በቅርቡ በአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ የተመረቀው የሳይንስ ሙዚየም ትውልዱ ከዘመን ጋር የሚያስታርቅ፤ሀገርንም ወደፊት ከዘመን ጋር የምታደርገውን ጉዞ የሚያሳልጥ ማለፊያ ተግባር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ውስጥ መጪውን ጊዜ ባለመ መልኩ የሚሰሩ መሰል ፕሮጀክቶች ተጠናክረው መቀጠልም ይኖርባቸዋል።
በማደግ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ እድገትዋ ፈጥኖ፤ ብልፅግናዋ ተረጋግጦና ህዳሴው እውን ይሆን ዘንድ ዛሬ ላይ ተገንብተው ነገዋን ብሩህ የሚያደርጉ መሰል ስራዎች ላይ ጠንክሮ መስራት ተገቢ ነው።በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጣሉ አሻራዎች በማንም ተሰሩ አልያም ማንም አቅዶ አሻራውን አሳረፈባቸው ውጤቱ የሀገር ለውጥ ነውና በበጎነት መመልከትና ለዚያም የራስን በጎ ሚና መጫወት ይገባል።
በጥረት የሰሩትን ማድነቅ በትጋት የለፉበትን እውቅና መስጠት ደግሞ ከእኛ የሚጠበቅ የመልካም ስራው ክፍያ ነው።ከተቻለን በእያንዳንዱ ጥረት ውስጥ የራሳችን ሚና በተገቢው መልኩ መወጣት ይገባል።እንደ ዜጋ ለሀገራዊ ግንባታውና የህዳሴው ጉዞ ይሰምር ዘንድ የየራሳችንን ጠጠር መወርወር ግዴታችን ነው።
ነገር ግን ከዚህ በተፃራሪ ቆሞ የሰሩትን ማንተብ የገነቡትን ማንኳሰስ ከተገቢነት የራቀና የተንሸዋረረ እይታ ነው። አንድ የሚያስማማን የጋራ ነጥብ ወይም ጉዳይ አለ። ያም በጎና መልካም ነገር ለሁሉም ሁሌም መልካም ነው። በጎን መጥፎ ነው ብሎ ማሰብ አልያም ብርሀንን በጭለማ መስሎ ማቅረብ ግን ከትክክለኛነት መራቅ ነው።
ጉዳዮችን አንስቶ የዚያ ጉዳይ የተሻለ አተያይ ወይም እሳቤ በወጉ ማቅረብ ተገቢ ነው።በእርግጥ አንድን ተግባር ተመልክተን ወይም ስራውን ተረድተን የዚያ ተግባር የተሳሳተና ሊታረም የሚገባው ነገሩን መጠቆም ችግር የለውም። የሚያስተዛዝበው ጥሩን ተመልክቶ አለማድነቅ ለመልካም ተግባር እውቅናን መንሳት ነው።
እርግጥ ብዙዎች ጭለማው ገዝፎ ስለሚታያቸው ወይም ሆን ብለው የደመቀውን ብርሀን ላለማየት ሲሞክሩ ታዝበናል። ከዚህ በፊት በነበሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ጅማሮ ላይ ብዙ የማጥላላት ሀሳብ ሲዘነዝሩ ቆይተው ውሎ አድሮ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሲመለከቱ የቀድሞ ትችታቸው ወደ ዝምታ ለውጠውታል። የተሰራው ነገር አፍ አውጥቶ ገዝፎ እዩኝ የሚል ነበርና እራሳቸው እንዲታዘቡ አድርጓቸዋል።
ያኔ መስቀል አደባባይ ላይ በተሰራው አስደናቂ የገፅታ ለውጥ ስራ ያልተደሰተ፤ የነበረውን የተሰላቸ ገጽታ መቀየር ያልወደደ፤ ለተጠቃሚው ምቹ ለሀገር ገፅታ ግንባታ ለመዲናዋ ሌላ ድንቅ ውበት መሆኑን ያላመነ ግለሰብ ወይም አካል ኢትጵያን እወዳለሁ፤ለውጥዋን እፈልጋለሁ ሊል እንዴት ይቻለዋል። ሳይንስ ሙዚየምን ተመልክቶ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ ያልታየው ሰው የዚህ ሀገር ዜጋ ነኝ ቢል እንዴት ይታመናል።
ወደፊቱን የሚያስብ ዛሬ ላይ አሻራውን ያኖራል። እዚህም ሀገር ላይ እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ነገ ኢትዮጵያ ታላቅ እንድትሆን በየመስኩ ወሳኝ የሆኑ መሰረቶች ይጣላሉ። የሸገር ፓርኮችን መሰራት የተቃወመ፤ የመናፈሻዎች መደልደል ለተጠቃሚ ምቹ መሆን ያልተመቸው፤ የሸገር ጎዳናዎች ማማር ለተጓዦች ምቹና ፅዱ መሆን ያላስደሰተው ኢትዮጵያዊ ስለዚህች ሀገር መልካም መሆን ቢያስብ ስለ ህዝቡ ያገባኛል እያለ ቢሞግት ማን ሊሰማው ይችላል? መልካም የሰሩትን ማበረታታት ቢያቅት እንዴት ዝምታ ከእኛ ይጠፋል፤የራስን በጎ ሚና አለመጫወትና በበጎው ተግባር አለመሳተፍ ከዚህም ባለፈ የተሳተፉትና ያለሙትን ማንኳሰስ ምን አይነት የተዛባ ሚዛን ነው?
ሀገርን የሚወድ ለሀገሩ መልካም ተግባር ይፈፅማል፤ሀገሬ የሚል ለኢትዮጵያ ብሩህ ህልም ያልማል፤በተሰማራበት መስክ ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል። ነገር ግን የቀረበንን ብሩህ ገፅታ ትተን አሻግረን ጭለማ መመልከት ካዘወተርን ግን ጤነኝነት አይመስልም። አንድ መልካም ስራ በመልካምነቱ አይተን ለዚያ ስራ ተገቢ የሆነ መልካም አተያይና አስተያየት መስጠት ደግሞ ጤነኝነት ነው።
በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እንደመገኘታችን በትጋትና በብዙ ጥረት ከስኬት ደርሰው ለምርቃት የበቁና ሂደታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደ ዜጋ መጠናቀቃቸውን ናፍቀን መጠበቅ መጠናቀቃቸውን ስናውቅ ለተሳተፉት እውቅናና ምስጋና ማቅረብ የጨዋ ዜጋ መለያ ባህሪ ነው።
ማንም በፖለቲካ አቋሙ እንቃወመው አልያም ፈፅሞ ከኛ ጋር የሚጣረስ ይሁን ነገር ግን በሌላው አካል የሚተገበር አልያም የሚሰራን ሀገር ሊጠቅም የሚችል ተግባር ላይ በተሳሳተ እይታ የመመልከት ምን ያህል ሞራል ሊኖረን ይችላል? አመለካከታችን ይህ ከሆነ የተሳሳተ መንገድ ላይ ነኝ ማለት ነው።
በጎ ነገር በማንም ተተገበረ በማን በጎነቱን ካልመሰከርን የቆምንበት ሚዛን ትክክለኛ መሆኑን ማመን ይከብዳል። መጀመሪያ ነገር እንደ ሀገር ለሀገሬ መልካም ተመኝቼ ከራሴ አልፎ ለሀገሬ የሚሆነውን በጎ ነገር ሁሉ ሊያስደስተኝ ይገባል ብለን ማመን አለብን።ያኔ ነው ሚዛኑ ትክክል የሚሆነው። ያ ነው እይታዬ ከራስ አልፎ ሀገሬ ከግል ጥቅምና ፍላጎቴ ባየለ ለወገኔ ማለት የምንጀምረው።ይሄ ነው የጥሩ ዜጋ መለያ ባህሪው።
አቅዶ በትጋቱ እና በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የሰራውን በጎ ስራ አለማድነቅ ብሎም አለማመስገን ያስኮንናል። ይህ አተያይ በፍፁም ስህተት ላይ ይጥላልም። በጎን ነገር ተመልክቶ የዚያን ተግባር በጎነት ከመጥቀስ ይልቅ በሌላ አሉታዊ መልክ መመልከት ከበጎ እሳቤ የመነጨ አተያይ ሊሆን አይችልም።በጎነት በራሱ የሚታደሉት በጎ ባህሪ ነው። በጎ አስተሳሰብ ብሩህ የሆነ ተስፋን ይወልዳል። ይሄን እንለማመደው።
የሃሳባችን ሀያልነት ማሳያው ሌላውን በመቃወም የእኛ ተቃራኒ የሆነ ሰው የተገበረውን መኮነን መሆኑን የምናምነው እስከመቼ ነው? የምናቀርበው የተሻለ ሀሳብና ልንተገብር የምናቅደው ሌላ አሸናፊ የሚያደርገን የተሻለ በጎ ነገር መሆኑን የምንረዳው መች ነው።
አንፀባራቂ የሆነ ገፅታ መፍጠር እንደምንችል ለማስረዳት ዛሬ ላይ በትጋት ሰርተው በጥረታቸው ያሳኩትን መንቀፍ ሳይሆን አብረናቸው ቆመን በማበረታታት ለሰሩትም እውቅና በመስጠት ነው። በየትኛውም አካል የሚሰራ ሀገራዊ በጎ ተግባር በጎ ነው። የእኛም ኃላፊነት በእኩል ስሜት መረዳትና ለዚያ በጎ ተግባር እውቅና መስጠት ነው።
ወገን ከትናንት የተሻለ ዛሬን ያሳየኝን ሳላደንቅ ከዛሬው የተሻለ ነገ እገነባልሁ የሚለኝን በምን ማሳመኛ ልቀበለው እችላለሁ? ዛሬን በትክክል አመላክቶኝ ለነገ የተሻለ ተስፋ የሚመግበኝ ነው ለኔ ግዝፈት የሚሰጠኝ። እኔ የሚኖርብኝ አተያዩ የተቃና ሀገሬ እና ህዝቤ የሚጠቀሙበትን፤ ነጋቸውን ለማሳመር የሚተጋውን ማድነቅ ነው።
ምን አልባት ሰዎችን በማሳሳት በጎን ስራ ተመልክተን ህፀፁን በማግዘፍ አልያም በተሳሳተ ምልከታ በመመልከት ለራሳችን ስውር አላማ በሚሆን መልኩ ማንኳሰስ ዛሬ እንችል ይሆናል። ያ ተግባር ግን መነሻውም በጎነት ውጤቱም መልካም መሆኑ አይቀርምና የምናፍረው በራሳችን ተግባር ይሆናል።
ሀገራችን ብሎም ከተማችን ላይ እየተሰሩ ያሉ ትላልቅ በጎ ተግባራት ተግባሪያቸውም አሳቢያቸውም የሚያስመሰግን መሆኑን መካድ ይከብዳል። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጠናቀው የተመረቁ ሂደታቸው ተፋጥኖ ወደ ምርት የተሸጋገሩ ፕሮጀክቶች ዜና መስማታችን ደስ የሚያሰኝ ነው።
አንዳንዶች በሰሙት መልካም ዜና አልተደሰቱም፤ የተሰራውን እያጥላሉ የተገነባውን እያንኳሰሱ ሃሳባቸውን በአደባባይ ሲገልጡ ሲታይ ለትዝብት ይዳርጋል። ለመልካም ስራ መልካም ያልሆነ አስተያየት ከየት የተለመደ ባህሪ፤እንዴት ያደገ ልምድ እንደሆነ መገመት ይከብዳል።እውቅና መስጠት የአዋቂነት ጥግ መሆኑን እንዴት ዘነጉት ?! ጎበዝ።
አንድ ዜጋ ለሀገሩ በጎ አለመስራት ባያስጠይቀው ሌሎች በጎ አልመው በትጋትና በተለዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ያሳኩት በጎ ተግባር አለማድነቅ ጤነኝነት ሊሆን አይችልም።መልካም ተግባርን ስናይ መልካም የሆነ አስተያየት መስጠት ከለመድን ኢትዮጵያ በመልካም ስራዎች ትደምቃለች። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015