ከሸገር ዋና ዋና የንግድ ሥፍራዎች ውስጥ መርካቶ፤ፒያሳ ፣ቂርቆስ፣ ቦሌና መገናኛ ለሸማቾች ይጠቀሳሉ። ንግዱ የሚካሄደው በቀበሌ ቤቶች፣ ቀድሞ ኪቤአድ በምንለው በአሁኑ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ቤቶች፣ በግል ሕንፃና ንግድ ቤት አከራይ ባለቤቶችና፤ የራሳቸውን ቤት ለንግድ በሚገለገሉ ሰዎች ነው።
ከላይ ያነሳናቸው የንግድ ቤት ዓይነቶች በዋናነት እንጥቀሳቸው እንጂ፤ ሌሎች ተለጣፊ ሱቆች፣ ተነጣፊ ሱቆችና ተንሳፋፊ ሱቆችም ማለቴ ሱቅ በደረቴዎች ይገኛሉ። በዚህ መልኩ የሚካሄዱ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሰበብ አስባቡ ያለ በቂ ምክንያት በሚፈጥሩት የዋጋ ጭማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋቸው የማይቀመስ እየሆነ መጥቷል። ይህ ሲሆን ደግሞ የዋጋ ንረቱና ንዝረቱ፣ ክፋቱና ክርፋቱ ቀድሞ የሚሰማቸው ሸማቾች ናቸው።
ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት መጋቢት ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ34 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጦ ነበር። የዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ፍጆታ በሆኑት ለምግብነት በሚውሉት አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እና እህሎች፣ ቅመማ ቅመም እና ዘይት፣ ቅቤ እና ቡና ላይ ይፀናል።
አጠቃላይ በሆነው አተያይ ነጋዴው ጥቂት ፤ ሸማቹ ብዙ መሆኑን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ዜጋው ሁሉ ሸማች ነው ማለት ይቻላል።ቢሆንም ግን የተሻለ ገቢ ያለው፤ የምርት ዋጋ ቢቆለል ባይቆለል ጉዳዩ አይደለም። ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው ደግሞ ዋጋ በተቆለለ ቁጥር በሀሳብ ይሳቀቃል፤ ይጨነቃል። የአገራችን አብዛኛው ዜጋ ደግሞ ኖረ ከመባለውም በዝቅተኛ ገቢ የሚኖር ነው።
ከላይ እንደጠቀስነው ዜጋው ሁሉ ሸማች ነው ስንል፤ ነጋዴውን የት ደበቃችሁት? የሚሉን አይጠፉም። በአንድ ንግድ ቤት አልባሳት የሚሸጥ ሰው መደበኛ ሥራው ነጋዴ ቢሆንም፤ ምግብ ቤት ገብቶ ይመገባል፣ መጠጥ ቤት ገብቶ ይጠጣል፣ የቤት ቁሳቁስን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ይገዛል፣ እህል ይሸምታል፤ ስለዚህ በተራው ሸማች የሚሆንበት መንገዱ ብዙ ነው።
የዋጋ ንረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይኑሩታል፤ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች በዶላር ዋጋ ጭማሪና ሌሎች ምክንያቶች ዋጋቸው ይጨምራል። በዚህ ምክንያት ሸማቹ ላይ ዋጋ ይጨምራል፤ የግል ቤት (መኖሪያ ቤት በሉት የንግድ ቤት ሕንፃ አከራዮች) በሰበብ አስባቡ የኪራይ ዋጋ ይጨምራሉ። የኪራይ ዋጋ ሲጨምር የቁሳቁሶች መሸጫ እና የምግብ ቤቶች መስተንግዶ ዋጋ ጨምሮ ይጠብቃችኋል።
ዋጋ ሲጨምር ሁልጊዜ የሚገርመኝ ነገር አለ፤ ነጋዴው በሙሉ ተሰብስቦ በአንድ ድምፅ የወሰነ እስኪመስል ሁሉም ቦታ ብትሄዱ ዋጋው ጨምሮ ይጠብቃችኋል። መቼም ነጋዴው በኪሣራ ይሥራ (ይነግድ) የሚል ጭፍን አመለካከት የሚኖረው የለም። ነገር ግን ነጋዴዎች ለዋጋ ጭማሪዎቻቸው አመክንዮ ሊኖራቸው ይገባል። ማትረፍ እንዳለባቸው እናምናለን፤ ሲያተርፉ ግን ከመጠን በላይ ከሆነ ማትረፍ ሳይሆን መዝረፍ ነው። የትርፍ ጣራ ወይም ኅዳግ ሊበጅለት ይገባል።
ነጋዴዎቻችን ማኅበራዊ ኃላፊነት(Social Responsibility) የሚባለውን አያውቁትም ፤ መነገድን ብቻ አስበው የሚሠሩ ናቸው። ማኅበራዊ ኃላፊነት በመነገድ ውስጥ ማገልገል የሚባል ሰብዓዊ ትርፍ ነው። ሲነግዱ ቁ(ኪ)ሳዊ ትርፍን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ትርፍን ከግምት ማስገባት አለባቸው። ለብር ሲሠሩ ሲሮጡ ሸማቹን እየዘነጉ እየረገጡ መሆን የለበትም። ሰው ሲዘነጉት፤ ይጥላቸዋል ይረግጣቸዋል። ንግድ ቦታቸው እንደ እሳት አደጋ የመሳሰሉ ቢደርስበት ቅድሚያ ዜጋው ባቅሙ ይታደጋቸዋል።በገንዘብ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።
ነጋዴው ወጥቶ ነግዶ ወደ ቤቱ በሰላም የሚገባው የፀጥታ ኃይሎች ግዴታቸውን ስለሚወጡ ነው። ሸማቹ በንግዱ እየተማረረ ሁከት ቢፈጠር፤ በቅድሚያ የሚጎዳው ነጋዴው ነው። ነግዶ መግባት አይችልም፤ በሁከት ንግድ ቦታው ሊዘረፍ ሊቃጠል ሊወድም ይችላል። ማኅበራዊ ግዴታውን ከተወጣ ግን ዜጋው ንብረቱን ከዘራፊዎች ይጠብቅለታል።
የውጭ አገር ነጋዴዎች ለአገራቸው ግብር እየገበሩ፤ ማኅበራዊ ግዴታቸውን ደግሞ በአግባቡ ይወጣሉ። የችግረኞችን ቤት በመሥራት፤ ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ በመግዛት፤ ወዘተ። የመርካቶና የሌላ ቦታ ነጋዴዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች የወዳደቀ መኖሪያ ቤታቸውን በማደስና በመሥራት፤ መጸዳጃ ቤት በመገንባት ምንም የሠሩት የለም።
በእድሮቻቸው መሥራት ይችላሉ፤ ግንዛቤም የሚሰጣቸው የለም፤ የክፍለ ከተማው አመራሮች ከቦሮ ወጥተው ይሄን ማስተባበር ይችሉ ነበር። ለነገሩ እነሱም ግንዛቤ ያላቸው አይመስሉም፤ ወይም ማገነዘብ የሚጀምሩት ምርጫ ሲደርስ ነው። ይሄም ሁሉ ቀርቶ ግን ነጋዴው ዋጋውን እያናረ ሕዝቡን እያመረረ ባይሄድ ሸጋ ነው።
የግለሰቦችን ቤት የተከራዩ ነጋዴዎች የኪራይ ዋጋቸውም ውድ ስለሆነ የሚሸጡትን ዕቃ ውድ ሊሆን ይችላል። የንግድ ቦታዎችም ለዋጋ ንረት ወሳኝነት አላቸው፤ ቦሌ የሚነግዱ ዋጋቸው ውድ ሲሆን በተመጣጣኝ ዋጋ እገዛለሁ የሚል መገናኛ ቂርቆስ መርካቶ ኮልፌ ይሄዳል።
ነገር ግን በራሳቸው ንግድ ቤት፣ በቀበሌ፣ በመንግሥት ቤቶች ተከይራተው የሚነግዱት ከግል አከራዮች ጋር ሲነፃፀር ለኪራይ የሚያወጡት ኢምንት ነው። እናም በሰበብ አስባቡ ዋጋ ከሚጨምሩ ጋር እየተባበሩ ሸማቹን አያማሩ።
ለሸማቹም የሚከራከርለት ማኅበር የለም፤ ንግድ ምክር ቤትም በዚህ በኩል ከአስመጪዎችና ላኪዎች በመነጋገር ቢሠራ እላለሁ፤ በዚህ ላይ ካልሠራ፤ ለከበርቴው ነጋዴ ብቻ ሊቆም ነው? መንግሥትም በሚመለከታቸው አካላት በኩል ግዴታውን ይወጣ።
መግለጫ መስጠት ብቻውን ግዴታ መወጣትን አያሳይም። ቢያንስ የቀበሌና የመንግሥት ቤት ተከይራተው የሚነግዱ የትርፍ ኅዳግ ይኑራቸው። ማኅበራዊ ቀውስ ሳይፈጠር ከወዲሁ የሚነግዱ ሸማቹን እንዳይጎዱ የሚደረግበት መንገድ ይመቻች።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2015