የዕድሜ ጧት የትዝታ ወግ፤
የሕወሓት ነገር ቢወቅጡትም ሆነ ቢሰልቁት እነሆ ግራ እንዳጋባ ዘልቋል። “ነገረኛ ሰው ከቤቱ አይሞትም” ይላሉ አበው – እውነታቸውን ነው። “ነገረኛ ናቸው አጥልቃችሁ ቅበሯቸው፤ የተነሱ እንደሆን ብዙ ነው ጣጣቸው” እየተባለም ይነገራል። ለማንኛውም ወደዋናው ጉዳያችን ከመግባታችን አስቀድሞ ረዥሙ ንባበ መንገዳችን “የውሃ መንገድ” እንዲሆንልን ጉዟችንን በነበር ወግ እናሟሽ።
ድርጊቱ ተፈጸመ የሚባለው ኮልፌ ጅማ ሠፈር አካባቢ ነው። ዘመኑ ደግሞ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ላቅ ይላል። ይህንን ክስተት የምታስታውሱ የያኔዎቹ ታዳጊ የዕድሜ እኩዮቼ ወይንም ዕድሜውን ያደላችሁ የወቅቱ የአባባ ባጫ እድር አባላት በቃላችሁ ምሥክርነት እውነታውን ብታጎላምሱት አይከፋም። “ጉድ! ጉድ!” እየተባለ በዘመኑ የተወራለት ታሪክ እነሆ እንደሚከተለው ይታወሳል።
ሴትዮዋ የአካባቢውን ነዋሪዎች በባህርይም ሆነ በግብር እጅግ ያስቸገሩ ነበሩ ይባላል። የተንኮል ተግባራቸው፣ ነበልባል እሳት እየተፋ ለጠብ የሚጋበዙበት አንደበታቸው፣ ፈጠራ እያከሉበት የሚያዛምቱት በሬ ወለደ ወሬያቸው የአካባበውን ነዋሪ ጤና መንሳት ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን አቃቅሮ ለከፋ ድርጊትም አዳርሶ ነበር ይባላል። አልፎም ተርፎ ነፍስ ያላወቁ ታዳጊ ሕጻናትንና ልጃገረድ ሴቶችን ወደ አልባሌ ሕይወት እንዲገቡ ያስኮበልሉ ነበርም እየተባለ ይወራል። እኚሁ ሴትዮ እንኳን ለሰፊው ማኅበረሰብ ይቅርና ለራሳቸው ቤተሰቦችም ሳይቀር ፈተና እንደሆኑባቸው በአሉ ተባባሉ የአንደበት ቅብብሎሽ እየተነገረ በስፋት ተወርቷል።
አይቀሬው ሞት ቀጠሮውን ማክበሩ ግድ ነውና እኚህ ሞገደኛ ሴት በጥቂት ቀናት በሽታ አልጋ ላይ ሲያጣጥሩ ሰንብተው ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋገጠ። በወጉና በደንቡ መሠረትም ከቤተ ዘመዶቻቸው መካከል አንድ ሰው ወደ “የአባባ ባጫ” የእድር ዳኛ ዘንድ በመሄድ የቀብሩ ሁኔታ እንዲመቻች ሪፖርት አደረገ። መልእክቱን የተቀበሉት የእድሩ ዳኛም እልፈታቸው፣ የቀብሩ ሰዓትና ቦታ ለእድርተኞቹ እንዲለፈፍ ለጡሩንባ ነፊው ትዕዛዝ አስተላለፉ።
ጡሩንባ ነፊውም በተሰጠው የአለቃው ትዕዛዝ መሠረት ወፍ ጭጭ ከማለቱ አስቀድሞ በአካባቢው እየዞረ “የአባባ ባጫ እድርተኛ የሆናችሁ በሙሉ ወ/ሮ…ስላረፉ ለቀብር እንድትወጡ። ቀብሩ የሚፈጸመው አማኑኤል ቤ/ክርስቲያን በስድስት ሰዓት ላይ ነው።” በማለት ልፈፋውን አጧጧፈው።
የሟችቷ ዜና እረፍት በይፋ መገለጡን ያልተስማሙ የቤተሰቡ አባላት ለልፈፋ የወጣውን ጡሩንባ ነፊ እያዋከቡ ወደ እድሩ ዳኛ ዘንድ በመውሰድ በአስቸኳይ ቀብሩ እንደማይፈጸም ማስተባበያ እንዲሰጥ ግብ ግብ ፈጠሩ። ምክንያታቸው ደግሞ ሞታቸውን የአካበቢው ሰው እንዳይሰማ ስለፈለጉ ነው።
በባህርያቸውና በተግባራቸው ጥዩፍነት በቁማቸው ሲታሙና ሲብጠለጠሉ የኖሩት አንሶ ከሞቱ በኋላም ሕዝብ በነቂስ ተሰብስቦ “እንኳን ድብን አሉ! ሞት ሲያንሳቸው ነው” እየተባለ በሙሾና በረገዳ ተሳቦ እንዲታሙና መሳለቂያ እንዲሆኑ ስላልፈለጉ ነበር። ቀብሩን ራሳቸው የቤተሰቦቹ አባላት በጨለማና በድብቅ ወስደው እንደሚቀብሯቸውም ለእድሩ ዳኛ አስረግጠው አስታወቁ። ከዚያ በኋላስ “ምን ተፈጸመ?” የሚለው የታሪኩ መደምደሚያ ለጊዜው በይደር መተላለፉን መርጠናል። ሁኔታው ሲመቻች ታሪኩን እንደመድማለን።
የሙሾ ነገር ከተነሳ አይቀር፤
በበርካታ የሀገራችን ባህሎች ውስጥ ለሟች ቀብር ከሚከወኑ የጋራ ልማዶች መካከል አንዱ ሙሾ ነው። ሙሾ በተመረጡ ግጥሞችና ዜማ እየተዋዛ ከቀብር በፊት ለአስከሬን ሽኝት የሚፈጸም የረገዳ ትርዒት ነው። ሟች ሴትም ይሁን ወንድ፣ ወጣትም ይሁን አዛውንት፣ ፈሪም ይሁን ጀግና ብቻ ለሁሉም አፈር ቀማሽ በድን የሚዥጎደጎደው ግጥምና ዜማ በመወድስ የደመቀ ነው።
ሙሾ አውራጇ ወይንም አውራጁ ቀብሩን ለማድመቅ የሚጋበዙት ጠቀም ያለ ክፍያ ተከፍሏቸው ነው። የሟቹን ማንነት ማወቅ ያለማወቅ ግዴታ አይደለም። የሚፈለገው መሠረታዊ የሚባሉትን የሟቹን ዕድሜ፣ ፆታ፣ ቤተሰባዊ አቋምና የሙያውን መረጃ ጠይቆ መረዳት ብቻ ነው። ከሙሾ ረገዳው ስምሪት አስቀድሞ ዋናው ሙሾ አሙሺ የምግብና የመጠጥ መስተንግዶም ይቀርብለታል። ግብዣው የሚፈጸመው ብዙውን ጊዜ ጠንከር ባሉ የአልኮል መጠጦች ታጅቦ ነው። የዚህ ምክንያቱ ሙሾ አስረጋጁ በአልኮሉ ድጋፍ እንዲበረታታና ድካም እንዳይሰማው ለማድረግ ታስቦ ይመስላል።
ከዚያ በኋላማ ምን ይጠየቃል፤ “ባለሙያው ሙሾኛ ካጠራቀማቸው የግጥም ስብስቦቹ መካከል እየመዘዘ “ሆ! ሆ!” በማሰኘት እምባ ማራጨት ነው። እርሱ ወይንም እርሷ ደረታቸውን ለአመል ያህል ነካ ነካ እያደረጉ ግጥሙን ሲያዥጎደጉዱ አንዳንድ ቀብርተኞችና የቤተሰቡ አባላት ደረታቸውን እየደቁ ሀዘናቸውን አምርረው ይገልጻሉ። አንዳንዶችም ምርር ትክን ብለው የሚያለቅሱት የራሳቸው የቀደመ ሀዘን እየታወሳቸው እንደሚሆንም አይካድም።
አልቃሽ አያለቅስም፤ እንዲያለቅስም አይገደደም። የእርሱ ተልዕኮ ሌሎችን ማስለቀስና ማስረገድ ነው። ምንም እንኳን የምር ነው ብለን ባንቀበለውም አንዳንዴ ከቤተሰብ አባላት መካከል አብሬ ካልተቀበርኩ ብለው ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግሩ አይጠፉም። ይህን መሰሉ በትራዠዲ ክስተት ውስጥ የሚስተዋለው የኮሜዲ ትርዒት በብዙ የሀገራችን ክፍሎች ዛሬም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ስለመቅረቱ አስረግጦ ለመናገር ያዳግታል።
ለማንኛውም አልቃሽ ያስለቅሳል እንጂ አብሮ እንደማያለቅስ ካስታወስን ዘንድ ወደ ዋናው ጉዳያችን ዘልቀን ሞቶም ቢሆን ቀብሩ እንዲደበቅለት ስለሚፈለገው፤ ሞቱን በተቀበሉ አንዳንዶች ዘንድም “ወደ መቃብር ከመወሰዱ አስቀድሞ ሙሾው እየደመቀለት ስለሚንቆለጳጰሰው አሸባሪው ትህነግ ና አስለቃሾቹ ጥቂት አጠቃላይ ዳሰሳ እናደርጋለን።
የአሸባሪው ትህነግ አልቃሾችና አስለቃሾች፤
አሸባሪው ትህነግ የቀብር ዝግጅት ከሩቅ ዘመኑ የአባባ ባጫ የእድር ታሪክ ጋር የሚቀራረብ ጠረን ያለው ይመስለናል። ሕወሓት እኮ ከበደነ ሰንብቷል። ችግሩ ነፍሱ ፈጥና ያለመውጣቱና ሠልስቱ፣ ሰባቱም ሆነ አርባው በይፋ ያለመገለጡ ብቻ ነው። “ልጡ ተርሶ፤ ቀብሩም ተምሶ” እየተጠበቀ እንዳለ ዓለም ሁሉ ገብቶታል። ሞገደኛው፣ እብሪተኛው፣ ጨካኙ፣ የጦርነት ሱሰኛውና ዘረኛው የትህነግ ቡድን እስትንፋሱ ጭል ጭል ይበል እንጂ የቆመው መቃብሩ አፋፍ ላይ ነው።
እጅግ የሚያስገርመው ነገር የቡድኑ ሞት ሳይሆን ሞቱን ይፋ እንዳይገለጥ በሙሉ ኃይላቸው እየተንፈራገጡ፣ በአደባባይም ጭምር እየተንከባለሉና አብረን ካልተቀበርን እያሉ በምስለ ሬሳ ተመስለው የሚያላዝኑት ቁጥራቸው መብዛቱ ነው። “ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ” እያሉ ጥብቅና የቆሙት ኃይላት ቁጥርም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። “ሞቱን ብንቀብለም እንኳን ኮሽ ሳይልና ጡሩንባ ሳይነፋ በስውር የምንቀብረው እኛ ብቻ ነን!” በማለት በድብቅና በጨለማ ሲዶልቱ ውለው የሚያድሩት ፀረ ኢትዮጵያ እኩያንም ብዛታቸውም ሆነ ዓይነታቸው የትዬለሌ የሚሰኝ ነው። ሞቱ ለዓለም በይፋ እንዳይገለጥ፣ ቀብሩም በአግባቡ እንዳይነገር የሚውጠነጠነው የሴራ ዓይነት “ቀብር ሸሻጊዎቹን” ትዝብት ላይ መጣል ብቻም ሳይሆን ታሪክ ራሱ ፊት እንደሚነሳቸው የገባቸው እስከማይመስል ድረስ ድብብቆሹን ተያይዘውታል።
ዳሩ በደነደነና እብሪት ባሰባው ልብ የእውነት ቃል ተንቆርቁሮ መች በቀላሉ ሊሰርግ ይችላል? እስትንፋሱ ድርግም ሊል አንድ ሐሙስ ለቀረው ሕወሓት ይሉት ጉድ “አልቃሽና አስለቃሽ” በመሆን የረገዳውን ሜዳ የተቆጣጠሩት ዓለም አቀፍ አስረጋጆች ስማቸውና ዓይነታቸው የተለያየ ይምሰል እንጂ የተልእኳቸው አተገባበር ግን አንድና ተመሳሳይ ነው። በጥቅል ማሳያ እናመለካት።
