“ዓደይ ሽኮር” – መቐለ፤
መቐለ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ መሆኗ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። የአጼ ዮሐንስ 4ኛ መንግሥታዊ መቀመጫ ሆና ከታወቀችበት ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ገደማ ጀምረን ዕድሜዋን ብናሰላ እንኳን ከአገራችን ቀደምትና አንጋፋ ከተሞች መካከል አንዷ እና ታሪካዊ ክብር የተጎናጸፈች መዲና መሆኗን እንገነዘባለን።
“ሰሜናዊት ኮከብ”፣ “አደይ ሽኮር”፣ “ብሌን ትግራይ” ወዘተ. እየተባለች በበርካታ የቁልምጫ ስሞች የምትጠራው ይህቺ ፍልቅልቅ የአገራችን ከተማ ዛሬ ደስታ ርቋት፣ ፈገግታዋ ጨልሞና እያንዳንዱ ቤተሰብና ነዋሪ በመሪር ልቅሶና እዮታ ሲያነባ መመልከት በእጅጉ ልብን በሀዘን ያናውጣል። የምግብ ብቻም ሳይሆን የሰላም ርሃብተኛ ከተማ ሆና መቆጠሯም ኅሊና ያለውን ሁሉ እረፍት የሚነሳ ክስተት ነው።
ሕወሓት በመቐለ ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈረደው “ይሙት በቃ” ይሉት ዓይነት ውሳኔ ነው። ቢቸግረን ራሱ ሲያስተዳድረው የኖረውን ክልል ጠቀስን እንጂ በአማራና በአፋር ክልሎች በተቀናጀ ጦርነት፣ በተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የመገንጠል አብሾ እየጋተ ባሳደጋቸው ተላላኪዎቹ አማካይነት የፈጸማቸውን ግፎች እንዘርዝር ብንል ገጹ ሊያስተናግድልን አይችልም።
የትግራይ ልጆች የትምህርት መሣሪያ ሳይሆን ክላሽ እንዲያግቡ መፍረድ በዛሬው ትውልድ ብቻም ሳይሆን በቀጣዮቹ ዘመናትም ድርጊቱ ሲኮነን የሚኖር ነው። ሌላው የአገሪቱ ክልል ስለልማት፣ ስለዕድገት፣ ስለተሻለ የውጤት ግብ እያቀደ ሌት ተቀን በሚሰራበት በዚህ ወቅት ሕወሓት ጦርነት እየለኮሰና ሕዝብ እያስጨረሰ ዕድሜውን ለማራዘም መሞከሩ ዞሮ ዞሮ የግፍ ብድራቱን እጥፍ አድርጎ እንደሚከፍል የገባው አይመስልም።
“የባሩድ ጠረን” ካልታጠኑ በስተቀር ህዋሳቸው የማይሰራው የአሸባሪው ብድን መሪዎች በምን ቋንቋ ቢገለጹ እኩይ ድርጊታቸውን በዝርዝር ለማሳየት እንደሚቻል እስከሚያስቸግር ድረስ ግራ ያጋባል። ለእናቶች ጩኸት ግድ የሌላቸው፣ ለአባቶች እምባ ቁብ የማይሰጡና የፈጣሪን ፍርድ የሚዳፈሩት የቡድኑ መሪዎችና ጀሌዎች ወደ ቀልባቸው እስካልተመለሱ ድረስ የትግራይ ምድር ይፈወሳል ማለት ዘበት ነው።
ስሜትን በሀዘን የሚያናውጠውንና በድቅድቅ ጨለማ የሚመሰለውን ይህንን የክልሉን ወቅታዊ መከራና የመቐለ ከተማን ጉስቁልናና ምድራዊ አሳር ባሰብኩ ቁጥር ፈጥኖ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው የነፍሰ ሔሩ ባለቅኔያችን የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን “እሳት ወይ አበባ” የሚለው የግጥም መድበል ነው።
“የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” በሚል ርዕስ ከቀረበው ተወዳጅ ግጥሙ ውስጥ ጥቂት ሀረጋትን ተውሻለሁ። በግጥሙ ውስጥ ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት “ሩቅ አልመው ቅርብ ያደሩት” ቴዎድሮስ እስትንፋሳቸውን በገዛ እጃቸው “እፍ ብለው” ከማጥፋታቸው አስቀድሞ የነበረውን አጭር የምጥ ቅጽበት በምናባዊ መነጽር ለማሳየት ታስቦ ነው።
“ልጆቼ” የምትላቸው ግፈኞቹና እብሪተኞቹ የሕወሓት መሪዎች በመላው ትግራይ፤ በተለይም በመቐለ ከተማ፤ እየፈጸሙ ያለውን ዘግናኝ በደል ለማሳየት ይረዳ ስለመሰለኝ ከግጥሙ ውስጥ ጥቂት ስንኞችን በመዋስ የዛሬዋን ሀዘንተኛ ከተማ ለመግለጽ ተጠቅሜበታለሁ። ስለተዋስኳቸውና ዐውዳዊ ትርጉም ስለሰጠኋቸው ስንኞችም የታላቁን የጥበብ መልሕቃችንን ብዕር
በማመስገን ስለ ችሮታው አክብሮቴን እገልጻሁ።
“ምነው! ምነዋ! ‹ዓደይ ሽኮር›፤ ኮከብሽን አጨለሙት?
እንደ ሬት ልግ አክስለው፤ እንደ ኮሶ አስመረሩት።
ከማኀጸንሽ እቅፍ ወጥተው፤ ከጡቶሽ እግት ጠብተው፣
ምነው እውነትሽን መግደላቸው፤ ፈገግታሽን አጨልመው።
በጥቀርሻ እንዳጀሉት፤ እንደ ወላድ ጣውንት ጡት፣
አርማ ጉሳ እንዳቀለሙት፤ ፈገግታሽን አጠቆሩት።
እምቢ በያቸው “አደይ”፤ ገፍትረሽ ወዲያ ጣያቸው፣
ለአንቺም ለአገር አይጠቅሙም፤ ከተመኙት “ሲዖል” ላኪያቸው። ”
“ሰነፍ ልጅ ለእናቱ ሀዘን ነው” ይላል፤ ቅዱስ መጽሐፍ። ይህንኑ ሃሳብ ሲያጠናክርም “ባለ አእምሮ ልጅ የወላጁን ተግሳጽ ይሰማል፤ የአመጸኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች” በማለት በግልጽ ቋንቋ ያስተምረናል። “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም” እንደሚልም ይሄው ቅዱስ ቃል አስረግጦ ይመሰክራል።
ጨካኞቹ ጥቂት የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች ወላጆቻቸውንና ሕዝባቸውን ላለመስማት ልባቸውን ማደንደን ብቻም ሳይሆን ፈጣሪን ለማወቅና ለመፍራትም ጭምር ኮሚኒስታዊው ስሪታቸው የፊጥኝ ተብትቦ ስለቀየዳቸው ምክርም ሆነ ተግሳጽ የሚሰማ ጆሮ የላቸውም። ለዚህን መሰሉ እብሪታቸውና ድፍን ኅሊናቸው ምስክሩ የአመጣጣቸውን ታሪክና ነባራዊውን የግፍ ድርጊታቸውን ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች ፍቅርን የማያውቁ፣ ዕርቅን የማይወዱ፣ ራሳቸውን የሚያመልኩ፣ ሐሜተኞች፣ ከዳተኞች፣ ስግብግቦች፣ በትዕቢት የተሞሉ፣ የንጹሐንን ደም በማፍሰስና በማስፈሰስ “እርኩስ ነፍሳቸው ሃሴት የሚያደርግ” መሆናቸው የባህርያቶቻቸው ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው።
የአገሪቱና የአፍሪካዊያን ዋና መዲና አዲስ አበባ፣ “ሀዋሳ ቤሌማ” እየተባለ የሚዘመርላት ደቡባዊቱ የፍቅር ከተማ፣ የጣና ተጎራባቿ ውቧ ባህር ዳር፣ “አቦ ጭንቅ አንወድም!” የሚሉ ነዋሪዎቿን በመተሳሰብ አስተቃቅፋ የምታኖረው ድሬዳዋ፣ የዜማ ቅኝቶቻችን መፍለቂያዋ ደሴ (የደስታ ምንጭ)፣ ታሪካዊቷ የነገሥታት መናገሻ ጎንደር እና ሌሎች የአገራችን በርካታ እህትማማች ከተሞች ለልማትና ለሥልጣኔ ቀን ከሌት እየተጉ የሕዝባቸውን ኑሮ ለመለወጥ ሲተጉ “አደይ መቐለ” ግን በሀዘን ጨርቅ ተጀቡና፣ በመንታ ጉንጮቿ ላይ እምባዋን እያፈሰሰች እንድትኖር የፈረዱባት እነዚያው የክፋት መልእክተኞቹ የአሸባሪው የሕወሓት ጉዶች ናቸው።
ከአሁን ቀደም ደጋግመን ለመግለጽ እንደሞከርነው እነዚህ የመከራ ማቅ ያለበሷት እፍኝ የማይሞሉ አሸባሪዎች እስከ ወዲያኛው እስካልተወገዱ ድረስ “የአደይ መቐለ” አበሳ ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ እረፍት ታገኛለች ለማለት ያዳግታል። “መቼ?” ለሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለመስጠት ቢያዳግትም አሸባሪ ቡድኑ ግን በቅርብ ጊዜ ግባ መሬቱ እንደሚፈጸም ለማመን አይከብድም።
መቐለ ከዐይኗ የሚመነጨው እምባ ደርቆ እያነባች ያለችው ቁልቁል ወደ ውስጧ ነው። አራት፣ አምስት፣ ስድስት ልጆቿን ለዓላማ ቢስ ጦርነት ተገዳ ያልሰጠች እናት፣ ዕለት በዕለት መርዶ ቤቷን ያላንኳኳ ወላድ፣ በማያምኑበት ጦርነት ተገደው አካል ጉዳተኛ ሆነው ለምጽዋት ልመና አደባባዮቿን የሞሉት የዚህች ከተማ ልጆች ቁጥራቸው ሺህ ምንተ ሺህ ነው። በአንጻሩ “እከሌ” ተብለው የማይጠሩትና ቁጥራቸው በውል የማይታወቀውን፣ ባልገባቸውና ባልተረዱት ጦርነት ውስጥ ተማግደው ያለቁትን እንቁጠር ከተባለም የሚሞከር አይደልም።
በአንጻሩ የሽብርተኞቹ መሪዎች ልጆች በየውጭ አገራቱ በምን ዓይነት መንደላቀቅ እየኖሩ እንዳለ ከአሁን በፊት ተደጋግሞ የተገለጸ ስለሆነ እነእከሌ ማለቱ ብዙም ፋይዳ የለውም። ሕዝቡን ወደ እሳት፣ ራሳቸውንና
ቤተሰቦቻቸውን ወደ እረፍት ሥፍራ እየነጠሉ ከወሰዱ በኋላ ባሕር ማዶ እየተንፈላሰሱ “ተነስ! ዝመት! ተዋጋ! ግፋ በለው!” እያሉ በመፎከር በወጣቱ ደም እጃቸውንና ነፍሳቸውን እያጠቡ ላሉት ጨካኞች ሕዝቡ እንደምን ትዕግሥት ሰጥቶ እንደሚሰማቸውና እንደሚታዘዛቸው ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል። እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመከራ የዳረጋቸውን ይህንን ኃይል ምን እስኪያመጣባቸው እንኮኮ ብለው እንደተሸከሙትም ግራ ያጋባል።
በዚህ ክፍል መቐለ ከተማ ተነጥላ ትኩረት የተደረገባት ሌሎች የትግራይ ከተሞች ተዘንግተው ወይንም መላው የክልሉ ክፍል የተረጋጋ ስለሆነ ወይንም ችግሩ ያለው በዋናዋ ከተማ ብቻ እንደሆነ ሊቆጠር አይገባም። የዋና ከተሞች የውክልና ጽንሰ ሃሳብ ከውስን ጂኦግራፊያው ክልል ሰፋ ብሎ ስለሚታይ ነው። ፖለቲካው የሚዘወረው በዋና መዲና መሆኑ፣ ሴራና አመጹ የሚጎነጎነውም እዚያው በዋና ከተማ ውስጥ ስለሆነ እንጂ “የመቐለ” ከተማን ጉስቁል ሕይወት መላው የትግራይ አካባቢና ሕዝብ እንደሚጋራ ተዘንግቶ አይደለም።
በአሸባሪው ሕወሓታዊ የጥፋት ሴራ ደማቅ ኮከቧ መደብዘዝ ብቻም ሳይሆን ብርሃኗ ጭል ጭል እያለ በትካዜ ውስጥ ያለችው ታሪካዊቷ ከተማ በቆራጥ ልጆቿ የትግል መስዋእትነት “የእኔ ከምትላቸው የእንግዴ ልጆቿ” መንጋጋ ነፃ እስካላወጧት ድረስ ፈጥና ታገግማለች ብሎ ለማሰብ ያዳግታል።
በተለይም ከፖለቲካው ጋር የወገኑት የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩትን የንስሃ ትምህርት ለራሳቸው ተግብረውና ተጸጽተው ለእውነት እስካለቆሙና አጥፊዎቹን በመገሰጽ አደብ እንዲገዙ እስካላደረጉ ድረስ ከፈጣሪ ፍርድ ስለማምለጣቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። “ተማርኩ” በማለት ብቻ በውስጡ ባልዘለቀው እውቀት እየተመጻደቀ ታሪክን በማዛባት ጊዜያዊ ትርክት በመፍጠር ኅሊናውን በመሸጥ ላይ ያለው “ምሁርም” ቆም ብሎ ራሱን ሊፈትሽ ይገባል።
የፖለቲካቸው ቀለብተኛ የሆኑት ካድሬዎቻቸውም በተጣመመ አይዲዮሎጂ ከናወዙበት “አራራ” ተላቀው ወደ ቀልብያቸው ሊመለሱ ይገባል። ከአሁን ቀደም የጠየቅነውን ጥያቄ ደግመን እንጠይቅ። ለመሆኑ የቅድስት ጽዮን ማርያም የማለዳ ደውል ምእመናንን የሚቀሰቅሰው ምን መልእክት እየተላለፈበት ነው? የትግራይ አድባራት ሱባኤና እግዚኦታስ በእርግጡ ምን የሚል ነው። “ቂም ይዞ ጸሎት፤ ሳል ይዞ ስርቆት” እንዲሉ፤ በእውነቱ ምልጃውና ኪራላይሶኑ ከፈጠሪ ዘንድ የጸሎትን መልስ ሊያስገኝ ይችላልን? በነጃሺ አዛን ውስጥ ወደ “ፈጣሪ” እንዲደርስ የሚላከው መልእክትስ በእርግጡ እብሪተኞቹ የጥፋት ኃይሎች ለሰላም እጅና ልባቸውን እንዲሰጡ ምን ያህል ግፊት ተደርጓል?
“የሃይማኖት ምድር” እየተባለ ቱሪስቶች ሲጎርፉበት ዘመናት ባስቆጠረው ክልል ውስጥ ሞት ሲረክስ፣ ግፍ ሲበረታ፣ እናቶች ደረት እየደቁ ሲውሉ የአገሬው ሽማግሌዎች ምን አሉ? ምንስ ብለው አጥፊዎቹን ገሰጹ? የትግራይ ሕዝብ በአንድነት ሰብሰብ ብሎ የዛሬንና የነገ ዕድሉን ያጨለሙትን “የራሱን ግፈኞች” በቃችሁ ለማለት እንደምን ተሳነው? በውጭ አገራት “የበሰለ እየገመጡ፣ የቀዘቀዘ እየተጎነጩ” ለሞት ድግስ ሕዝቡን የሚቀሰቅሱትንም እንዲሁ ምክራቸውን ከንቱ ሊያደርጉባቸው እንዴት ብርታት አጡ? “ከመፈቅፈቅ ማለቅለቅ” አሉ አበው። ሰላም ይሁን።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015