ዶክተር ጋሹ ሃብቴ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የያዙ፤ በጅማ እርሻ ኮሌጅ በመምህርነት፣ በትምህርት ክፍል ኃላፊነት፣ በኮሌጅ ዲንነት እና የተማሪዎች ዲን በመሆን አገልግለዋል። በመቀጠልም በኦክለሁማ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ የሰሩ ሲሆን፤ በአርከንሰስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነው አገልግለዋል። አሁን ላይ በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛል። በዛሬው የአዲስ ዘመን የነጻ ሃሳብ አምድም የከፍተኛ ትምህርት ጥቅምን መሰረት በማድረግ በዓለም አገራት ያለበትን ደረጃ በማመላከት በኢትዮጵያ ያለውን ሁነት በሚከተለው መልኩ ለአንባብያን ይድረስልኝ ብለው አቅርበዋል።
ከፍተኛ ትምህርት በማንኛውም አገር ዜጎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በተለያየ ደረጃ የሚከታተሉት የትምህርት ደረጃ ነው። ከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት በተለያዩ አገራት በተለያየ አቀራረብ ለዜጎች የሚሰጥ አገልግሎት ነው። ይህ የተለያየ የከፍተኛ ትምህርት አሰጣጥ አገልግሎት በተለያዩ አገራት የተለያየና እጅግ በጣም የተራራቀ ደረጃ አለው። በዘርፉም የሚሰጠው አገልግሎት የተለያየ በመሆን ለህብረተሰብ የሚሰጠው የጥቅምና ለውጥም እንደተሰጠው የትምህርት ደረጃ እና አገልግሎት ይለያያል።
የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማው በዚህ ረገድ አገራችን የት ነው ያለችው የሚለውን ለመዳስስ ሲሆን፤ ለፖሊሲ አውጭዎችም የከፍተኛ ትምህርትንም አስፈላጊነት በተመለከተ አቅጣጫ ይሰጣል የሚል ግምት ስላለኝ ነው። አሁን ስላለው የተለያዩ ደረጃ ጠለቅ ብለን ከማየታችን በፊት ለመሆኑ የከፍተኛ ትምህርት በአጠቃላይ ሲታይ የሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ማየቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ስራቸው መሆንና ማካተት ያለባቸው የሚከተሉትን 5 ዋና ዋና አገልግሎቶችን ነው።
1ኛ. የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በዋነኝነት የሚታወቁበትና የሚታየው የማስተማር አገልግሎት ነው። በርካታ ተቋማት ይህን የማስተማር አገልግሎት በመስጠትና ዜጎችን በተለያየ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ለአገርና ለእራሳቸው የሚውል አገልግሎቶች ይሰጣሉ። በዚህ ረገድ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገሮች ለዜጎቻቸው የሚሰጡት የማስተማር አገልግሎት የተለያየ ደረጃ ያለው ሲሆን፤ ይህን እንደየአገሮቹ አቅም፣ ጥረቶችና ለትምህርት እንደሚሰጡት ዋጋ ይለያያል። በየአገሩ ያለው የተማረ ሰው ቁጥር መለያየት በተለያየ ምክንያት ቢሆንም ዋነኛዎቹ ግን የመንግስትና የአገር አቅም፣ ጥረትና ትኩረት ዋነኛውን ሚና ይጫወታሉ።
2ኛ. የአብዛኛው ወይም የብዙዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረትና አገልግሎት የጥናትና ምርምር ስራ ነው። በዓለም ዙሪያ ባሉ አገሮች ሁሉ እጅግ የተማረ ሰው በብዛት ከሚታይባቸው ተቋሞች ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት አንዱና ከፍተኛውን ቦታ የያዘ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። በግል ችሎታቸውም ሆነ በአመችነቱ የከፍተኛ ትምህርት መምህራን ከብሔረሰብ ተኮር እስከ አገራዊ እና አለማቀፋዊ በሆኑ ጉዳዮች በመመራመር አዲስ ግኝቶችንና ላለ ችግር መፍትሄ የሚሆኑ አገልግሎቶችን በመስጠት ይታወቃሉ። ስለሆነም ይህ አቅም፤ የአመራርና የአላማ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሌላው ዋናው የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ኃላፊነት ነው። በዚህ ረገድ በከፍተኛ ትምህርት መምህራን የተገኙ የጥናት ውጤቶች ለዓለም ህብረተሰብ በተለያየ ዘርፍ እድገት እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል።
3ኛ. የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ኃላፊነትና የስራ ድርሻ ለአካባቢ እድገት አገልግሎት መስጠት ነው። (outreach program) ይህ በአብዛኛው ጎልቶ የሚታየው በእርሻ፤ በጤና፤ በትምህርት፤ በከተማ ልማትና በሌሎች አገልግሎቶች የሚሰለጥኑ ተማሪዎችና መምህራን የሚሰጡት አገልግሎት ነው። በአደጉ አገሮች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዚህ አገልግሎት ዘርፍ እጅግ በጣም ሰፊና ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። በአገራችንም የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፤ የጅማ የእርሻ ኮሌጅና በሌሎችም ተቋሞች፤ በዚህ ረገድ ጠንካራ ፕሮግራም እንደነበራቸው ይታወቃል። መምህራን ከማስተማርና ከመመራመር ስራቸው በተጨማሪ በዋነኝነት የከፍተኛ ትምህርት ቤት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚያከናውኑት ኃላፊነት ነው። በማስተማር የበለጸገ እውቀትንና በምርምር የሰላ ችሎታን በተግባር ላይ በማዋል ለአካባቢ ህብረተሰብ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እና ስራ በተለይ በሰለጠኑት አገሮች እጅግ በጣም ከፍተኛ ውጤትና ጥቅም ያስገኘ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች የአገልግሎት ዘርፍ ነው።
4ኛ. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ድርሻ ችሎታው ኑሯቸው መማር ወይም መሳተፍ ላልቻሉና የተወሰነ ደረጃ ተምረው የሚቀጥለውን የትምህርት ደረጃ መማር ለሚፈልጉ የተለያዩ ትምህርትን (continuing education or extinction education) የመስጠት ኃላፊነት ነው። በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በርካታ ዜጎች በመደበኛ ትምህርት ለመማር ያላገኙትን እድልና ተሳትፎ እንዲያገኙ የሚያደርጉበት አገልግሎት ነው። በተለያየ ምክንያት ችሎታው ሳያንሳቸው መማር ላልቻሉ አገልግሎት የመስጠትና በሚሳተፉበት ስራ ምርታማ እንዲሆኑ ለዜጎች የሚሰጥ አገልግሎት ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ አገሮች እጅግ አድርገው ለዜጎቻቸው ከፍተኛ ትምህርት እንዲዳረስ አድርገዋል። ታዳጊ አገሮች ግን ብዙም ትኩረት ያልሰጡት የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ አገልግሎት ተምረው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም ይህ ዘርፍ በህብረተሰቡ ብዙ የማይታወቅና የሚወራለት የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት አይደለም።
በ1988 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን የከፍተኛ ትምህርት በተለያዩ አህጉራት ምን እንደሚመስል የሚያጠና በርካታ ቡድን ልኮ ነበር። በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከፍተኛ ትምህርት ምን እንደሚመስል የሚያጠኑ ሁለት አንጋፋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ሪፖርትን እንደማስታውሰው፣ በጠቅላላው በኢትዮጵያ ያሉ 3 ዩኒቨርሲቲ እና 6 ኮሌጆች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ አስመራ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ እርሻ ኮሌጅ፣ አምቦ እርሻ ኮሌጅ፣ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት፣ የኮተቤ ኮሌጅ፣ የፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤትና የናዝሬት ቴክኒካል ትምህርት ቤት) ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር 18,000 ገደማ ሲሆኑ በግብጽ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የተከታታይ ትምህርት ተማሪዎች ቁጥር 12,000 እንደነበረ ሪፖርት መደረጉ አስታውሳለሁ። ስለዚህ አገሮች በዚህ አገልግሎት ትኩረት በመስጠት ለዜጎቻቸው ከፍተኛ ትምህርት አገልግሎትን በማዳረስ የዜጎችን ምርታማነትና የስራ እድል መለወጥ እንደሚቻል መጤን አለበት።
5ኛ. የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በየአካባቢው በተለያየ ደረጃ የስራ እድልን በመክፈት በርካታ የአካባቢ ነዋሪዎች የስራ እድል እንዲያገኙ በማድረግ ይረዳሉ። በተጨማሪም ዘመናዊ አኖኑዋርን (ትምህርት፤የጤና፡ ቤተሰብ አያያዝንና በርካታ አገልግሎቶችን) ያሳድጋል።
በዚህ አገልግሎት ዘርፍና ሌሎችም ካሉ ይህን ጉዳይ ለምን ማንሳት አስፈለገ ለሚሉ ከወዲሁ መልሱ ከፍተኛ ትምህርት መስፋፋትና መብዛት ለአገር እድገትና ለዜጎች የተሻለ ሕይወት መኖር በርካታ አገልግሎቶችና ጥቅም ስላለው ነው። ዘርዘር ባለ መልኩ ሊጠቃለሉ ከሚችሉ የከፍተኛ የትምህርት ጥቅሞች መካከል፡-
• የተማረ ዜጋ ለአገሩና ለሌሎች የሚተርፍ የመፍጠር ችሎታ (critical thinking and innovative personality) ሊኖረው ይችላል። ይህም የፈጠራ ስራ እያደገና እየሰፋ ሲሄድ የአካባቢ፤ አገራዊና አላማ አለማቀፋዊ ቅርጽ ሊይዝ ይችላል። ይህንን ስናነሳ ሊታወሰን የሚገባው አውሮፕላን ስለፈጠሩ ሰዎች፣ ስልክን ስለፈጠሩ ሰዎች፣ መኪናን ስለፈጠሩ ሰዎች፣ ኮምፒውተርን ስለፈጠሩ ሰዎች፣ መድኃኒትን ስለፈጠሩ ሰዎች እና ስለሚፈጥሩ ማሰቡ ብቻ የከፍተኛ ትምህርትንና የፈጠራን ስራ አንድ ላይ ለማየት ያስችላል።
• ከፍተኛ ትምህርት አገልግሎቶች ዜጎች የተደላደለ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይህም ማለት ትምህርት ድህነትን ይቀንሳል አማካኝ ገቢንም ይጨምራል:: በአጠቃላይ የተማረ ዜጋ በአማካኝ ገቢው ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ የሌሎች ዜጎች ሕይወትን የመጥቀም አስተዋጽኦ አለው።
• የከፍተኛ ትምህርት ዜጎችን በተለያዩ ዘርፍ የበለጠ ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ይረዳል።
• ከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት ስነስርዓት እና ህግ አክባሪነትን ያሳድጋል በአንዳንድ ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል ባላቸው የዓለም አገሮች በውትድርናና፣ በጥበቃ የሚያገለግል ዜጋ በጣም አነስተኛ ነው።
• የከፍተኛ ትምህርት በዜጎች መካከል ያለውን የእኩልነት ሀሳብ ያሳድጋል በተለይ የጾታ እኩልነትን ከፍ ያደርጋል።
• የከፍተኛ ትምህርት ለህብረተሰብ ጎጂ የሆኑ ባህሎችን በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ለምሳሌ ያህል ያለእድሜ ጋብቻ ልማድን ይቀንሳል።
• የተማረ ህብረተሰብ በአካባቢ የአየር ለውጥ ደህንነት(environmental changes development) ላይ አውንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል።
• የከፍተኛ ትምህርት ዜጎች ዘመናዊና በማንኛውም መልኩ ጤናማ ኑሮ (Modern society that is willing to use science) እንዲኖር ይረዳል።
• የከፍተኛ ትምህርት በራስ መተማመንንና እራስ መቻልን ያሳድጋል (develop confidence and independence)፤ እጅግም አድርጎ ያጠናክረዋል፤
• ከፍተኛ ትምህርትን መማር የመረጃን ከቦታ ወደ ቦታና በአገሮችም መካከል እንዲዘዋወርና እንዲተላለፍ አቅም ያሳድጋል (carey and transfer use full information and knowledge )
• ከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት ከሌሎች ባህሪይ የአሰራር ልምድና ባህል ተምሮ ለራስና ለሌሎች ለማስተላለፍ እንዲቻል ይጠቅማል።
• ከፍተኛ ትምህርት መማር በተለያየ መልክ ያሉ ችግሮችን የመቅረፍ ችሎታን ያሳድጋል ( problem solving skill)
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሩ ዜጎች በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ለማህበረሰብ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። በአገሮች መካከል ያለ የሀብትና የአኗኗር ልዩነት በአብዛኛው በተማሩ ዜጎች መጠን፤ ጥራትና አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም በርካታ ጥቅሞች ለዜጎች ይሰጣል። ይህን ካልን ለመረጃነት ዜጎቻቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያስተማሩ ጥቂት አገራትን ከላይ ከጠቀስኩት ጥቅሞች ጋር በማጣጣም በመረጃነት የሚከተሉትን ሰንጠረዦች መመርመር እንችላለን።
ጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር)
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2015