ታሪካዊ ማነጻጸሪያ፤
ቀዳማዊ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ (1769 – 1821) እውቅ ፈረንሳዊ የጦር መሪና የሀገሪቱም ንጉሠ ነገሥት እንደነበር ገድሉ ድምቆ ይተርክልናል ። ይህ ዝነኛና ብርቱ መሪ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ግድም አብዛኞቹን የአውሮፓ ሀገራት አንበርክኮ ማስገበሩ በታሪክ ተመዝግቧል። ተጠቃሹ ወታደራዊ መሪ በዓለም ላይ ከተነሱት መሰል መሪዎች መካከል በላቀ ደረጃ ግለ ታሪኩና ጀብዱው ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ መጻሕፍት የተዘገቡለት ገናና ገዢ ነበር ። ዛሬም ድረስ የዜና መዋዕሉ ግለ ታሪክ በመጻሕፍትና በልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎች ያለማቋረጥ እየተተረከለት ይገኛል ።
የፈጠራ ድርሰት የሚመስሉት በርካታ የውሎ ገድሎቹ በጽሑፍ ብቻም ሳይሆን በአሉ ተባባሉ የትርክት ዘዴ እየተነገረለትና እየተዘመረለት ዛሬም ድረስ መዝለቁ ሌላው የናፖሊዮን አስገራሚ ታሪክ ነው ። ከዚሁ ገድለኛ መሪ የመረጥናቸውን ሁለት አስገራሚ “የነበር ታሪኮች” ለመንደርደሪያነት ጠቅሰን ወደ ራሳችን ዋና ጉዳይ ዘልቀን እንቆዝማለን ።
አንድ፡- ናፖሊዮን ቦናፓርቴ አውሮፓን ለመውረር በዘመተበት አጋጣሚ በተዋጊ ጦረኞቹ ፍልሚያ መካከል አንድ ክስተት ይፈጸማል ። ፍርሃት ያንዘረዘረው አንድ ወታደር የውጊያውን መፋፋም ሲያስተውል የሚመራውን የሠራዊት አሀድ ሜዳ ላይ በትኖ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሲፈረጥጥ በጦር ሜዳ መነጽሩ አሻግሮ ይመለከተዋል ። አይቶት ብቻ ዝም አላለም ። ከወታደሮቹ መካከል ጥቂቶቹን መርጦ ያን ወታደር የፊጥኝ አስረው እንዲያመጡለት ያዛቸዋል ።
በትዕዛዙ መሠረትም ፍርሃት ያራደው ወታደር ተይዞ ወደ ናፖሊዮን ፊት እየተንቀጠቀጠ ቀረበ ። “ለመሆኑ ስምህ ማነው? ለምንስ በተፋፋመው ጦርነት መካከል ሠራዊቱን ከድተህ ለመሸሽ ሞከርክ?” አዋጊው ጄኔራል ናፖሊዮን ይጠይቀዋል ። “ጌታዬ ስሜ “ናፖሊዮን” ይባላል። የሸሸሁትም ነፍሴ አሳስታኝ እንዳልሞት ፈርቼ ነው ።” በማለት ሳይዋሽ እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ነገረው ።
ናፖሊዮንም እንዲህ በማለት ውሳኔውን አሳወቀው፤ “ፈርተህ በመሸሽህ አልገልህም ወይንም አላስርህም ። አንድ ነገር እንድትፈጽም ግን አዝሃለሁ ። እንደ እኔ እንደ ጀግናው ናፖሊዮን በጽናት ተዋግተህ በጠላትህ ላይ ድልን ተቀዳጅ ። ይህ የማይሆንልህ ከሆነ ግን “ናፖሊዮን” የሚለውን ስምህን በአስቸኳይ መልስልኝ ።” የወታደሩ መጨረሻ ከምን እንደደረሰ ለጊዜው በወረቀት የሠፈረም ሆነ አፈ ታሪኩ የሰጠን ምንም ፍንጭ ስለሌለ የታሪኩን መደምደሚያ በእንጥልጥል መተውን መርጠናል ።
ሁለት፡- ናፖሊዮን ወደ ሥልጣነ መንግሥት መሰላል ላይ የወጣው የዘመኑ ባህል በሚፈቅደው መሠረት ዘሩን ከነገሥታቱ የደም ሀረግ ስለመዘዘ አልነበረም ። አመጣጡ ለዚህን መሰሉ ክብር የታደለ ባይሆንም ዕድልና ጊዜ ተገጣጥሞለት የዘመኑን ገናና አውሮፓዊ ሀገር የፈረንሳይን መንበረ ዙፋን ለመቆናጠጥ የበቃው “በሀገሩ ምድር ተቀጣጥሎ የነበረው አብዮት” ረድቶት ነው ። “የደሙ ንጥር” የመነጨውም ከወደ ጣሊያን እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል ። ያውም የሥልጣን ደረጃቸው ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ ።
ይህንን የናፖሊዮን ዘር ጠቀስ ታሪክ የሚያውቁ የወቅቱ የሚዲያ ባለሙያዎች አልፎ አልፎ በሽሙጥና በምፀት ወጋ ሲያደርጉት የሚሰጣቸው መልስ ከበቀል ይልቅ ብልሃት በተላበሰ ዘዴ እያዋዛ ነበር ። “ጀግና ለበቀል አይቸኩልም” የሚለው ብሂል እውነትነት ሳይኖረው ይቀራል? ለማንኛውም በሁለተኛነት በመረጥነው ታሪክ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጋር የገባበትን እሰጥ አገባ በተመለከተው ታሪክ ላይ እናተኩር ።
“ጀግናው ንጉሠ ነገሥታችን! የነገሥታት ዝርያ ሳይኖርህ እንደምን ወደ ተከበረው የፈረንሳይ መንበረ ዙፋን ከፍታ ላይ ልትደርስ ቻልክ?” በአንድ ወቅት የቀረበለት ጥያቄ ነበር ይባላል ። “እርግጥ ነው” አለ ናፖሊዮን ሲመልስ፤ “የነገሥታቱ ደም ከደሜ ጋር አልተዋሃደም ። የአመጣጤ ታሪክም ከዚህ እውነታ በጣም የራቀ ነው ። ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ በፓሪስ አውራ ጎዳናዎች ላይ ስንሸራሸር አንድ ዘውድ በመንገዴ ላይ ወድቆ አገኘሁ ። ያንን የከበረ ዘውድ ዝቅ ብዬ በእጆቼ ለማንሳት ስለተጠየፍኩ እንዳያደናቅፈኝ ፈልጌ ከመንገዴ ላይ ለማስወገድ በእግሬ ወደ ሰማይ አጉኜ ለመወርወር ስሞክር ዘውዱ ቁልቁል ተምዘግዝጎ በአናቴ ላይ አረፈ ። ከዚያ ክስተት በኋላ የታላቋ ፈረንሳይ ገዢ ሆኜ ራሴን አገኘሁት ።” – የተራቀቀበት ድንቅ ምፀታዊ አባባል ነበር ። በንጉሥ ቃል ላይ ስለማይጨመር ወይንም ስለማይቀነስ፤ “እንቆቅልሹን ፍቱ?” ብዬ አንባብያንን ሳልሞግት ወደ መነሻ ሃሳቤ አቀናለሁ ።
“የኢትዮጵያን ስም ተሸክመው የሚያነክሱ የሙያ ማኅበራት፤
“የኢትዮጵያ” የሚል ክቡር ስም እየታከለበት የሙያ ማኅበራትን ለመመስረት አቅም ቢኖረንም ባይኖረንም ባህላችን ቸርና ደፋር አድርጎናል ። እንኳን ራእያቸው ገዝፎ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ “ጠብታ” ሊያክሉ ቀርቶ እግራቸው ራሱ በቀዬአቸው ድክ ድክ ለማለት ልምሻ የያዘው አንዳንድ የሙያ ስብስቦች ለማኅበራቸው ስም ሲያወጡ “በኢትዮጵያ ስም ለማሽሞንሞን” ምን ያህል ደፋሮች እንደሆኑ ዕድሜና ተሞክሮ በሚገባ አስተምሮናል ።
በመንፈሳዊ ሕይወት በጎ ምሳሌነታቸው የማከብራቸው አንድ አባት በጭውውታችን መካከል ይህ ርዕሰ ጉዳይ ድንገት በተነሳበት አንድ አጋጣሚ የተናገሩት ንግግር ፈገግ ማስደረግ ብቻ ሳይሆን ትልቅ “መገለጥ ሆኖ” ትምህርት የሰጠኝ ጭምር ነበር ። እንዲህ ነበር ያሉት፡- “የኢትዮጵያን ስም አልከስክሰው የተሸከሙ አንዳንድ የሀገራችን የሙያ ማኅበራት፤ የሃይማኖታዊውን የጽዋና የሰንበቴ ማኅበራት ያህል እንኳን አቅም ቢኖራቸው ለሀገራችን ወቅታዊ ፈተናዎችና ችግሮች ከፍ ያለ በጎ አሻራ ማሳረፍ በቻሉ ነበር። ብዙዎቹ የኢትዮጵያን ስም ያነገቡ ‹የሙያ ማኅበራት› ተብዬዎች ስማቸው አምሮ ግብራቸው ግን ኮስምኖ “በተከድኖ ይብሰል” መታለፋቸው የሚመለከተውን ክፍል ሊያስወቅስ ይገባል ።” – ጸሐፊውን የሚያስማማ ትክክለኛ ገለጻ ነው ።
የሙያ ማኅበራቱን በተመለከተ የጸሐፊው ምደባ፤
ለግርድፍ ቅኝት እንዲመች “የኢትዮጵያን ስም ከተሸከሙት” ማኅበራት መካከል የተወሰኑትን ብቻ መርጠን ለማሳያነት እንዲረዳን አቧድነን እንዳስሳቸው። እርግጥ ነው አንዳንድ የሙያ ማኅበራት ስማቸውም ሆነ ግብራቸው ገዝፎ አንቱታን ማትረፋቸው አይካድም። በሚያሳዩት ሀገራዊ መልካም ውጤትም መመስገን የሚገባቸው ቢሆንም ። ችግሩ የዚያኑ ያህል በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያ ማኅበራት “ስማቸው እኩል፤ ሥራቸው ስንኩል” እንዲሉ “ሲያነክሱ መኖራቸው ነው። ለማንኛውም ውጤታቸውን ሳይሆን የማኅበራቱን ሙያ ነጥለን በቡድን በቡድን እያቀናጀን ጥቂት ምልከታ እናድርግ ።
ብዙዎቹ ማኅበራት የሚቋቋሙት የአባላቱንና የሙያቸውን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑ አይካድም፤ ትክክልም ነው ። ከዚህ ባለፈ ግን ሙያቸው “ስሟን ለተሸከሙት ኢትዮጵያ” አንዳች ፋይዳ ያለው ሀገራዊ አስተዋጽኦ የማያበረክት ከሆነ ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ሆኖ “ዶሮ ከጋጥ፤ አህያ ከቆጥ”ን ብሂል ማስታወሱ አይቀርም ።
እንቀጥል፡- አንዳንድ የሙያ ማኅበራት የአባላቶቻቸውን ጥቅም ከማስከበር በዘለለ ከኢኮኖሚ ፋይዳ አንጻር ልንመድባቸው እንችላለን ። ለምሳሌ፡- የአታሚዎችና አሳታሚዎች ማኅበር፣ የቡና ላኪዎች ማኅበራት፣ የአትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ ላኪ ማኅበራት፣ የምህንድስናና የአርክቴክት ባለሙያዎች ማኅበራት ወዘተ. እንደምንመኘው ይሁኑም አይሁኑ ለሀገር የሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በቀላል የሚታይ አይደለም ። ብርታት ጥንካሬያቸው እንዳለ ሆኖ ።
አንዳንድ ማኅበራት “የኪነ-ጥበባት ማኅበራት” የሚሰኙ ናቸው ። የተውኔት ማኅበራት፣ የደራስያንና ደራስያት ማኅበራት፣ የሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ ማኅበራት፣ የሙዚቃ ማኅበራት ወዘተ. ትኩረታቸው ወደ ማዝናናቱና ማስተማሩ ስለሚያመዝን በጥበቡ ጎራ መቧደናቸው አግባብ ይሆናል ። ንቃተ ኅሊናን ከፍ በማድረግና ሀገራዊ ህጸጾች እንዲታረሙ በማስተማሩ ረገድ ለማሕበረሰቡ ፋይዳ ያለው አስተዋጽኦ ለማድረግ አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ከሚታመኑ የሙያ ማኅበራት መካከል ደግሞ የዳኞችና የዐቃቤ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኃን ልዩ ልዩ ማኅበራትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህን ውስኖችን ብቻ ለአብነት ጠቀስን እንጂ በሕክምናው ዘርፍ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ወዘተ. የተደራጁትን እጅግ በርካታ “ብሔራዊ ማኅበራት” በተቋቋሙበት ተቀራራቢ ሙያቸው እያቧደንን በመዘርዘር ብንፈትሻቸው ብዙ ማለት ይቻላል ። ከሙያ ጉዳይ ውጭም በዕድሜ፣ በጾታና በአካል ጉዳተኝነት ወዘተ. የተደራጁትን ማኅበራት በመጠቃቀስ ዕይታችንን አስፍተን ብንወያይ ብዙ ገመናዎች ሊዘከዘኩ በቻሉ ነበር ።
ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ የስማቸው ክብደት ወይንም የተቋቋሙበት ዓላማ ግዝፈትና ውሱንነት ሳይሆን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምን ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አኖሩ የሚለው ይሆናል። በተለይም ሀገር እንደ ዛሬው መከራ ላይ ስትወድቅ “ስሟን የተሸከሙት ማኅበራት ምን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው?” ብለን ብንጠይቅ ሊያስኮርፍ ወይንም ሊያስቆጣ አይገባም ።
ይህንን ሀገራዊ ችግር ከናፖሊዮን ቦናፓርቴ ሁለት ታሪኮች ጋር ለምን ለማጣቀስ እንደፈለግን ጥቂት ሃሳቦች እንፈነጣጥቅ ። በርካታ የሀገሪቱ “ብሔራዊ ማኅበራት” ስማቸው እንጂ ምን እንደሰሩ ወይንም ምን ሊሰሩ እንዳቀዱ ስሟን ያዋሰቻቸው “ኢትዮጵያ” በወከለችው ተጠሪ መንግሥታዊ ተቋም በኩል ያለመጠየቋ መልሰን የምንወቅሰው ራሷን “እምዬን” ነው ። ቢያንስ ልክ እንደ ናፖሊዮን “ወይ ስሜን መልሱ፤ አለያም የስሜን ልክ ያህል ቁምነገር ሥሩ” ብላ “መብቷን” ለማስከበር የዐይን አፋርነቷን “ዐይነ ርግብ” ለመግለጥ ለምን እንደማትፈልግ አልገባንም ። በዚህ ጉዳይ “ስሟን ተሸክመን ከመንገዳገድ ውጭ ምን ፈየድን” በማለት የየማኅበራቱ አባላት መሪዎቻቸውን ሊሞገቱ ይገባል ።
“ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ “በፍሬያቸው” መታወቁ እንኳን ቢቀር “እንክርዳዳቸው” በዝቶ ሀገሪቱን ለራስ ምታት ባይዳርጉ ይበጅ ይመስለናል ። በግልጽ እንጠይቅ ። የኢትዮጵያን ስም የተሸከሙ ስንት የስፖርት ማኅበራት አሉ? ለምን የጋራ ዓላማ ቀርጸው አብረው መሥራት አቃታቸው? ስንት የሙዚቃ ማኅበራት አሉን? እኮ ለምን ተቀባብሎ በጋራ ተደጋግፎ ለሀገር ቁም ነገር መዋል ተሳናቸው? ብዕር ያሰባሰባቸው ምን ያህል የድርሰት ማኅበራት አሉን? “ያለእኔ አይሆንም” የሚሉትን የመሪዎቹንና የአባላቱን ግልጽና ስውር ፍልሚያ ለጊዜው ትተው ስለምን ተቻችለው በአንድ ዓላማ ሥር ለመሰባሰበ ተሳናቸው? ስለምንስ የችግር ቀን ደራሽ ለመሆን ተልፈሰፈሱ? ብንጠያየቅና ብንተራረም አይከፋም ።
ሰብሰብ ብለው የጋራ አቅም በመፍጠር በወቅታዊ ችግሮች ላይ የሙያቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቢሳናቸው እንኳን ማኅበራቱ በየግላቸው በዚህ ወሳኝ የሀገራዊ ፈተና ወቅት ስለምን የግላቸውን ጠብታ ለማኖር ራእያቸው ጨለመ? ይህ የገዘፈው ሀገራዊ ጉዳይ ለጊዜው ይቆይ እንኳን ብንል ለራሳቸው ለሙያ ባልደረቦቻቸው ወይንም አባላቶች “እዚህ ግባ የሚባል” ምን ተጠቃሽና ተጨባጭ ውጤት አስመዘገቡ ። ስለዚህም ነው “ስሜን መልሱልኝ!” በማለት “ራሷ ኢትዮጵያ” እንድትሞግታቸው የምንቀሰቅሳት ።
“ማኅበሬ የሚሉት ተቋም” እግሩን ሲጎትት አብረው ላለመደነቃቀፍ በመጨከን በራሳቸው የግል ጥረት ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ጀግነው ያጀገኗት ባለሙያ ልጆቿ እንኳን በቁማቸው በሞታቸው እንዴት እንደተከበሩ ደጋግመን አስተውለናል ።
ድፍረት ካልሆነ በስተቀር ብዙ “ብሔራዊ” የሚል ቅጽል ስም የያዙ ማኅበራት የተቋቋሙት ልክ እንደ ናፖሊዮን በሚገባ አስበውበት ሳይሆን ባልተዘጋጁበት ሁኔታና በሆይ ሆይታ ሞቅታ “የሙያ” ማኅበር የመሆንን የዕድል ዘውድ” መንገድ ላይ ውድቆ ስላገኙ ይመስላል። ሜዳ ላይ ወድቆ ያገኙትን እድል ደግሞ መሪዎቻቸው “ባትጋሩን” በማለት የግል ጓዳ አድርው አባላቱን ሲከፋፍሉና ሲያባሉ እያስተዋልን ነው ።
በዚህ ጸሐፊ እምነት የሀገራችንን የሙያ ማኅበራትና የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያመሳስሏቸው በርካታ የጋራ ባህርያት እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል ። አንድም፡- ፈጥኖ ለመከፋፈልና ለመካሰስ ሱሰኞች ናቸው ። ሁለትም፡- ለመደማመጥ ጆሯቸው የተደፈነ ብቻ ሳይሆን የመሪዎቹ ልብም የደነደነ ነው ። ሦስትም፡- አመራሮቹ ለውጤታማ ግብ ከመድከም ይልቅ “በግለሰባዊ አምልኮ” (Personal cult) በሽታ የተለከፉ ስለሆኑ የማኅበር መሪ ከመሆን ይልቅ ራሱን ማኅበሩን ካልሆንን በማለት በትዕቢት ያበጡ ናቸው። እነዚህ ሦስት ባህርያት የሀገራችንን የሙያ ማኅበራት በሚገባ ይገልጧቸው ይመስለናል ።
ኢትዮጵያ ሆይ! “ጽናቱን ይስጥሽ!” ብለን ብቻ አንደመድምም ። ይልቅስ ስምሽን ለማስከበር ኮስተር ብለሽ ፈትሻቸው ። “የኢትዮጵያ…የሙያ ማኅበር” ብለው ስምሽን አለቦታው ሲያውሉም “ወይ የስሜን ክብር ያህል ስሩ፤ አለያም ስሜን መልሱልኝ” በማለት ልትሞግቻቸውና ልታስሞግቻቸው ይገባል ። ስምሽን የሚጠቀሙት ራሳቸው ሊያጌጡበት ሳይሆን ለውጤታማ ተግባር መገለጫነት እንዲያውሉት መሆኑን “ለወከልሽው መንግሥታዊ መዝጋቢ ተቋም” ኮስተር ያለ ትዕዛዝና ውሳኔ ልታስተላልፊለት ጊዜው አልመሸም ። “ከሩቁ በቅርቡ፤ ከደረቁ በርጥቡ” ብሂልን ልብ ይሏል ። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም