ትምህርት በሁለመናዊ ትኩረቱ በእውቀትም በክህሎትም አቅም ያለው ዜጋ ማድረግ፤ ምክንያታዊ ዜጋ መፍጠር ነው ። የትምህርት ፋይዳው በዚህ መልኩ ሊገለጽ የሚችለው ግን ተደራሽነቱን ከጥራት ጋር አሰናስሎ ማስጓዝ ሲቻል ነው ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት የነበረው የትምህርት ስርዓት ከዚህ እውነት የተፋታ ሆኖ ስለመቆየቱ በርካቶች በማሳያ አስደግፈው ሲናገሩ ይደመጣል ። ከዚህም ባለፈ የለውጡ ማግስት መንግስት ይሄንኑ እውነት ተገንዝቦ የጥራት ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ርምጃዎችን ሲወስድ ተመልክተናል ። ምክንያቱም የቀደመው ሂደት የትምህርት ሂደቱ ቁጥር (በተመራቂም፣ በትምህርት ቤቶች ግንባታና ተደራሽነትም) ተኮር በመሆኑ ነው ።
በዚህ መልኩ ቁጥርን እንጂ ጥራትን መሰረት ያደረገ ስራ ያለመሰራቱ፤ ተመራቂ ተማሪዎች የሚፈለገውን እውቀትና ክህሎት ጨብጠው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር ስለማይወጡ ከግለሰብ ጀምሮ አገርና ሕዝብ ዋጋ ከፍለዋል። ምክንያቱም፣ ጥራት ባለው ትምህርት ውስጥ ያለፈ ተማሪ ሙሉ ስብዕናው የተስተካከለ፤ ራሱን፣ አካባቢውን፣ ማህበረሰቡን፣ አገሩንም በእውቀቱ የሚመራ፤ በማንነቱ ኮርቶ ሌሎችም እንዲኮሩበት የሚያደርግ ነው ። ሆኖም እውነቱ ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ ተገልጿል ።
ለትምህርት ጥራት መጓደል እንደየሰው ምልከታ የተለያየ ምክንያት ሲሰጠው ይደመጣል ። ለምሳሌ፣ የትምህርት ጥራት የወደቀው በፖሊሲ ምክንያት ነው የሚሉ ምሑራን አሉ ። በአንጻሩ፣ ችግሩ ከፖሊሲው ሳይሆን ፖሊሲውን የመተግበር ሂደት የወለደው ነው የሚል ምክንያት ደግሞ ከደም ካለው መንግስት ሲደመጥ ቆይቷል ። በሌላ በኩል፣ ‹‹የልጄን ስነምግባር ያጎደለው ትምህርት ቤት በአግባቡ ስለማይቆጣጠሩት ነው›› የሚል ወቀሳ አዘል ምክንያት ከወላጅ ይደመጣል ። ትምህርት ቤቶች በተራቸው ‹‹ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ስለማይቆጣጠሯቸው እኛን አስቸግረውናል›› ሲሉ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም እንዲሁ ‹‹አሁን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ማንበብ ፣ መፃፍ አይችሉም›› በማለት ችግሩን ወደሌላ አካል የማዛመት ሂደት ውስጥ ይገባሉ ።
ተማሪዎችም ቢሆኑ ለድክመታቸው ምክንያት አያጡም ። ‹‹እንዴት ብለን እውቀት እንገብይ የስድስት ወር ትምህርቱ በሶስት ቀን ለብ ለብ ተደርጎ ይሰጠናል›› ሲሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ክፍተት ለመጠቆም ይጥራሉ። ምክንያቱ ያም ሆነ ይህ ግን ሁሉንም የሚያስማማ አንድ ነገር የትምህርት ጥራት ጉዳይ መውደቁ ነው ። ለዚህም ነው የለውጡ ማግስት መንግስት የትምህርት ጥራት ጉዳይ አንዱና ትልቁ አጀንዳው አድርጎ ሲሰራበት የቆየው፤ የፖሊሲና ተያያዥ ማሻሻያን በማድረግ ለተግባራዊነቱ ሲጥር፤ እና ይሄን ጥረቱን ለፍሬ የሚያበቁ ርምጃዎችንም ሲወስድ እየተስተዋለ ያለው ።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በዋናነት ሶስት ትልልቅ ምሶሶዎች እንደሚያስፈልጉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ ። እነዚህም ብቃት ያላቸው መምህራን፤ ጥራት ያላቸው የትምህርት ግብአቶችና ግብአቶችን የሚጠቀሙ ባለሙያዎች እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀና ለትምህርት ጥራት የተመቻቸ አካባቢ ናቸው ። ይሄንን የባለሙያዎች ምልከታ ይዤ፤ በኢትዮጵያ ያለው እውነት ምን ይመስላል? የሚለውን ለመመልከት ጥቂቶቹን በማሳያነት ልጠቃቅስ ወደድሁ ።
በቅድሚያ የመምህራንን ብቃት እንመልከት ። ብቃት ማለት እውቀት፣ ክህሎት እና ሰብዕናን ተጠቅመን የታሰበውን ወይም የተፈለገውን ውጤት ማምጣት መቻል ነው ። ስለሆነም ይህንን ብቃት የሚያሟላ መምህር አለ ወይ ስንል መልሱን አፍ ሞልቶ አዎ የማይባልበት ነው። ምክንያቱም በመምህሩ የተዘራውን ዘር በተማሪው አማካኝነት ፍሬውን እያየነው ስለሆነ ነው ። መምህሩ ሲማርም ሆነ ተማሪዎችን ሲያስተምር በአንድ አይነት መልኩ ነው ። የእርሱ ባህሪ ተማሪዎች ላይ ያጋባል ። በመሰል ስርዓት ውስጥ እንደማለፉም ማስተማርን በቸልታ የሚያየውም ቀላል አይደለም ።
ስለዚህም ነው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመምህሩም ለተማሪውም ስለማይደርስ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ እንዲመጣ አድርጎታል ። መንግስትም አሁን ላይ ይሄን የመምህራን ብቃት ችግር ለማረም እንዲችል አቅምን ለመለየት የሚያግዘውን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና መጀመሩም ለዚሁ ነው ። በዚህም መምህራን በምን ደረጃ ላይ ናቸው የሚለውን ምዘናው ያሳየ ሲሆን፤ ጅማሮውም ብዙ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ተስፋ ተጥሎበታል ። ምክንያቱም በዚህ መልኩ ነጥሮ የሚወጣ መምህር እውቀቱን የበለጠ እንዲያዳብር እና ተማሪዎችን በመደገፍና ማብቃት ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ።
በሁለተኛ ደረጃ የምናነሳው ጉዳይ ጥራት ያላቸው የትምህርት ግብአቶችና ግብአቶችን የሚጠቀሙ ባለሙያዎች የሚለውን ሲሆን፤ ከመምህራኑ በተለየ መልኩ የሚታይ አይደለም ። በእርግጥ እንደ አገር በርካታ ፈተናዎች ያሉብን እንደመሆኑ፤ በዛው ልክ የተሟላና ጥራት ያለው የትምህርት ግብዓት ማግኘት ፈታኝም ፈተናም ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ። ግብዓቱ ከሌለ ደግሞ ባለሙያው ከየትም አይመጣውም ።
ወደ ሦስተኛው ምሰሶ ስንገባ ደህንነቱ የተጠበቀና ለትምህርት ጥራት የተመቻቸ አካባቢ መፍጠር የሚለው ነው ። እንደ መንግስት በዚህ ውስጥ በርካታ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች እንደተከናወኑ መመልከት ይቻላል ። አንዱ አዲሲቱ ኢትዮጵያ በሚል የተጀመረው የትምህርት ቤት ግንባታ ጉዳይ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ላይ ጅማሮዎቹ እየታዩ ናቸው ። ሌላው አዲስ የትምህርት ስርዓት ቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ለውጦች ከወዲሁ እየመጡ ናቸው ። ማለትም በ10 ዓመቱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የተካተቱት ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ አመላካች ነገሮች አሉ ።
ለአብነት ተማሪዎች ታሪካቸውንና ባህላቸውን አውቀው በጥሩ ስብዕና እንዲማሩ ከማድረግ አኳያ ከአገር በቀል እውቀት የሚቀዳው ግብረገብነት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ተደርጎ ይሰጣል ። ሌላው እንደ አገር ያስቸገረውና ዓመታትን ያስቆጠረው የስርቆትና ኩረጃ ጉዳይ መፍትሄ እንዲበጅለት የተደረገበት አዲስ ጅማሮም ከለውጡ ቱርፋቶች መካከል የምናስቀምጠው ነው ። ይሄን አስመልክቶ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ፤ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ላይ እየመጣ ላለው ለውጥ አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ነው ያመለከተው ።
በመግለጫው እንደተመላከተውም ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ከገባችበት ጀምሮ በርካታ ተቋማዊ እና የፖሊሲ ሪፎርም ርምጃዎችን ወስዳለች ። ከእነዚህ የለውጥ ርምጃዎች መካከልም አንዱና ዋነኛው የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም ነው። ባለፉት ዓመታት ከተደራሽነት አንፃር መልካም ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም የትምህርት ጥራት ጉዳይ በእጅጉ ተዳክሞ ቆይቷል ። እናም መንግሥት የትምህርት ጥራትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ፓኬጆችን በመቅረፅ በርካታ የሪፎርም ርምጃዎችን ወስዷል ።
ከተወሰዱ ርምጃዎች መካከል የምዘና ሥርዓትን ማሻሻል አንዱ ሲሆን፤ ይህንን ለማሳካት የሚያስችለውን የመጀመሪያ ዙር የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ ዝግጅትና ተቋማዊ ቅንጅት ተሰጥቷል ። ይሄም ከዚህ በፊት በብልሹ አሠራር፣ በስርቆት እና በማጭበርበር ይደረግ የነበረውን የፈተና ሂደት በማስቀረት ሁሉም ተማሪ እኩል የሚመዘንበት ዕድል እንዲፈጥር የሚያደርግ ነው ።
ተፈታኝ ተማሪዎችና የተፈታኝ ወላጆችም ቢሆኑ የዘንድሮውን የብሔራዊ ፈተና በመልካም ጎኑ አይተውታል። በምክንያትነት የሚያነሱትም ሁለቱም አካላት ተፈታኞች የላባቸውን የሚያገኙበት አጋጣሚ ይፈጥራል ብለው ማሰባቸው ነው ። ፈተናው ሲጠናቀቅ ደግሞ የሂደቱን ውጤታማነት የበለጠ መመልከት የሚቻልበት እድል መኖሩ እሙን ነው ። እናም ለውጡ እንዳለ ሆኖ ችግሮችን እያዩ መፍታት አሁንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ በመጠቆም ለዛሬ ሃሳቤን በዚህ ልቋጭ ። ሰላም!!
ክብረ መንግስት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም