አዲስ አበባ፡- ጥቂት የአሸባሪው ትህነግ መሪዎች ሥልጣናቸውን ለማስመለስ ሲሉ የትግራይ ህፃናትና ወጣቶችን በጦርነት በመማገድ እያስጨረሱ ይገኛሉ ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) መስራችና አማካሪ አቶ መኮንን ዘለለው ገለጹ፡፡
አቶ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሽማሌዎቹ የአሸባሪው ትህነግ መሪዎች ሥልጣናቸውን ለማራዘም ባላቸው ፍላጎት የትግራይን ወጣቶችና ህጻናት ለጦርነት እየማገዱ ነው የመጡት፣ አሁንም የቀረውን እድሜያቸውን ሥልጣን ላይ ለመቆየት የትግራይ ህፃናትና ወጣቶችን እያስጨረሱ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ማለት በሥልጣኔ የማያምን በሃይልና በጦርነት ብቻ ሥልጣን መያዝ የሚፈልግ ነው ያሉት አቶ መኮንን፣ መሪዎቹም የትግራይ ሕዝብን ሳይጨቁኑ መኖር አይችሉም ብለዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሓት ታፍኖ እየኖረ ነው ያሉት አቶ መኮንን ፣ ሕዝቡን ለህልውናቸው ጦርነት እየማገዱት ነው ብለዋል፡፡
የሚያሳዝነው ነገር የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ለጦርነት እየማገደ ያለው እና ንብረቱን እያጠፋ ያለው ለዚህ ቡድን መጠቀሚያ መሆኑ ነው ያሉት አቶ መኮንን ፣ የትግራይ ሕዝብ ከገባበት ችግር ሊወጣ የሚችለው ሕወሓት ሲጠፋ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አቶ መኮንን እንዳሉት፤ አሸባሪው ሕወሓት ሕዝብን ወደ ባሰ ዕልቂት እየመራው ይገኛል፤ ምክንያቱም ሕወሓት ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ል ምድ የለውም፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው ትግል የትግራይን ሕዝብ መጠቀሚያ በማድረግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ እንደረሳው የሚታወስ ነው ያሉት አቶ መኮንን፤ አሸባሪው ሕወሓት ያንን ታሪክ መድገም ነው የሚፈልገው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ትምህርት፣ ህክምና እንዲሁም ፍትህ እንዳይኖር እያደረገ ያለው አሸባሪው ሕወሓት ትግራይን መንግሥት አልባ በማድረግ በአሸባሪዎች እንዲመራ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ይህን ኃይል ካለበት ቦታ ለማስወገድ የትግራይ ሕዝብ ብቻ ኃላፊነት አይደለም ያሉት አቶ መኮንን ፣ የሁሉም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ከትግራይ ውጪ ያለው የትግራይ ተወላጅ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
አቶ መኮንን ፣ በተለይም ትግራይን ወክለን እየተንቀሳቀስን ያለነው የትግራይ ፖለቲከኞች ከትግራይ ውጪ ካለው የትግራይ ተወላጅ ጋር በመሆን ልቦናው ወደ እውነታው እንዲመለስ የማድረግ ሥራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
መሰረት ገ/ዮሃንስ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም