ባለፈው ሳምንት በተካሄደው በርሊን ማራቶን በሴቶች አሸናፊ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ ውድድሩን ያጠናቀቀችበት 2:15.37 ሰዓት የኢትዮጵያ ክብረወሰን የዓለማችንም ሦስተኛዋ የማራቶን ፈጣን አትሌት አድርጓታል። ይህች በማራቶን ውድድሮች ትልቅ ስምና ልምድ የሌላት አትሌት ያስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት ብዙዎችን ያነጋገረና ትእግስት አሰፋ ማን ናት? ብለው እንዲጠይቁ ያደረገ ነው። የዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም በዚህችው አስደናቂ አትሌት የአትሌቲክስ ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው።
ሙሉ ስሟ ትእግስት አሰፋ ተሰማ ይባላል። የተወለደችው እኤአ በ1994 መጋቢት ወር ላይ ነው። አሁን ላይ የኢትዮጵያን የማራቶን ክብረወሰን ጨብጣ የርቀቱ የዓለማችን ሦስተኛዋ ፈጣን አትሌት ለመሆን የበቃችው ትእግስት የአትሌቲክስ ሕይወትን የጀመረችው በሆለታ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በ100ና በ200 ሜትር ሩጫ ነው። በ2001 ዓም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ200፣400 ሜትርና በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ወርቅ አጥልቃለች። በወቅቱ በነበራት ውጤት ክለቦች ቢፈልጓትም እንቢ በማለት ወደ ሆለታ ተመለሰች። በ2003 ኢትዮጵያ ሻምፒዮና በድጋሚ በማሸነፍ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብን ተቀላቀለች። እኤአ 2012 በሱዳን የምስራቅ አፍሪካ ውድድር በ400 ሜትር ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። 2012 በአፍሪካ ሻምፒዮና ቤኒን ላይ በተመሳሳይ ርቀቶች ጥሩ ተፎካካሪም ነበረች።
እኤአ በ2013 በአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ8 መቶ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ትእግስት፣ ከዓመት በኋላ ሞሮኮ ማራኬሽ በተካሄደው በአዋቂዎቹ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክላ በመወዳደር 4ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። የ28 ዓመቷ ድንቅ አትሌት ባለፈው ሳምንት በማራቶን ታላቅ ስኬት ካስመዘገበችባት በርሊን ከተማ ጋር የተዋወቀችው ከ8 ዓመት በፊት ነበር። ይህም በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4ኛ ሆና ባጠናቀቀችበት ተመሳሳይ ወር በርሊን ላይ በ8 መቶ ሜትር ያሸነፈችበት አጋጣሚ ነበር።
እኤአ በ2016 የፖርትላንድ ኦሪገን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ8 መቶ ሜትር ሀገሯን ወክላ ተወዳድራለች። ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ውድድር ማለፍ አልቻለችም። በተመሳሳይ ዓመት በሪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ ኢትዮጵያን ወክላ ለመወዳደር ብትበቃም ከመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ማለፍ አልቻለችም። ይሁን እንጂ በማጣሪያው የውድድር ዓመቱ የራሷን ፈጣን ሰዓት በ2:00:21 አስመዝግባለች።
ትእግስት ከሪዮ ኦሊምፒክ በኋላ በትልልቅ ውድድሮች አልታየችም። ምክንያቱ ደግሞ እኤአ ከ2014 ጀምሮ የእግር ሕመም በተለይም የተረከዝ ጅማት ሕመም አጋጠማት እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ ከሕመም ጋር በመታገል ነበር ስትወዳደር የቆየችው። በወቅቱ ሐኪሞችም ‹‹ከአሁን በኋላ የትራክ ሩጫ በስፓይክ ጫማ መሮጥ አትችይም›› እንደተባለች ለኢትዮ ራነርስ ተናግራለች። የገጠማት ሕመም እየጠነከረ በመምጣቱም 2017 ሙሉ በሙሉ ከውድድር ርቃለች። በ2018 መጨረሻ ወር አንድ ውድድር ብቻ በ10 ኪሎ ሜትር ሮጣም ሁለተኛ ነበር ያጠናቀቀችው።
በ2019 ሦስት ውድድር አድርጋ በዓመቱ መጨረሻ በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን ሕመሙ እየተሰማት 68:24 ሮጣ ውድድሩን እንደጨረሰች ሕመሙ በከባድ ነበረና በሸክም ወጣች። እዛው ስፔን ወደ ሕክምና በተወሰደችበት ወቅት ነበር ሐኪሞች ሩጫን ትታ ሌላ የሥራ ዘርፍ ላይ እንድትሠማራ ምክር የለገሳት። በሌሎች የአውሮፓ አገራትም ባደረገችው ሕክምና ተመሳሳይ ምክር ነበር የተሰጣት። በሰላም ለውድድር ከቤት የወጣችው አትሌት በሁለት ክራንች ወደ ሀገሯ ለመመለስ ተገደደች።
‹‹ዳግም እችላለሁ እሮጣለሁ›› በማለት በእምነት በፅናት የቆመችው አትሌት ከወራት በኋላ እያገገመች መጣች። 2021 አጋማሽ በኋላም ክራንቿን ጥላ ወደ ልምምድ ለመመለስ በቃች። 3 የ10 ኪሎ ሜትር ውድድርም አድርጋ ሶስቱንም አሸነፈች። በሁለት ግማሽ ማራቶን ውድድሮችም ድል ቀናት።
ዛሬ ላይ በማራቶን ገናና ስም ያተረፈችበትን የማራቶን ውድድር ግን መሮጥ የጀመረችው ባለፈው መጋቢት ነበር። በሳውዲ ዓረቢያ መዲና ሪያድ ማራቶን ከወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ውድድሯን ያደረገችው ትእግስት በ2:34:01 ሰዓት ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው።
ከግማሽ ማራቶን የመጀመሪያ ድሏ በኋላ ድምጿን አጥፍታ ባለፉት ጥቂት ወራት ጠንካራ ዝግጅት ስታደርግ የቆየችው ይህች ድንቅ አትሌት በበርሊን ማራቶን ሦስተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት አስመዝግባ ታሸንፋለች ብሎ የጠበቀ አልነበረም። በተለይም የበርሊን ማራቶን በርቀቱ ገና ሁለተኛ ውድድሯ እንደመሆኑ ካላት ትንሽ ልምድና በመጀመሪያ ውድድሯ ካስመዘገበችው ደካማ ሰዓት አኳያ እንኳን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ለጠንካራ ተፎካካሪነትም ያጫት አልነበረም።
በዓለም ታላላቅ ከሚባሉ የማራቶን ውድድሮች አንዱና ዋነኛው በሆነው የበርሊን ማራቶን በወንዶች በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች ቢሰበሩም በሴቶች ረገድ ያለው ታሪክ ተቃራኒ ነው። ማንም ያልጠበቃት ኢትዮጵያዊት አትሌት ግን 2:15:37 ሰዓት በማጠናቀቅ በአንድ ውድድር ሦስት የተለያዩ ክብረወሰኖችን መጨበጥ ቻለች። አንዱ የውድድሩን ክብረወሰን ከሁለት ደቂቃ በላይ ያሻሻለችበት ሲሆን ሌላኛው የኢትዮጵያ የማራቶን ክብረወሰን የጨበጠችበት ነው፣ ቀሪው ደግሞ በታሪክ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችበት ነው።
ትእግስት በዚህ ውድድር ቀድሞ በማራቶን ካስመዘገበችው ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ያላነሰ መሻሻል ማሳየቷ ለማመን የሚከብድ ነው። ይህም በማራቶን ታሪክ ከኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌና ከእንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ቀጥላ ስሟ እንዲጠራ አድርጓታል። ከዚህች ኢትዮጵያዊት አትሌት የተሻለ የማራቶን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡት ኮስጌ በ2019 የቺካጎ ማራቶን 2፡14፡14 ሲሆን የራድክሊፍ 2፡15፡25 የተመዘገበው እኤአ በ2003 ለንደን ማራቶን ላይ ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2015