈልገን አበክረን አስበንና አቅደን መሥራት ይጠበቅብናል። ተገዶም ሆነ ፈቅዶ የሽብርተኛውን ክፉ መንፈስና የተሳሳተ ትርክት እንደ ቀኖና የተቀበለ፤ እንደ ክፉ ደዌ በሰራ አካላቱ የተሰራጨበት ትግራዋይ ቁጥር ቀላል አይደለምና ከፊታችን ገና ከባድ ፈተና ይጠብቀናል።
ከኢትዮጵያና ከእውነት አምላክ ጋር ተገደን የገባንበት ጦርነት በእኛ አሸናፊነት እየተቋጨ ነው። የድህረ ጦርነቱ ዳፋ ግን ላልተወሰነ ጊዜ አብሮን ይኖራል። አሸባሪውና ከሀዲው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ይዞ ለመጥፋት ታጥቆ እየማሰነ ነው። ትግራይን ሴቶችና ጨቅላዎች ብቻ የሚባዝኑበት የመናፍስት ክልል ሊያደርገው ቆርጦ ተነስቷል። እያደረገውም ነው። አሁንም ባለቀ ሰዓት እንኳ በፈጣሪ ምህረት የተራረፈውን ወጣት ለማስጨረስ ትህነግ ጉድጓዱ ከተማሰ ልጡ ከተራሰ በኋላ እንኳ ለማስጨረስ በዚህ ሰዓት መርዙን እየነዛ ነው። መጀመሪያ ወጣቱን በመቀጠል ሕፃናትን ከዚያ አረጋውያንንና አካል ጉዳኞችን በጦርነት እየማገደ እየጨረሳቸው ነው።
በእብሪትና በማንአለብኝነት እያስገደደና እያታለለ ትግራዋይን በሕዝባዊ ማዕበል በየግንባሩ እየማገደ እያስፈጃቸው ነው። አሸባሪው ሕወሓት ካፈርሁ አይመልሰኝ ብሎና ተስፋ ቆርጦ ትግራዋይን ይዞ እየሞተ ነው። ከዚህ የከፋና የባሰ ምን ይመጣል በሚል ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ጣዕረ ሞት ላይ ሆኖ እንኳ ትግራይን የወላድ መካን እያደረጋት ነው። በ17 አመቱ ጦርነት 70ሺህ ልጆቹን በመነጠቁ ጧሪና ቀባሪ ማጣቱ ሳያንስ ዛሬ የተረፉ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ትርጉም ለሌለው ጦርነቱ ተማግደው ሲያልቁ ዛሬ ተረኛው እሱ ሆኗል።
አሸባሪውና ከሀዲው ትህነግ የእሱን ተስፋ መቁረጥ ወደ ሕዝቡ በማጋባት ስለነገ ሕይወቱና ኑሮው ተስፋ እንዲቆርጥና እንዳይጨነቅ በማድረግ፤ ከአማራ ከኤርትራ ከአፋርና ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ተቆራርጦ ከጎኑ እንዲሰለፍ እያደረገ ይገኛል። ሆኖም የተረፈውን ትግራዋይ ከአሸባሪው ሕወሓት መንጋጋ ለመታደግ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠላትነት እንደማያየው ለማረጋገጥና የአሸባሪው ሕወሓትን ሰንኮፍ ለመንቀል የትግራዋይን ልብ ስለመማረክ አበክሮ ማሰብና መሥራት ይጠይቃል። የጸረ ሽብር ትግሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የትግራዋይን ልብ በመማረክ ሲታጀብ ነውና።
የጸረ ሽብር ትግል በአውደ ወጊያ በሚቀዳጁት ድል ብቻ አይረጋገጥም። የአሸባሪው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሆነውን ሕዝብ ልቦና እና አመለካከት ከወዲሁ መማረክ ግድ ይላል። አሸባሪውን ከሕዝብ የመነጠል የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል። አሜሪካ ለ20 አመታት ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገፍግፋ በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ሰውታና አካል ጉዳተኛ አድርጋ በባዶ እጇ አጨብጭባ ተሸንፋና ተዋርዳ የወጣችው የአፍጋኒስታውያንን ልቦና ማሸነፍ ባለመቻሏ ነው። የግንባሩን አውደ ውጊያማ ከ20 አመት በፊት ታሊባንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ አሸንፋ ነበር።
በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በሊቢያ፣ በናይጄሪያ፣ በማሊ፣ በሞዛምቢክ ወዘተረፈ አሸባሪዎችን በቀላሉ ማሸነፍ ያልተቻለው ለዚህ ነው። አሸባሪዎችን በጦርነት ለማንበርከክ ከሚደረገው ፍልሚያ ባልተናነሰ ርዕዮተ ዓለማቸውን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ከሚጠቀሙበትና በአካልም በሥነ ልቦናም ካገቱት ሕዝብ ማውጣትና ማጽዳት ይጠይቃል። በአሸባሪው ሕወሓት ላይ ከሦስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ የተቀዳጀነውን አንጸባራቂና በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተዋጀውን ድል ማጽናት ያልቻልነው የትግራዋይን ልቦና በቅጡ ባለመማረካችን ነው። አሁንም የማይቀረውን ወታደራዊ ድል ለማጽናትና ለማዝለቅ ከወዲሁ የትግራዋይን ልብ በማሸነፍ ልናጅበው ይገባል። ይበል የሚያሰኙ ሕዝባዊ ውይይቶችና ሌሎች ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ከሸኔ፣ ከጉሙዝ ታጣቂዎችና ከሌሎች አሸባሪዎችና ሽፍቶች ጋር የምናደርገውን ትግልም እንደዚሁ።
በውል ባንገነዘበውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያውያንን በተለይ ደግሞ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ ብዙ ጥረዋል። ሩቅ መንገድ ተጉዘዋል። ዋጋም ከፍለዋል። ለሰላም ካላቸው ቁርጠኝነትና ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በውትድርና ሕይወታቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት፤ ጓደኞቻቸውንና ወንድማቸውን ስለነጠቃቸው፤ ጦርነት የአገርን ኢኮኖሚ ምን ያህል እምሽክ ድቅቅ እንደሚያደርግና እንደሚያወድም አበክረው ስለተገነዘቡና የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ይበቃዋል በሚል ጽኑ እምነትና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች የድሀን ልጅ የእሳት ራት ያደርጋሉ እንጂ እነሱ አይዋጉም በማለት ለትግራይም ሆነ ለሌሎች ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ እስከ መጨረሻው ሰዓት ሆደ ሰፊነትንና ትዕግስትን መርጠዋል።
አበው «ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች» እንዲሉ በከሀዲውና የእናት ጡት ነካሹ በሆነው ትህነግ መከላከያችን ፣ ሉዓላዊነታችን ፣ አገራችንና ሕዝባችን ለሰላም በታመኑ ከጀርባ ተወጉ። ባጎረሱ ጣታቸውን ተነከሱ። አሸባሪው ሕወሓት በእብሪት በጫረው እሳት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፋ፤ አካል ጎደለ፤ የአገር ኢኮኖሚ ክፉኛ ደማ፤ የሽብር ኃይሉ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማቶች መልሶ ለመጠገን ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆነ። አሁንም ከዚህ ያልተናነሰ የመልሶ ግንባታ ወጪ ይጠይቀናል።
ዛሬም ጥምር ኃይሉ በየደረሰበት ሽብርተኛው ሕወሓት ከትግራዋይ ጉሮሮ ቀምቶ ለሰራዊቱ ስንቅ ሊያውለው የነበረውን እና ከመሐል አገር የገባውን የዕለት ደራሽ እህል እያሰራጨ ነው። በወረራው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዕለታዊ እርዳታ ለማቅረብ ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ተደርጓል። ልብ አድርጉ ይህ ወታደራዊውን ወጪ አይጨምርም። ጥገና ሲያካሒዱ የነበሩ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በግፍ ተገደሉ። ይህ የትግራዋይን ልብ የማሸነፍ ጥረት አካል ነበር። መንግሥት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀውም ለዚሁ ሰናይ አላማ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ከጠብ መንጃ አዙሪት ለማውጣትና ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች ያልሄዱበትን የሆደ ሰፊነትና ቁጭ ብሎ የመነጋገር አዲስ መንገድ በመምረጣቸው በልኩ እውቅና ሊሰጣቸውና አብዛኛው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ሲገባ መንግሥታቸው በልፍስፍስነት ከመወቀሱ ባሻገር ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ደጋፊያቸውና ተከታያቸው ብዥታና ድንጋሬ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የትግራዋይን ልብ ለመማረክ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ግንዛቤ አልተያዘም። ይሁንና የእፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24ቱን ታላቅ ክህደት ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የአገር ህልውናን ለማስቀጠል ያሳዩት ቁርጠኝነት እና ሰራዊቱ ከተፈጸመበት ታሪክና ትውልድ ይቅር ከማይለው ክህደት በኋላ ሞራሉና ወኔው አንሰራርቶ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ እጅን በአፍ የሚያስጭን አንጸባራቂ ድል በማስመዝገቡ አገራዊ ሞራሉ እንዲያንሰራራ አድርጓል።
እፉኝቱ ትህነግ ይታበይበትና ይመካበት የነበረውን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም መቐሌ ሊገባ ችሏል። ለዛውም እጅ የመስጫ የመጨረሻ ቀነ ገደቡን ጨምሮ ስድስቱ ቀናት ሳይታከሉ። በሁለተኛው ወረራም ጣርማ በር ደርሶ የነበረው ወራሪ በሳምንታት ተጠራርጎ እንዲደመሰስና እንዲወጣ ተደርጓል።
እንደ መውጫ
አሸባሪው ትህነግ እንደ ሰብዓዊ ጋሻና እንደ መደበቂያ የሚጠቀምበትን የትግራዋይ ልብና አመለካከት ማሸነፍ ሳይቻል ወታደራዊ ድሉ ሙሉኡ አይሆንም። በጦር ሜዳ የሚገኘው ወታደራዊ ድል የትግራዋይን ልብና አመለካከት በማሸነፍ ካልታጀበ የአሸባሪው ሕወሓት መደምሰስ ብቻ ድሉን ዘላቂና አስተማማኝ አያደርገውም። የኢፌዴሪ መንግሥት ከጦርነቱ ባልተናነሰ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ የተግባቦት ስልት ነድፎ ሌት ተቀን መሥራት አለበት። ደጀኑን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ለማነቃነቅ እና የአሸባሪው ትህነግ ጭካኔና አገር የማፍረስ ደባ ለማጋለጥ እየሠራው ባለ ልክ የትግራይ ሕዝብን ለመማረክም በአግባቡ መንቀሳቀስ አለበት።
ለ50 አመታት ያህል እንደ መዥገር ደሙን ከሚመጠው፤ የወላድ መካን ካደረገው፤ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ በአፈናና ጭቆና ባሪያ ካደረገው፤ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ደም እያቃባው ካለ፤ በስሙ እየማለና እየተገዘተ የቡድናዊ ጥቅም ማሳደጃ ካደረገው፤ ወዘተረፈ ይልቅ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት በፍቅር በሰላም በነፃነትና በአንድነት የመበልጸግ አቅምና ተስፋ እንዳለው፤ ለአሸባሪው ትህነግ ግለኛ ጥቅም ሲባል ልጆቹ ከጉያው እየተነጠቁ ለጦርነት እንደማይማገዱ፤ የትግራዋይ ዕጣ ፈንታ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመስዋዕትነት የተሳሰረና የተገመደ መሆኑን ደጋግሞና በጥበብ አዋዝቶ በመግለጽ ልቡንና አመለካከቱን ማሸነፍ አለበት።
በስሙ እየማለና እየተገዘተ ለ27 አመታት አገርንና ሕዝብን በጠራራ በአደባባይ እየዘረፈ ራሱን ሲያበለጽግ እሱን ከድህነት አረንቋ ከሴፍቲኔትና ከተረጂነት ነፃ እንዳላወጣው፤ አንድ ጊዜ ዐቢይ ሊያንበረክክህ ነው ሌላ ጊዜ አማራ ሊያጠፋኸ ነው እያለ ፤ በተሳሳተ ትርክትና ቁጭት ሲያታግለውና ሲማግደው የኖረው ፤ ከተደቀነብህ አደጋ የምታደግህ እኔ ብቻ ነኝ የሚለው ለግል ጥቅሙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን ደጋግሞ ማጋለጥ ያስፈልጋል።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015