የመጀመሪያዎቹ አልቃሾችና አስለቃሾች የዚህቺው የአህጉራችን ቤተሰብ አባላት የሆኑ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። እነርሱን የሚያስለቅሳቸውና ሌሎችንም እንዲያላቅሱ የሚያስገድዳቸው በዋነኛነት የወዳጃቸው የሕወሓት ሞቶ መቀበርና አፈር የመልበስ ጉዳይ አይደለም። አሸባሪውን ቡድን ተገን አድርገውና ከፊት አሰልፈው ሲፈጽሙት የኖሩት ሴራ ተበጣጥሶ አብረው ግባተ መሬታቸው መፈጸሙ እያንገበገባቸው እንጂ። “ምንትስን የሚወጉት በአህያ ተከልሎ ነው” እንዲሉ፤ እንደ ጋሻ ሲገለገሉበት የኖሩት “የአህያ ባል” ከአንበሶች እንደማያድናቸው በሚገባ ስለተረዱ ነው። ተስፋ አድርገው ሲቃዡ የሚያድሩትም መቃብሩን እያስተዋሉ ሳይሆን “ቢሞት እንኳን በትንሣኤ መነሳቱ አይቀርም” ብለው ተስፋ በማድረግ ጭምር ይመስላል።
ሁለተኞቹ ሙሾ አሙሺዎች ማርቲን ፕላውት የሚወክላቸው ስብስቦች ናቸው። አሸባሪው ትህነግ ከሀገር ካዝናና ከሕዝብ ጉሮሮ ሲዘርፍ በከረመው ሀብት የቀጠራቸው እኒህን መሰል ግለሰቦችና “በሰብዓዊ መብቶች አስከባሪነት ስም” እያደናገሩ ያሉ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የሚወድቁት እዚሁ ነጥብ ሥር ነው።
እነዚህ “ቀብር አዘግይዎች” የሚታያቸው አሸባሪው ትህነግ ሲሰፍርላቸው የኖረው ቀለብና ዳረጎት አብሮ መቀበሩ እንጂ የቡድኑ ዘለዓለማዊ ህልፈት “አንጀታቸውን” አላውሶ ርህራሄ ስለገባቸው አይደለም። የብድኑን የቀብር ዜና ለማስተባበል የሚሞክሩትም እንደ ተዝካር ድስት ተጥደው በሚውሉበት ቲዩተር እና ሌሎች ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሀዘን ፍራሽ ጎዝጉዘው የፈጠራ ዜና እየፈበረኩ ነው።
ሦስተኞቹ ሙሾ አስረጋጆች ታዋቂነት ካልሆነ በስተቀር ኅሊና ያልፈጠረባቸው አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማትና የሀሰት ካባ ደርበውላቸው እሶሶ የሚሏቸው ጋዜጠኞቻቸው የበሬ ወለደ ዜና እየተቀባበሉ የሕወሓትን “ድል እንጂ ሞቱን እንዳያውጁ” የታወሩት እውነታው ጠፍቷቸው ሳይሆን ጉርሻው እንደሚከብዳቸው ስለተረዱ ነው። የኅሊናቸውን ግሳጼ በጨው አለቅልቀው “ወተቱን እያጠቆሩ፤ ከሰሉን ሲያነጡ” መመልከት እንግዳ አይደለም። ለሀሰታቸው መሸፈኛ የሚጠቀሙት የሶምሶንን ታሪክ ብጤ ነው። የቅዱስ መጽሐፉ ሶምሶን ሹሩባው ተሸልቶ ያበቃለት ቢመስልም እንደገና ፀጉሩ ሲያቆጠቁጥ ኃይሉ ታድሶ ተገዳዳሪዎቹን በሙሉ እንደሚፈጅ በጨበጡት ማይክራፎን እያስተጋቡ የማደንቆር ስልት እየተጠቀሙ ነው።
የባእዳኑ አስቂኝ ድርጊት እንዳለ ሆኖ እጅግ የሚያሳዝነው “ኢትዮጵያዊ” የሚል ቅጽል ተሸክመው ሀገርና ሕዝብን ሲያዋርዱ የሚውሉት “የእንግዴ ልጆች” ተግባር ነው። እነዚህ “የቤት ውላጅ” የቀብር ጡሩንባ ነፊዎች ዛሬ በርቀት ሆነው የሚያስወነጭፉት የውሸት ቀስት ራሳቸውን ነድፏቸው አንገት ደፍተው እንዲኖሩ እንደሚያስገድዳቸው የገባቸው አይመስልም። “ወያኔም ተቀብሮ ሶልዲውም ያልቅና፤ ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና” ብለን የትዝብታችንን አሻራ አትመን ለትውልድ እናስተላልፍላቸዋለን።
አራተኞቹና ዋነኞቹ የአሸባሪው ትህነግ አለንልህ ባዮች “በእኛ ብቻ” የትምክህት ክፉ ደዌ ተለክፈው ለራሳቸው አንቱታን ከሌሎች ዘንድም መወድስ በመራብ የተለከፉ “ታላላቅ ተብዬ” ሀገራት ናቸው። “የፍየሏን ሞት አሳበው፤ የውሽሜ ህልፈት የሚያንገበግባቸው” እነዚህ መንግሥታት የሕወሓት የቀብር ሙሾ ወደ ቀረርቶና ሽለላ እንዲለወጥ ቀን ከሌት በመትጋት “በድኑ አፈር እንዳይለብስ” እየተከላከሉ ያሉት የሚገጥማቸው የነገ ውርደት እየታወሳቸው ነው። ለአደራዳሪነትም፣ ለአስታራቂነትም፣ ለእርዳታውም ሆነ ለሰብዓዊ መብት ሙግቱ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በሚል ክፉ እብሪት የተለከፈችው ፊት መሪዋ የያኒኪዎቹ ሀገር አመሏም ሆነ ተግባሯ እንኳን ለሌላውና ለራሷ ሕዝብም ሳይቀር እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘመን መሽቶ ጠብቷል።
ኢትዮጵያ በቀጣናውና በመገኛዋ አህጉር ገንና ከወጣችና እንደ ተገዳዳሪ ከሚያዩአቸው ሌሎች ወዳጅ መንግሥታት ጋር በእኩልነት ወንበር ስባ መቀመጧ እንደማይቀር ሲታወሳቸው ይንገበገባሉ፤ ይንጨረጨራሉ። ስለዚህም የመሰሪ እቅዳቸው ሽል ከትህነግ ጋር አብሮ መቀበሩ እንደማይቀር ስላመኑ በተቻላቸው መጠን ይንፈራገጣሉ። የሕወሓት አይቀሬ ቀብር እንዳይፈጸምም አጥብቀው ይከላከላሉ። ቀብሩ እንኳን ቢፈጸም “በጀግና ቀረርቶ እየተፎከረለትና በጃዝ ፋንፋር እየተዘመረለት እንጂ ዋይ! ዋይ!” እየተባለ እንዳይለቀስ እስከ ማስጠንቀቅ ይደርሳሉ።
ያሻቸውን ይበሉና ያድርጉ እንጂ ትህነግ ሞቷል አፈር መልበሱም ግድ ነው። ኢትዮጵያም በዓለም መድረክ ላይ ከፍ ብላ መታየቷ አይቀርም። ፈረሳቸው አሸባሪው ትህነግ ተቀብሮ ጋጣው ባዶ ሲሆንባቸው ምን ብለው ያወሩና ያስወሩ ይሆን? የከርሞ ሰው ይበለንና ሁሉንም በትዝብት እናስተናግደዋለን። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 / 2015