በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ እና አሸንፎ ሀገሪቱንም እየመራ ያለው አዲሱ መንግሥት ምሥረታውን ያካሄደው በወርሃ መስከረም ነበር ። አንድ ዓመትን ያስቆጠረው አዲሱ መንግሥትም በአጭር ጊዜ እና ረዘም ባሉ ዓመታት ውስጥ የሚያከውናቸውን በርካታ ሥራዎች ለመሥራት ከማቀድ በተጨማሪ እቅዶቹን የተሳካ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ። እኔም በዛሬው መጣጥፌ ከለውጡ ማግስት በምርጫ ስልጣን የያዘው መንግስት በአንድ ዓመት ጉዞው የነበሩትን ጥንካሬዎች እንዲሁም የነበሩበትን ደካማ ጎኖች በተወሰነ መልኩ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ።
መንግሥት በተለይም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ከማስመረቅ አንጻር እጅግ የሚያስመሰግነውን ስራ የሠራ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ፕሮጀክቶች ቀድሞ የነበረባቸውን በተቀመጠላቸው ጊዜና በጀት ተጠናቅቀው ለሚፈለግባቸው አገልግሎት ያለመዋልን ችግር ያስቀረ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ ህብረተሰቡን እንዲጠቀሙ ማድረጉ ይበል እና ይቀጥል የሚያሰኝ ነገር ነው ። እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማያልፈው የዓባይ ግድብም ቢሆን ለሦስተኛ ዙር ውሃ መሞላት መቻሉም መንግሥት ይህንን ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ማስቀጠልና ለውጤት እንዲበቃ የማድረጉም ነገር በቀላሉና ሁለተኛው ተርባይን ወደ ኃይል ማመንጨት ስራ መግባቱ በትልቁ የሚነገር ስኬት ነው ።
በሌሎች አገራት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆነ የመጣው ተገጣጣሚ ቤቶችን በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ማድረጉም የዜጎችን ችግር ከመፍታት አኳያ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ በዚህ ይቀጥል የሚያስብል ሥራ ነው ። ይሁን እንጂ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተመለከተ መንግሥት እንደ መንግሥት ሥራውን ከተረከበ በኋላ ይህ ነው ተብሎ የሚነገር ለዐይን የሚሞላ ሥራ አልታየም ቢባል ብዙዎቻችንን ሊያስማማ የሚችል ነው ። እንደውም በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ጉዳይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በድጋሚ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይወጣል ተብሎ በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ቢገለጽም እስካሁን እጣው በድጋሚ ለምን እንዳልወጣ የተገለጸ ነገር የለም ። ይህም የሕዝብን አመኔታ የሚያሳጣ ድርጊት በመሆኑ መንግሥት አንድ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል ።
በተጨማሪም መንግሥት የቤት ተከራዮች ላይ ኪራይ እንዳይጨምር ለማድረግ በተለያዩ ጊዜ አከራዮች ዋጋ እንዳይጨምሩ እና ተከራዮችን እንዳያስወጡ ማድረጉ በአንድ በኩል የሚመሠገን ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለቤት ኪራይ መናር የአከራዮች ብቻ ሚና ሳይሆን ለዚህ ችግር መበራከት እንዲሁም በመባባሱ በኩል ድርሻውን እየተወጣ ያለውን ህገ ወጥ ደላላ ለመቆጣጠር አስተማሪ የሆነ ሥራ የተሠራ አይመስልም ። ይህ ችግር ደግሞ የህዝቡን ብሶትና ችግር የሚያባባስ ድርጊት መሆኑን ተገንዝቦ መንግሥት በቀጣይ ሊቀርፈው የሚገባው ነው ።
መንግሥት ከመሥረታው በኋላ ከሠራቸው ሥራዎች በገበያ በኩል የኑሮ ውደነቱን ለመቀነስ በርካታ ጥረቶች አድርጓል፤ በተወሰነ መልኩም ችግሩን መከላከል ችሏል ። ሆኖም ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል ። በተለይ ከህገ ወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ አንድ ምርት ዋጋ ከመጠን በላይ ሲወደድ ይህንን ተከታትሎ ጥፋተኞች ላይ ርምጃ ወስዶ ለሌሎች መማሪያ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ።
ሳይንስና ቴክኖሎጂውን ከማስፋት አንጻርም በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሳይንስ ሙዚየም እውን ማድረግ ተችሏል፤ በቴሌኮም ዘርፉም ተወዳዳሪነትን ለማስፋት የ ሳፋሪ ኮም ያሉ የቴሌኮም ኩባንያዎች በሀገር ወስጥ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ሆኗል ። በዚህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርላቸው ሲሆን ለሕብረተሰቡም ቢሆን አማራጭ መቅረቡ የሚያስመሰግነው ሥራ ነው ። በቀጣይም የባንክና ሌሎች ዘርፎች ላይ መሰል ማሻሻያዎችን መመልከት ተገቢ ይሆናል ። ይሄም የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ሀገሪቱንም በኢኮኖሚ እንድታድግ እና በባንኩ ዘርፍም ጥሩ ውድድር እንዲኖር ያስችላል ።
ከሰላምና ደህንነት አንጻርም መንግስት በሆደ ሰፊነት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የአገርን ክብርና ጥቅም ባስከበረ መልኩ የሚሄድባቸው መንገዶች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ። በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ለስኬት አይብቃ እንጂ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ያለውን ልዩነት በድርድር ለመፍታት የሄደበት ርቀት የሚያስመሰግን ነው ። ዛሬም ቢሆን ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ እና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ሕይወታቸውን መገበር፤ የአገርም አንጡራ ሃብት መውደም ስለሌለበት መንግስት ለሰላም የሰጠው እድል የአገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ሊቀጥል የሚገባው ነው ። ምክንያቱም በኑሮ ወድነት እና በመሰል ችግሮች እየተናጠች ላለች ሀገር ጦርነቱ የኢኮኖሚ ድቀት ከማከናነብ ውጭ ይዞላት የሚመጣ ትርፍ ባለመኖሩ መንግሥት ከዚህ በፊት ሲያደርጋቸው የነበሩትን የሠላም ጅምሮች የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል ። ለሠላም የተዘረጉ እጆችም መታጠፍ የለባቸውም ።
በዚህ ረገድ ብዙዎች መንግሥት ሠላምን በማስፈን እና እዚህም እዛም የሚታየውን ግጭት ለመፍታት አቅም እንደሚኖረው ያምናሉ ። ይሁን እንጂ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ሠዎች በማንነታቸው ምክንያት ሕይወታቸው እየጠቀጠፈ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመንግስትን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡም አልታጡም ። በመሆኑም ይህንን ያላባራ ችግር መንግሥት ሊያስወግደውና የዜጎች በሠላም ወጥቶ መግባት እና የመሥራት መብታቸው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት ይጠበቅበታል ።
ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ከምርጫው ማግስት መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ብዙም ያልተስተዋለውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን የማጋራቱ ነው ። ይህም እንደ መንግሥት ተባብሮ እና ተደጋግፎ ከመሥራት በተጨማሪ ብዙ ጊዜ ‹ትችት እንጂ ሥራ አይችሉም› ተብለው ለሚነቀፉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገራቸው የአቅማቸውን እንዲያደርጉ እድል መስጠቱም የሚያስመሰግነው ሥራ ሲሆን፤ ይህ አይነቱ ድርጊት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ብሎ ደፍሮ መናርገም ይቻላል ። ከዚህ ጋር በተያያዘም እንደ መንግሥት በጣም ጥሩ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ከሚታዩት ሥራዎች መካከል በተለይም የትህምርት ዘርፉ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ለአብነት እናንሳ ከተባለም የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በኩል በያዝነው ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ሀገሪቱ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን እንድታፈራ የሚያስችል በመሆኑ በመንግስት በኩል ይህ ዓይነቱ ውሳኔ መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን ለመረዳት አመታትን መጠበቅ አያሻም ። የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱም ቢሆን ሌላው በበጎ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ነው ። ፈተናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠቱ እና ለመኮራረጅ እንዳያመች አራት የነበሩት የፈተና ኮዶች ወደ 12 ከፍ እንዲል መደረጉም የነገው ሀገር ተረካቢ ዜጋ በራሱ ጥረት የሚሠራ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችለው ነው ።
በግብርናው፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣… ዘርፎች የተሰጠው ትኩረት፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የከተማ ግብርና እንዲለመድ ለአትክልት ልማት የሠጠውን ጉዳይ ማንሳቱ ተገቢ ነው ። ከታች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ድረስ ለአብነት እየተተከሉ ያሉ እና በቀላሉ ለምግብነት የሚደርሱ ተክሎችን እንዲተከሉ ማስቻል እና ማስተማር መንግሥትን የሚያስመሰግነው ሥራ ነው ። እኔም እነዚህን መሰል በመልካምም በችግርም የሚነሱ ነገሮችን መጠቃቀሴ መንግስት ከጥንካሬው ብርታትን፣ ከድክመቱ ቁጭትን ይዞ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ስራ እንዲያከናውን በማሰብ ነው ።
በምስጋና ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/ 2015 ዓ.ም