ዓለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶችና ግኝቶች እየተመራች ነው። ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በዚሁ ዘርፍ መመራት ከጀመሩ ክፍለ ዘመን ሊቆጠር ምንም ያህል አልቀረውም። ሃገራት ኃያልነታቸውን በቴክኖሎጂና የሳይንስ ምርምር ውጤቶች ላይ ተመርኩዘው ነው የሚገነቡት። ወታደራዊ ጡንቻቸው የሚለካው በዚሁ ዘርፍ ባስመዘገቡት ስኬት ልክ ከሆነ ሰነባበተ። በሰው ልጅ ጉልበት አይሳኩም የተባሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ብሩህ የመፍጠር አቅም ባላቸው ጥቂቶች በተፈለሰፉ ቴክኖሎጂዎች እውን ሲሆኑ አይተናል። አሁን ሁሉም ነገር በቴክኖሎጂና ረቂቅ ሳይንሳዊ ጉዳዮች ይመራል። ለዚህም ይመስላል አዲሱ ትውልድ ከዚሁ ጋር በተያያዙ እውቀቶች እንዲበለፅግ የሚፈለገው።
ምድራችን በሉላዊነት (globalization) መርሕ እየተመራች ነው። ለዚህ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ እና መሰል የግንኙነት መድረኮች የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል። ገበያው እንዲሁ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚል መስመር የያዘ ነው። ደህንነትና ጦርነቱ በሳይበር ምህዳር ውስጥ የሚጠቃለል ነው። በግርድፉ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ውጤቶች የዘመናችን የኃያልነት ቁልፉን በመዳፋቸው ስር ማስገባት ችለዋል። በዚህ የፉክክር መድረክ ላይ ከፊት ለመሰለፍ ደግሞ ከጫወታው መርሕ ጋር መግባባትን ያሻል። በቅድሚያ ለቴክኖሎጂና መሰል ሳይንሳዊ ጉዳዮች በርን ክፍት ማድረግ ይጠይቃል።
ታላላቅ አገራት ይህን መስመር በሚገባ እየተከተሉት ነው። የኢንዱስትሪውን አብዮት ከጨረሱ ክፍለዘመን አስቆጠሩ። እድገታቸው አልጋ ባልጋ ካደረጉ ታላላቅ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች ጋር ወደፊት ብለው ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። አሁን ወደ አራተኛው ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሸጋግረዋል። አዲሱን ትውልዳቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ከማነፃቸውም ባሻገር አዕምሯቸው እንዳያፈገፍግ የተለያዩ ስልቶችን ይነድፋሉ። ከዚህ ውስጥ አንዱ “የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየሞችንና የልህቀት ማዕከላትን” መገንባት ነው።
በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ የሚገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም “The Powerhouse Museum” ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው። ትውልዱ ከዚህ የእድገት ማሽን ላይ እንዳይወርድ እና አዳዲስ መረጃዎችን እንዲያገኝ በማሰብ የተገነባ ነው። ታዳጊዎች ሕፃናት ዓለማችን አሁን ላይ በቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች ምን ያህል እንደተለወጠች ይማሩበታል። በቀጣይ ደግሞ ይህን ዙፋን ተረክበው ጉዞውን ያስቀጥሉታል። የትውልድ ቅብብሎሽ ማለት ይህ ነው። በአሜሪካዋ ግዛት ቴክሳስ ሂውስተን የሚገኘው “The Space Center houses” ሌላኛው ምሳሌያችን ነው። ያለፈው ትውልድ ከየት ተነስቶ ጠፈር ላይ በቴክኖሎጂና ሳይንስ ምርምር ሊወጣ እንደቻለ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ታዳጊዎች ሕፃናት ህልማቸውን በዚያ ሙዚየም ውስጥ አጮልቀው ያዩበታል። ነጋቸውን በዚያ ውስጥ ሆነው ይመለከቱበታል። የአያቶቻቸውን ረቂቅ የምርምር ውጤት አይተው ከማድነቅ ባለፈ ፈለጋቸውን ለመከተል የሚያስችል መረጃን አጋብሰው ይወጣሉ። በሩሲያ ሞስኮ የሚገኘው “The Planetarium in Moscow” በቻይና የሚገኘው “Science and Technology Museum in China” በሜክሲኮ፣ ስፔን እና መሰል ታላላቅ ሃገራት የሚገኙት ሙዚየሞች ዓለማችን ያሳለፈችውንም ሆነ አሁን የምትገኝበትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃ ቁልጭ አድርገው ከማሳየታቸው ባሻገር አዲሱ ትውልድ ላይ እውቀትን ለማተም ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
በዚህ ረገድ ሀገራችን የት ቦታ ላይ ትገኛለች? ከታዳጊ ሃገራት ተርታ የተሰለፈችው ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዚህ ዘርፍ ወደኋላ ከቀሩ ሃገራት ተርታ ትመደብ ነበር። አሁን ላይ ግን መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ የተለያዩ ማሻሻያዎችን የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በተለይ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያበረታቱና ታዳጊዎችን የሚያፈሩ ማዕከላት ግንባታ ላይ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በሚኒስትር መሥሪያ ቤት ደረጃ የተደራጀው የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና ሌሎች የዘርፉ ማዕከላትን ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ በተሻለ መልኩ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ ወደ መስመር እየገቡ ነው። ይህ ደግሞ በቅርብ ግዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደሚመዘገቡ ያመላከተ ነው።
ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ጥበባት ሙዚየም ደግሞ የመንግሥትን ጥረትና ሊመዘገብ የሚችለውን ውጤት በጉልህ ያመላከተ ነበር። በተለይ ወጣቶች ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና የተሻለ ከባቢያዊ ሁኔታ አግኝተው መጪዋን ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች ወደፊት ማራመድ እንዲችሉ ሰፊ እድል የሚከፍት እንደሆነ ያሳየ ነው። ለመሆኑ ይህ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም በውስጡ ምን ይዟል? መጪው ትውልድ ሃገሪቱ የፈለገችውን ራዕይ እንዲያሳካስ ምን አስተዋፅዖ ያበረክታል? ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሙዚየሙን መርቀው በይፋ ሲከፍቱ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።
“የሳይንስ ሙዚየሙ በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል” በማለት በሃገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ቢኖርም ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የተመቻቸ ቦታ ባለመኖሩ የወጣቶችን እምቅ የፈጠራ አቅም መጠቀም እንዳልተቻለ ነው የገለጹት። እንዲህ ያለ የሳይንስ ሙዚየም መኖሩ ወጣቶች ተሰጧቸውን አውጥተው ለመጠቀም እድል የሚፈጥርላቸው ሲሆን፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተነቃቃ አዲስ ትውልድ ለመቅረጽም አይነኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።ኢትዮጵያ “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ”ን ቀርፃና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይታ እየሠራች መሆኑንንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባ የተገነባው ይህ የሳይንስ ሙዚየም ይህንን በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።የሳይንስ ሙዚየሙ የአዲስ አበባ ከተማን በቴክኖሎጂ የታነፀች ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን ጉልህ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። ሳይንስና ጥበብን በሁለት አተያይ ያጣመረው ሙዚየሙ በሃገር ውስጥ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ የሚቀርቡበትና የሚተዋወቁበት፣ ምርምር የሚደረግበት፣ የምርምር ሥራዎች የሚቀርቡበት እና ወጣቶች ንድፍ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት እንደሆነም አመልክተዋል።
ሙዚየሙ ምን ይዟል
በሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ የሳይንስ ሙዚየም፤ የቀለበት ቅርጽ ያለውና መሐሉ ላይ የጉልላት ቅርጽ ያለው ሕንጻ ነው፡፡ ሕንጻው እንዲህ ያለ ቅርጽ መያዙ “ምሉዕነትን፣ የማያቋርጥ የከፍታ ጥረትንና ምኞትን ማሳያ፣ ረቂቅ የሆነውን የኢትዮጵያዊ ጥበብ እንዲሁም ኢትዮጵያ የወደፊቱን ቴክኖሎጂ ለመጨበጥ ያላትን ፍላጎት” የሚያሳይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሙዚየሙ ውስጣዊ ክፍል ወደ 1400 ሜትር ስኩየር ስፋት ያለው ድምጽ የማያስተላልፍ ቋሚ እና ጊዜያዊ የአውደ ርዕይ ቦታዎችን የያዘ ሲሆን፣ሙዚየሙ ካረፈበት ቦታ 80 በመቶ የሚሆነው መሬትም ከአራት ሺህ በላይ አገር በቀል እጽዋትና ውብ አበቦች የተሸፈነ ነው። በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራም አለው። በተጨማሪም ሙዚየሙ ከተፈጥሮ ጋር በማይቃረን መልኩ የታነጸ ሲሆን፣የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘውም ከፀሐይ ብርሃን ነው።
የመጀመሪያው ትዕይንት
በሙዚየሙ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም የፈጠራ ባለሙያዎች በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በተጨማሪም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አዳዲስ ይፋ የሚያደርጓቸውን የፈጠራ ሥራዎች እንዲሁም ቴክኖሎጂ ነክ ጉዳዮች ለእይታ ለማቅረብ ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል። በተለይ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለመፍጠር ይህ ስፍራ እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ይታመናል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ሙዚየሙ እንደተመረቀ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሳይንስ ሙዚየም ውስጥ ምርትና አገልግሎቶቹን አቅርቦ ነበር።
በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ በተከፈተው የሳይንስ ሙዚየም ውስጥ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያቀረባቸውን የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን ለጎብኚዎች ክፍት አድርጎ በርካቶች ተመልክተውታል፡፡ኢመደአ ይዞ ከቀረባቸው ምርትና አገልግሎቶች መካከል “የኢመደአ አገልግሎቶች – INSA Service” አንዱ ሲሆን፣በዚህም ኢመደአ ለተለያዩ ተቋማት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች፤ የሳይበር ደህንነት ፍተሻና ግምገማ፣ የሳይበር ደህንነት አስተዳደር፣ የሳይበር ደህንነት የኦንላይን ትምህርት (e-learning)፣ የአጭር ሞገድ ራዲዮ፣ የጸረ ስለላ ቴክኒካል አገልግሎት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ሌላው ኢመደአ ይዞት የቀረበው በተቋም አቅም የተመረተና ከአገልግሎት ጥራት፣ ከዋጋ፣ ከፍጥነት እና ከአጠቃቀም አኳያ ምቹ የሆነ የሰርቨር ምርት ነው፡፡ በተጨማሪም በተቋም ደረጃ የሚገኝ የ “PCB – printed circuit board” ለዐውደ ርዕይ ቀርቧል፡፡
የሳይበር ታለንት ልማት ፕሮግራም በኢመደአ ዐውደ ርዕይ ላይ ሌላው ለእይታ የቀረበ ነው፡፡ በዚህም በኢመደአ የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል ውስጥ ታቅፈው የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ለእይታ ያቀረቡ ታዳጊ ወጣቶች በዐውደ ርዕዩ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በሌላም በኩል የሰው አልባ አውሮፕላን ምርምርና ልማት እንዲሁም አገልግሎት፣ የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ሥራዎች፣ የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ አገር በቀል ምርቶች፣ የደመና ማልማት ፕሮግራም ወ.ዘ.ተ በኢመደአ ዐውደ ርዕይ ላይ የቀረቡ ሌሎች ተቋማዊ ምርትና አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ኢመደአ በሳይንስ ሙዚየም ካቀረባቸው ምርትና አገልግሎቶች በተጨማሪ ጎብኚዎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊናቸውን ለመፈተሽ የሚያስችላቸው የተለያዩ አዝናኝ ውድድሮችን (cyber awareness & hacking games) አካቶ ቀርቧል፡፡
እንደ መውጫ
ዓለም በቴክኖሎጂው ዘርፍ እጅግ የረቀቀና የዘመነ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሉላዊነት የፈጠረው ትስስር ቴክኖሎጂ በፍጥነት እንዲያድግና ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የበራችን ደጃፍ የቀረቡን ያህል እንዲሰማን እደረገ ይገኛል። ምድራችንን ይፈትኑ የነበሩ ውስብስብ ችግሮች አሁን ላይ በቴክኖሎጂ አስደናቂ የፈጠራ ውጤቶች መፍትሔ እያገኙ ነው። ሃገራት የንግድ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች መሰል ትስስሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ (በይነ መረብ) ያደርጋሉ። ይህ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ከፍተኛ ወጪንና የተዛባ አሠራርን ከማስቀረቱም በላይ ደህንነትንና አስተማማኝነትን ያረጋገጠም ነው። በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ምርምር በሰው ልጅ አቅም የማይታሰቡትን ሁሉ እንዲተገበሩ፣ ረቂቅና ሚስጥራዊ የሆኑ ትንግርት የሚመስሉትን እውን እንዲሆኑ ያስቻለ ነው።
ኢትዮጵያም በዚህ ሰፊ የቴክኖሎጂ ባህር ውስጥ መልህቋን መጣል እንድትችል ወጣቱ ትውልድ እራሱ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ምቹ አጋጣሚ እንዲፈጠርለት ይሻል። እንደ ሳይንስ ሙዚየም አይነት የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ሌሎች ድጋፎች ደግሞ ሂደቱን በእጅጉ እንደሚያፋጥኑት ይታመናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/ 2015 ዓ.ም