ጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር) ከጂማ እርሻ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ፣ከኦክለሆማ እስቴት ዩኒቨርስቲ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ በእርሻ ምጣኔ አግኝተዋል ።በግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ወኪልነት፣ በጂማ እርሻ ኮሌጅ በአስተማሪነት፣በክፍል ኃላፊነት፣በተማሪዎች ዲንነትና በኮሌጅ ዲንነት አገልግለዋል ። በአሜሪካን ሀገር ደግሞ በአርከንሳስ እስቴት ዩኒቨርስቲ በአስተማሪነት ሠርተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የውሃ ማማ ተብላ የሚነገርላትና የምትታወቅ ሃገር ብትሆንም ሀብቱን ተጠቅማ ሕዝቦቿን መመገብ በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት አልቻለችም። ከዚህም የተነሳ ዛሬም ቢሆን ይህንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ በምግብ እህል እራስን የመቻል ጉዳይ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ እንደሆነ ነው ፡፡ ይህንን ሀገራዊ አጀንዳ ወደ ተጨባጭ ልማት ለመለወጥ ሰፊ የሆነ ኩሬ ውሃ የማልማት /የመጠቀም/ ዘመቻ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል።
ኩሬ ማለት ውሃን ከተፈጥሯዊ ፍሰት አቅጣጫውን አስለውጦ ለሰዎች ጥቅም በሚውል መልኩ ማጠራቀም ማለት ነው፡፡ የወንዞችን ፍሰት አቅጣጫ በመግታት፣ በመለወጥና ማጠራቀሚያ በማዘጋጀት ኩሬ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጎርፍ ውሃን በተዘጋጀ ቦታ በማጠራቀምና ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ በማድረግ ለሰዎች ጥቅም ማዋል በሚቻል መልኩ ኩሬ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ጉድጓድ ተቆፍሮ የሚገኝ ውሃም የኩሬ ውሃ ሊሆን ይችላል፡፡ እጅግ በጣም ትንሽ ኩሬ ደግሞ ሰዎች በጓራቸው በተለያየ መንገድ የሚያጠራቅሙት ውሃ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የኩሬ ውሃ ማለት ሰዎች አስፈላጊ ሲሆን የሚጠቀሙበት የመጠባበቂያ ውሃ ማለት ነው። የኩሬ ውሃ እኔ ካልኩት በተለየ ሌሎች በሌላ መልኩ ሊገልጹት ይችላሉ። በአጠቃላይ ግን የኩሬ ውሃ ማለት ለተለያየ ተግባር የሚውል ለመጠባበቂያ የተጠራቀመ ውሃ ነው። በተለይ ዝናብ በሌለበት ወቅት በአጭር ጊዜ ለሚደርሱ ለማንኛቸውም ምርት ማምረቻ የሚውል ውሃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ገና ከመጀመሪያው ኩሬ ማለት ግድብ ማለት እንዳልሆነ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
ዘመቻውስ ከየት መጣ ለምንስ አስፈለገ ለምትