ችግሮች እስካሉ ድረስ መፍትሄዎች ሁሌም አሉ። መፍትሄዎቻችን ዋጋ እንዲያመጡልን ግን ከችግሮቻችን መላቅ አለባቸው። ከችግሩ ያልበለጠ ሀሳብ፣ ያልበለጠ እውቀት ዋጋ አይኖረውም። ጨለማ በብርሀን እንደሚሸነፍ ሁሉ ችግሮቻችንም በመፍትሄዎቻችን የሚሸነፉ ናቸው። ከችግሮቻችን ለመላቅና መፍትሄ ለማምጣት መጀመሪያ የችግሮቻችንን መነሻ ምንጭ ማወቅ አለብን። አሁን ላይ ያሉብንን ሀገራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ከመነጋገራችን በፊት የችግሮቻችንን መነሻ ምክንያት መረዳት ይኖርብናል።
ብርሀን የመልካም ነገር መገኛ ነው ፤በተቃራኒው ጨለማ ደግሞ የክፉ ነገር አብራክ ነው ። ችግሮቻችንን ለማሸነፍ ብርሀናዊ ሀሳብና እውቀት ያስፈልጉናል። ህይወት በብርሀን ውስጥ ደስ ትላለች፣ መኖር በተስፋ ውስጥ ያጓጓል። መልካም ነገር የምንመኝ ብዙዎች ነን ግን መልካም ነገር እንዴትና የት እንደሚገኝ አናውቅም። ዝም ብለን የምንፈልግ፣ ዝም ብለን የምንመኝ ነን። እዚህ አለም ላይ ካለ ፍለጋ፣ ካለ ልፋት ዝም ብሎ የሚገኝ መልካም ነገር የለም።
የምንፈልጋቸውን የሰላምም ሆኑ የአንድነት አማራጮች እንዴት ማግኘትና እንዴት ጠብቆ ማቆየት እንዳለብን ማወቅ አለብን። አብዛኞቻችን ጨለማ ውስጥ ተቀምጠን ብርሀን የምንናፍቅ፣ ሳንሰራ መብላትን፣ ሳንለፋ መልካም ህይወትን የምንሻ ነን። ለዚህም ነው እስካሁን ድረስ በነጋልን ማለዳ ላይ ጥሩ ነገር ሳንሰራ አመሻሽ ላይ የቆምንው። ለዚህም ነው ሰላም አጠገብ ቆመን ሰላም የራቀን።
እንደ ሀገር እንደ ዜጋ የእርስ በርስ ፍቅራችንን ያወየቡ በፖለቲካ እድፍ የቆሸሹ በርካታ ትላንትናዎችን አሳልፈናል። እነዚህ ትላንትናዎች ዛሬን እንዲመሩ መፍቀድ የለብንም። የትላንት የፖለቲካም እድፎችን በእርቅና በመነጋገር ፈተን ወደ ብርሀናማ ነገ መራመድ አለብን። ሰው የሚያስብ ፍጥረት ነው..ማሰብ እውነት የሚሆነው ደግሞ በተግባር ሲገለጥ ነው። ተግባሮቻችን ነፍስ የሚዘሩት ተነጋግረን ስንስማማና የትላንት ችግሮቻችንን በእርቅ እልባት ስንሰጣቸው ነው።
ያኔ ሰውና ሀሳቡ ጥቅም መስጠት ይጀምራሉ። ሰው ለራሱም ሆነ ለሌላው ጥቅም የሚሰጠው ሀሳቡን ተጠቅሞ በጎ ነገር ሲሰራ ነው። በሀሳባችን በጎ ነገር መፍጠር ይኖርብናል። የትላንት ጨለማዎቻችን የተፈጠሩት በጎ ሀሳብ በሌለን ጭንቅላታችን ነበር። የትላንት ጨለማዎቻችን የዛሬ ብርሀናችንን እንዳይወርስብን በሃሳባችን በጎ ልንሆን ይገባል። ተነጋግረን መግባባት፣ ተነጋግረን መስማማት ይኖርብናል።
ሰው በሀሳቡ ችግሮቹን ማሸነፍ ካልቻለ፣ ጨለማዎቹን ወደ ብርሀን መቀየር ከተሳነው፣ ከወንድሞቹ ጋር ተነጋግሮ መግባባት ካልቻለ ከነውጥ ፈጣሪነት ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በሀሳቦቻችን ችግሮቻችንን መፍለጥ ጨለማዎቻችንን መግለጥ አለብን። የትላንት ችግሮቻችን፣ ነውሮቻችን ዛሬን እንዳንኖር ካደረጉን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ማሰብ እንችላለን።
ሀገራዊ ችግሮቻችን በሀገራዊ እሳቢዎቻችን የተፈጠሩ ናቸው። መፍትሄ የሚያገኙትም በሀገራዊ ተግባቦት ነው። ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ተግዳሮቶቻችን ከየትም የመጡ ሳይሆኑ እኛን ታከው፣ እኛኑ ተደግፈው ነፍስ የዘሩ ናቸው። እኚህ ችግሮቻችን እልባት እንዲያገኙ ችግር ፈጣሪ ሀሳቦቻችን ወደ መፍትሄ ፈጣሪነት መመለስ አለባቸው። በትችት፣ በወቀሳ፣ በእርግማንና በአሉባልታ ያለፈ ጊዜአችን ሀገር ወደመጥቀም፣ ለሀገር ወደመልፋት መዞር አለበት።
እኛ ለራሳችን በቂዎች ነን። መነጋገር ከቻልን ብዙ ሀሳብ፣ ብዙ እውቀት ያለን ህዝቦች ነን። ሀገራችን ተስፋ በጣለችበት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮቻችንን ማሸነፍ እንችላለን። ጨለማዎቻችንን ወደ ብርሀን መለወጥ ይቻለናል። ትላንት ምንም ይሁን እኛ ለአንድነትና ተነጋግሮ ለመስማማት ከበረታን ችግሮቻችን አይበልጡንም። ችግሮቻችን እየበለጡን ያሉት እኛ ከችግሮቻችን ስላነስን ነው። እስከዛሬ ዝቅ ያልነው ከፍ የሚያደርግ የአንድነት ሀሳብ አጥተን ስለኖርን ነው። ከችግሮቻችን ስላነስን ነው።
ዘመኑ የስልጣኔና የአንድነት ነው። በሀሳባችን ሌሎችን ማሸነፍ ካልቻልን ሌሎችን ልናሸንፍበት የምንችልበት ምንም እድል የለንም። ለራሳችንም ሆነች በብዙ ነገሯ ለተራቆተችው ሀገራችን የሚበጃት ዘመኑን የዋጀ ሀሳብና ተግባቦት ነው። በዚህ ዘመን ላይ ተፈጥረን በጋራ ጉዳያችን ላይ በጋራ ተነጋግረን ካልተግባባን የሌሎች መሳቂያ ከመሆን ውጪ ምንም አናተርፍም። ራሳችንን መፍጠር አለብን..በሀሳባችን፣ በአንድነታችን የተሰፈረ ጸጋችንን፣ የተሰወረ ክብራችንን ማግኘት አለብን።
ሰው ተነጋግሮ ካልተግባባ ሰውነቱ እዛ ጋ ያበቃና አውሬ መሆን ይጀምራል። ከአውሬነት የሚያወጣን ሀሳብ ብቻ ነው። ሀሳብ ስላችሁ ግን ተነጋግሮ በማሸነፍና ተግባብቶ በመሸነፍ ውስጥ ያለውን ሀሳብ ማለቴ ነው። እንዲህ ካልሆነ ሰውነት ምንም ነው። ተነጋግሮ መስማማት ከምንምነት መውጫ መንገዳችን ነው። የዘመናት የእምነታችን ሚስጢር ሀሳብ ማጣታችን ሳይሆን ላለመስማማትና ላለመሸነፍ መነጋገራችን ነው። ሰው የሚነጋገረው በተሻለ ሀሳብ ችግሮቹን ለማሸነፍ። በተሻለ ሀሳብ መፍትሄ ለማምጣት፣ በተሻለ ምክረ ሀሳብ ወደፊት ለመራመድ ነው። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ ሌላ እምነትን በራስ ላይ ከማከል ውጪ የሚፈጠር ተዐምር የለም።
ትላንትን እንርሳው..ወደሚያግባባን አንድ ወደሚያደርገን የጋራ እውነት እናምራ። ባለመነጋገር የፈጠርናቸው ጨለማዎች ዛሬ እንዲያበቁ አስታራቂ ሀሳቦችን እናዋጣ። ችግር ከመፍጠር ወደመፍትሄ አመንጪነት እንሸጋገር። በጋራ ሀሳብ የጋራ ህልም እንትለም። ወደ ነገ..ወደ አዲስ ቀን፣ ወደ ተሻለ ከፍታ ሊያራምደን በሚችል ጉዳይ ላይ ጊዜና እውቀታችንን እንገበር። ትላንት ላይ በእውቀት..በአስተሳሰብ የተሻልን ብንሆን ኖሮ ዛሬ ላይ እነዚህ ሁሉ ስቃዮቻችን ባልነበሩ ነበር። ስቃዮቻችንን በእርቅ እንግደላቸው።
ጉስቁልናዎቻችንን በምክረ ሀሳብ እናሸንፋቸው። ሁሉንም ሞክረው የቀረን መግባባት ነው..መስማት ነው። እስኪ እንስማማና ያልደረስንበትን ከፍታ እንድረስበት። የማንፈልገው ነገ እንዳይፈጠር በምንፈልገው ዛሬ ላይ መሆናችንን ልብ ልንል ይገባል። የማትፈልጉት ነገ እንዳይፈጠር በምትፈልጉትና በሚያስፈልጋችሁ ዛሬ ላይ መሆናችሁን ልብ በሉ። ዛሬ የእኔና የእናንተ የትላንት መልክ ነው..አስተሳሰባችን ነው የፈጠረው። ነጋችን የተሻለ እንዲሆን ከትላንቱ የተሻለ ሀሳብ፣ እውቀት፣ ተግባቦት ያስፈልገናል።
የህይወታችን ብሎን የሀገራችን አናጺዎች እኛ ነን። ትውልዱ የሚገነባው ዛሬ እኛ በምንሆነው መሆን ነው። ለምንም ነገር መልካም ልብ ያስፈልገናል። መልካም ልብ በውስጡ ነውር የለውም። ሰውነታችንን የሚፈጥሩት ልቦቻችን ናቸው። መልካም ልብ ካለን ያለጥርጥር መልካም ዜጋ መሆን እንችላለን። መልካም ዜጋ ደግሞ መገለጫው ፍቅርና አንድነት ነው። እናም ልቦቻችንን ለበጎ ሀሳብ እናስገዛ።
ከፊታችን ያሉ ሀገራዊም ሆኑ ግለሰባዊ ተስፋዎች አብበው የሚለመልሙት በእኛ ልብ ላይ በእኛ ሀሳብ ተዘርተው ነው። ልቦቻችን ጭንጫ ከሆኑ..ሀሳቦቻችን ጭንጋፍ ከሆኑ መልካም ዘር አያበቅሉም። መልካም ፍሬ አይሰጡንም። ልባችን ሰላሳና ስልሳ መቶም የምናፈራበት ማሳችን ነው። ሀሳባችን ደግሞ ዘር። በልባችን ማሳ ላይ መልካም ፍሬ እንድንበላ በመልካም ልብ ውስጥ የበቀለ መልካም ሀሳብ ያስፈልገናል። የሚጠቅመን ይሄ ነው..በመልካም መሬት ላይ መልካም ዘርን መዝራት። ዛሬ ላይ እያሰቃዩን ያሉት በአዳፋ ልብ ላይ በአዳፋ ሀሳቦቻችን የዘራናቸው ዘሮች ናቸው። እኚህ እኩይ ዘሮች እንዲደርቁ..እንዲጠወልጉ ሀሳብ ያስፈልጋል..የእርቅና የተግባቦት ሀሳብ።
ማንም ገሎን አያውቅም..ማንም ክፉ ሆኖብን አያውቅም። ማንም አጠገባችን ደርሶ አያውቅም ችግሮቻችን ሁሉ ሀገር በቀል ናቸው..በክፉ ልብ ላይ በክፉ ሀሳብ የተዘሩ። ላለመግባባት እየተሰበሰብን፣ ላለመስማማት እየተነጋገረን እንዴት ነው ሀገርና ህዝብ የምንገነባው? እንዴት ነው ከጥላቻና ከመገፋፋት የምንወጣው? እንዴት ነው ከህልማችንና ከተስፋችን ወደብ የምንደርሰው? መጀመሪያ ልቦቻችንን መልካም እናድርግ ። የትም መቼም የህይወታችን አድማቂዎችም አደብዛዦችም እኛ ነን። ከእኛ ውጪ እኛን ሊረዳ፣ እኛን ሊታደግ፣ ከጨለማ ሊያወጣን የሚችል ሀይል የለም።
ሀይላችን ያለው መግባባታችን ውስጥ ነው። ህልምና ራዕዮቻችን የተቀመጡት በመስማማታችን ውስጥ ነው። መልካም ነገ እንዲኖረን መልካም ዛሬ ያስፈልገናል። ነገ እኮ በዛሬ አስተሳሰብ፣ በዛሬ ብርሀን የሚፈጠር እንጂ እንዲያው ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን ተስፋ የምናደርገው ነገር አይደለም። ከዚህ ውጪ ሌላ ሰዋዊም ሆነ አምላካዊ ቀመር የለም። ተፈጥሮ በእኛ ቁጥጥር ስር ነው። በተፈጥሮ ላይ የበላይ ሆነን ነው ወደዚህ አለም የመጣነው። በአስተሳሰባችን መልካሞች ከሆንን የሚያሸንፈን ምንም ነገር የለም የውድቀታችን..የተስፋቢስነታችን መነሻም መድረሻም በውስጣችን አዎንታዊ አስተሳሰብ አለመኖር የፈጠረው ነው።
ይሄ አለም በአምላክ አስተሳሰብ ተፈጥሮአል በእኛ አስተሳሰብ ይቀጥላል። ብዙ ነገዎች ብዙ ዘላለማት ከፊታችን አሉ። እልፍ ንጋቶች እልፍ ምሽቶች ይጠብቁናል። ሁሉም ነገር በእኛ ቁጥጥር ስር ነው በጨለማ እየኖርን የምንፈጥረው ብርሀናማ ነገ የለም። በቁጭትና በጸጸት እየኖርን አዲስነትን መላበስ አይቻለንም። ተነጋግረን መስማማት ከቻልን አሁኑኑ ተዐምራቶቻችንን መፍጠር እንችላለን። ተምረን የከሰርንው፣ ሀይልና ጉልበት እያለን ጠባቂ የሆነው፣ ውድ ጊዜአችንን በከንቱ የምናሳልፈው በውስጣችን ለለውጥ የሚሆን ተነሳሽነት ስለሌለን ነው።
በማሰብ..በማሰላሰል፣ በእርቅና በተግባቦት በበላጭ እውነት ከጨለማ እስካልወጣን ድረስ ሀገራችንም ሆነ ህዝባችን መልካም ነገን ማየት አይቻለውም። በፍቅርና በአንድነት ተዐምራችንን መፍጠር ካልቻልን ተአምር የሚፈጥርልን ማንም ሀይል የለም። የተዐምራት ሀይል ያለው በፍቅርና በአንድነት ሀይል ውስጥ ነው። በመነጋገርና በመስማማት ውስጥ ነው። የፈጣሪ አይኖች እንኳን በልበ ብርሀኖች ላይ ናቸው። ለራሳችን፣ ለክብራችን፣ ለሀገራችን፣ ለሚመጣው ጊዜ ዋጋ ካልሰጠን ጨለማ ውስጥ ለመኖር ፈቅደናል ማለት ነው።
ትላንትን በመድገም፣ ካለመፍትሄ ችግሮቻችንን ብቻ እየመላለስን በመነጋገር የሚመጣ ለውጥ..የሚመጣ ብርሀን የለም። ብርሀን ከጨለማ ቀጥሎ የሚመጣ ነው..ብርሀን እንዲመጣ ጨለማ ገለል ማለት አለበት። ባልተኖረ ዛሬ፣ ተስፋቢስ በሆነ አሁን ላይ ቆመን ታላቅ ነገን መገንባት አንችልም። ሀሳቦቻችንን እንባርክ..ለብርሀናችን ጨለማዊ አስተሳሰባችንን ገለል እናድርግለት። አለም ያስደነቀንና እያስደነቀን ያለው በተግባቦት ሀሳብ ነው። አለም ላይ ካለአንድነትና ካለተግባቦት ሀሳብ የሆነ የለም።
ሀሳብ ከአንድ ሰው ሊነሳ ይችላል ያ ሃሳብ ዋጋ እንዲያገኝ ግን በዙሪያው በርካታ ሀሳቦች ሊከቡት ይገባል። እኛ ሀገር ይሄ እውነት የለም..ስብሰባ የምንቀመጠው ተነጋግረን ለመግባባት ሳይሆን ተነጋግረን ለመለያየት ነው፣ ተነጋግረን የበላይነታችንን ለማሳየት ነው። ይሄ አስተሳሰብ ነው ዛሬ ላይ ጨለማን የጋረጠብን። ይሄ አስተሳሰብ ነው አለም ጥሎን እንዲሄድ ያደረገው። ከድጥ ለመውጣት ብዙዎቻችንን ያስማሙ፣ ያግባቡና ይሁንታ የተቸራቸው ሀሳቦች ያስፈልጉናል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅም እስከዛሬ በራሳችንም ሆነ በሀገራችን ላይ ብዙ ስህተቶችን ሰርተናል። የነዛ ስህተቶቻችን ማብቂያ ቀን ሳይታወቅ ነውሮቻችንን አቅፈንና ደግፈን እሹሩሩ ስንል ኖረናል። አሁን ነውሮቻችንን ገለን ቀብረን የምንፈልገውን ህይወት፣ የምንፈልገውን ከፍታ የምናይበት ጊዜ እንዲሆን መበርታት አለብን። በችግሮቻችን ተበልጠን፣ ለመፍትሄ ሳይሆን ለጥፋት በርትተን የኖርንባቸው ጊዜዎች አብቅተው በእርቅና በምክክር አዲስ ተስፋን የምንሰንቅበት የመታደስ ጊዜ እንዲሆን ሀሳብ ማዋጣት አለብን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015