ዝክረ ቀዳማይ ንቅናቄ፤
ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ “አሻራ” የሚለው ቃል ወደ ሕዝባዊ የዘወትር ቃልነት ከፍ ብሎ በሁሉም ዜጎች አፍ እየተጠቀሰ ይገኛል:: ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው:: በየክረምቱ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ንቅናቄ “አረንጓዴ አሻራ” በሚለው መሪ ቃል በየቋንቋዎቻችን ከትንሽ እስከ ትልቅ ከዳር ዳር በተነቃቃ መንፈስና በፍቅር ተወዶ “ስለሚዘመርለት” ለሁሉም ዜጎች ቤትኛ ወደመሆን ደረጃ ከፍ ብሏል::
በዚህ ታላቅ የየዓመቱ ንቅናቄ (በተለይም ባለፉት አራት ክረምቶች ውስጥ) በመላው አገሪቱ ከሃያ ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለው ኢትዮጵያን አረንጓዴ ሥጋጃ አልብሰዋታል:: ይህን መሰሉ ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከራስ ድንበር ተሻግሮ ትሩፋቱ ለጎረቤት አገራትም ጭምር ለመትረፍ ችሏል:: ለተገኘው ስኬት ለባለ ራዕዩ መሪያችን፣ ለአስፈጻሚዎቹ አካላትና ለመላው ሕዝባችን ምሥጋናና አክብሮት ይገባቸዋል::
የተተከሉት ችግኞች ፋይዳ ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ብቻም ሳይሆን ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጤንነትም ሳይቀር በጎ ተጽእኖው የጎላ መሆኑ ውጤቱ ምስክር ነው:: በንቅናቄው የተገኘው ይህ ውጤት በምድራችን ላይ በሚታተሙ የድንቃ ድንቅ የህትመት ውጤቶች ላይ ሳይቀር ጎላ ባሉ አርእስት ለመተዋወቅ መቻሉ ለመኩራራት ሳይሆን ለብርታት ጥሩ አቅም ሆኖናል::
በዘመቻ መልክ የተጀመረው ይህ “የአረንጋዴ አሻራ” ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደፊት የጋራ ባህላችን ቋሚ መታወቂያ ወደ መሆን ደረጃ ከፍ እንደሚል ጅማሬው ለፍጻሜያችን ማረጋገጫ እንደሚሆንም መመስከሩ አግባብ ይሆናል:: የክረምቱ ወራት ተፈጥሯዊ ድርሻውን አጠናቆ ስለተሰናበተ ለተከልናቸው ችግኞች የእንክብካቤውን ጉዳይ ባለመታከትና ባለመሰልቸት በአግባቡ እንድንወጣ የተፈጥሮ አደራ በእጃችን ላይ የወደቀ ስለሆነ “የአረንጓዴው አሻራችን” ወይቦ “አደራ በል በመሆን” እንዳንወቀስ ክትትላችን ሊቋረጥ አይገባም::
የሁለተኛው ምዕራፍ “የደም አሻራ” ንቅናቄ፤
አደጋ ላይ የወደቀውን የአገር ሉዓላዊነት ከአሸባሪ ወራሪዎች ለማጽዳት የሚደረገውን ታላቅ የተጋድሎ ፍልሚያ በሁለተኛ የንቅናቄ ምዕራፍ መስዬዋለሁ:: ግፈኛው ሕወሓትና በእርሱ እኩይ ማህጸን ውስጥ የተፈለፈሉት የእንግዴ ልጆች ያፈሰሱት የንጹሐን ዜጎቻችን ደም፣ ያወደሙት የአገር ሀብትና የሥነ ልቦና ጉዳት ብዛት በዝርዝርም ሆነ በስፍር ተቆጥሮም ይሁን ተመዝኖ ይህን ያህል ነው ተብሎ ውጤቱን በምልዓት ለመግለጽ ከቶም የሚቻል አይደለም:: የወደቀብንን የመከራ አሳር በአግባቡ አጥርቶ ለታሪክ ፍርድ ለማስተላለፍም ብዙ ጊዜ፤ ምናልባትም በዓመታት የሚቆጠር ልፋት ሊጠይቅ እንደሚችል ይገመታል::
ሕወሓት የሚሉት ይህ “የሳጥናኤል መልእክተኛ” ከምድሪቱም ላይ ብቻ ሳይሆን ከታሪካችን ገጽ ላይ ጭምር ግብሩም ሆነ ስሙ ተፍቆ እስካልጠፋ ድረስ ኢትዮጵያና ጎረቤት አገራት በሰላም ይኖራሉ ማለት ዘበት ነው:: ይህ እኩይ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በመደበኛ የጦርነት ስልት፣ በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በፈለፈላቸውና “የመገንጠል ጡጦ እያጠባ” ባሳደጋቸው እርካሽ ቡድኖች የፈጸሙትና እየተፈጸሙ ያሉት አረመኔያዊ ድርጊቶች ከጆሯችንና ከዕይታችን እየደረሱ ያለው ተቆንጥረው እንጂ በሚገባ ተዘርዝረው አይደለም:: ወደፊት ሰይጣናዊ ድርጊቶቹ በጥናት ተደግፈው በይፋ መገለጥ ሲጀምሩ ምናልባትም ከናዚና ከፋሽስት ወራሪዎች ድርጊት ጋር መቀራረብ ብቻ ሳይሆን በዓይነትም ሆነ በቁጥር ስለሚገዝፉ እንደየባህርያቸው ተመዝግበው ለታሪክ መተላለፋቸው አይቀርም::
አገሪቱንና ሕዝባችንን መከራ ላይ የጣለው ይህ የሕወሓት ወረራ እየተቀለበሰ ያለው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንንና በልዩ ልዩ አወቃቀር ተደራጅተው በፍልሚያው ጎራ ላይ የሚዋደቁትን የሕዝባዊ ኃይል አባላት የደም አሻራ እያስከፈለ መሆኑ በሚገባ ይታወቃል:: ይህ የደም ግብር እየተከፈለ ያለው ፍልሚያው በሚካሄድበት የጦርነት ቀጣና ብቻ ሳይሆን ንፁሐን ዜጎች “አገር ሰላም” ብለው በተቀመጡበት የመኖሪያ ቤታቸውና አካባቢያቸው ድረስ ዘልቀው በገቡ ጨካኝ ወራሪዎች መስዋዕትነት ጭምር መሆኑም አይዘነጋም:: ይህን መሰሉ የጨካኞች ክፋት የሚዳኘው በምድራዊ ፍትሕ ብቻ ሳይሆን በሕያው አምላክ ዙፋን ፊትም “በይግባኝ” እንደሚሞገቱ አልገባቸው ከሆነ ይግባቸው:: ካሻም የደነደነ ልባቸውንና ጆሯቸውን ከፍተው የአካባቢያቸው የሃይማኖት አባቶች ምን ምላሽ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ ይጠይቋቸው::
በየግንባሩና በየግዳጅ ቀጣናው ሉዓላዊነታችንን “በደም አሻራቸው” እያተሙልን ላሉት የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የጥምር ጦር አባላትና በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ለታቀፉት ጀግኖቻችን ታላቅ ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው:: በሁለተኛው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምዕራፍ የተወከለው ይህ የአገርን ክብር የማስጠበቅ ፍልሚያ ተጠናቆ ወደ ፍጻሜ እየተቃረበ መሆኑም በእጅጉ ያጽናናል:: በደም የታተመው ይህ ሕዝባዊ አሻራ ከትወልድ ትውልድ ተሸጋግሮ በጀግንነት ሲተረክ መኖሩን የምናውጀው በይሆናል ተስፋ ተሞልተን ሳይሆን እውነታችንም እምነታችንም ስለሆነ ነው:: ስለዚህም ከድል በኋላ መቀጠል ስለሚገባው አገራዊ ጉዳይ ቀድመን መወያየቱ ተገቢ ስለሆነ በተከታዩ ንዑስ ርዕስ ሥር ለማሳየት የሚሞከረው ከባዱንና ለሕዝባዊ ንቅናቄ የሚያዘጋጀንን ሣልሳዊው የቤት ሥራ ይሆናል::
ሣልሳዊውና ቀጣዩ “የላብ አሻራችን” ምዕራፍ፤
ይህ ጸሐፊ ይህንን ሃሳብ የሚያብራራው እንደ ላይኞቹ ንዑሳን አርእስት በደስታና በመነቃቃት ስሜት ውስጥ ሆኖ ብእሩን እያጀገነ አይደለም:: ይልቁንስ በቁዘማና በቁጭት ውስጥ ሰጥሞ እየተከዘ እንጂ:: “በላብ አሻራ” የተወከለው ዋና ጉዳይ “የሥራ ባህላችንን” የሚመለከት ነው:: ርዕሰ ጉዳዩ ብዙ ስለሚያወያይ ጊዜና ወቅት ሲፈቅድ በስፋት መወያየቱ ስለሚመረጥ ለጊዜው የጥቆማ ያህል ጠቅሰን የምናልፈው ዋናውን አንኳር ሃሳብ ብቻ ይሆናል::
በኢኮኖሚያቸው የበቁና በአስተሳሰባቸው “መጥቀዋል” የሚባሉት አገራት ወቅታዊውና አሳሳቢው ችግራቸው ዜጎቻቸው ከመጠን በላይ በሆነ የሥራ ጫና የመጠቃታቸውና የሟቾችም አሀዝ እያሸቀበ የመሄዱ ጉዳይ ነው:: በዚህ መሠረታዊ ችግር ከተጠቁት አገራት መካከል ጃፓኖች የቀዳሚውን ድርሻ ይዘዋል::
ጃፓኖች ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ተስኗቸው ሥር ሰዶ የዜጎቻቸውን ሕይወት እየቀጠፈ ፈተና የሆነባቸው “የሥራ ፍቅር መውደድ/ጫና” በቋንቋቸው ካሮሺ (Karoshi) “Death from over work” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል:: ይህ ስያሜ በጃፓን ቋንቋ ውስጥ ጎንኖ ለመውጣት የቻለው እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ዓመታት ውስጥ ሲሆን በእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ገብቶ ብዙ የዓለማችን አገራት ቃሉን መዋስ የጀመሩት ደግሞ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ2002 ውስጥ ነበር::
ጃፓኖች የረጂም ታሪክ ባለቤቶች፣ ጠንካራ የመከባበር ባህል ያላቸው፣ ትህትናቸው፣ ሥነ ሥርዓት አጠባበቃቸውና ለሥራ ያላቸው ክብር በዋነኛነት የሚታወቁበት መለያቸው ነው:: ይህንን በሥራ ውጥረት የሚፈጠር ድንገቴና አስደንጋጭ የሞት መርዶ ጉዳይ በተመለከተ በዲፕሎማቱ ደራሲ በአሰፋ ማመጫ አርጋው ተጽፎ በቅርቡ ለህትመት የበቃው “የጃፓን መንገድ ” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝርና በግልጽ ቋንቋ ተብራርቶ ስለቀረበ ለተጨማሪ መረጃ መጽሐፉን ማንበብ ይቻላል::
“የእንግሊዙ ቢቢሲ የዜና ማሰራጫ በሥራ ጫና ምክንያት የሚሞቱትን የጃፓን ሰራተኞች በተመለከተ በሠራቸው በርካታ ጥናቶች ለማሳየት እንደሞከረው ዋነኛው ሰበበ ምክንያት የራሳቸው የጃፓኖቹ አፍቃሬ የሥራ ባህርይ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችሏል:: ረዘም ላለ ጊዜም ሆነ ለአጭር ቀናት ከመደበኛ ስራ ለማረፍ እረፍት መጠየቅ ሥራን እንደመሸሽና እንደ ስንፍና ስለሚያስቆጥር ሠራተኞቹ ዓመታዊ እረፍት ከሚጠይቁ “ሞታቸውን” እንደሚመርጡ ሪፖርቶቹ በግልጽ ያስረዳሉ::
እረፍት የሚጠይቁ ሠራተኞች በአለቆቻቸው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው ዝቅ ማለቱ ሌላው ፍርሃታቸው መሆኑም በጥናቶቹ ተረጋግጧል:: የጃፓኖች የሥራ ባህርይ በአብዛኛው በቡድን ሥራዎች ላይ መመሥረቱም የአንድ ሰው ከሥራ ገበታ ላይ መቅረት በሌሎቹ ሠራተኞች ዘንድ ውጤታቸውን ስለሚያሳንስ ይህም እረፍትን እርም ለማለት ሌላው ምክንያታቸው ነው::
በጃፓን የሥራ ባህል የቅርብም ሆነ የበላይ አለቃ እንደ ጌታ እንጂ እንደ ሥራ መሪ ያለመቆጠሩም አደጋው እንዲከፋ ያደረገ ሌላው ምክንያት ነው:: ሠራተኞች የዕዝ ሠንሠለታቸውን በጥብቅ ማክበር ይጠበቅባቸዋል:: ከቅርብ አለቃ ጋር መጨቃጨቅ ወይም አለቃን መክሰስም ሆነ መውቀስ ያልተለመደ ብቻም ሳይሆን ስለመሞከሩም የሚያጠራጥር ነው:: “አለቃ ሁልጊዜ ትክክል ነው” የሚለው መርህ ለጃፓኖች ዋነኛው የሕይወታቸው መርህ ነው::
የጃፓን የሥራ ሚኒስቴር ባካሄደው ጥናት በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠሩ የአገሪቱ ሠራተኞች በሳምንት ከ60 እስከ 90 ሰዓታት መሥራታቸው ተረጋግጧል:: በዚህ ምክንያትም ከ90% በላይ ሠራተኞች ማሕበራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ሥራ ገበታቸው ላይ መገኘትን እንደሚመርጡ በተሰራው ጥናት ሊረጋገጥ ችሏል:: እነዚህ ምክንያቶች ተዳምረው ነው የጃፓን ዜጎች በውጥረት እየተጠቁ “መደበኛ ሥራቸው” ለሞታቸው ምክንያት ሊሆን የቻለው::
እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2021 በተጠና ጥናት በጃፓን ውስጥ በየዓመቱ ከሥራ ውጥረት የተነሳ የሚሞቱት ዜጎች በ2472 – 1935 ቁጥር ውስጥ እንደሚወድቁ ጥናቶች ያመለክታሉ:: ይህንን አደገኛ የሥራ ጫናና የሞት ግስጋሴ ለመግታት በየጊዜው የሥራ ሰዓትን ለመቀነስና ዜጎቹ እረፍት እንዲወስዱ ለማበረታት በርካታ ሕጎችን የሚያወጣው የጃፓን መንግሥት እንዳሰበው ስላልተሳካለት ጥረቱን እንደቀጠለ ነው::
የአገራችን ገመና!
የሰለጠኑት አገራት ከፍላጎታቸው በላይ በሥራ ውጥረት እየተሸነፉ ለሞት ሲዳረጉ እኛ ግን መሥራት እየተሳነን በርሃብ ለማለቅ መገደዳችን ለዕንቆቅልሻችን ውስብስብነት ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል:: አንኳን ትርፍ ሰዓት ሠርተን ከጉስቁልና አረንቋ ለመውጣት ቀርቶ በተመደበልን የስምንት ሰዓት ጊዜ ውስጥ እንኳን በአግባቡ ለመሥራት የሥራ ፍላጎታችን ሐሞት ቀጥኖ ወኔያችን ተሰልቧል::
በእኛ ባህል ለአብዛኞቻችን በሥራ ከመትጋት ይልቅ “መለገም” ባህላችን እንዲሆን ለራሳችን ያጸደቅን ይመስላል:: “ጽድቁ ቀርቶ፤ በቅጡ በኮነነኝ” ብላ ተርታለች እንደምትባለው ሆደ ባሻ እህት እኛም ስለሌሎች አገራት የሥራ ውጥረት ከመዘርዘር ይልቅ የራሳችንን “ገመና” አራቁተን ንስሃ መግባቱ ይበልጥ ይረዳን ይመስለናል::
የማይነጻጸረውን ለማነጻጸር የሞከርነውም ቢቸግር መሆኑ ሊታወቅ ይበገባል:: በየመንግሥታዊ ተቋማት ለሥራ ሰዓት የሚሰጠውን ግምት፣ ተወስኖ የተሰጠን አንድን ሥራ በወቅቱ ለማጠናቀቅ የሚፈጀውን “ምጥና ጣር” እየዘረዘርን መተንተኑ “ለቀባሪው ከማርዳት” ስለማይተናነስ “ኅሊናችን ይፍረደው!” ብሎ በመደምደም ዘርዘር በሚል ሌላ ትንታኔ ዳግም መገናኘቱ ይበጅ ይመስለናል:: ለማንኛውም በመለገም ያከማቸነው ላባችን “በፍርድ ቀን” ከሳሻችን ሆኖ እንዳይሞግተን ከወዲሁ ለተግባራችን አክብሮት ሰጥተን “በላባችን ወዝ ጥረን ግረን መብላትን” እንለማመድ:: የሣልሳዊውና ቀጣዩ “የላብ አሻራችን” ምዕራፍ ተጋድሎ ሊሆን የሚገባው የማጠቃለያ ሃሳብም ይሄው ነው:: ሰላም ይሁን
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015