በሃሳብ ልዩነቶችን አምኖ፣ ተቀብሎ፣ ተቻችሎ መኖር ለእኔ ትልቅነት ነው። እነዚህ 27 ዓመታት ተዘርተዋል የምንላቸው ሃሳቦች አሁን ላይ ለመበጣበጣችን ምክንያት ሊሆን የቻሉት በአግባቡ ስላልተሰራባቸው ነው
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው እንዲውለበለብ ካደረጉ ታላላቅ አትሌቶች መካከል ነው። ከግል ጥቅሙ ይልቅ አገሩን በማስቀደም እስከህይወት የሚደርስ ዋጋ በመክፈሉ ይታወቃል። በማህበራዊ ህይወቱና ባለው መልካም ስብዕናም ብዙዎቹ በአርዓያነት ይጠ ቅሱታል። በ1976 ዓ.ም በትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ልዩ ስሙ ፀንቃኔት በሚባል አካበቢ ነው ተወልዶ ያደገው። ከባለቤቱ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ ጋር በትዳር 15 ዓመታትን አስቆጥሯል። የሁለት ልጆች አባት ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም። በወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- ዝግጅት ክፍላችን ላቀረብልህ ጥያቄ ፈጣንና ቀና ምላሽ በመስጠት ተባባሪ መሆንህን አስመስክረሃል። በቅርበት የሚያውቁም ትሁትና እና መልካም ሰው እንደሆንክ ይገልፃሉ። ይህ ከምን የመነጨ ነው ትላለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- አንድ ሰው በሚዲያ ከተፈለገ ከአንድ ሰው በላይ ሆኗል ማለት ነው። ይሄ ማለት ደግሞ ከእኔ የሚማር ሰው አለ ማለት ነው። ስለዚህ ማክበር አለብኝ። በሁለተኛ ደረጃ እኔ የምችለውን ያህል ለሰው ምቹ ለመሆን እጥራለሁ። በተረፈ ግን ሰው እንዲወደኝ ብዬ ለማስመሰል የማደርግው ነገር ግን የለም።
አደስ ዘመን፡- አሁን ላለው መልካም ስብዕናህ አስተዳደግህ ምን አይነት አሻራ አሳርፏል?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የገበሬ ልጅ ገጠር ነው ተወልጄ ያደግሁት። የገበሬ ልጅ ብሆንም የእኛ ቤተሰብ አስተዳደግ ትንሽ ለየት ይል ነበር። በተለይም በእኛ ቤት የእውነት ዋጋ ከፍተኛ ነው። አባታችን ስለእውነት ብለው ብቻቸውን የሚቆሙና የሚሞቱ ሰው ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ከአባታችን ጋር እናሳልፍ ስለነበር ያ ባህሪ በእኔ በሌሎች ቤተሰቦቼ ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጥሮብናል የሚል እምነት አለኝ። እናታችንም ብትሆን አሁን ላለው ማንነቴ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክታለች ብዬ አምናለሁ። ሁልጊዜም ቢሆን ሰው ቀና ብለን እንዳናይ እንድናከብር፣ የተቸገረ ካለ እንድንረዳ ኮትኩታ አሳድጋናለች። በተለይ ወንድ የሌላቸውን ጉረቤቶቻችንን በእርሻ ስራ እንድናግዝ ታደርገን ነበር። ከዚህ በበለጠ ደግሞ የኛን ቤተሰብ ከሌላው ይለየዋል ብዬ የማስበው እናታችን አልተማረችም፣ አትፅፍን፣ አታነብም፤ አባታችንም አልተማረም ግን ስሙን ብቻ መፃፍ ይችላል። በተመሳሳይ ታላቅ እህታችንም አልተማረችም፤ ግን በሚገርም ሁኔታ ሁልጊዜ ሀሙስ ሀሙስ በእህቴ ሰብሳቢነት የቤተሰብ የውይይት መድረክ ነበረን። በዚያ የቤተሰብ መድረክ የቀን ውሏችንን እንወያያለን፤ እንዴት ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር እንደምንችል እንመካከራለን። ይህ ደግሞ ያኔን ቀርቶ አሁንም በሌሎች ቤተሰቦች ላይ የማየው ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የልጅነት ህልምህ ምን ነበር? ወደ አትሌቲክስ እንዴት ገባህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ገጠር በመወለዴ ስራዬ ግብርና ይሆናል የሚል ነበር። ነገር ግን አንድ ጊዜ በሰማይ ላይ አውሮፕላን ሲበር ከተመለከትኩ በኋላ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። ይህንን በሰማይ ላይ የሚበር ግዙፍ አካል የሰራው የሰው ልጅ በመሆኑ እኔም ስለአውሮፕላኑ አሰራር ለማወቅ እጓጓ ነበር። አንድቀንም አበረዋለሁ ብዬ አልም ነበር።
ወደ ሩጫ የገባሁበት አጋጣሚ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ሳለሁ ትምህርት ቤታችን ለ20 ደቂቃ በእግር የሚኬድበት ስልነበር በየቀኑ እንዳይረፍድብኝ ስል እየሮጥኩ ነበር የምሄደው። በተለይ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል የተማርኩት በድሮ ስሟ «ሰንቃጣ» አሁን «ፍረወይኒ» በምትባለው ከተማ ነው። ስንሄድ አንድ ሰዓት፤ ስንመለስ አንድ ሰዓት ይፈጅ ነበር። ስለዚህ በየቀኑ ሁለት ሁለት ሰዓት በመሮጥ ነው የምደርሰው። ከዚያ የጀመረ ልምድ ታዲያ ሁለተኛ ደረጃ ከገባሁ በኋላም በሩጫ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አንደኛ ሆኜ አጠናቅቅ ጀመር። ከእዛ እያደገ መጥቶ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድሉን ማግኘት ቻልኩ።
አዲስ ዘመን፡- አንተ ከምትታወቅባቸው መለያዎች አንዱ ለአገር ያለህ ልዩ ፍቅር ነው። ከፍተኛ ጉዳት ውስጥ ሁነህ መርፌ ተወግተህ በለንደን ማራቶን መካፈልህ ነው። ይህ አጋጣሚ ከስፖርቱ እንዲርቅ አድርጎታል ይላሉ። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- የለንደን 2012 የግራ እግሬ ችግር አጋጥሞት ነበር። ወደ ሩጫው ከመግባቴ በፊት ለሁለት ሰዓታት የሚቆይ ማደንዘዣ መድሃኒት ነበር የተሰጠኝ። ይህ መድሃኒት ሀኪሞቹ ምንአልባትም እግሬን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ሊያደርገው ወይም ለሶስትና ሁለት ዓመት ከስፖርት ሊያርቀኝ እንደሚችል አስረድተውኛል። እንዳልሽው ግን በወቅቱ ለኢትዮጵያ ሶስተኛ ሰው ነበርኩ። ኢትዮጵያ በሁለት ሰው እንድትሰለፍ አልፈለኩም ነበር። ስለዚህ የወሰንኩት ውሳኔ መርፌውን ተወግቼ መሮጥ ነበር። ከዚያ ውድድር በኋላ እንደተባለው ሁለት ውድድር ብቻ ነው የሮጥኩት። አሁንም ድረስ አንደኛው እግሬ በአግባቡ እየሰራ አይደለም። ግን ቀስ እያለ ይተወኛል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለአገር ፍቅር ላነሳሽው ነገር እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በግላችን የምንኖረጠው ለኪሳችን ነው። ግን ደግሞ አገራችንን ወክለን ከሮጥን የ110 ሚሊዮን ህዝብን ፍላጎት ለማርካት እንጂ ኑራችን ላይ አንድ ነገር ለመጨመር አይደለም። ስለዚህ ከምንም ነገር በላይ ለአገራችን በመሮጣችን ክብርና ኩራት ይሰማናል። ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማችን በእኔም ከፍ አለ በቀነኒሳ፤ በወርቅነሽም ሆነ በጥሩነሽ ዋናው ቁምነገር የአገራችንን ስም ማስጠራት መቻላችንና ህዝባችን የጣለብንን አደራ መወጣታችን ላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ማድረጋችን ጥሩ እንቅልፍ እንድንተኛና ደስተኛ እንድንሆን አድርጎናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ለአንተ ምን ድን ነው?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ኩራትና ክብር ነው። ኢትዮጵያዊ መሆኔ ከምንም በላይ ያስደስተኛል። የእኛ ህዝብ በጣም ዝብርቅርቅ ያለ እምነት፣ ቀለማት፣ ቋንቋ፣ ብሔር ኖሮት ግን ኢትዮጵያ ሲባል ገና በአንድ መስመር ሆኖ የሚመጣ ህዝብ ነው። ይህም ከሌላው ሀገር ህዝብ ለየት ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ። በእርግጥ እርስ በርሳችን ዋጋ ያለመሰጣጣትና ያለመቀባበል ችግር አለብን። ግን ደግሞ ከውጭ ጠላት ሲመጣም ከጫፍ እስከጫፍ በጋራ ሆ ብለን እንተማለን። ኢትዮጵያውያን የራሳችን የሆነ በጣም ጥልፍልፍ ግን ወደ አንድ መስመር የሚመጣ ህብረ ብሔራዊ ውበት አለን። እኔ በሄድኩበት ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ምንም የሚያሳፍረኝ የሚያሸማቅቀኝ ነገር የለም። ኢትዮጵያዊነት መቻቻል፤ መረዳዳትና መከባበርም ነው ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ፈሪሃ እግዚአብሄር በትልቁ አለ። እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ የሚበላው ለሌለው አንድ ህፃን ልጅ መቶ ብር ሰጥቼው ካርድ ግዛልኝ ብዬ ብልከው በታማኝነት ይዞልኝ ይመጣል። ይህ ልጅ ምንም እንኳ የሚበለው ባይኖረውም ብሩን ይዞ መጥፋት እየቻለ በታማኝነት የሚያመጣው በህሊናው ውስጥ ተፅፎ ያደገው የፈሪሃ እግዚአብሄር በመኖሩ ነው።ይህ ደግሞ በዓለም ላይ የሌለ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ድንቅና አኩሪ ባህል ነው። ስለዚህ ሁላችንም ኢትዮጵውያን በዚህ ባህል ልንኮራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በርካታ አትሌቶች አንተ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እንድትሆን ይፈልጉ እንደነበር ይገለፃል። ይህ ከአንተ መልካም ስብዕና ጋር ይያያዛል ብለህ ታምናለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ በአንድነገር አምናለሁ። የተለየ ጫፍ ወጥቼ የመምራት ፍላጎት የለኝም። የማውቀውን ሰው ወይም ባለቤቴ ወርቅነሽን ለመጥቀም ብዬ አንድም የማደርገው ጥረት የለኝም። የምሰጣቸው ሃሳቦች ሰውን ያማከሉ ሳይሆኑ በእውነትና በፍትህ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው። እንዳልሽው ብዙዎች ለፕሬዚዳንትነት እንድወዳደር ሲጠይቁኝ ነበር። እኔ ግን ከኃይሌ በላይ ለመሆን ህሊናዬ አይፈቅድም። ይልቁንም ኃይሌን ባግዝ የተሻለ ነው የሚሆነው። ደግሞም የማዋጣው ሃሳብ አይደለም ምክትል ሆኜ አባል ብሆን እንኳን ያግዛል የሚል እምነት ነው ያለኝ። አሁንም ደራርቱ እያለች እኔ ፕሬዚዳንት መሆን ነበረብኝ የሚል አቋም የለኝም። ምክንያቱም በልምድም ትበልጠኛለች። በጥቅሉ ግን እኔ ከኋላ ሆኜ ትክክለኛና ውጤታማ የሆኑ አሰልጣኞች ወደ ሜዳ እንዲመጡ፤ ስፖርቱም በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ ሚናዬን የመወጣት ዓለማ ነው ያለኝ። እርግጥ አትሌቶች የሚሰጡኝ ሃሳብ ከከበሬታ የመነጨ መሆኑን አምናለሁ። ለዚህም ምስጋናዬ የላቀ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጣም ከሚታማባቸው ችግሮች መካከል ዘረኝነትና ቡድንተኝነት ነው። አንተ ወደ እዚህ ተቋም ከመጣህ በኋላ ይህንን ብልሹ አሰራር ለመቀየር ምን ያህል ጥረት አድርገሃል?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ፌዴሬሽኑ ከሁሉም የመንግሥት ተቋም በላይ የብዙዎችን አይንና ፍላጎት ያለበት ነው። ለብዙ ነገር የተጋለጠ ነው። ስለዚህ ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን ክፍተቱም በጣም ብዙ ነው።እኛ አትሌቲክስ ላይ መስራት አለብን ስንል ራሳችንን ለመጥቀም አይደለም። የግል ህይወታችን ፈጣሪ ይመስገን ጥሩ የሚባል ነው። እርግጥ ነው በዚህ መስሪያ ቤት እንጀራ በልተንበታል ብዙም አይተንበታል። ስለዚህ ዝም ብለን እያየን እንዲበላሽና ወደ ባሰ ሁኔታ እንዲገባ አንፈልግም። በተለይም እንደኛ ከምስኪን ማህበረሰብ የመጡ አትሌቶች ፍትሃዊ በመሆን መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድርግ ነው ዋናው ትግላችን። አሁን ያልሽው የቡደንተኝነትና በቲፎዞ የተሞላ አሰራር በስፋት ይታይ ነበር። ስራዎች የሚሰሩት በአጠቃላይ በቡደንተኝነት ላይ ተመስርተው ነበር። ደጋፊ ያለው አትሌት ነበር ወደ ውጭ የሚጓዘው። እኛ ወደ እዚህ እንደመጣን መጀመሪያ ያልነው ነገር ሁላችን ወደ አንድ መርከብ መጥተናል፤ በዚህች መርከብ ላይ ሰርቶ የሚያሸንፍ ይቀጥላል። በአንድ መንፈስ ወደ አንድ ስራ በመግባት ህዝቡ የሚፈልገው ስፖርት እንፈጥራለን ብለን ነው የተነሳነው። በዚያም ከዚህ ቀደም ሊቀራረቡ እንኳ የማይችሉ አስተሳሰቦችን ለማጥበብ ሞክረናል።
ይሁንና ብዙ ብንጥርም እስካሁን ከነበረው አስተሳሰብ ያልወጡና ያልተመለሱ ሰዎች በፌዴሬሽኑ ውስጥ አሁንም አሉ። እነዚህን የተጣረሱ አስተሳሰቦች ስንመልሳቸው በራሳቸው ራሳቸውን የቻሉ አደጋዎች ሆነው የሚመጡበት ሁኔታ አለ። በአስተሳሰብ አትሌቲክሱን ይጎዳል ብለን በምናመጣቸው ሃሳቦች ደስተኛ ልንሆንም ላንሆንም እንችላለን። ሙሉ ለሙሉ ቀይረነዋል ብለን ባናስብም ግን በጣም መስመር ይዞልናል ማለት እንችላለን። እየተጠቀሙ መጥቀም አንድ ነገር ነው። እየተጠቀሙ መጎዳት ግን አደጋ ነው። ብዙ ሰው ግለኝነት ያጠቃዋል። አሁንም በፌዴሬሽኑ ውስጥ በዚህ መንፈስ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ። ግን በሂደት ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ፈዴሬሽኑ በጣም ከሚወቀስበት ችግር አንዱ የውጭ ጉዞ ጉዳይ ነው። ይህንን አሰራር ከአድሎ የፀዳ ከማድረግ አኳያ እንዲሁም አሰራርና መመሪያዎች በተጨባጭ እንዲተገበሩ ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- አሁንም ትልቁ ማነቆ አሰራርና መመሪያን የመፈፀም ጉዳይ ነው። ሲጀመርም አሰራርና መመሪያ እንዲኖር አይፈለግም። የሚተገበሩበትም መንገድ ተሸራርፈው ስለሆነ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። እኛ ወደ ተቋሙ እንደመጣን መጀመሪያ የሰራነው የስነምግባር መመሪያ ማውጣት ነው። በዚህ መመሪያ ላይ ከአትሌቱ ጀምሮ ማናጀሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ግብዓት እንዲሰጡ ጥረት ብናደርግም ግን እንዳልኩሽ እንዲፈፀም የማይፈልጉ ሰዎች ስላሉ በይፋ ሃሳብ ለመስጠት አልደፈሩም። ስለዚህ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ አምጥተናል ማለት አይቻልም። በአጠቃላይ እስካሁን የተሰራው ስራ እንደስኬት የሚቆጠር አይደለም። በተለይ አገሪቷ ካላትመልካዓምድርና የሰው ኃይል አኳያ ዘርፉን ለማሳደግ በሚያስችል ቁመና ላይ ነን ለማለት አልደፍርም። በተለይም ታች በመውረድ ሰዎችን በማምጣት እንዲ ጠቀሙ በማድረግ ረገድ ብዙ አልሰራንም።
አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ የዘረኝነት ችግር ስር የሰደደ በመሆኑ ለአገሪቱ ውጤት ማጣት ዋና ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል። ይህን ችግር ለማስቀረት ምን እየሰራችሁ ነው?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እሱ ላይ እውነት ለማነገር ተቀላቅሎብናል። አዲስ ዘመን፡- እንዴት? አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እንዴት መሰለሽ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። አትሌቶቻችን የአንድ ማህበረሰብ አባሎች ናቸው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደሀገር የምንጠራቸው ሰዎች እስከ መንደር ድርስ ታች ይወርዳሉ። እኔ ለወለደችኝ እናቴ ልጅ ልሆን እችላለሁ። አሁን ግን የሁሉም ኢትዮጵውያን እናቶች ነኝ ማለት እችላለሁ። በፌዴሬሽናችን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች እስካሁን ድረስ አሁንም ከዛ የመንደር አስተሳሰብ አልወጡም። በዚህ ምክንያት ፖለቲከኞችም ይጠቀሙብናል። ይህም በስፖርቱም ውስጥ ፖለቲካ እንዲስፋፋ አድርጓል። ስለዚህ የተወሰነ ነገር ተቀላቅሏል ብዬ ነው የማምነው። ይህንን ለማስቀረት በተለየያ ደረጃ እውቀት እንዲሰርፅ አድርገናል። ስፖርቱ ዘረኝነትንም ሆነ ፖለቲካን እንደማይፈልግ አስተምረናል። ስፖርቱ የሚፈልገው የስፖርት ቋንቋ ብቻ ነው። እውነት ለመናገር ብዙ ጓደኞቻችንም በዚህ ምክንያት ተስፋ የቆረጡበት አጋጣሚ አለ። የሚገባቸውንም ክብር ሳያገኙ ቀርተዋል። ስፖርት እንዲህ ያለው ሁኔታ አያስፈልገውም። ምክንያቱም እኛ ይህችን ሰነደቅ ዓላማ ይዘን የምንሮጠው መንደራችንን ወክለን ሳይሆን አገራችን ወክለን መሆኑን ተገንዝበው ከዘረኝነት፣ ከአድሎ አመለካከት እንዲወጡ ተደጋጋሚ ውይይቶች አድርገናል። ግን አሁንም ድርስ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ከዚህ አመለካከት ለመውጣት ሲቸገሩ እናያለን። ስለዚህ እዚህም ላይ የምንፈልገውን ለውጥ እያመጣን ነው ማለት አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አትሌቶች በውድድር የሚያገኙትን ምዋለንዋይ ህንፃ ከመስራት ባለፈ ለህዝብ ጥቅም የሚውል ተግባር ላይ አያውሉም ተብላችሁ ትተቻላችሁ። አንተ ከዚህ ትችት ነፃ ነኝ ብለህ ታምናለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ፎቅ መስራታችን እንደውለታ አይቆጠርልንም ማለት ነው? እንደውምየእኛ መዋለንዋይ የደም ጠብታ የታከለበት በመሆኑ ለአገር ገፅታ ግንባታ ጉልህ ሚና እያበረከትን ነው ብዬ ነው የማምነው። እውነቱን ለመናገር በእኔ በኩል ይህንን አድርጌያለሁ ማለቱ ከንቱ ውዳሴ ይመስለኛል። ከእኔ ይልቅ የተደረገላቸው አካላት ቢናገሩ ደስ ይለኛል። ግን ስለጠየቅሽኝ ያህል በምግባረሰናይ ድርጅቶች ላይ አቅሜ በፈቀደው ሁሉ እሳተፋለሁ። በተለይም አዲስ አበባ ላይ ባሉ የህፃናት ማሳደጊያዎችና የአረጋውያን መንከባከቢያ ድርጅቶች ላይ ድጋፍ አደርጋለው። ለአንዳንድ ትምህርት ቤቶች መፃፍና የመሳሰሉትን ድጋፎች ያደረግሁበት አጋጣሚ አለ። አንድ ነገር ግን አምናለሁ፤ ሰዎችን በገንዘብ ከመርዳት ይልቅ ህይወታቸውን መቀየር የሚችሉበትን መንገድ ማሳየት የተሻለ ይሆናል። አለበለዚያ ግን ሁልጊዜ ተረጂ እንዲሆኑ ነው የምናበራታታቸው። እኛ እዚህ የደረስነው ነገሮች ሁሉ ተመቻችተውልን አይደለም፤ ጥረን ግረን እንጂ። ሌላውም ለፍቶ ግሮ ውጤታማ ለመሆን መጣር አለበት የሚል አቋም አለኝ። እንዳልሽው ግን ብዙዎቹ ህንፃና ሆቴል ከምትገነቡ ኢንዱስትሪ ቢሆን ጥሩ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ግን አብዛኞቻችን የምንፈልገው ከኑሯችን ጋር የሚመች በቀላሉ ልንቆጣጠረው፤ ልንከታተለው የምንችልው የሚታይ እሴት መገንባት ነው። ፋብሪካ ቢሆን ግን ስራውን የማናውቀው ከመሆኑና እኛም ጊዜውና እውቀቱ የሌለን በመሆኑ የሆነ ወቅት ላይ ሊከሽፍ ይችላል የሚል ስጋት አለን።
አዲስ ዘመን፡-ግን እኮ የውጭ አገር አትሌቶች በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ከመሆናቸው ባለፈ ለታታላቅ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ላይም በመሳተፍ ስማቸው ይጠቀሳል?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እንግዲህ እኛ አንኳክተን በመሄድ እንስራላችሁ አንልም። እንደውም አልተጠቀሙብንም የሚል እምነት አለኝ። አንድ ጊዜ ኤስ.ኦ.ኤስ የተባለ የህፃናት ማሳደጊያ ድርጅት እኔና ባለቤቴ እንድናስተዋውቀው ጋብዘውን እኛም ፈቃዳችንን ሰጥተናቸው ነበር ግን በመሃል ጠፉ። ተመልሰው አልጠየቁንም።እኛ ጎትጉተን እናስተዋውቅላችሁ ልንላቸው አንችልም። በማንኛውም ጊዜ ማህበረሰብን ለሚለውጥ ነገር ራሴን ሽጬ ብጠቅም ቅር አይለኝም። በሌላ በኩልም በእኔ እምነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልተጠቀመብንም። ደራርቱንና ኃይሌን የመሳሰሉ ታላላቅ አትሌቶች ባሉባት ከ100 በላይ ኢምባሲዎች ባሉባት አገር ሀገርን በሚጠቅም መልኩ መስራት አልቻልንም። እኔ በግሌ ኃይሌ ወይም ደራርቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ወጣቶችን በሚያስተምሩ ትልቅ የአስተሰሰብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ግን እስካሁን መንግሥት ይህንን አቅም ሊጠቀምበት አልቻለም። ይህ ደግሞ የእኛ ፕሮፖዛል መሆን የለበትም። ስለዚህ መንግሥት በባለቤትነት ሊሰራ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የዜግነትና የብሔር የፖለቲካ አስተሳሰቦች ውዝግብ ውስጥ ገብቷል። በአንተ እምነት ለኢትዮጵያ የሚበጃት የቱ ነው ትላለክ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ሁለቱም ጉዳዮች የሰዎች ፍላጎት ላይ ይጣላሉ። እኔ አምስት ጣቶቼ ተደምረው ነው እጅ የሆኑልኝ። አምስቱም ጣቶች ካልተባበሩ እንጀራ ለመቁረስ እንኳ አልችልም። ስለዚህ በመጀመሪያ በአምስቱም ጣቶች ልዩነት ማመን አለብኝ። እጅ ሊሆኑ የሚችሉት ሲደመሩ ወይም አንድ ላይ ሲሆኑ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ አለብኝ። ይሁንና የአጭሯንም አጭርነቷን ከድቼ፤ የረጅሟንም ረጅምነቷን ከድቼ እጅ ሆናችሁ እንጀራ ቁረሱልኝ ልላቸው አልችልም። የተለየየ ቋንቋ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ያለን ትልቅ ህዝቦች ነን። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች ብሔርን ወደ ሚፈልጉት ጥቅም ይወስዱታል።ያ ቡድን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት የሚያፍር ከሆነ ዘር ሐረጉ አያስፈልገውም ማለት ነው። ስለዚህ የእኔን ትክከለኛ ቋንቋ በመናገሬ፤ ሌላውም የራሱን በመናገሩ የእኔና የእሱ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ የሚኖረን ከሆነ ስህተቱ ይፈጥራል። በእኔ እምነት ሰዎች ቤታቸውን ሳያከብሩ ጎረቤታቸውን ሊያከብሩ አይችሉም። ማንኛውም ሰው መነሻውን የማያውቅ ከሆነ መድረሻውን ሊያውቅ አይችልም። መነሻውን ግን ከመድረሻው በላይ የሚያመልከው ከሆነ የሚያምንበት ከሆነ መድረሻው ላይ ሳይደርስ ይሞታል። ስለዚህ እኔ በብሔርና በቋንቋ ልዩነት ላይ ችግር የለብኝም። ሲመጡና አንድ ላይ ሲሆኑ የእኔ ቋንቋ ከሀገሩ በላይ አድርጌ የማስብ ከሆነ እኔ የመጣሁበትን አካባቢ የበላይ አድርጌ የማስብ ከሆነ መነሻ እንጂ መድረሻ አይኖረኝም። በሌላ አነጋገር ማንም ወንድ ከእናቱ እንደተወለደ ይረሳዋል ብዬ አላስብም፤ የመጣንበትን ቀዬ እንዲሁ። ግን መነሻችን ለዋናዋ ኢትዮጵያ ከምትባለው አገራችን የምናስበልጠው ከሆነ ለአንድነታችን ጠንቅ ነው የሚሆነው። ተፈጥሯዊ ማንነታችን ሳንክድ ግን ደግሞ ሁሉንም አካሎቻችንን እንደየተፈጥሯቸው ልንጠቀምባቸው ይገባል። ስለዚህ ፖለቲከኞች ወይም ገዥዎች የሚጠቀሙት የተለያዩ አስተሳሰቦች ህዝብ ላይ ውዥንብር በመፍጠርና ስልጣናቸውን ከማራዘም በዘለለ እንደአገር ለመቀጠል አያስችለንም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ሁለት ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች መስፋፋት ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራ ዘር ነው ብለው ይናገራሉ። አንተ በዚህ ላይ ያለህ አቋም ልትነግረን ትችላለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ በሃሳብ ልዩነት አምናለሁ። እኔና አንቺ ወንድና ሴት መሆናችን ሃቅ ሆኖ ሳለ እንካደው ብንል እንኳ ልንክደው አንችልም። ልዩነታችንን ሳንቀበል በደፈናው የምንጓዝ ከሆነ የሆነ ቦታ ላይ መለያየታችን አይቀርም። ስለዚህ በሃሳብ ልዩነቶችን አምኖ፣ ተቀብሎ፣ ተቻችሎ መኖር ለእኔ ትልቅነት ነው። እነዚህ 27 ዓመታት ተዘርተዋል የምንላቸው ሃሳቦች አሁን ላይ ለመበጣበጣችን ምክንያት ሊሆን የቻሉት በአግባቡ ስላልተሰራባቸው ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ አሁንም ድረስ ስለብሔር ወይም ስለአብሮነት ሲነሳ እንደቁስል የምንፈራቸው ጉዳዮች አልፈናል። እስከዛሬ ድረስ በግል እየተነገሩ እየተወያየንባቸው ብንመጣ ኖሮ መተማመን ላይ እንደርስ ነበር። እኔ እና አንቺ ስለክልሎች አወቃቀርና ብሔሮች በግልፅ ሳንወጃጀል እየተወያየንበት ብንመጣ ኖሮ የአንቺና የኔ ሀሳብ ተደምሮ ውጤቱ ይታይ ነበር። እኔ ለወደፊቱም መሆን አለበት ብዬ የማስበው በሃሳቦች እንዳይንሸራሸሩ የምናደርገው ክልከላ ማቆም ነው። ሌላውን አፍኖ የመሄድ አስተሳሰብ ማስቀረት ከቻልን መተማመን ላይ እንደርሳለን ብዬ አምናለሁ። አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ግን እንደውም ልዩነታችን እየተነገርን በመኖራችን ነው ከአንድነት ይልቅ ለመለያየት የምንዳዳው ሲሉ ይሟገታሉ? አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እንግዲህ እኔም የእነዚያ 27 ዓመታት ውጤት ነኝ ብዬ አምናለሁ። እነዚያ የልዩነት ሃሳቦች ተሰራጭተው ከሆነ ችግሩ ያለው ከአቀባበላቸው ነው ብዬ አምናለሁ። በእኔእምነት ሃሳቡን የሰጠንበት፣ ያሰረፅንበት መንገድ ችግር አለበት ብዬ ነው የማምነው። በተለይም ኢትዮጵያ የምትባለው አገር መሰረቷ የሁሉም አካበቢዎች ድምር ውጤት ነው። ግን ደግሞ ለውድድር በሄድኩባቸው አገሮች ከየት ነህ ሲሉኝ መቼም ከትግራይ አልላቸውም። እዚህ ሆኜ ግን ከየት ነው ብባል የመጣሁበትን ቦታ መጥቀሴ አይቀርም። ይሁንና እኔ የመጣሁበት አካባቢ እዚህ ካሉት 80 በላይ ከሚሆኑ ብሔሮች በላይ ነው ብዬ የማምን ከሆነ የእኔ ችግር ነው የሚሆነው። ግን ደግሞ ሰዎች ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ መደረጉ በራሱ ስህተት ነው ብዬ አላምንም። የመጨረሻ ግቡ ግን የሁላችንንም አገር የሆነችውን ኢትዮጵያ የሚያጎላ መሆን ነው ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ከመጣ አንድ ዓመት ተቆጥሯል። አንተ በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል እንዴት ታየዋለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ ለውጥ አለ ብዬ አምናለሁ። ለውጡን ተከትሎ ብዙ በሮች ተከፍተዋል። እነዚህ ብዙ በሮች እንደለውጥ የምንወስዳቸው ከሆነ ለውጥ ሊሆን ይችላሉ። ለእኔ የሃሳብ ልዩነት ያላቸውና ለህዝብ ይጠቅማል ባሉት ሃሳቦቻቸው ምክንያት ለረጅም ጊዜ እስር ቤት የነበሩ ተፈተው በነፃነት መንቀሳቀሳቸው ትለቅ ለውጥ ነው። እኔ ከፅንፍ ድጋፍ ውጪ አሁን የተፈጠረው የመናገር፣ የመፃፍና የመተቸት ነፃነት ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ነው የምረዳው። ግን ደግሞ ለውጡን ተከትሎ በተከፈቱት በሮች ልክ የአገሪቱን ህልውና ስጋት ላይ የሚጥሉ ነገሮች ገብተዋል። በተለይም አንዳንድ አገራት በተከፈተላቸው በር ተጠቅመው አገሪቱ ያላትን ሰፊ የሰው ሃብት በቅኝ ለመግዛትና እነርሱ ወደ ሚፈልጉት መስመር ለመንዳት ጥረት የሚያደርጉበት ሁኔታ እየታየ እንደሆነም እረዳለሁ።
ስለዚህ አሁን ያለው መንግሥት አመራር የለውጡ ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ለተፈጠሩ አለመረጋገቶችም ባለቤት መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ብዙ ህይወት አጥተናል፤ ብዙ ሰቀቀን አይተናል። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰው የተሰቀለበት አጋጣሚም ተፈጥሯል። እስካሁንም ቢሆን ብዙ ያልተረጋጉና ሰላም የሌላቸው አካባቢዎች አሉ። በአጠቃላይ ለውጡ በጥንቃቄ እየተመራ አይደለም የሚል እምነት አለኝ። እንደ ብዛታችንና እንደ ልዩነታችን፤ እንደፍላጎታችን እንዳሳለፍነው ችግር በጥንቃቄ አልተያዘም። አንዳንድ ጉዳዮች ወደ ህዝቡ ከመለቀቃቸው በፊት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተለቀዋል ብዬ አላስብም። ከምንምና ከማንም በላይ ታማኝና ተወዳጅ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚናገሩት ነገር ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ማህበረሰቡ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ነገር በጥቃቄ ለህዝብ አላደረሱም። በተለይም አገሪቱ ከምንም ጊዜ በላይ አይን ውስጥ የገባችበትና በአፍሪካ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነችበት ወቅት እንደመሆኑ ለውጡን የሚመራው ኃይል በሰጡት ነፃነትና በከፈቱት በር ልክ የባሳ ችግር ይዞ እንዳይመጣ ሊጠነቀቁ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡ በጥንቃቄ ላለመያዙ አብነት አድርገህ የምትጠቅስልኝ ነገር ይኖር ይሆን?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ለምሳሌ የኢት ዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት በሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ተጉዟል። ያንን አስተሳሰብ እንዴት በሂደት ልንሸረሽረው ይገባል? የሚለው ጉዳይ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ አልተመራም። ለዓመታት ተይዞ የቆየ ችግር በአንድ ጊዜ እንዲበተንና እንዲለቀቅ መደረጉ ህዝቡ በውስጡ ጥሩ ያልሆነ ነገር እንዲያሳድር አድርጎታል። ደግሞም ለውጡ ተጨባጭና ሃገራዊ ይዘት ያለው ነው ለማለት አያስደፍርም። በጥቅሉ ጥንቃቄ ይጎድለዋል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አንተ አገሪቱን ላለፉት 27 ዓመታት ሲመራ ከነበረው ህውሃት አካባቢ የመጣህ በመሆንክ የተለየ ጥቅም አግኝቻለሁ ብለህ ታምናለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ እንደማንኛ ውም ኢትዮጵያዊ አትሌት ተሸልሜ ነው ያገኘሁት። ከዚህ ውጭ አንተ ከመጣህበት አካበቢ የበቀለ ስርዓት ስለሆነ ተጠቅመሃል ወይ? ካልሽኝ ሳቅ ነው መልሴ። እኔ እንደውም ብዙ ጓደኞቼን የምመክረው ነገር እኛ ከመንደር ወጥተን ሃገር መሆናችን ማሰብ እንዳለብን ነው። ስለዚህ ያ አይነት አስተሳሰብ በአዕምሮየ ውስጥ ተመላልሶ አያውቅም። አሁንም ቢሆን የምገፋውና የምጠላው አካል የለኝም። በፊትም ሆነ አሁን በየትኛውም አካበቢ ድጋፍ አድርግ ስባል ወደ ኋላ አልልም። ወደ ፊትም ይህንን አስተሳሰቤን ነው የምቀጥለው።
አዲስ ዘመን፡- እንደምታውቀው ከዚህ ቀደም ትላልቅ የፖለቲካ ስልጣን ላይ የነበሩየህውሃት ፖለቲከኞች ለውጡን ባለመቀበል ወይም ኩርፊያ በሚመስል ሁኔታ መቀሌ ላይ ከትመዋል። ይህ ሁኔታ ወደ ፊት እንገነባታለን ለምንላት አገር ተገቢ ነው ብለህ ታምናለህ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔ እንደማንኛ ውም ኢትዮጵያዊ ነው እነዚህ መረጃዎች የደረሱኝ። በስራ ላይ ከሌሉ ለምን መቀሌ ከተሙ ማለት አልች ልም። ከኩርፊያ ጋር ተያይዞ ከሆነ ግን መጀመሪያም እንዳልኩት ለውጥ ይኖራል። ወንበር የሚያዘው ህዝብ ለማገልገል እስከሆነ ድርስ ለውጥ ሲመጣ የሚያጣላ የሚያቀያይም ነገር ሊኖር አይገባም። ተጨማሪ ሃሳብ መምጣት የሚያስቀይመንና ወደ ኋላ የምንል ከሆነ ማን በሰራት አገር ትኖራለህ ታዲያ? ስለዚህ ሁሉም ሰው ከየትኛው ጥግ ይምጣ በአገሩ መስራት የሚችል ሁኔታ መኖር አለበት ብዬ አስባለሁ። ኩርፊያ ለማንም ይበጃል ብዬ አላስብም። በሃሳብ አለመግባባት እስከወዲያኛውም ሊኖር ይችላል። ግን በልዩነቶቻችን ላይ እየተማመንን መኖር የማንችልበት ምክንያት ግን አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት ለተፈ ፀሙ የህግ ጥሰቶች የተወሰኑ አመራሮችን በህግ ተጠያቂ ቢሆኑም አሁንም ብሔራቸውን ተገን አድርገው የተሸሸጉ ባለስልጣናት አሉ። ይህ ደግሞ የህግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ እያስገባው እንደሆነ ይጠቀሳል። አንተ ከዚህ አኳያ በመንግሥት ሊወሰድ ይገባል የምትለው እርምጃ ምንድን ነው?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- ቤታችን በር ከሌለው መውጫና መግቢያው እንደማይታወቀው ሁሉ በአንድ አገር ህግ ማስከበር ካልተቻለ የዜጎች የመኖር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ህግን የተላለፉ ባለስልጣናትም ሆነ ማንኛውም ወገን ተጠያቂ ማድርግ ይገባል። ይህ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም መሆን ያለበት። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መፍጠን ይገባናል የሚል እምነት አለኝ። ሲጀመርም ለውጥ የምንለው ሪፎርም እንጂ የተለየ መንግሥት መጥቶ አይደለም። ዶክተር አብይ የሚመሩትም መንግሥት ኢህአዴግ ነው። ስለዚህ አሁንም ሆነ ከዚህ ቀደም የነበረው ችግር ህግ የማስከበር ጉዳይ ነው። ህግን የማስከበር ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ መሆን የለበትም። ከሁሉ የበላይ የሆነው ህግ ማክበር ስንችል ነው ካለፈው ስህተታችን መማር የምንችለው። ይህ ሲደረግ ግን በጥንቃቄና በሰከነ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከሁለት ዓመት በፊት የመልካም አባት ሽልማት አግኝተሃል። ለመሆኑ አንተ መልካም አባት ነኝ ብለህ ታምናለህ? እስቲ ለሽልማት ያበቃህንም አጋጣሚ አስታውሰን?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እውነት ለመናገር ይህንን ጥያቄ ባለቤቴና ልጆቼ ቢመልሱት ይሻላል። ግን እኔ አቅሜ በፈቀደ መጠን ለልጆቼ የሚገባውን ትኩረትና ድጋፍ አደርጋለው። ምክንያቱም እኔ ቤቴንና ቤተሰቤን ሳላከብር ሌላውን ላከብር አልችልም። ስለዚህ ክብር፣ መገዛትና መታዘዝ ከቤት ይጀምራል። በስራ አጋጣሚ በጣም ቢከፋኝ እንኳ ልጆቼ ከፍቶኝ እንዲያዩኝ አልፈልግም። ከባለቤቴ ወርቄ ጋር በትዳር መኖር ከጀመርን 16 ዓመታት አሳልፈናል አንድም ቀን በመጥፎ ቃላት ተነጋግረን አናውቅም። ይህ ደግሞ የእኔ ብቻ ሳይሆን የእሷም መልካም ባህሪ ሊሆን ይችላል። ይህም ለመልካም አባትነት ያሳጨኝ ምክንያት እንደሆነ አምናለሁ። ሽልማቱን የሰጠኝ ዩኒሴፍ ሲሆን ለሌሎች መልካም አርዓያ መሆን ትችላለህ በሚል መነሻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለባለቤትክ ካነሳህ አይቀር አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ አዕምሮ እንዳትዘነጋ ከሚያደርጓት የተለዩ መገለጫዎቿ አንዱ በሩጫው ዓለም ራሷን መስዋዕት በማድረግ የራሷን ጥቅም ለሌሎች አሳልፋ በመስጠት አገሯን የማስቀደም ጉዳይ ነው። ይህ መልካም ባህሪ ይሆን ከአንተ ጋር ይበልጥ ያስተሳሰራችሁ?
አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እንዳልሽው ወርቄ ከማንኛውም አትሌት የሚለያት ባህሪዋ ከምንም በላይ አገሯን ማስቀደሟ ነው። ይህንን በማድረጓ ደግሞ አሁንም ድርስ የምትተኮርበትና የምትደሰትበት ጉዳይ ነው። እኔ ግን የወደድኳት በእዚህ ባህሪዋ ሳይሆን በራስዋ ስብዕና ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ሁላችን ያጣመረን እርስበርስ መቀባበላችንና መተሳሰባችን ነው። አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም አመሰግናለሁ። አትሌት ገብረእግዚአብሄር፡- እኔም አመሰግ ናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2011
ማህሌት አብዱል