ስፖርታዊ ውድድሮች ለስፖርት ቤተሰቡ ስሜት እንዲሰጡ የቀጥታ ጨዋታ አስተላላፊዎችና የስፖርት ጋዜጠኞች በሚሰሯቸው ፕሮግራሞች እንዲሁም ዘገባዎች በጣፈጠና ለዛ ባለው አቀራረብ የበለጠ ጣዕም የሚሰጡ ቅመሞች ናቸው። በሌላው ዓለም ስፖርታዊ ውድድሮችን በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት ለህዝብ ማስተላለፍ የተጀመረው እአአ በ1920ዎቹ ነው። በኢትዮጵያ ስፖርት መገናኛ ብዙሃን ታሪክ በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ደግሞ አንጋፋው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት መልካም ስምን ከተከሉ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱት እኚህ ባለሙያ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው። ከሃገር አልፎ እስከ ዓለም አቀፍ ስፖርት ተቋማት አገልግሎት በመስጠት አንቱታን ያተረፉት አቶ ፍቅሩ ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ስነስርዓታቸውም በዛሬው ዕለት የሚፈጸም ሲሆን፤ የዛሬው የስፖርት ማህደር ዓምዳችንም አንጋፋውን የስፖርት ሰውና ስራዎች የሚያስታውስ ይሆናል።
አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1927ዓ.ም ፍልውሃ ሆስፒታል እንደነበር የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ልጅ ሆነውም አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊ በመሆናቸው የክለቡን ተጫዋቾች ከትምህርት ቤት ወደ ውድድር ሜዳ ከዚያም ወደ ትምህርት ቤት ያመላልሱ ስለነበር ታዳጊው ፍቅሩ አብረዋቸው ጨዋታ የማየት ዕድል ነበራቸው፡ ፡ በልጅነት ዕድሜያቸው በስፖርት ፍቅር የተጠለፉት አቶ ፍቅሩ እድሜያቸው ከፍ ሲል በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ የሚታተሙና ከውጪ ሃገራት የሚመጡ ጋዜጦችን ማገላበጥ ጀመሩ፡፡ የሊሴ ገብረማርያም ተማሪ መሆናቸውም ሁለቱን ቋንቋዎች ለመረዳት አይቸግራቸውም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታም በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ አለመኖሩን ለማስተዋል ቻሉ፡፡
አጋጣሚ ሆኖም ትምህርት ሚኒስትር ስፖርትን ለማስፋፋት በሚል አላማ ስልጠና ሲሰጥ ተካፋይ በመሆን በስፖርት መምህርነት ወደተማሩበት ሊሴገብረማርያም በመመለስ እንዲሁም በድሬዳዋ አገልግለዋል፡፡ በወቅቱም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ስፖርት እንዲዘግቡ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነትን በማግኘታቸው ከመምህርነት ጎን ለጎን በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ሙያ ይሰሩ ነበር፡፡ «ወደ ጋዜጣው አለም የመጣሁት ”በዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ላይ አቶ አሃዱ ሳቡሬ የሚባሉ ኃላፊን አነጋግሬ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የስፖርት ጋዜጠኛ የሚባል የለም፤ እኔ ልጀምር? ብዬ ስጠይቃቸው ጀምር አሉኝ። ከውጭ ሆኜ እያስተማርኩ መፃፍ ጀመርሁ። በኋላ ለምን እዚህ መጥተህ አትሰራም ተባልኩ፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ተብዬ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የቀጠረው እኔን ነው፡ ፡ ከዛም የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያ የስፖርት ፕሮግራም ጀምርሁ። በኋላ ለሌሎቹም ጋዜጦች ለአዲስ ዘመን እና ሄራልድ በሙሉ ስለ ሀገሬ ስፖርት እንዲጽፉ እያበረታታሁ እንዲሁም ራሴም እየጻፍኩ እየሰጠሁ ስፖርት በጋዜጣ እንዲነበብ አደረግሁ” በማለት አቶ ፍቅሩ በተለያዩ ቃለመጠይቆች በሰጡት ምላሽ በዚያ ወቅት የነበረውን ታሪክ አውግተዋል።
እአአ በ1957 አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ከሚያደርጉት የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ጋር ተያይዞ ሱዳኞች ጨዋታውን በራዲዮ ለማስተላለፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ጨዋታው በአማርኛም የቀጥታ ስርጭት እንዲያገኝ ተወሰነ።
በወቅቱም አቶ ፍቅሩ አስቀድመው ሳይዘጋጁ ጨዋታው ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ጨዋታውን እንዲያስተላልፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን በሚመሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት፤ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ የመጀመሪያውን ውድድር በራዲዮ አስተላለፉ፡፡
አቶ ፍቅሩ ያንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአንድ ወቅት ከኤስቢኤስ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲህ ሲሉ አስታውሰውታል። “በአንድ ወቅት ስታዲየም ሄጄ ጨዋታ እስኪጀመር ቁጭ ብዬ ስጠብቅ ”አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በአስቸኳይ ይፈለጋሉ” የሚል መልዕክት መጣ፡፡ ምን መጣ ብዬ ቦታዬን ያዙልኝ ብዬ ወረድኩ፡፡ በኋላ አቶ ይድነቃቸው እኔን ሲያይ ጮኸ፡፡ «የት ጠፋህ?» አንተ እኮ ነህ ጨዋታውን በራዲዮ የምታስተላልፈው» አለኝ፡፡ «ማን ነገረኝ እኔ ማስተላለፌን?» አልሁት። «ታድያ ማን ያስተላልፍልህ?» ብሎ የቡድኖቹን አሰላለፍ ሰጥቶኝ ሂድ አለኝ፡፡ ወደ ትንሿ ጠረጼዛ ሄጄ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታዲየም አንድ ኢንተርናሽናል ጨዋታን አስተላለፍኩ፡፡»
አቶ ፍቅሩ የጋዜጠኝነት ስራቸውን እየከወኑ ሳለ ወደኮንጎ ከሚዘምተው የኢትዮጵያ ልኡክ ጋር እንደሚጓዙ ተነገራቸውና ጥቂት ስልጠና ወስደው ወደዚያው አመሩ፡፡ እዚያም ሆነው ስራቸውን ያላቋረጡ ቢሆንም፤ ከዘመቻው መልስ ግን ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጣሪነትና ከጋዜጠኝነት ወጥተው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀጠሩ። ለጥቂት ጊዜያትም በአፍሪካ ሃገራት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ዳግም ወደሃገራቸው ተመልሰዋል።
ይሁንና በወቅቱ በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በድጋሚ ሃገራቸውን ለቀው ወደ ፈረንሳይ ለማቅናት ተገደዱ፡፡ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ በሀገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት ችለዋል። በርካታ ቋንቋዎችን ማወቃቸውም ለዚህ በብዙ ጠቅሟቸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ሆነው እንዲሰሩም አስችሏቸዋል።
አቶ ፍቅሩ በተለይም የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ቴኒስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። በአለም አቀፍ ተቋማት ባገለገሉባቸው ጊዜያትም በርካታ አለም አቀፍ ሽልማቶችን ለመሸለም በቅተዋል።
ለኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት መሰረት የጣሉት እኚህ ታላቅ ባለሙያ ከቀናት በፊት በሚኖሩበት ፓሪስ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ ፍቅሩ የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ፤ ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ስርአተ ቀብራቸውም ዛሬ በፓሪስ የሚፈጸም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም