አዎን አንድ ዓመት ነገ ነው። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደው የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ መርሀ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ይከናወናሉ ያሏቸውን ስራዎች ይፋ አድርገዋል፤ ስለተፈጻሚነታቸውም እርግጠኛ ሆነው በሙሉ ልብ ለህዝብ ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መድረክ ላይ በኢኮኖሚው መስክ፤ በመጪው መስከረም ወር ብሔራዊ ሙዚየም ለመላው ኢትዮጵያዊያን ከአስደሳች ስራዎቹ ጋር ክፍት ሆኖ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆን፤ ከመስከረም እስከ ወዲያኛው መስከረም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አበባ የማድረግ ስራው አንድ አራተኛ ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ፤ በትናንሽና መካከለኛ መስኖ በዚህ ዓመት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የተሻለ ስራ እንደሚሰራ፤ የማዕድን ዘርፉም ጎልብቶ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከፍ እንደሚያደርጉ ከፍ ያለ ቃላቸውን ለህዝብ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቃላቸው ይህ ብቻ አይደለም፤ በፖለቲካው መስክም በተመሳሳይ በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተጀመረውን ለውጥ በደንብ መሬት አስረግጠው ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል አይን የሚያገለግሉ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚሰሩ እነሆ ቃሌን ሲሉ ቃል ገብተዋል። የህግ የበላይነትን በሚመለከትም የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስቀጥለው እያንዳንዱ ዜጋ ከጥቃት ነጻ የሚሆንበትን ህጎች ሊያረቁና ሊያሻሽሉ፤ ፍትህንም ዜጎች ከፍርድ ቤት እንዲያገኙ የሚያደርግ ስራ ይሰራል ብለዋል። ህዝብም ይሁን! ይደረግ! ብሏል።
የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ብቻ ሳይሆን ባሉበት እንዲጠናከሩ መንግሥት ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ይሰራል፤ ምርጫው ፍጹም ነጻና ዴሞክራሲያዊ በማድረግ ዳግም ለአፍሪካ አዲስ ትምህርት ለመስጠት አርአያ የምንሆንበት ስራ እንሰራለን ሲሉ ተስፋቸውን አጋርተው ቃላቸውን እነሆ ሲሉ ሰጥተዋል። ህዝብም ተቀብሏል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ተግባር ይሆን ዘንድ አንደኛ እና ሁለተኛ ኃላፊነቱ የእርሳቸውና የመንግሥታቸው ነው። ይሁን እንጂ ሶስተኛው ባለድርሻ ህዝብና ያገባኛል የሚለው ብዕሩንም አንደበቱንም ለትችት የሚያሰላው አካል ሁሉ ነው ብለን እናምናለን።
“በአንድ እጅ አይጨበጨብም”፤ “አንድ እንጨትም አይነድም” ነውና ብሂሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ብቻቸውን ምንም ሊፈይዱ አይችሉም። እርሳቸውም እንዳሉትም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለ ህዝብ ምንም ነው። ስለሆነም ቃሉ የእርሳቸው ይሁን እንጂ ስራው የጋራ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቅና በዚያ አግባብ ሊሰራ ይገባል። ቃል የእምነት እዳ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ይፈጸም ዘንድ መንግሥት ተግቶ መስራት የግድ ይለዋል። ህዝብ ከዚያች ቀን ጀምሮ እለቱን ይቆጥራል፤ ምን ቀረ? ምን ተሰራ? እያለ መጠየቁ አይቀርም።
አንድ ዓመት ነገ ነው። እንኳንስ “እሰራልሀለሁ” ተብሎ ይቅርና ይሰራልኝ እያለ የሚሞግት ማህበረሰብ በተፈጠረበት አገር ላይ ምንምሳይሰራ በቃላት ጨዋታ ብቻ ሸንግሎ የሚታለፍበት ጊዜ አክትሟል። አመርቂ ስራ ካልተሰራና ህዝብን ማርካት ካልተቻለ አንድ ዓመት ድረስም መቆየት እንደማይቻል ህዝብ በተግባር አሳይቷል፤ ከለውጡ በፊት የነበረው ኢህአዴግና ታሪኩ ለዚህ እማኝ ነው። ስለሆነም መንግሥት ሆይ! የመጣኸው ከምትሄደው ያነሰ፤ የምትሄደውም ከመጣኸው የሚበልጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በውል ተረዳ። የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጥክም ጭምር ቃል የተገቡትን በጊዜ መስራት እንዳለብህ አትዘንጋ። ቃል የተገቡት በተግባር ካልተደገፉ ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ የተቀበሩ ቦንቦች መሆናቸውን ልብ በል።
ይህንን ማክሸፍ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድም “አንድ ዓመት ነገ ነው” በሚል መንፈስ በርትቶ መስራት ሲቻል ብቻ ነው። ህዝቡም “በይቅርታ እና በትግስት በሁሉም የአገሪቷ ጫፍ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እንደ ወንድማማች በጋራ እየዘመርን በማንግባባበት እየተወያያን ኢትዮጵያን የምናደምቅበት እንዲሆን ጥሪ አቀርባለሁ” በሚል የቀረበለትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል በአግባቡ ተረድቶ መተግበር ይጠበቅበታል። ይህንን ማድረግ ያልቻለ ህዝብና አክቲቪስት ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ቃል ገብተው ነበር የታለ ቃልዎ?” ብሎ ሊሞግት ሞራል አይኖረውም። ስለሆነም ህዝብም መንግሥትም አንድ ዓመት ነገ መሆኑን ልብ ሊሉና የየራሳቸውን ስራ ሊሰሩ ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011