የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽምና አየር ላይ ከዋለ ዋለ እንጂ እንዳልዋለ ማድረግ ከማንም ሰብአዊ ፍጡር አቅም በላይ ነው። በመሆኑም፣ ዛሬ ዶክተሩ ይይዙ ይጨብጡትን ቢያጡ፤ ባሉት፣ ባወሩት፣ በዋሹና በቀባጠሩት ቢፀፀቱና ቢንገበገቡ ጉዳዩ የፈሰሰ ውሀ ነውና እዳው ገብስ አይደለም።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በአሁኑ ሰዓት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ናቸው። በመሆናቸውም መቀመጫቸው ጄኔቭ ይሆን ዘንድ ግድ ብሏል። ማለትም ጄኔቭ ናቸው ማለት ነው።
ዶክተሩ ጄኔቭ ይሁኑ እንጂ እየሠሩት ያለው ግን የጄኔቩ ወንበራቸው የሚፈልገውን ተግባርና ኃላፊነት ሳይሆን የበረሃው ምሽግ የሚፈልገውን ነው። እሚመሩት በጤና ድርጅቱ ሕግና ደምብን ሳይሆን በደደቢት ማኒፌስቶ ይመስላል። በመሆኑም ጉዳዩ ለዓለም ቸገር ብሎ ይገኛል።
ሰውየው፣ በተለይም በአሁኑ ሰዓት እየፈፀሙት ባለው ስህተታቸው ምክንያት ከኢትዮጵያውያን ጋር ብቻ አይደለም፤ ከሰላም ወዳዱ የዓለም ማኅበረሰብ ጋር ሁሉ ነው የተጋጩት። «ወደጃችን» ከሚሏት አሜሪካ ጋር ሳይቀር ተላትመዋል (ሕወሓት ጎጠኛ፣ ሙሰኛ፣… ድርጅት መሆኑን እና መቀጠል የሚገባው ድርጅት አለመሆኑን በመግለፅ አስተያየታቸውን በቲውተር ገፃቸው ላይ ያሰፈሩትን የኸርማን ኮኸንን አስተያየት ልብ ይሏል)።
የአፍሪካ መሪዎች ተበሳጭተውባቸዋል። ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰውየውና ድርጅታቸው ነገር ቆርጦላቸዋል። እነ ዩኤን ሳይቀሩ የሰውየው መረን የለቀቀ አስተያየት በሕግ እንዲታይና ውሳኔ ላይ እንዲደረስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እየደረሰባቸው ያለው ብዙ … ብዙ ነው።
እስኪ ትንሽ ወዳ ኋላ ሄደን ስለ ዶክተሩ ሰብእና ጥቂት እንበል።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ዘመን ቻይና አፍሪካ ውስጥ እያደረገች ያለችውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ መስፋፋት ያሳሰባት አሜሪካ «ምነው ምን አድርገናችሁ ነው ፊታችሁን ያዞራችሁብን?» ለማለት የሚመስል ስብሰባ ለማካሄድ በርከት ያሉ የአፍሪካ መሪዎችን ቤተ መንግሥቷ ድረስ ጋብዛ ነበር።
በዚያ «የሃሳብ ልውውጥ»፤ «ምክር»፤ «ምክክር» ምንትሴ … በተባለው ስብሰባ ላይ (የእራት ግብዣና የዋሺንግተን ዲሲን ጉብኝትን ጨምሮ) ድግስ ላይ በመልካም የዴሞክራሲ ጅምራቸው የሚወደሱት የጋናና የደቡብ አፍሪካን መሪዎች ጨምሮ፣ ጠ/ሚ ደሳለኝ ኃ/ማርያምን አጅበው የሄዱት የያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም ተገኝተው ነበር። ችግሩ መገኘታቸው አይደለም፤ ችግሩ መናገራቸው ነው።
ሰውየው በዲሲ ቆይታቸው ወቅት ብዙዎችን፣ ሰነባብቶም ራሳቸውን ያሳፈረ ቃለ መጠይቅ መንግሥታቸው ከደሀ ጉሮሮ ቀንሶ የአየር ላይ ወጪ እየከፈለ ሲያስተዳድረው ከነበረ ሬድዮ ጋር አድርገው ነበር። ነገሩ አፍ ሲያመልጥና ራስ ሲመለጥ አይታወቅም ሆነና በቃለ መጠይቁ ወቅት የተናገሩትን አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ በፌስቡክ ገፃቸው ሊያስተባብሉ ቢሞክረሩም ሳይቻላቸው ቀርቶ እነሆ «ታግ» ሆኖ (ዕድሜ በወቅቱ ሀሳቡን ላጋሩን ኤፍሬም ማዴቦና ለመሳሰሉት) እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ዘልቆ እየጠቀስነው እንገኛለን።
ዶክተሩ «ሬድዮ አገር ፍቅር» በሚል ከሚታወቀው ሳምንታዊ ሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉትና፣ በተለይም ዲያስፖራውን ማህበረሰብ ባስቀየመው ቃለ ምልልሳቸው፤ «በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ መሪዎች የአሜሪካ መንግሥት ጓንታናሞ ውስጥ ካሠራቸው የአልቃይዳ አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ማረጋገጫ አግኝተናል»፤ «የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግንኙነት አስመልክቶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ኢትዮጵያ ድረስ ሄዶ ለማነጋገር ለመንግሥታችን ጥያቄ አቅርቧል» … ነበር ያሉት።
በወቅቱ፣ ይህንን ንግግራቸውን ተከትሎ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ እሳቸው በአባልነት የሚገኙበት ትህነግ የሚባለው ድርጅት ሃያ ሦስት አመት ሙሉ እየዋሸ የዘለቀ ድርጅት መሆኑ ከበቂ በላይ ሲነገር ነበር የቆየው። ግማሽ ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ቱባ ቱባ ውሸቶችን በመዋሸታቸው ምክንያት በወቅቱ የቀለሉት እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በእሳቸው አማካኝነት ፓርቲያቸውም ጭምር ነበር የስም ስብራት የደረሰበት።
ለዚህ፣ ለእሳቸው የአፍ ወለምታ አቢይ ምክንያት እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የኖሩበት ድርጅት መሠረታዊ ባህርይ መሆኑም ነበር በወቅቱ አየር ላይ ይውል የነበረው። «ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም» እንዲሉ ሆነና እነሆ ያ የአፍ ወለምታ ዛሬም ድረስ አብሯቸው ኖሮ ለዳግም ቅሌት ዳርጓቸው ይገኛሉ።
ችግሩ ቅሌቱ አይደለም። የአሁኑን ለየት የሚያደርገውና ችግሩን ከመቅለልም በላይ ይሆን ዘንድ የሚያስገድደው ጉዳያቸው ወደ ሕግ የማቅናቱ ጉዳይ ነው። አዎ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አቤት ብለዋል። «ባፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ» ነውና በለፈለፉት ጉዳይ ሊጠየቁ ይገባል እያሉ ናቸው። ሰላም ወዳዱ የዓለም ሕዝብም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ጎን መሆኑን ማህበራዊ ሚዲያውን ያጥለቀለቁት አስተያየቶች እያመላከቱ ነው።
እንደሚታወቀው፣ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት የለም። አለ ከተባለ እንኳን «ከመቆሙት በታች፣ ከሞቱት በላይ» የሚባለው ዓይነት ነው። ይሁን እንጂ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ያንን የሚያክል ወንበር ላይ ቁጭ ብለው፤ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም እዛ ወንበር ላይ ፊጥ ብለው፣ ድፍን የዓለምን ሕዝብ ወክለው፤ የታመመውን ሊያድኑ፤ ያልታመመውን ሊከላከሉ ምለው ተገዝተው እያሉ፤ የዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ ሆኖባቸው የሌለ ድርጅታቸው ዳግም ሊያኖሩ በማሰብ ከድፍን ዓለም ጋር ተጋጩ።
«ከማንም ጋር አንወግንም፤ የቆምነው ለእውነት ብቻ ነው» የሚለውን የሬዲዮ ጣቢያ ከአድማጮቹ ጋር ያቆራረጡት ዶክተሩ በወቅቱ «የኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከአልቃይዳ ጋር ማገናኘት እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያነሱትን ሕጋዊ የመብትና የነፃነት ጥያቄ ላለመመለስ የሚደረግ አጉል ውጣ ውረድ» እንደሆነ ሲሰነዘሩባቸው ከነበሩት ትችቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ሰውየው ከልምድም ይሁን ከሕይወት የመማር ልምድ አልታደሉምና ዛሬም እዛው ተገኙ።
የዛን ጊዜው ቅጥፈትና የራስን ወገን ከአልቃይዳ ጋር ማዛመድ ዋናው ምክንያቱ «ወዳጃችን» የሚሏትን አሜሪካንና የኦባማን አስተዳደር ማስደሰት ነበር። የአሁኑ፣ ምንም ሳይታክቱ፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ ያለ ምንም እፍረት (ካፈርኩ አይመልሰኝ በማለት ይመስላል) «በትግራይ ዘር ማጥፋት እየተካሄደ ነው …» ማለታቸው ደግሞ፣ መቀመጫቸውን ጄኔቭ (ስዊዘርላንድ)፣ መተማመኛቸውን አሜሪካ አድርገው ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ከወከሉት ዓለም አቀፍ ወንበር ወደ ጎጥ የመንከባለል አባዜ ነውና በአንድ በኩል ሰውየው ያሳዝናሉ።
ሰውየው በዚህ ብቻም ያበቁ አይደሉም። ሁሌም ከትህነግ በላይ ትህነግ ከመሆን ቦዝነው አያውቁም። ያለመቦዘናቸው ማሳያም ባለፈው ኦገስት መግቢያ ላይ «ምዕራብ ትግራይ (ወልቃይት)ን ነፃ ለማውጣት እንገደዳለን!!» በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነታቸውን ትተው የውጊያው ፊት መሪ ሆነው መገኘታቸው ነው።
በመጨረሻም፣ «በቃላት የማይገለፁት የዶክተሩ ስህተቶች» በሚል ርእስ የጀመርነውን (ወደን ሳይሆን የአገር ክህደት ተግባራቸውን በቃላት መግለፅ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው) ጽሑፋችንን እዚሁ ላይ እናቁም። ስናቆም ግን ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ሕግ በመያዙ ምክንያት ወደ ዝርዝር ጉዳያቸው፣ ጥልቅ ስህተታቸው፤ አገርና ሕዝብ ክህደታቸው … ባለመግባት፤ ለጊዜውም ቢሆን በመታገስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015