«ምንም ያልተደረገባቸው አስርት አመታት እንዳሉ ሁሉ፤ የአስርት አመታትን ያህል የሆነባቸው ሳምንታት አሉ፤»የቦልሸቪኩ መሪ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን የራሽያው ንጉሳዊ አገዛዝ ዛርን በፍጥነት መንኮታኮት ታዝቦ ከ100 አመታት በፊት የተናገረውና ዛሬ ድረስ እንደትንቢት በሚወሳለት አባባሉ። ሌኒን ዛሬ ቢኖር ደግሞ፣ «የክፍለ ዘመናት ያህል የተከናወነባቸው አስርት አመታት አሉ፤» ይለን ነበር ይለናል የአሜሪካው ፎሪን አፊርስ ፖሊሲ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና ደራሲ ሪቻርድ ሀስ።
አዎ ! ባለፉት አራት አመታት በአገራችን የሆነው በአራት አስርትም ሆነ ክፍለ ዘመናት ከሆነው ይበልጣል። በአሉታም በአውንታም። አገራችን በታሪክ እንደነዚህ አራት አመታት ተፈትናም፤ ተስፋ ሰንቃም አታውቅም። በአዎንታ የሆነውን በሌላ መጣጥፌ የምመለስበት ሆኖ፤ ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽና እነ ሽብርተኛው ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በአንድ ወገን፤ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲውና ሚዲያው በሌላ ወገን እንዲህ እንደ ጎን ውጋት ቀስፈው ይዘዋት አያውቁም። የራሽያና የዩክሬን ጉዳይ ሰቅዞ ይዟቸውም ዛሬም አልተኙልንም። ለ15 ጊዜ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እየጎተቱን ነው።
የራሽያና የዩክሬን ጦርነት ባጠላበት፤ አለማችን በአንጻራዊነት ለ75 አመታት እንደ 2ኛው የዓለም ጦርነት ካለ ፍጅት የተጠበቀችበት ዘመን መጨረሻ የተቃረበ በሚመስልበት ሰዓት እየተካሄደ በነበረው የ77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የአገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ያህል ገዳዳና ወጥ እንዳልሆነ የሚያሳብቅ አንድ አባባል ጣል አርገዋል። “ራሽያ ወረራዋን ብታቆም ሰላም ይሰፍናል። ዩክሬን መከላከል ብታቆም ግን ከዓለም ካርታ ትፋቃለች። ትጠፋለች። ዩክሬን የምትባል አገር አትኖርም። “ብለው መነጋገሪያ ሆነዋል። ይሄን ንግግራቸውን የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶተንበርግ ሰሞኑን ቃል በቃል ደግመውታል።
አባባሉ በራሱ ለሙግትና ለክርክር የሚጋብዝ ቢሆንም ለዛሬ አጀንዳዬ ስላልሆነ በዚሁ ገታ ላድርገውና ወደ ተነካሁበት ነጥብ ልመለስ። ብሊንከን ለራሽያና ለዩክሬን ሲሆን የተከተሉት ፖሊሲና ያራመዱት አቋም፤ ለሌላ አገር ሲሆን ግን ፍጹም ይገለበጣል። ይቃረናል። ሶሪያ ከአሸባሪዎች ጋር፣ ሊቢያ ከአማጽያኑና ከአሸባሪዎች ጋር፤ ባለፉት ሁለት አመታት ደግሞ ኢትዮጵያ ከሽብርተኛው ሕወሓትና ከቡችሎቹ ጋር ለሉዓላዊነቷና ለሕልውናው ስትል ለዛውም ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ተገዳ ወደ ጦርነት ገብታ ስትከላከልና ሽብርተኛው ሲቀጠቀጥ ግን መንግስታቸው ጦርነቱን ለማስቆም ከሚደረግ ጫና ጀምሮ እንደ ሒውማን ራይትስ ዋች ባሉ ተቋማትና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የፈጠራ ክሶችን መደረት ይጀምራል። የሰሞኑን የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ የአውሮፓ ሕብረት፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፤ ወዘተረፈ እንቅስቃሴ ሽብርተኛውን ሕወሓት ለመታደግ የሚደረግ ሌላ ዙር መጋጋጥ ነው። ለዩክሬን ህልውና ጥብቅና የቆመው መንግስታቸው፤ ተገልብጦ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበተን ገሀነም ቢሆንም እወርዳለሁ ካለው አሸባሪው ሕወሓትና ከጋላቢው ግብጽ ጎን ቆሟል።
ሽብርተኛው ሕወሓት በማምታት የድል በለስ የቀናው ሲመስላቸው ደግሞ እምጥ ይግቡ ስምጥ ይጠፋሉ። ባላየ ባልሰማ ያልፋሉ። ይባስ ብለው አገራችንን በወሬ ለመፍታት ተቀናጅተውና ተናበው ይሰራሉ። ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ መብረቃዊ ሲል በአደባባይ በዕብሪት የታየበትን ትውልድም ሆነ ታሪክ የማይረሳውን ክህደትና ጭፍጨፋ ሲፈጽም፤ ለ2ኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ያን ሁሉ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን ግፍ፣ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል።
ቡድኑ ለ3ኛ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ ሲፈጽም፤ የእርዳታ መጋዘን ሲገለብጥና ሲዘርፍ፤ እርዳታ ለማድረስ የተላኩ ተሽከርካሪዎችን አግቶ ለሰራዊት ማጓጓዣ ሲጠቀም፤ ወደ ግማሽ ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ሲዘርፍ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ትግራይን አስመልክተው በጋራ ስላወጡት ሪፖርት፤ ይሄን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቋቋሙት የሚንስትሮች ግብረ ኃይል ሰሞኑን ይፋ ስላደረገው አስደንጋጭ ግኝት፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሽብርተኛው ሕወሓት በወልቃይት ጠገዴና በሌሎች አጎራባች አካባቢዎች የፈጸመውን ዘር ማጥፋት ይፋ ሲያደርግ፤ የይምሰል መግለጫና አስተያየት ለመስጠት የተቸገሩት እነ አሜሪካና ጭፍራዎቿ፤ የሰሞነኛውን የስሚ ስሚና የፈጠራ የኤክስፐርቶችን ሪፖርት ግን ያለሀፍረት ተቀብለው የለመዱትን ጫና መፍጠር ተያይዘውታል።
ሽብርተኛውን ለመታደግ ከኬኒያው ፕሬዝዳንት ሩቶ እስከ ደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎዛ የድረሱለት ጥሪ እያስተላለፉ ይገኛል። ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ኢምቤክም “የባለጠጋውን ልጄን/prodigal son/ሕወሓት” ነገር አደራ በሰማይ አደራ በምድር ብለዋል። በነገራችን ላይ ከዚህ ጀርባ የግብጽና የእስራኤል ፖለቲካዊ ጥልፍልፍ እጅ እንዳለበት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ያም አለ ይህ ሚስተር ብሊንከን እርስዎ ስለ ዩክሬን ከፍ ብሎ እንዳሉት እኛም፤ “ሽብርተኛው ሕወሓት ወረራውን ቢያቆም ፣ ትጥቅ ቢፈታ ሰላም ይወርዳል፤ እኛ መከላከል ብናቆም ግን አያት ቅድመ አያቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን አገር ትፈርሳለች። ነገ በትውልድም በታሪክም ፊት ተወቃሽ እንሆናለን። “መከላከል የሕልውናችን የማዕዘን ራስ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በተባው ብዕራቸው ይሄን እውነታችንን እንዲህ ሸጋ አድርገው ገልጸውታል።
“…ትዕግሥታችን …” አሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የመስቀል በዓልን አስመልክተው በዚያ ሰሞን ባስተላለፉት መልዕክት ፤ “…ትዕግሥታችን እንደ ፍርሃት፣ ሰላም ፈላጊነታችን እንደ ድክመት ተቆጥሮ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ተፈጸመብን። የታገሥነው በዚህም ሆነ በዚያ ወገን የሚያልቀው የእኛው ሕዝብ ነው ብለን ነው። እነሱ ሲከፉ እኛ የለዘብነው፣ የአንድ አገር መንግሥትና የአንድ አገር ዐመጸኛ እኩል ለሕዝብ አያስቡም ብለን ነው። ከጸብ ይልቅ ፍቅር ይሻላል ስንል ምላሹ እብሪት እየሆነብን ጭምር በንግግር ፋንታ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት አላደረብንም። ከጦርነት በላይ ከሰላም እናተርፋለን ብለን እየተወጋንም ቢሆን የሰላም እጆችን ከመዘርጋት አልተቆጠብንም። ሰላም ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይመጣም። በዚህ የተነሣ አገራዊ ሕልውናችንን ለማስጠበቅ ስንል ወደ መከላከል እንድንገባ ተገድደናል። የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጭውም ትውልድ አደራ አለብን።
ኢትዮጵያን ከመጥፋት ለመታደግ፣ ሕዝብን ከብተና ለማዳን እና አገር እንደ አገር ቀጥላ የልጅ ልጆቻችን ሉአላዊት ኢትዮጵያን እንዲወርሱ ስንል የመጨረሻውን የመከላከል አማራጭ ወስደናል። አሁንም እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ይኼንን ታሪካዊ አደራ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል ያሰበ ነው። ለኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ለዓሣ ዋናን ለወፍ መብረርን ማስተማር ነው።
‘ሰላም’ ራሷ የኢትዮጵያ መንግሥት የከፈለላትን ዋጋ ያህል የከፈለላት የለም። የገጠመን ወረራ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከሚፈለግብን በላይ አድርገናል። የእኛን ጥረት በተገቢ መንገድ የሚያወድስና የሌላኛው ወገን እምቢታ በተገቢው ልክ የሚያወግዝ ግን ጥቂት ነው። ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሰላምን የሚመርጡት፣ ጦር ለመያዝ ስለማይችሉ አይደለም፤ ሰላምን ስለሚመርጡ ብቻ ነው። ለሰላም የዘረጋነው እጅ ምንም ዋጋ ስላላገኘ ጦር እንዲይዝ እየተገደደ ነው። …”
አገራችንንም ሆነ ዓለማችንን እዚህ አጣብቂኝ ላይ የጣለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የቁልቁለት ጉዞ ነው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዘመኑን የማይዋጅ ከመሆኑ ባሻገር መንታ መንገድ ላይ ተቅበዝባዥ ሆኗል። የ”ልዕለ ኃያሏ” ዲፕሎማሲም ሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የቁልቁለት መንገዱን ከተያያዘውም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል። በእኛ የተጀመረ በእኛም የሚቋጭ አይደለም። ሪፐብሊካንስ አልያም ዴሞክራቶች መጡ ሔዱ ከተያያዘው የቁልቁለት መንገድ አያስቆሙትም።
አገራችን ሰሞነኛውንም ሆነ መጪውን የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ፍርደ ገምድልነት ለማረቅና አሰላለፏን ከዚህ አንፃር ለመበየን ወይም ስትራቴጂካዊ እይታን ለመግለጥ የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነት የቁልቁለት ጉዞ ከተጀመረበት አንስቶ መመልከት፣ መገምገምና መተንተን ግድ ይላል። በመነሻነት ቢያገለግል በሚል ቅንነት ይህን ስንክሳር በአለፍ ገደም በተከታታይ ክፍሎች ለመቃኘት እሞክራለሁ። የሳትኩት እውነት ቢኖር ለመታረም፣ ይቅርታ ለመጠየቅ አላቅማማም።
ሪፐብሊካኑ ነጩ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ፖሊሲው በአዲሱ ወግ አጥባቂነት ፈለግ ይወሰድና ዴሞክራቶች በእግሩ ሲተኩ ደግሞ ቀኝ ኋላ ይዞርና በሊበራል ዓለም አቀፋዊነት ይመለሳል። በትራምፕም ሆነ በባይደን የታዘብነው ይሄን ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እንዲህ ባለ ውልውል ከመመናተሉ ባሻገር የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አልያም ፕራግማቲስት አለመሆኑ ተደጋግሞ ይተቻል። እንዲያውም እንደ ማይክል ሒርሽ ያሉ አንዳንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱዎችና ፀሐፊዎች ያለርህራሄ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሽፏል እስከማለት ደርሰዋል።
ሪፐብሊካን የነፃ ገበያ አክራሪና የነጭ ወግ አጥባቂዎች ማለትም የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ደጅ ያረገጡ ነጭ አሜሪካውያንና በተለምዶ አንድ በመቶ የሚባሉ ባለጠጎችን ማህበራዊ መሠረት ታሳቢ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዳናን ይከተላል። የባለጠጋዎችን ግብር ይቀንሳል። እነሱን ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደርጋል። ስደተኛን ይጠላል። አያበረታታም። በ”አሜሪካ ትቅደም!” ስም የነጭ ወግ አጥባቂዎችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር ይተጋል። የገበያ ከለላ ይሰጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ድጎማ ያደርጋል። ሉዓላዊነትን እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይሆን እንደስጋት ይቆጥራል።
የመንግሥታቱን ድርጅት፤ የዓለም ባንክን፤ ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም፤ የዓለም የንግድ ድርጅት፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን/ኔቶ/፤ የአውሮፖ ሕብረትን፤ ወዘተረፈ በጥርጣሬ ይመለከታል። ጎልቶ የማይታየው ይህ የቀራጮች ፖሊሲ እድሜ ለትራምፕ አደባባይ ወጥቶ ተሰጥቷል። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ላለፉት 70ና ከዚያ በላይ ጊዜ በዓለም ላይ ለሰፈነው አንፃራዊ ሰላም በባለውለታነት የሚወደሱትን ኔቶንና የአውሮፓ ሕብረት አናንቋል። ያረጁና የጨረቱ ናቸው ሲል በሸንጎ መሀል አጣጥሏቸዋል። አዋርዷቸዋል። ከፓሪሱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እና ከኢራኑ የፀረ ኒውክሌር ስምምነቶች አፈንግጧል።
አገሩ ለዓለም ጤና ድርጅት ታደርገው የነበረውን ድጋፍ አቋርጧል። የእንግሊዝን ከሕብረቱ የመነጠል ውሳኔ ሕዝብ ደግፎ ቆሟል። የአሜሪካንን ዓለም አቀፍ ሚና አቀዛቅዟል። በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን ክፍተት በተለይ ቻይና እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማበታለች። ራሽያም በእንግሊዝ መነጠል፤ በኔቶ መብጠልጠልና በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት ግንኙነት ንፋስ መግባቱ ጮቤ አስረግጧታል። የልብ ልብ እንዲሰማት አድርጓል።
አሜሪካ ስትለቅ ቻይና እግር በእግር ትተካለች። ከሁሉም በላይ ሽንፈቱ አልቀበልም በማለትና ደጋፊዎቹ እንደ አሜሪካ ዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚመለከውን ካፒቶል ሒል በማስወረርና በማስቀመጥ መፈንቅለ መንግሥት የማድረግ ያህል ሙከራ በማድረጉ አሜሪካውያንን ለዘመናት ሲመፃደቁበት የነበረውን ዴሞክራሲ አፈር ድሜ አብልቶታል። ቻይናና ራሽያ ድንቄም ዴሞክራሲ እያሉ እንዲሳለቁ፤ ዴሞክራሲ አይሰራም እንዲሉ አደፋፍሯቸዋል። በአምባገነንነት እንዲመፃደቁና የልብ ልብ እንዲሰማቸው እና አሜሪካውያን እርስበርስ እንዲከፋፈሉ አድርጓል።
የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደግሞ በተቃራኒው በሊበራል ዓለም አቀፋዊነት ላይ መልሕቁን የጣለ ነው። ሉዓላዊነትን፣ ትብብርንና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማስፋት የሚሰራ። ከቀራጮች በተቃራኒው የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ከፍ ብሎ ለተዘረዘሩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማትና ስምምነቶች ተገዥ ነው። ለዚህ ነው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከመግባታቸው የትራምፕን የውጭ ጉዳይና የአገረ ቤት ውሳኔዎች መሻርና መቀልበስ የጀመሩት።
የፓርቲው ማህበራዊ መሠረትም በተለምዶ 99 በመቶ የሚባለው በመካከለኛና በታችኛው መደብ የሚገኘው አሜሪካዊ ነው። ከሞላ ጎደል በማህበራዊ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሚያምን ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ ደጅ የረገጡ ነጭ ሴቶች፣ ጥቁሮች፣ እስፓኒኮችና መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሌሎች አሜሪካውያን የፓርቲው ማህበራዊ መሠረቶች ናቸው። ዳሩ ግን በየራሳቸው አዕማድ የቆሙ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የታለመላቸውን ግብ ማሳካት እየተሳናቸው እንደሆነ ሒሽ ይተቻል። እኛም ከቻይናና ራሽያ ጋር የገባችበትን ቅርቃር፤ በቬትናም፣ በኢራን፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በፊሊፒንስ፣ በቬኒዞላ፣ ወዘተረፈ የቀራጮችም ሆነ የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲከሽፍ ታዝበናል።
አንዳንድ ጉምቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቃውንት ቢቸግራቸው የ99 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ወደ ሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደራሲ እስከ መባል ወደ ሚሞካሸው ሄነሪ ኪሲንጀር ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የታነፀ ዲፕሎማሲ ማማተር ጀምረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሠረቱ ተናግቷል በማለት ማሳያዎቻቸውን ያነሳሳሉ። በቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮት ዓለምን ተከትሎ ያራምደው የነበረው የእመቃ ዲፕሎማሲ በዊልሰናዊያን የተስፋፊነት የተሳሳተ አባዜ ከቬትናም ጋር የተካሄደው ጦርነት የ50 ሺህ አሜሪካዊ ወታደሮች ያስገደለ፤ ከ70 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አክስሯል። ከሁሉም በላይ የሽንፈት ከል አከናንቦታል። የአሜሪካን ገጽታ ክፉኛ ጎድቶታል።
እንዲሁም በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት በአዲሱ የሬጋን “ሰይጣን”አገዛዞችን በኃይል የማስወገድ እርምጃ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ተሞክሮ ከሽፏል። 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ደግሞ የ1950ዎቹንና 60ዎቹን “አሜሪካ ትቅደም!” ፖሊሲ አቧራውን አራግፎ ወደፊት ቢያመጣውም አሜሪካን ነጥሎ ብቻዋን በማስቀረት ከስሯል። ባሪ ጌዌን” The Inevitability of Tragedy” በተሰኘው የሄነሪ ኪሲንጀርና የዛን ዘመን የዲፕሎማሲ አካሄድ በሰነደበትና በተነተነበት ማለፊያ መጽሐፉ”በእርግጥ ሔነሪ ኪሲንጀርን ልትጠላውና ከይሲ ነው ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ልትረሳው አልያም ልትተው ግን አትችልም።
ለዛውም በዚህ ጊዜ። እውነት ለመናገር የኪሲንጀር እሳቤም ሆነ ተፈጥሮው ወይም ደመነፍሱ ክፉኛ ያስፈልገናል።” በማለት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚታደገው ኪሲንጀርና መንፈሱ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። ቀራጮች የሚከተሉትም አዲሱ ወግ አጥባቂነት Neoconservative አልያም ዴሞክራቶች የሚያራምዱት ሊበራል ዓለም አቀፋዊነት Liberal internationalism የአሜሪካን ዲፕሎማሲ ከገባበት ቅርቃር አያወጣውም። ለዚህ ነው ጌዌን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ወደተቀረፀው የሔነሪ ኪሲንጀር የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንመለስ ሲል የሚወተውተው ።
አገራችን ኢትዮጵያ ክብሯንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015