ከከፍተኛ ትምህርት በኋላ ስራ የጀመርሁት በ1988 ዓ.ም በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ የብሔረሰብ ዞን ነው። ለሶስት አመት ያህል የቋንቋና የታሪክ ባለሙያ ሆኘ አገልግያለሁ። በዞኑ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ላይ ወደ ደርዘን የሚጠጉ ጥናታዊ ጹሑፎችን አዘጋጅቻለሁ። አካባቢው ከትግራይ ባልተናነሰ የሕወሓት የትጥቅ ትግል ማዕከልና ነጻ መሬት ሆኖ አገልግሏል። ሕዝቡ በተለይ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ እነ ሀይሎምን፣ ተፈራን፣ በረከትን፣ ታምራትንና ሌሎች “ታጋዮች” ከቤተሰቡ እንደ አንዱ ያህል በደንብ እንደሚያውቃቸው ስረዳ እኔም የማወቅ ጉጉት አደረብኝና ጥናት ማድረግ ፈለግሁ።
ግን ደሞ የትጥቅ ትግሉ አንጎቨር ገና አልወጣምና ሌላ መዘዝ እንዳያመጣብኝ የማወቅ ጉጉቴ ላይ ሕጋዊ ካባ መደረብና ሽፋን ማግኘት እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ ፤ ለምሰራበት የባህል ቱሪዝምና ማስታወቂያ መምሪያ(ባቱማ) ፤”የዋግ ሴቶች የትጥቅ ትግል ተሳትፎ “ላይ ጥናት ለማድረግ የመነሻ ሀሳብ አቀረብሁ። መምሪያውም ወዲያው ፈቀደልኝ። እውነት ለመናገር የጥናቱን ርዕስ የመረጥሁት፤ የዛን ጊዜው ኢህዴን በኋላ ብአዴን የተባለው ድርጅት አስኳል ተደርገው የሚታዩትን ወ/ሮ ብርሃኔ አበራን(ማዘር ታጋይ)ቃለ መጠይቅ ለማድረግና ሽፋን እንዲሆነኝ እንጂ ማወቅ የፈለግሁት አጠቃላይ ስለትጥቅ ትግሉ ታሪክ በተለይ ደግሞ የዋግ ሕዝብ እንዴት የሕወሓት ደጋፊ ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄዬ መልስ ማግኘት ነው።
ለወራት በትጥቅ ትግሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት አላቸው የተባሉትን ሁሉ ቃለ መጠይቅ አድርጌ የተገነዘብኩት ግን ያልተጠበቀ ነበር። የዋግ ሕዝብ ሕወሓትን ይደግፍ የነበረው በደርግ ላይ ተስፋ ስለቆረጠና አማራጭ ስላጣ እንጂ ሕወሓትን ስለተቀበለ አልነበረም። ሕወሓት በ70ዎቹ ወደ አካባቢው ሲመጣ ሆ ብሎ የተቀበለውና የደገፈው አልነበረም። አካባቢዎን ደርግ ሲያስለቅቅ ልጆቹን አስገድዶ ትጥቅና ስንቅ አሸክሞ ወደ በርሃ ይወስዳል። ፈቃደኛ ያልሆኑትን መቀጣጫ እንዲሆኑ ይገላል። ቤተሰባቸውን ያሰቃያል። ሕወሓት መልሶ ደርግን አስለቅቆ አካባቢውን ሲቆጣጠር ደግሞ ነዋሪውን ደርግን ደግፋችኋል ብሎ ቁም ስቅላቸውን ያሳያል። ይደበድባል። በርሃ ወስዶ ተቆፍሮ መሬት ውስጥ በተሰራ /አንደር ግራውንድ/ እስር ቤት አስሮ ያሰቃያል። ይገርፋል። ይገላል።
ደርግ በለስ ቀንቶት አካባቢውን መልሶ ሲቆጣጠር ደግሞ ወያኔን ደግፋችኋል ያላቸውን በተራው ያሰቃያል። በዚህ አዙሪትና ምልልስ አሳሩን ያየው የዋግ ሕዝብ ደርግን እንዳይደግፍ ወያኔ ነገ ብትመጣ ብሎ ይሰጋል፤ ወያኔን እንዳይደግፍ ነገ ደርግ ቢመጣስ እያለ ሲወራከብና ሲወዛገብ ኖሮ ፤ ከአመት አመት ወያኔ እየተጠናከረች ስትመጣ ደርግ እንደማያስጥለው ሲረዳና ተስፋ ሲቆርጥ የቻለው ተሰደደ። ያልቻለው ግን ሳይወድ ተገዶ የወያኔ ደጋፊ ሆነ። አማራጭና ተስፋ ሲቆርጥ፤ ነጋ ጠባ በፕሮፓጋንዳ ሲቀጠቀጥ “ትግሉን” በስፋት መቀላቀል ጀመረ። የአልሻባብ፣ የቦኮሀራም፣ የሁቲ አማጽያን፣ የታሊባን፣ ወዘተረፈ ማህበራዊ መሠረት የተገነባው በዚህ አግባብ ነው።
ካርል ማርክስ ፣ “ታሪክ ራሱን ይደግማል፤ መጀመሪያ በአሳዛኝ በኋላ በአስቂኝ ሁኔታ፤” እንዳለው ፤ በትግራይ ይህ የዋግና የአካባቢው ታሪክ እንዳይደገም እሰጋለሁ። የትግራይ ሕዝብ ተስፋ እንዳይቆርጥብን በብርቱ እሰጋለሁ። ትግራዋይ ቀድሞም በደርግ ተስፋ ስለቆረጠና አማራጭ ስላጣ ነው ተገዶ የሕወሓት ደጋፊ የሆነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን አግቶ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው እስከማለት የደረሰው በዚህ አልፎ ነው። ዛሬም ተስፋው እንዳይሟጠጥ፣ እግር ከወርች ቀፍድዶ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ቀይዶና አፍኖ ፍዳ እያስከፈለው፤ እያስራበው፣ እያስራዘውና ልጆቹን እንደተኩላ ከጉያው እየነጠቀ የጥይት ማብረጃ እንዲሆኑ እየማገደ የወላድ መካን እያደረገው ካለ እፉኝት በማያዳግም ሁኔታ ነጻ ልናወጣው ይገባል ።
ከአንድም ሁለት ጊዜ ራሱን ነጻ የማውጣት እድል ቢፈጠርለትም በልኩ ተሳትፎ ማድረግ ስላልቻለ ሳይሰካ ቀርቷል። ሽብርተኛው ሕወሓት አሁንም ወደ ሰላማዊ ድርድር ለመምጣት እግሩን እየጎተተና ቅድመ ሁኔታ እየደረደረ ስለሆነ መንግስትንም ሆነ ኢትዮጵያውያንን አማራጭ እያሳጣ ስለሆነ የቀረው አማራጭ የትግራይን ሕዝብ ከዚህ አሪዎስ በኃይል ነጻ ማውጣት ነው። መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊ የትግራይ ሕዝብ ተስፋው ሳይሟጠጥ ሊደርሱለት እንደሚገባው ሁሉም ትግራዊ ደግሞ ለነጻነቱ ተባባሪና ተሳታፊ ሊሆን ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን ሚዲያው፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ አንቂዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ሌሎች የትግራዋይን ልብ ማሸነፍ ላይ የበለጠ በርትተውና ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል። በ97 በድምጽ፣ በ2010 ዓ.ም በሕዝባዊ አመጽ በዝረራ ያሸነፈ፤ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ተገዶ ቢሆንም በጦርነት የረታና እየረታ ያለ፤ እንኳን ሰውና ወፍ የሚያለምድ ሕዝብ የትግራዋይን ልብ በደም ከጨቀየው የሕወሓት እጅ ፈልቅቆ ነጻ ማውጣትና ማሸነፍ አይከብደውም። ይሁንና ራሱን ችሎና አቅዶ መስራትን ይቀጥላል። ጦርነቱን ለ3ኛ ጊዜ አሸንፈን የትግራዋይን ልብ ማሸነፍ ካልቻልን ድሉ እንደቀደሙት የተሟላ አይሆንም።
የሕወሓትን የጸረ ሽብር ትግል በአውደ ወጊያ በሚቀዳጁት ድል ብቻ አይረጋገጥም። የአሸባሪው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሆነውን ሕዝብ ልቦና እና አመለካከት ከወዲሁ መማረክ ግድ ይላል። አሸባሪውን ከሕዝብ የመነጠል የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል። አሜሪካ ለ20 አመታት ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገፍግፋ በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ሰውታና አካል ጉዳተኛ አድርጋ በባዶ እጇ አጨብጭባ ተሸንፋና ተዋርዳ የወጣችው የአፍጋኒስታውያንን ልቦና ማሸነፍ ባለመቻሏ ነው።
የግንባሩን አውደ ውጊያማ ከ20 አመት በፊት ታሊባንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ አሸንፋ ነበር። በቬትናም የሆነውም ተመሳሳይ ነው። በኢራቅ በሶሪያ በሶማሊያ በየመን በሊቢያ በናይጀሪያ በማሊ በሞዛምቢክ ወዘተረፈ….. አሸባሪዎችን በቀላሉ ማሸነፍ ያልተቻለው ለዚህ ነው። አሸባሪዎችን በጦርነት ለማንበርከክ ከሚደረገው ፍልሚያ ባልተናነሰ ርዕዮተ አለማቸውን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ከሚጠቀሙበትና በአካልም በስነ ልቦናም ካገቱት ሕዝብ ማውጣትና ማጽዳት ይጠይቃል።
በአሸባሪው ሕወሓት ላይ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ የተቀዳጀነውን አንጸባራቂና በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተዋጀውን ድል ማጽናት ያልቻልነው የትግራዋይን ልቦና በቅጡ ባለመማረካችን ነው። አሁንም የማይቀረውን ወታደራዊ ድል ለማጽናትና ለማዝለቅ ከወዲሁ የትግራዋይን ልብ በማሸነፍ ልናጅበው ይገባል። ይበል የሚያሰኙ ሕዝባዊ ውይይቶችና ሌሎች ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ከሸኔ ከጉምዝና ከሌሎች አሸባሪዎችና ሽፍቶች ጋር የምናደርገውን ትግልም እንደዚሁ። በይፋ ባንገነዘበውም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያውያንን በተለይ ደግሞ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ ብዙ ጥረዋል። ዋጋም ከፍለዋል።
ለሰላም ካላቸው ቁርጠኝነትና ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በውትድርና ሕይወታቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት፤ ጓደኞቻቸውንና ወንድማቸውን ስለ ነጠቃቸው፤ ጦርነት የአገርን ኢኮኖሚ ምን ያህል እምሽክ ድቅቅ እንደሚያደርግና እንደሚያወድም አበክረው ስለተገነዘቡና ፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ይበቃዋል በሚል ጽኑ እምነትና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች የድሀን ልጅ የእሳት ራት ያደርጋሉ እንጂ እነሱ አይዋጉም በማለት ለትግራይም ሆነ ለሌሎች ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ እስከ መጨረሻው ሰዓት ሆደ ሰፊነትንና ትዕግስትን መርጠዋል።
አበው “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንዲሉ በከሀዲውና የእናት ጡት ነካሹ በሆነው ትህነግ መከላከያችን፣ ሉዓላዊነታችን ፣ አገራችንና ሕዝባችን ለሰላም በታመኑ ከጀርባ ተወጉ። ባጎረሱ ተነከሱ። አሸባሪው ሕወሓት በእብሪት በጫረው እሳት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፋ፤ አካል ጎደለ ፤ የአገር ኢኮኖሚ ክፉኛ ደማ፤ የሽብር ኃይሉ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማቶች መልሶ ለመጠገን ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆነ። ልብ አርጉ ይህ ወታደራዊውን ወጪ አይጨምርም። ጥገና ሲያካሒዱ የነበሩ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በግፍ ተገደሉ። ይህ የትግራዋይን ልብ የማሸነፍ ጥረት አካል ነበር።
መንግስት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀውም ለዚሁ ሰናይ አላማ ነበር። አሸባሪው ሕወሓት ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የትግራይ ክልሎችን በመውረር በአፋር ፈንቲ ረሱ ዞን በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ፤ በራያ ቆቦ አጋምሳና በሌሎች አካባቢዎች ንጹሐን በመግደል አስገድዶ በመድፈር በመዝረፍ ግፍ መፈጸሙ ሳያንስ የቤት እንስሳትን በጥይት በመደብደብ ጥረቱን ዋጋ አሳጥቶታል።
ጠቅላይ ሚንስትር አገሪቱን ከጠብ መንጃ አዙሪት ለማውጣትና ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች ያልሄዱበትን የሆደ ሰፊነትና ቁጭ ብሎ የመነጋገር አዲስ መንገድ በመምረጣቸው በልኩ እውቅና ሊሰጣቸውና አብዛኛው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ሲገባ መንግስታቸው በልፍስፍስነት ከመወቀሱ ባሻገር ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ደጋፊያቸውና ተከታያቸው ብዥታና ድንጋሬ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የትግራዋይን ልብ ለመማረክ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ግንዛቤ አልተያዘም።
ይሁንና የእፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24ቱን ታላቅ ክህደት ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የአገር ህልውናን ለማስቀጠል ያሳዩት ቁርጠኝነት እና ሰራዊቱ ከተፈጸመበት ታሪክና ትውልድ ይቅር ከማይለው ክህደት በኋላ ሞራሉና ወኔው አንሰራርቶ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ እጅን በአፍ የሚያስጭን አንጸባራቂ ድል በማስመዝገቡ አገራዊ ሞራሉ እንዲያንሰራራ አድርጓል። እፉኝቱ ትህነግ ይታበይበትና ይመካበት የነበረውን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ በሶስት ሳምንታት ውስጥ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም መቐለ ሊገባ ችሏል። ለዛውም እጅ የመስጫ የመጨረሻ ቀነ ገደቡን ጨምሮ ስድስቱ ቀናት ሳይታከሉ።
በነገራችን ላይ ይህ ሕግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ሶስት ግንባሮች አሉት። የመጀመሪያው ከእፉኝቱና ከሀዲው የአሸባሪው ሕወሓት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀሰተኛ፣ የተዛባና በሴራ ኀልዮት የተለወሰና የተበረዘ መረጃ ከሚነዛው የትህነግ መደበኛና ማህበራዊ (ዲጂታል ወያኔ) ሚዲያ ጋር ነው። ስለ ሁለት ግንባሮች በቀጣይ መጣጥፎች በዚሁ ጋዜጣ በቅርቡ ዳግም እመለሳለሁ። ሶስተኛው ግንባር ደግሞ ትህነግ ላለፉት 50 አመታት በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ በስሙ ሲነግድበት፣ ሲምል ሲገዘትበትና በፈጠራ ትርክት፣ በአስገድዶ ማጥመቅ (ኢንዶክትሬሽን) እና በፕሮፓጋንዳ ያለ ፈቃዱ ሲወቀር የኖረውን የትግራዋይ ልብ የመመለስና የመማረክ ግንባር ነው። ይህ ከሁለቱ ግንባሮች ባልተናነሰ ጽናትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ማጤን ያሻል።
ከአሁኑ ትግራዋይን ከአሸባሪው ሕወሓት የመነጠል፤ አመለካከቱንና ልቡን የማሸነፍ ስራዎች ጎን ለጎን መሠራት አለባቸው። አሁንም ጦርነቱን ብቻ ማሸነፍ ድሉን ሙሉ ስለማያደርገው የትግራዋይን ልብ ማሸነፍና ማሳመን የጦርነቱ ስትራቴጂ አካል መሆን አለበት። ፈጣሪ ከብልቶቻችን ሁሉ ያስቀደመው ልባችንን ነው። እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሁሉ አንድ የሕግ አዋቂ ፈጣሪን ሊፈትነው፤ “መምህር ሆይ ፥ ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ” ፈጣሪም በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ማቴዎስ 22 ÷ 37 -38 ላይ እንዲህ ሲል ይመልስለታል ፤ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።”
በዚህ ታላቅና ቀዳሚ ትዕዛዝ እየሱስ ክርስቶስ ከነፍስም ሆነ ከአሳብ በፊት ልብን እንዳስቀደመ እንረዳለን። የ32ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የፍራንክሊን ዴሎን ሮዝቬልት ባለቤትና ቀዳማይ እመቤት ኤሌንኖር ሮዝቬልት፤ ሮዝቬልትን ጨምሮ የበርካታ ፕሬዝዳንቶች አማካሪና ሊቅ የነበረውን በርናንድ በሩክ፤ “አእምሮየና ልቤ በሀሳብ ቢለያዩ ማንኛውን ልከተል!? ” ስትል ትጠይቀዋለች፣ እሱም ያለምንም ማወላወል፣” ልብሽን ተከተይ” ሲል ይመልስላታል። እነዚህ መንፈሳዊና አለማዊ ዋቢዎች ልብ በሰው ልጅ ዘንድ ያለውን ከፍ ያለ ስፍራ ያሳያል።
እንደ መውጫ
አሸባሪው ሕወሓት እንደ ሰብዓዊ ጋሻና እንደ መደበቂያ የሚጠቀምበትን የትግራዋይ ልብና አመለካከት ማሸነፍ ሳይቻል ወታደራዊ ድሉ ምሉእ አይሆንም። በጦር ሜዳ የሚገኘው ወታደራዊ ድል የትግራዋይን ልብና አመለካከት በማሸነፍ ካልታጀበ የአሸባሪው ሕወሓት መደምሰስ ብቻ ድሉን ዘላቂና አስተማማኝ አያደርገውም ። የኢፌዴሪ መንግስት ከጦርነቱ ባልተናነሰ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ የተግባቦት ስልት ነድፎ ሌት ተቀን መስራት አለበት።
ደጀኑን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ለማነቃነቅ እና የአሸባሪው ሕወሓትን ጭካኔና አገር የማፍረስ ደባ ለማጋለጥ እየሰራው ባለ ልክ የትግራይ ሕዝብን ለመማረክም በአግባቡ መንቀሳቀስ አለበት። ለ50 አመታት ያህል እንደ መዥገር ደሙን ከሚመጠው፤ የወላድ መካን ካደረገው ፤ በአንድ ለአምስት ጠርንፎ በአፈናና ጭቆና ባሪያ ካደረገው ፤ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ደም እያቃባው ካለ ፤ በስሙ እየማለና እየተገዘተ የቡድናዊ ጥቅም ማሳደጃ ካደረገው ፤ ወዘተረፈ……. ይልቅ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት በፍቅር በሰላም በነጻነትና በአንድነት የመበልጸግ አቅምና ተስፋ እንዳለው ፤ ለአሸባሪው ሕወሓት ግለኛ ጥቅም ሲባል ልጆቹ ከጉያው እየተነጠቁ ለጦርነት እንደማይማገዱ ፤ የትግራዋይ እጣ ፈንታ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመስዋዕትነት የተሳሰረና የተገመደ መሆኑን ደጋግሞና በጥበብ አዋዝቶ በመግለጽ ልቡንና አመለካከቱን ማሸነፍ አለበት።
በስሙ እየማለና እየተገዘተ ለ30 አመታት አገርንና ሕዝብን በጠራራ በአደባባይ እየዘረፈ ራሱን ሲያበለጽግ እሱን ከድህነት አረንቋ ከሴፍቲኔትና ከተረጅነት ነጻ እንዳላወጣው ፤ አንድ ጊዜ ዐቢይ ሊያንበረክክህ ነው ሌላ ጊዜ አማራ ሊያጠፋህ ነው እያለ፤ በተሳሳተ ትርክትና ቁጭት ሲያታግለውና ሲማግደው የኖረው፤ ከተደቀነብህ አደጋ የምታደግህ እኔ ብቻ ነኝ የሚለው ለግል ጥቅሙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን ደጋግሞ ማጋለጥ ያስፈልጋል ።
የትግራይ ሕዝብ መጻኢ እድል ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ነው !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015