አንዳንዴ መጥፎና ዘግናኝ ድርጊት ፈጻሚዎችን አግኝቼ አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ።ጥያቄዬም አሰቃቂ ወንጀል ለመፈጸም አንጀታችሁ እንዴት ቻለ? የሚል ነው። በተለይም ህፃናት ላይ እጃቸውን የሚያነሱትን በምን ቃል እንደምገልፃቸው ግራ ግብት ይለኛል። በህጻናት ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ምን ዓይነት አእምሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው? ምን አይነት ስነ ልቦና ቢኖራቸውስ ነው ወደ እርምጃ የሚገቡት? ምንስ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ቢያድጉ ነው? ምን አይነት ሞራል ያላቸው ይሆኑ እልና ጤነኞችስ ናቸው ስል እጠይቃለሁ? ብቻ ሁሉም በህጻናት ላይ የሚፈጸም ድርጊት ከአዕምሮ በላይ ነው።
ህጻናት የአካል ዕድገታቸው የአእምሮ ብስለታቸው በደንብ ያልዳበረ፤ በቀላሉ ሰዎችን የማመንና የመታለል ባህሪ ያላቸውና መሰረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላ በትልልቅ ሰዎች ላይ ጥገኛ የሆኑ ናቸው።ታዲያ ምነት ጥለውብን በንጹህ ልቦናቸው የተጠጉንን ህጻናት ምን ሲባል ለማጠቃት ልብ ይነሳሳል? እንዴት ነው የህፃንነት ጠረናቸው ከላያቸው ሳይጠፋ፣ ኮልተፋ አንደበታቸው በደንብ ሳይፈታ ለእኩይ ምግባር መፈፀሚያ የሚሆኑት? ይህ ሁኔታ ከልክ በላይ ግራ ያጋባል። የዛሬ ባለታሪካችን ህፃን ፅናት ትባላለች። የዚህችን ልጅ ታሪክ ልነግራችሁ ስለወደድኩ ነው የጥያቄ ጋጋታ ማብዛቴ። ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
የትንሿ ፅናት እናት
የፅናት እናት ወጣት ናት፤ ያውም አፍላ ወጣት በሚባል የእድሜ ክልል የምትገኝ። በኑሮ ዝቅተኛ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኘች ልጅ ናት። እናት አባቷን ጨምሮ አራቱ ታላላቆቿ በቀን ያገኙትን ለመስራት ተፍ ተፍ ሲሉ ይውላሉ። ለቤተሰቧ አምስተኛ ልጅ የሆነችው የፅናት እናትም ገና ባልጠና ጉልበቷ ነበር ራሷን ለመርዳት ቆሎ መሸጥ የጀመረችው። በየጠጅ ቤቱና በየግሮሰሪው በምሽት እየተዘዋወረች ቆሎ በመሸጥ ራሷንም ሆነ ቤተሰቧን ለመደጎም ትጥራለች።
ቀላ ያለች ናት፤ ሰውነቷ ከሳ ያለ ቢሆንም ቆንጆ መሆኗን ተክለ ሰውነቷ ይመሰክራል። ያችን እንቡጥ ጽጌረዳን እንኳን መጠጥ ቤት ያያትን ይቅርና የአላፊ እግዳሚውን አይን ጭምር ታማልላለች።ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ግሮሰሪው ውስጥ ቁጭ ብሎ የሚጠጣ አንድ ጎልማሳ አይን ውስጥ ገባች። ቆሎ ከገዛት በኋላ ያለሰበችውን ለእሷ ብዙ ብር አስጨብጦ ሸኛት።
ባልታሰበው ልግስና የተደሰተችው የፅናት እናት የያዘችውንም ቆሎ ሳትጨርስ ነበር ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ነገር ገዛዝታ ወደ ቤቷ የገባችው። ከዛ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ግሮሰሪው እየሄደች ቆሎ ትሸጥና ከለመደችው የተሻለ ገቢ እያገኘች ትመለሳለች።
እንዲህ እንዲህ እያለ የተወሰነ ጊዜ የመጠጥ ቤቱ ሰውዬ የፅናት እናትን ካላመዳት በኋላ አብራው ተቀምጣ መጠጥ እንድትጠጣ ይጋብዛታል። ከዛ ቀን በፊት አልኮል ቀምሳ ባታውቅም ያንን ደግ ሰው ላለማስቀየም ስትል መቀማመስ ጀመረች ። ቀምሳ የማታውቀው አልኮልና በቅጡ ጠግቦ የማያውቀው ሆዷ ባዶነት ተደምሮ የፅናትን እናት ለመጣል ብዙም አልፈጀበትም ወዲያው ሰክራ ዝልፍልፍ አለች። እያደባ ቀን ሲጠብቅ የነበረው አጥማጅ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደ መኝታ ክፍል ይዟት ገባ። ያኔ ነው እንግዲህ ይህች የሁሉ ልጅ የሆነችው ፅናት የተፈጠረችው።
ከሆነው ነገር በኋላ ያንን ሰው ዳግም በአካባቢው ያየው ሰው አልነበረም። ብታጠያይቅም ከስሙ በስተቀር ምንም አይነት አድራሻ ያልነበራት የፅናት እናት በፍለጋ ላይ ሆና ቀናት በቀናት ላይ እየተደራረቡ ሶስት ወር ተቆጠረ። የፅናት እናት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ያማት ጀመር። ሆዴን አሞኝ ነው በሚል በአቅራቢያዋ ያለ አንድ ጤና ጣቢያ ስትመረመር የሶስት ወር ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች። የወጣቷን ማርገዝ የሰሙት ቤተሰቦቿ ክብራችን ተነካ፤ አዋረደችን ብለው ከቤት ሲያባርሯት የሚያውቋት ሰዎች ሰብስበው በሰጧት ትንሽ ገንዘብ አሁን የምትኖረበትን ቤት ተከራየች።
አቅሟ እስከደከመ ድረስ ቆሎ እየሸጠች ወሯ ሲሞላ ፅናትን ወለደች፤ አራስነቷን በጎረቤቶቿ ድጋፍ አልፋ ልክ ጉልበቷ ሲጠና ዳግም ወደ ለመደችው ስራ ልጇን አዝላ ተመለሰች። ፅናት ከጀርባዋ ከወረደች ቀን አንስቶ ግን ጎረቤቶቿ ግማሹ አልባሽ፤ ገሚሱ አጉራሽ ሆኗት አንድም ቀን ስለልጇ ስጋት ሳይገባት ፅናት አምስት አመት ሞላት።
ተወዳጇ ፅናት
ድንቡሽቡሽ ያለች ደስ የምትል ህፃን ናት። ከመጣው ከሄደው ጋር መለጠፍ የምትወድ ሁሉ ዘመዴ የሆነች ልጅ ናት። አንዱ አቅፎ ወስዶ ከረሜላ ገዝቶ ይመልሳታል። ሌላኛዋ ወስዳ ገላዋን አጥባ ፀጉራን ሰራርታ አሳምራ ትመልሳለች። ብቻ እዛው ሰፈር ውስጥ ድክ ድክ ትበል እንጂ ለማያውቃት ሰው የየትኛው ቤት ልጅ እንደሆነች በቅጡ መለየት ይከብደዋል።
ፅናት አራት አመት እንደሞላት በአቅራቢያዋ ያለ የመንግስት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ከጀመረች በኋላ የፅናት እናት ሰው አስቸገርኩ የሚለው ሀሳቧ ቀለል ብሎላታል። ቦርሳዋን አንግታ የግቢውን ሰው በሙሉ ተሰናብታ ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድ እናቷ ልብስ አጠባውንም የጉልበት ስራውንም ስትሰራራ ቆይታ ልጇን አምጥታ ግቢ ውስጥ ታስቀምጣታለች።ከዚያ በኋላ ቆሎ ለመሸጥ ትወጣና እስክትጨርስ አምሽታ ትመለሳለች።
ፅናትም ያገኘችው ቤት አምሽታ ከሰጧት በልታ እዛው ተኝታ ታገኛት ነበር። አንዲት የተረገመች ቀን ግን ይህንን እንድታደርግ አልፈቀደላትም። ያስጠጋኛል፤ ይደግፈኛል ያለችው ጎረቤት ልጅነቷን አስጣላት።
ክፉ አድራጊው ሰው
ብዙዎቻችን በህጻናት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ብለን የምንጠረጥራቸው ሰዎች መጠጥ በብዛት የሚጠጡ፤ የሚያጨሱ፤ በህጻንነታቸው ጥቃት የደረሰባቸው እና አፈንጋጭ የወሲብ ባህሪይ ያላቸውን ሰዎች ብቻ ናቸው ብለን እንገምታለን ።ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ ህጻናት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ አይችሉም ብለን የምናስባቸው ሰዎች በልጆች ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ልናገኛቸው እንችላለን።
ይህ ሰው ከየትኞቹ አይነት ሰዎች እንደሚመደብ ግራ ቢገባም ይህችን አንደ አባቷ አባባ የምትለውን ህፃን በክፉ አይን ሊመለከታት ችሏል። ባለትዳርና የልጆች አባት የሆነው አቶ ወልደሚካኤል አሚጋ ይህችን የአምስት አመት ህፃን የሚንከባከባት መስሎ ጥቃት ያደርስበታል።
የጭካኔው ሰይፍ
ሚያዚያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 12፡30 እስከ 3፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ደብረ-አባይ ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ዕድሜዋ 5 ዓመት የሆናትን ህፃን እጇን ይዞ ነው የሄደው። ሁልጊዜ እጇን ይዞ ሱቅ በመሄድ ዳቦም ብስኩትም ይገዛላት ስለነበረ የህፃን ልቧ ስለሚገዛላት ነገር እያሰበ ከሰሩ ድክ ድክ እያለች ተከተለችው።
ሱቁን አልፈውት ሲሄዱ በጥያቄ መልክ ቀና ብላ እየተቁለጨለጨች ‹‹አባባ ይሄው ሹቁ…›› አለችው። ‹‹ኦ ረሳሁት እኮ…›› በማለት ሎሊፖፕ ከገዛላት በኋላ ‹‹ነይ አንድ ቦታ ደርሰን እንመለሳለን›› በማለት ይዟት የታጠረ ባዶ ቦታ በመውሰድ መሬት ላይ በጀርባዋ አስተኝቶ ድርጊቱን ፈፅሟል።
ምንም ጉዳዩ ያልገባት ህፃን ሰውየው የሚያደ ርገውን ከመመልከት በስተቀር ምንም እንቅስቃሴ አላደረገችም። የልጅ ገላዋን ባላሰበችው ሁኔታ የሚሰነጥቅ የህመም ስሜት ሲሰማት ከማልቀስ በላይ በሆነው ስቃይ ውስጥ ደክሟት ራሷን ሳተች። ጨካኙም ሰው አባባ እያለች የተከተለችውን ህፃን ላይ የጭካኔ እርምጃውን ከመፈጸም አልተቆጠበም። ልቡም አርራራም ሰውነቱም አልታዘዝ አላለውም። እና ለዘላለም የማይረሳ የአካልም የስነ ልቡናም ጥቃት ፈጸመ።
የ5 አመቷን ህጻን የደፈረው ግለሰብ ይህ ድርጊቱ ይጋለጥ ሲለው ለመፀዳዳት ወደ ታጠረው አጥር ውስጥ የገቡ ወይዘሮ ይመለከቱታል። ድምፃቸውን በማጥፋትም የተወሰኑ የአካባቢውን ሰዎች በመጥራት እንዳያመልጥ እየጠበቁ ፖሊስ በማምጣት በቁጥጥር ስር እንዲውል ያደርጉታል። ፖሊስም እጅ ከፍንጅ የያዘውን ተከሳሽ ወደ ህግ ቦታ ህፃኗንም ወደ ጤና ተቋም ይልካል።
ምክር ለወላጆች
ኢንስፔክተር ተሻለ አየነው በህፃናት ላይ የሚከሰት ጥቃት ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን አንስተዋል። ይህንን ለመከላከል እንዲቻልም ወላጆች ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ያሉትን ለግሰዋል። ወላጆች በቤት ውስጥ ህጻናትን ብቻቸውን ትተው አለመውጣት፤ ህጻናት ልጆችን በቤት ውስጥ ከማን ጋር ትተን እንደሚወጡ ማወቅ፤ ከህጻናት ጋር በግልጽ መወያየት፤ ህጻናት ራሳቸውን የሚከላከሉባቸውን ዘዴዎች ማስተማር፤ በትምህርት ቤት ስለ ስርዓተ ፆታ ማስተማር፣ ልጆች ራሳቸውን የሚከላከሉባቸውን ዘዴዎች ማሳወቅ እንዲሁም ማኅበረሰቡን ስለ ስነ-ፆታና ወሲባዊ ትንኮሳ ማስተማር ያስፈልጋል። የስርአተ ፆታ ትምህርቶችን፣ በህጻናትና በልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ጭምር በማሳየት መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ማስተማር፣ ስልጠና መስጠት ብሎም ወርክሾፕ ከተቋማት ጋር በትብብር መስራት ችግሮችን ለማቃለል አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ይናገራሉ ።
የፖሊስ ምርመራ
በለጋ እድሜዋ በለጋ አካሏ ላይ ግፍ የተፈጸመባት ጽናት አካሏን መመለስ የህክምና እርዳታ እንድታገኝ ተደርጓል። ሆኖም ግን ድርጊቱ በአእምሮዋ ሊወጣ አልቻለም። አልፎ አልፎ የመደንገጥና የመርበትበት ሁኔታዎች እያሳየች ነበር።
የህግ የበላይነት መረጋገጥ አጥፊም መቀጣትና ለሌላውም መማሪያ መሆን አለበትና ፖሊስም የአይን ምስከሮችና የሆስፒታል የምርመራ ወረቀትን በመመልከት ወንጀለኛው ላይ ተጨማሪ ምርምራ ሲያካሂድ ቆይቶ የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናክሮና አደራጅቶ ለኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ዐቃቤ ህግ አቅርቧል።
የፖሊስን ማስረጃ ተከትሎም በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ዐቃቤ ህግ ግለሰቡ በፈፀመው በህፃናት ሴቶች ላይ የሚፈፀም የግብረ-ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ሴቶችና ህፃናት የወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ አቶ ወልደሚካኤል አሚጋ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል።
አቃቤ ህግም አራት የሰው ምስክሮችን አቅርቦ በማሰማት ተከሳሹ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ በበቂ ሁኔታ አስረድቷል። በዐቃቤ ህግ በቀረበበት ክስ እና ማስረጃ መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል። ውሳኔውንም ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጥቷል።
የውሳኔ ሀሳብ
ፍርድ ቤቱም በተከሳሹ ላይ የመጨ ረሻውን ፍርድ ለማሳለፍ በቀነ ቀጠሮ ተገኝቷል፡፡ ግራ ቀኙንም ተመልክቶ ተከሳሽ ወልደሚካኤል አሚጋን በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም