ትምህርት የአንድ አገር እድገት መሰረት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማው፤ የተሻለ አገርና ትውልድ ለማፍራት የሚተጋ፣ በፍትህ የሚያምንና ስለእውነት ዋጋ የሚከፍል ትውልድ በማፍራት ረገድ ትምህርት የማይተካ ሚና አለው፡፡ ለትምህርት ዋጋ ሰጥተው ትውልዱ ላይ መስራት የቻሉ አገራት በኢኮኖሚያቸውም ሆነ በአለም ፖለቲካ ልዕለ ሃያል መሆን ችለዋል፡፡
ዛሬ የዓለም የፖለቲካ መሪን እንዳሻቸው እያሽከረከሩ ለጥቅማቸው ሁሉንም ማንበርከክ የቻሉትም ትላንት የተማረ ኃይላቸው ላይ ምወለ -ንዋያቸውን፤ ጊዜያቸውን፤ አቅማቸውን ሁሉ ማፍሰስ በመቻላቸው ነው፡፡ አበውስ “ የዘሩት ይበቅላል” ይሉ የለ!? እነሱ የወደፊቱን አልመው ትላንትን በመልካም ዘር ምድራቸውን ቆፈሩ ዛሬ ደግሞ ጣፋጭ ፍሬያቸውን ሲያሻቸው በመሶብ ሲያሻቸው በአቁማዳቸው ይሰበስባሉ፡፡
እኛስ? እኛም ያው እንደለመድነው ሩቅ ናፋቂ ሆነን ቀርተናል፤ ትላንታችንን ከአረም ጋር አብረን አርሰን ዛሬ ምርቱን ከእንክርዳዱ መለየት ተስኖን መዳከራችንን ቀጥለናል፡፡ ሁሉ የሌላ ናፋቂ፤ ያልዘራውን ለማጨድ የሚሽቀዳደም ከንቱ ትውልድ ሆኗል፡፡ በአሸዋ ላይ እንደተሳራ ቤት የገነባነው ሁሉ እየፈረሰ እኛንም ጨርሶ ሊያጠፋን አቅማችን አሽመድምዶታል፡፡
የቆምንበት የእንቧይ ካባችንም እየተናደ መልሶ እኛኑ ይወግረን ይዟል፡፡ በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ተንሻፎ በተቀረፀውና ስራ ላይ በዋለው ትምህርት ምክንያት ጥቂት የማይባለው አገር ተረካቢ ትውልድ በእንጭጩ መክኖ ቀርቷል፡፡ ከላይኛው እስከታችኛው መንበረ ስልጣን ድረስ ሁሉ የአገር ሃብት በዝባዥ ሆኗል፡፡ ተርቦ ያጠገበውን የእናት ጡት ነካሽ ሆኖ የእናት አገሩን አካል አቁሱሏል፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቁ ‹‹ምን ሰርቼ ልደግ?›› ሳይሆን ‹‹ከምን? ምን ሰርቄ ልክበር?›› ባይ ሆኗል፡፡ ኧረ እንዳውም ሌባውን ከመፈለግ ይልቅ ሃቀኛውን መለየት ቀላል ሆኗል ብል ይቀለኛል፡፡
ብዙዎቻቹ ‹‹ሁሉንም በአንድ ቁና ሰፈርሽ!›› ብላችሁ እንደማትፈርዱብኝ ተስፋ አለኝ፤ ምክንያቴ ደግሞ እናንተም በአንድም ይሁን በሌላ የእዚህ እኩይ ፖሊሲ ጦስ ሰለባ መሆናችሁ ስለማይቀር ነዋ!፡፡ አንዳንዶቻችሁ በተገዛ ዲግሪ ተበልጣችሁ ስራ አልባ ሆናችሁ ዛሬም የልጅ ጡረተኛ ሆናችኋል፡፡ ሌሎቻችሁ በሰረቃችሁት ፈተና አልፋችሁ በያዛችሁት መዶሻ ፍትህን አዛብታችኋል፤ በጤና የመጣውን በሽተኛ ፤ በህይወት የነበረውን ህይወቱን ነስታችሁ ከሙታን ጎራ ቀላቅላችሁታል፡፡ ዛሬም የዚያ ብልሹ ፖለሲ ዳፋ ለትውልዱ ተርፎ በስርቆት የቆሸሸውን አካባቢ ለማፅዳት ፈተና ሆኗል፡፡
እርግጥ ነው፤ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ እጣ ፈንታ ያሳሰባቸው ግለሰቦች፤ ምሁራንም ሆነ የመንግስት ሰዎች ቆሻሻውን ለማፅዳት የየራሳቸውን መጥረጊያ አንስተው ስራቸው ጀማምረዋል፡፡ በተለይም የለውጡ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ የችግሩን ስር መሰረት ለማወቅ፤ በየስርቻው ተጋድሞ አላሰራ ያለውን ስርዓት ከአናቱ ለመቁረጥ ብሎም የተጣመመውን ትውልድ ለማቃናት ሲባል ያንን ወኔ ሰላቢ ፖሊሲን ለማስወገድ ደፋ ቀናቸውን ይዘዋል፡፡ በራሱ የሚተማመን፤ በእውቀት የታነፃና አገር ወዳድ ትውልድ ለማፍራት ።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ የፈተና ጣቢያ ይሰጥበት የነበረው አሰራር ተቀይሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲፈተኑ መወሰኑ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎች ከሃሰተኛ መረጃዎች፣ ከሐሰተኛ መልሶች እና ከሐሰተኛ የፈተና ወረቀቶች ራሳቸውን አግልለው ተረጋግተው እንዲፈተኑ ለማስቻል ያግዛልም ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በተለይም በዚሁ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዳይሰረቅ በጉዞ፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ባሉ እንቅስቃሴዎች ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እንኳን ፈተና ተሰረቀ ተብሎ የስንቱ ብርቱ ተማሪ ስነልቦና እንደተሰበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በመሆኑም ፈተና አውጥተናል የሚሉ አካላት ቢያወጡ በማሕበራዊ ሚዲያ እየለቀቁ ተማሪዎቹ ለቀጣይ ቀን እንዳይዘጋጁ በመረበሽ ውጤታቸውን ሲያበላሽ የነበረውን አሰራር ለማስወገድ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው ፈተና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ምንም አይነት የዲጂታል መሳሪያዎች እንዳይኖር የራሱን የቁጥጥር ስርዓት እንደዘረጋ ተስፋ አለኝ፡፡
አሁንም ቢሆን ግን በራሱ እውቀት የሚተማመንና ስርቆትን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት አሰራሩ በእውቀታቸውና በልፋታቸው ልክ ተማምነው እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ መሻሻል አንድ እመርታ እንደሆነ እምነቴ ነው፡፡
እንዲሁም ፀረ- ሕዝብ አቋም አንግበው የስርቆት ድርጊቱን የሚያራምዱም ሆነ፣ የተወሰኑ አካባቢዎችን ለመጥቀም በማሰብ የሚፈጸመውን ስርቆት፣ ሌብነትና ማጭበርበርን በፅኑ መከላከል ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ከማንም በላይ ደግሞ ሚኒስቴሩ ዋና ዓላማው የትምህርት ጥራት በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በትምህርት ቤቶች ጥረት እንዲረጋገጥ ማስቻል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንድን አካባቢ ለመጥቀም ታስቦ የፈተናውን ስርዓት ለመናድ የሚደረገውን እና ፈተናው ወጥቷል በሚል በማሕበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ተማሪዎች ውጤታቸው እንዲበላሽ የተደረገበትን አሰራር መቀየር /ማስወገድ/ የግድ ያስፈልጋል ፡፡
በዚህ ረገድ አዲሱ የትምርት ስርዓት በተለያዩ አካባቢዎችም የመንግስትን ሃላፊዎችና ስራ ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ አመኔታ የጎደለበት ክስተት በመስተዋሉ ወላጆች፣ ተማሪዎች እና መምህራን በውጤቱ ላይ አመኔታ እንዲያጡ በማድረግ መሰረታዊ ችግር የሆነውን አሰራር ለማረም ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡
ውሳኔው ተማሪዎች 12 ዓመታት የደከሙበትን የብሄራዊ ፈተና ተረጋግተው እንዲሰሩ፣ ለአገር ጠቃሚ፣ ለራሳቸውም እድገትን የሚያረጋግጡ ተማሪዎችን በውጤታቸው መዝኖ ለማሳለፍ የሚያስችል ነው፡፡
መንግስት የትምህርት ስርዓቱን ከመለወጥ ጀምሮ የቁጥጥር ስርአቱን ለማጠናከር እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የታሰበውና የታቀደው ሁሉ መሬት ላይ በማውረድ ረገድ ሁሉም የየበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይም ሁላችንም የዚህ ብልሹ ስርዓት ተገጂ እንደመሆናችን ሌብነትን የሚጠየፍ፤ በራሱ የሚተማመን ሃገር ተረካቢ ትውልድ የማፍራቱ ሂደት ከግቡ እንዲደርስ የየበኩላችን ጡብ ማስቀመጥ ይጠበቅብናል ፡፡
ነገ ለሚሆነው ሁሉ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ ማለት የማንችል መሆን ተገንዝበንም በሌብነት ባለመሳተፍ፤ ሌቦችን አጋልጦ ለፍትህ በመስጠትና ብርቱዎች የሚገባቸውን እንዲያገኙ በማገዝ ሚናችንን እንወጣ የዛሬው መልዕክቴ ነው፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2015