የአሜሪካ 26ኛው ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት በአንድ ወቅት “ጦርነት ባይኖር፣ የጦር ገበሬ የሆነ ጄነራል አይኖርህም። ያለ ከባድ ቀውስና ፈተና ታላቅ መሪ ልታፈራ አትችልም። አብርሀም ሊንከን የጦርነት ጊዜ ፕሬዚዳንት ባይሆን ኖሮ ዛሬ ላታስታውሰው ትችላለህ።” ብለው ነበር። እነዚህ አራት ዓመታት እንደ ሀገር፣ ሕዝብና ተቋማት በብርቱ የተፈተንባቸው ቢሆንም የዚች ሀገር መሪ ላይ ግን ፈተናው ከወፍጮ ድንጋይ ጋር ታስሮ ወደ ጥልቁ ጋር ከመውረድ የከበደ ነው። የሀገር፣ የሕዝብና ተቋማት ፈተና ቀድሞ መሪ ላይ የሚወድቅ ነውና። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ አመራርነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ እንደ መርግ በከበዱ ኅልቆ መሳፍርት በሌላቸው ፈተናዎች አልፈዋል። እያለፉም ይገኛል። እነዚህ ፈተናዎች ይዘውት የመጡ ግንባረ ብዙ ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ የኦነግ ሸኔና የቢጤዎቹ የንጹሐን ጭፍጨፋ፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሚያባራ የማይመስል በጎሳ ላይ የተመሠረተ ግጭት፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉበት፤ በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልሎች የተከሰተ ድርቅ፤ የዋጋ ግሽበቱን ተከትሎ የተፈጠረ የኑሮ ውድነት፤ የተጠና የኢኮኖሚ አሻጥር፤ የዓለማቀፍ ሚዲያው፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማትና ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ተቀናጅተውና ግንባር ፈጥረው በሀገራችን ላይ ያሳረፉት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ፤ ወዘተረፈ ደቅነውት የነበርና የአለ አደጋ ሁላችንንም የፈተኑን ቢሆንም ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት መሪ ላይ ሲሆን ግን የከፋ ነው።
ወርቅ በከዉር እንደሚፈተነው የሀገር መሪም እንዲህ በሀገራዊ አሳርና ፈተና አብሮ ይፈተናል ። አንድን መሪ መሪ የሚያደርገውም እነዚህን ፈተናዎች በጽናትና በአሸናፊነት መሻገር ሲችል ነው ። ታዋቂዋ የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ አጥኝና ደራሲ ዶሪስ ከረንስ ጉድዊን፤ “LEADERSHIP” በተሰኘ ግሩም ድንቅ መጽሐፏ፣ “የመሪዎችን አፈጣጠርና አነሳስ በቅርብ የሚያጠኑ የዘርፉ ልሒቃን የተዋጣለት መሪ ማለት በመከረና በፈተና ሳይበገር በጽናት ለዓላማው ስኬት ሌት ተቀን የታመነ ነው ትላለች። “የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የአመራር ብቃትም ሆነ ድክመት ልሒቃን በጥናትና በምርምር መዝነው ወደፊት የሚያሳውቁን ቢሆንም፤ ታሪክና ትውልድም በተራው የራሱን ፍርድ ቢሰጥም፤ አይደለም እንዲህ ባለ ፈተና ተረጋግቶና ጸንቶ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር መምራት ይቅርና አርሴናል የተሸነፈ ዕለት እንቅልፍ አጥቼ የማድርና ሰው በአጠገቤ ባለፈ ቁጥር ነገር ነገር ይለኝ የነበር ሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩን በቀውስ መሀከል ሆኖ የተገለጠ የአመራር ጥበብ ባላደንቅና እውቅና ባልሰጥ ንፍገት ስለሚሆንብኝ ፤ ሰሞነኛውን ዘመኑንና ትውልዱን የዋጀ የሳይንስ ሙዚየም ምረቃ መነሻ አድርጌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ/BIBLICAL/ሊባል በሚችል መከራና ፈተና መካከል ሆነው ፣ ሳይበገሩና አንድም ቀን ሸብረክ ሳይሉና ጥርሳቸውን ነክሰው እየቃተቱ አይናቸውን ከአፋቸው ከማትጠፋ ኢትዮጵያ ለቅጽበት ሳያነሱ ያከናወኗቸውንና ለሀገር ወሳኝ መታጠፊያ የሆኖ ግዙፍ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና ተግባራትን ከማነሳሳቴ በፊት ፤ እኔን ጨምሮ አይደለም ታሪክን በእነዚህ አራት ዓመታት እንኳ ያለፍንባቸውን መከራዎችና አሳሮች የምንረሳ ዝንጉና ባተሌ ስለሆን በወፍ በረር መለስ ብለን አብረን እንቆዝም ።
በተደጋጋሚ እንደምለው በዚች ሀገር የ”100”፣ የ3ሺህም ሆነ የ7 ሺህ ዓመት ዘመናዊ ሆነ ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ታሪክ እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት እና እንደዚህ ትውልድና ሕዝብ በኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል (ሱናሚ ) መካከል እንደምትቀዝፍ ታንኳ ከየአቅጣጫው የተላጋ ፣ የተናወጠ ፣ የተፈተነና መልሕቁን ለመጣል የተቸገረ የለም ማለት እችላለሁ ። ታሪካዊ ንጽጽሬ ላይ የዘመነ ጓዴነት/contemporaries/ ጥያቄ የሚያነሳ ካለ ደግሞ እንዲህ ላስተካክለው፡- ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በየትኛው አህጉር ያለ ሀገርና ሕዝብ እንደ ኢትዮጵያ የተፈተነ የለም። የመንም ፣ ሊቢያም ፣ ሶሪያምና ሶማሊያም ፣ ሌላም ሀገር ቢሆን ። በሰሜን ዕዝ ላይ ትውልድም ሆነ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደትና ጭፍጨፋ የተፈጸመበት ፤ በአማራና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሓት ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ጦርነት በከፈተበት ፤ በዚህ የተነሳ ከ12 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ተፈናቃይና ተረጂ በሆኑበት ፤ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተነሳ ግብጽና ግብረ አበሮቿ እንደ ውጋት ቀስፈው በያዙን ወቅት ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ የአርብቶ አደሩ የሕልውና ዋስትና የሆኑ እንስሳት አልቀው በሚሊዮኖች የሚገመት ሕዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊ በሆነበት ፤ በአናቱ የቀደሙትንና ሰሞነኛዎችን ሳይጨምር እስከ አለፈው ዓመት በአገሪቱ 120 ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ፣ ጥቃቶችና ግጭቶች በተቀናጀ አግባብ መፈጸማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ያስታውሷል ። የሕወሓት ቡችሎች ተናበውና ተቀናጅተው በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ጭፍጨፋና ጥቃት በከፈቱበት ፤ በመላ አገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ባለበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ፤ ስነ ምግባር የጎደላቸው ስግብግብ ነጋዴዎችና ደላላዎች ፤ ብልሹ ከሆነው የግብይት ሥርዓት ጋር አብረው ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ባሉበት ቀውጢ ሰዓት ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ እንድንሰንቅ ፤ የብሩህ ተስፋ እሸት እንድንቀምስ አድርገዋል ። ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች ቢኖሩም ።
ይሁንና ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭና ድቅድቅ ጨለማ ነው ማለት አይደለም ። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈት ተርፎ በሁለት ተርባይን 550 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መቻሉ በራሱ ትልቅ የአመራራቸው ስኬት ቢሆንም የቀጣናውን ጂኦፖለቲካ በመበወዝ የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው ። በድህነታችንና በተመጽዋችነታችን ሳቢያ ፖለቲካዊ ብቻ የነበረውን ግማሽ የነጻነትና የሉዓላዊነት ታሪካችን ሙሉ የሚያደርግ የስንዴ ልማትና አጠቃላይ የግብርና ውልጠት /transformation/ሌላው ተስፋ የሚያሰንቅ ተግባር ነው ። ሀገራችን በ2014 ዓም መኸርን ሳይጨምር በበጋ መስኖ ልማት ብቻ 25 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት የተቻለ ሲሆን ፤ በመኸር ደግሞ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ ኩንታል ስንዴ ፤ በዘንድሮው ዓመትም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ መያዙ ሌላው የአርቆ ተመልካችና የበሰለ አመራር አብነት ከመሆኑ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ወሳኝ መታጠፊያ ነው ። ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ከግብጽ ቀጥላ ስንዴን ለዓለማቀፍ ገበያ የምታቀርብ 2ኛዋ ሀገር እንደምትሆን እየተገለጸ ይገኛል። ኩታ ገጠም ግብርና እና ሜካናይዜሽን ላይ እየተሠራ ያለው ሥራም ተስፋን የሚያለመልም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ሉዓላዊነታችንን ሙሉ በኩልዬ የሚያደርግ ነው ። የአረንጓዴ አሻራውና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱም የብሩህ ተስፋችን ሌላው ቡቃያ ነው ። በአረንጓዴ አሻራ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉ ሌላው እጅን ባፍ ያስጫነ ስኬት ነው ። የአብርኆት ግዙፍ ቤተ መጽሐፍት ፤ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክቶች ፤ የእነ ኮይሻ ፣ ጎርጎራ ፣ወንጪ ፕሮጀክቶችም አይን ገላጭና መስፈንጠሪያ ሆነው ከሚያገለግሉን ሜጋ ፕሮጀክቶች ተርታ የሚሰለፉ ናቸው ። እኛም ከሰናይ ተግባራት ይልቅ በእኩያኑ፣ በሴራ ፣ በጎሰኝነትና በሐሰተኛ መረጃ ተወስደን ፤ ዓለማቀፉ ማኅበረሰቡና ሚዲያም ከእውነት ጋር ከመቆም ይልቅ ከሕወሓት ጎን መቆም ስለፈለገ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አፍላቂነትና አመራር የተመዘገቡ አንጸባራቂ ውጤቶች በታሪክ ታይተው የማያውቁ ከመሆናቸው ባሻገር የሀገሪቱን መጻኢ እድል በምቹ መደላድል የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ደረትን ነፍቶ በኩራት መመስከር የሚያስችሉ ናቸው ።
ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ መንግሥት ኮሚሽን በአዋጅ ማቋቋሙና ኮሚሽኖች በገለልተኛ አካል እንዲሰየሙ መደረጉ ፤ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ነው ። በማንነት በልዩነትና በጥላቻ የተጎነቆለውን ፖለቲካችንን እልባት የሚሰጥ ነው ። ሀገረ መንግሥቱን ከተቀለሰበት ድቡሽት አንስቶ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ ነው ። ትውልዶች ለዘመናት ሲያነሷቸው ሲታገሉላቸውና መስዋዕት ሲከፍሉላቸው የኖሩ ጥያቄዎችን በማያዳግም ሁኔታ የሚመልስ ነው ። ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ አገር ፣ የጋራ ሕልም ፣ የጋራ ራዕይ ፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ ፣ የጋራ ጀግና ፣ የጋራ ታሪክ ፣ ወዘተረፈ. እንዲኖረን የሚያግዝ ነው ። ገለልተኛነቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ከተመለሱና በቅንና ንጹሕ ሕሊና ከተመራ የትውልድ ተስፋና ለአገርም ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture/ ነው ። ሀገርን እንደ ንስር የሚያድስና በከፍታ የሚያበር ነው ። ከእነ ውስንነቶቹ በስኬት የተጠናቀቀው ሀገር አቀፍ ምርጫም በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል ። በተለይ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ኮሚሽንናና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምንና ፍርድ ቤቶችንና የፍትሕ አካላትን በነጻነትና በገለልተኝነት ለማቋቋም የተሄደበት እርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው ። በተለይ የሀገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጨረሻ ምሽግ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ፣ በሌሎች የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ላይ የመጣው ተጨባጭ ለውጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዙሪያ መለስ ዕይታና የአመራር ሚና የሚያሳይ ነው ። አንዱን ይዞ ሌላውን በመጣል ችግሮቻችንን መፍታት እንደማንችል በተግባር አመልክተውናል ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውና ዘመናዊ የሳይንስ ሙዚየም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል ። ግዙፍና በቀለበት ቅርፀ የተገነባው ሕንፃ ከ15 ሺህ ሜትር ካሬ በሚበልጥ መሬት ላይ የተንጣለለ ሲሆን ፤ 132 ሜትርም ይረዝማል ። ሙዚየሙ አዳዲስ ተሞክሮዎችና ዕውቀቶች የሚቀሰሙበት መድረክም መሆኑ ፤ ዛሬንና ነገን በአንድ ላይ አያይዞ ሳይንስን ጥበባዊ በሆነ መንገድ የያዘ ፤ ግቢውም ሰባት ሺህ ሄክታር እንደሚሰፋ ተገልጿል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በቲዊተራቸው ፤ “የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየምን መርቀን ከፍተናል። የቴክኖሎጂ ዐውደ ርዕይ አስጀምረናል። የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስ ከፍተናል። ምክንያቱም አፍሪካን ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማብቃት በአህጉሪቱ መተሣሰርን፣ መማማርንና በጋራ መፍጠርን ለማምጣት ሁሉም አስፈላጊ በመሆናቸው ነው”ብለዋል ። ቀደም ሲል የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ አገልግሎትንና የሰው ሰራሽ ክህሎት/አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ/ተቋማትን በመመሥረት ረገድ እርሾ ሆነዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ፤ ሀገራችን የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ ያስወነጨፈችውም በእሳቸው አመራር ነው ። ለዚህ ራዕይ እውን መሆን ከጥንስሱ ጀምሮ የእሳቸው ተሳትፎ የጎላ ነው ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይና ባልደረቦቹ ራዕይ እና የሌት ተቀን ጥረት ውጤት ማብሰሪያ እና የህዳሴ ምልክት የሆነችው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት ETRSS – 1 / Ethiopian Remote Sensing Satellite / ቻይና ከሚገኘው የስፔስ ሳይንስ አካዳሚ የሳተላይት ማስወንጨፊያ ማዕከል ለኢትዮጵያ መረጃ ልታቀብል ሰንደቃችንን አንግባ የቀደሟትን ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ወደ 9ሺህ የሚጠጉ ሳተላይቶች በመቀላቀል ኢትዮጵያ 41ኛ ሆና የባለሳተላይት ሀገራትን ዝርዝር ተቀላቅላለች። “…ከ8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ የተደረገባት ሳተላይቷ ከመጠቀች በኋላ በ30 ደቂቃ የተያዘላትን የ700 ኪሎ ሜትር ከፍታ orbital slot ትይዛለች። ከዚያ በኋላ ፍተሻውና የማስተላለፉ ሂደት በ1ወር ከ7 ቀን ይጠናቀቃል። ከዚያ ቀጥሎ በሚኖረው አንድ ወር የምታስተላልፈው መረጃ ትክክል መሆን አለመሆኑ ከተመረመረና የምትገኝበት ሁኔታም ከተረጋገጠ በኋላ ርክክቡ ይፈፀማል። ከዚያ ሳተላይቷ እስከ 10 ዓመት ድረስ አገልግሎት ትሰጣለች ። ኢትዮጵያ እነዚህን መሰል የሳተላይት መረጃዎች እስካሁን የምታገኘው ይህን አገልግሎት ከሚሰጡ የውጭ ሀገር ድርጅቶች በግዢ ነው። ሀገሪቱ ለሳተላይት ምስሎች ግዢ ብቻ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ታወጣለች። ሀገሪቱ ለሳተላይት መረጃ የምታወጣው ወጪ ከዚህም የላቀ ነበር ብለው ነበር ዶ/ር ሰለሞን ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከ2008 ዓ.ም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሳሉ ጀምሮ ለስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ልዩ ድጋፍና ክትትል ያደርጉ እንደነበርና ተቋሙ የራሱ ሳተላይት ለማምጠቅ የበቃውም በእርሳቸው ጥረት መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን አስታውቀው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ 2ኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀውን የአዋጭነት ጥናቱን አጠናቃ ሀብት የማፈላለግ ሥራውን በማከናወን ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀድሞው አይረሳም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ይፋ አድርገዋል:: በቀጣይ የሚመጥቀው የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ሲሆን ፤ ሳተላይቱ 60 ኩንታል የሚመዝን ሲሆን ከምድራችን 36ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በህዋ ይቀመጣል:: ለሳተላይቱ ግንባታና ለማስወንጨፍ የሚያስፈልገውን ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ በረጅም ጊዜ ብድርና በአነስተኛ ወለድ ለማግኘት መንግሥት በቅንጅትና በቁርጠኝነት በመሥራት ላይ መሆኑን እና በቀጣዩ የበጀት ዓመት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ ፕሮጀክቱ ይፋ ይደረጋል::
ሀገራችን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሳተላይቶቿን ቁጥር 11 ለማድረስ አበክራ በመሥራት ላይ መሆኗን ከዋና ዳይሬክተሩ አንደበት ከመስማት በላይ ለዚህ ትውልድ ልብን በሀሴት የሚሞላ ምን ብስራት አለ!? ይሁንና ሀገራችን ከ3ና 4ሺህ ዓመታት በፊት በህዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር የጥንት ብራና መጽሐፍትና ስንክ ሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር ዓለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በሀገራችን ልዕልት፣ ንግሥትና ንጉሥ ስም ኅብረ ከዋክብት constellations መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው!? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የስነ–ፈለክ /የሕዋ/ እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው የሮዳስ ታደሰና ጌትነት ፈለቀ (ሁሉም ፒ ኤች ዲ ሠርተዋል):: በጋራ በደረሱት፤ ” አንድሮሜዳ ” መጽሐፍ ላይ ፤”… ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች …’ ጥንታዊ ዘር‘ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን … አውሮፓና እስያ ባልሰለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሒሳብ ፣ ግብርና ፣ ሕክምና ፣የክዋክብት ጥናት …የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል::… ” ይህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለስነ ፈለክ የማይናወጥ መሠረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል::
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን እና ለስነ– ፈለክ ምርምር ወረት፣ መነሻ እንደነበራት የሚያረጋግጡ የቀደምት ሊቃውንት እማኝነት ከፍ ሲል በተገለፀው መፅሐፍ እንደሚከተለው ተዘግቧል:: “60 ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ የነበረው ዲዎዶርስ ሴኩለስ የተባለ የታሪክ ሊቅ ‘ አውሮፓውያን ኋላ ቀር እድገት አኗኗር ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላቅ ስልጣኔ ላይ የነበረች …ኢትዮጵያውያን ለግብጻውያን ስልጣኔ ያስጀመሩና እስከ ሕንድ ድረስ የገዙ ናቸው:: ‘ … በ700 ዓ.ም የነበረው የቤዛንታይኑ እስቲፋንስ ባካሄደው ጥልቅ ጥናት ‘ ኢትዮጵያ መሬታችን ላይ የተመሠረተች የመጀመሪያ ሀገር ናት ‘ ሲል አርኖልድ ኸርማን ሉድዊግ የተባለ የጀርመናዊ የታሪክ ፀሐፊ ደግሞ ‘ ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ ሀገር ወዴት ይገኛል!?‘ ሲል ይሞግታል … ከ800 ዓመት ክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሆሜር አሊያድና እና ኦዲሴይ በተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ ኢትዮጵያውያን ‘ እስከ መሬት ጫፍ ድረስ የሚኖሩና ከአምላክ ጋር ቅርበት ያላቸው ‘ በማለት ይገልጻቸዋል::
የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሔሮዶቶስ ኢትዮጵያውያንን ‘ከሰሐራ በታች የሚኖሩ፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው …ብልሆች፣ በዓላቶቻቸውና ሀሴታቸውም ሳይቀር አማልክትን ስለሚያስደስት የአማልክት አምላክ እየሄደ በዓላቱን በደስታ አብሯቸው ያሳልፋል ‘ ብሏል:: …ዲዮዶር የተባለ የሮም ፀሐፊ ደግሞ ‘ከግብፅ በፊት ስልጡንና ገናና ነበረች:: ግብፅን ቅኝ ገዝታ 18 የኢትዮጵያ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል:: …’ ይላል:: “መጽሐፉ ሀገራችን የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን በአደባባይ ካስመሰከረ በኋላ በዓለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት የተሰጣትን ቦታ ይተነትናል :: “…ኅብረ ከዋክብት constellations ማለት በሰማይ ላይ የሆነ አይነት ቅርፅ የሚሠራ የከዋክብት ስብስብ ሲሆን ቅርጹም ከማይቶሎጂ ጋር በተያያዘ መልኩ የሰው፣ የእንስሳት ወይም ሕይወት የሌለው ነገር ሆኖ ሊገለጽ ይችላል። ዓለማቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በ1930 ዓ.ም ከ88 ኅብራተ ከዋክብት ውስጥ ሶስቱን ማለትም አንድሮሜዳን ፣ ካሲዮፕያንና ሴፌውስን በኢትዮጵያውያን ስም መዝግቧል::… አንድሮሜዳ የኢትዮጵያ ልዕልት ስትሆን፤ ካሲዮፕያን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግስት ናት:: ሴፌውስ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉስ ነው :: …”
መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም