መንግሥት ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። የኢትዮጵያን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ የሰላም ድርድር ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክሯል። በሰላማዊ መንገድ ጦርነቱ እንዲቋጭ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አስመስክሯል። በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር ሰላማዊ ድርድር ለማድረግ ወንበር እስከመሳብ ተጉዟል። የጥረቱ ውጤት ፍሬ እስኪያፈራ እንደሚቀጥልም ይታመናል።
የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ግን በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር የቀረበለትን የሰላም ድርድር ረግጦ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነትና ወረራ ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትም ባቀረበው የሰላም አማራጭ ፋንታ የተከፈተበትን የእብሪት ወረራና ጦርነት በተባበረ ክንድ በመመከት ላይ ይገኛል። በዚህም በጀግናው የሀገር በመከላከያ ሠራዊት የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ጦር አሸባሪውን ቡድን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር በመገደዱ ሕወሓት ራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ይገኛል።
“የሚያጠግብ እንጀራ፤ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ፤ የመከላከያ ሠራዊትና ጥምር ጦሩ የተከፈተበትን ወረራ በሚገባ ከመመከት አልፎ በድል አድራነት ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛል። ይህም የአሸባሪ ቡድኑ ፍጻሜ እየተቃረበ መሆኑን በልበ ሙሉነት እነድንገምት ድፍረት ይሰጠናል። ግምታችን በእጅጉ ለእውነታው የቀረበ መሆኑን የሚያጠናክርልን ደግሞ ከሰሞኑ በተለያዩ ግንባሮች የተማረኩ የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች በገዛ በአንደበታቸው የሰጡት ምስክርነት ነው።
በበኩሌ በውድም በግድም ከአሸባሪው ቡድን ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ሲወጉ የነበሩ የወራሪው ኃይል ታጣቂዎች የሰጡት ምስክርነት የሽብር ቡድኑ ፍጻሜ ሩቅ አለመሆኑን የሚያመላክት ከመሆኑ ባሻገር፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት የሚሰጥ እንደሆነም ይሰማኛል። ይህን ያልኩበት ምክንያት ደግሞ ምርኮኞቹ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ትግራይን ከአሸባሪው ቡድን መፈንጫነት ነጻ ማውጣት አለበት” በማለት በተሰበረ ልብ ከሕሊና ሊጠፋ የማይችል ተማፅኗቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሲያቀርቡ በመስማቴ ነው።
በእርግጥም በመከላከያ ሠራዊት የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ጦር ምንም እንኳን ወደው የአሸባሪውን ቡድን የተቀላቀሉ ባይጠፉም ያለፍላጎታቸው ተገድደው ለጦርነት እየተማገዱ የሚገኙ በርካቶች ናቸውና እንዲህ ዓይነት ተማፅኖዎች ሕልም እውን የሚሆንበትና የትግራይ እናቶች እንባ የሚታበስበት ሩቅ እንዳልሆነ ይሰማኛል።
ባለፉት ጊዜያት ሕወሓት በተለያዩ ማታለያዎችና “ተባብረው ሊያጠፉህ ነው” … በሚሉ የሃሰት ትርክቶች በማነሳሳት የትግራይን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ ሞክሯል። በዚህ የውሸት ፕሮፓጋንዳውም ሆን ብለው ዓላማውን የሚደግፉ ተባባሪዎቹና የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዳሉ ሆኖ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡን ልብና ቀልብ መሳብ ችሎም ነበር።
አሁንም የጥምር ጦሩ የሚያካሄደውን መከላከል ተከትሎ የአሸባሪው ቡድን የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ባልተለመደ መንገድ ብቅ እያሉ ካሸንፈናል እስከ ድረሱልን የዘለቀ ዲስኩር፣ ፉከራና ልመና እየቀላቀሉ እንደለመዱት ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ለማደናገር እየዳከሩ ይገኛሉ።
ይሁን እንጅ በጊዜ ሂደት የአሸባሪው ቡድን ሀገር አፍራሽ ዓላማና በንጹሃን ደም ይህንን እኩይ ዓላማውን የማሳካት የፖለቲካ ቁማሩን ዓለም እየተገነዘበው የመጣ ይመስላል። የአሸባሪው ቡድን ጩኸቱ የውሸት ዲስኩር እንደሆነ ዘግይቶም ቢሆን የዓለም ሕዝብ ሆነ የትግራይ ሕዝብ በሚገባ እየተረዳው መጥቷል። በመከላከያ ሠራዊትና ጥምር ጦሩ የተማረኩ የአሸባሪው ተዋጊዎችም በገዛ በአንደበታቸው እየመሰከሩት የሚገኙትም ይህንኑ ሐቅ ነው።
የሕወሓት ማታለያ መንገድ ብዙዎቻችሁ የምታውቁት የውሸታሙን እረኛ ታሪክ አስታወሰኝ። ሌሎችን በማታለል የሚዝናናው ውሸታሙ እረኛ ቀበሮ መጥቶ በጎቹን እየበላበት እንደሆነ አድርጎ የድረሱልኝ ጥሪ በጩኸት በማቅረብ አላፊ መንገደኞችን ይሰበስባል። መንገደኞቹ ለእርዳታ ሲመጡ ታዲያ ቀበሮው በገሀዱ ዓለም ያለ ሳይሆን የእረኛው የምናብ ውጤት መሆኑን ይረዳሉ። በእረኛው ድርጊትም እየተበሳጩ ወደመንደራቸው ይመለሳሉ።
አሸባሪው ቡድንም “የትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ተፈጸመ፤ ንጹሃን በግፍ ተጨፈጨፉ”… እያለ ዓለም እስኪታክተው ድረስ አደንቋሪ የውሸት ጩኸቱን በተደጋጋሚ አሰምቷል። ጩኸቱን ሰምተው ስለሁኔታው ሊረዱት የሞከሩት ሁሉ በመጨረሻ እየተገነዘቡት የሚገኙት ግን የውሸታሙን እረኛ ታሪክ ዓይነት ነው። ይኸውም ሕወሓት የሚለፍፈው የንጹሐን ጭፍጨፋም ሆነ የዘር ማጥፋት ሕልውናውን ለማስቀጠልና ዕድሜውን ለማራዘም በውሸት የፈበረከው ምናባዊ ቅዠት እንጂ በተግባር የትግራይን ሕዝብን የሚጎዳ አንዳች አካል አለመኖሩን ዘግይቶም ቢሆን ዓለም እየተረዳው መጥቷል። የቡድኑ ጩኸትም የውሸታሙ እረኛ ከንቱ የድረሱልኝ የማጭበርበሪያ ጩኸት መሆኑን አብዛኛው የዓለም ሕዝብ እየገባው መጥቷል።
በመሆኑም ይህንን እውነታ ዛሬ ላይ መረዳት የቻሉ ትግራዋይ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመዋል። የሕወሓት የምናብ አውሬን አምነው የተቀበሉት የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ግን ዛሬም የአሸባሪውን እድሜ ለማራዘም ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል። የሰሞኑ የሕወሓትና የውጭ ጠላቶቻችን ሽፍንፍን የሠላም ዲስኩር ሲገለጥ የሚያመላክተውም ይሄንኑ ነው። አሸባሪው ቡድኑ በአፈ ጮሌው ጌታቸው ረዳ፤ በሀገር አዋራጁ ታደሰ ወረደ በኩል የሰላም ጥሪን አሰምቷል።
ከመጋረጃው ጀርባ ያሉ የሕወሓት ጌቶችም ጊዜ ለመግዛት የተመዘዘችውን ሽፍንፍን የሠላም ዲስኩር አብረው ሲያስተጋቡ የተደመጡትም ለዚህ ነው። ይህ የተናበበ የጋራ ጩኸት ሁለት መልክ ይሰጠናል። በአንዱ በኩል በመከላከያ ሠራዊትና ጥምር ጦሩ አሸባሪው ቡድን የደረሰበትን ጥቃት መቋቋም የተሳነው መሆኑን በመሆኑም በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ ራሱን ለማዳን እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ ያመላክተናል።
ሁለተኛው መልክ ሕወሓት የሀገር መከላከያና የጥምር ጦሩን ወደፊት ግስጋሴን ለመግታት የተለመደውን ‘ሠላም’ የሚለውን ካርድ የመዘዘ መሆን ይጠቁመናል። ሕወሓት የተጠቀመው ማዘናጊያ የሚያመላክተው ቡድኑ ካረጀው የፖለቲካ ርዕዮት ዓለሙ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሻገተው የውጊያ ስልቱ ጋር ዛሬም ድረስ አብሮ እየኖረ መሆኑን ነው። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ ይህን ዓይነቱ አሰልቺ የማዘናጊያ ታክቲክ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ቀድሞ የተረዳው እውነታ ነው።
የበድኑ ሽፍንፍን የሠላም ዲስኩር መዳረሻው በሠላማዊ ድርድር ይደረግ ሽፋን አከርካሪው እየተመታ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን እንዲያንሰራራ ለማድረግ ታልሞ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በተራዘመ ጦርነት ውስጥ እንድትቆይ ለሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። እናም የውጭ ጠላቶቻችን ህልም ሕወሓትን አጠናክረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም ለባርነት ለመዳረግ እየሄዱበት ያለውን ርቀት ይጠቁመናል። የኢትዮጵያን ውድቀት የሚሹ የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን እንዲህ በመናበብ እየሰሩ ይገኛል።
ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን ለማዳን በተባበረ ክንድ ብንነሳ ምን ይገርማል? የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ቡድን የፖለቲካ መቆመሪያነት፤ የኢትዮጵያ ራስ የሆነውን የትግራይ ምድር ከአሸባሪ መፈንጫነት ለማላቀቅ የሚደረገው ተጋድሎ ዳር ሳይደርስ ማቆም አይገባም። የሕወሓትን ሰሞነኛ ዕድሜን የማራዘም ሽፍንፍን ታክቲክ በሚገባ አጢኖ መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ጦሩ የመከላከሉን ውጊያ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ለዚህም ለሰላም በሩን ዘግቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ መንግሥትም የዘረጋውን የሰላም እጁን ሳያጥፍ ከገዛ አብራኳ ወጥቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚተጋውን መርዘኛውን ጠላቷንና መጥፋቷን የሚፈልጉ ጠላቶቿ ሁሉ ተሸካሚና አስተላላፊ የሆነውን ክፉ ተውሳክ ሕወሓትን ለሀገርና ለሕዝብ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ይጠበቅበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብም በስንቅ፣ በገንዘብ፣ በሞራል እና በተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የሚያደርገውን ድጋፍና የመከላከያ ሠራዊቱ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የአሸባሪውን ሕወሓት በንጹሃን ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጭፍጨፋ፤ ሀገር አፍራሽነት እና ጸረ ሰላም ባህሪውን ማስገንዘባቸውን አጠናክረው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መንገድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመተባበር ሠላማዊ ድርድርን አሻፈረኝ ያለውን አሸባሪ ቡድን በፈቀደውና በሚገባው መንገድ አነጋግሮ ማስጨረስ ተገቢ ነው።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2015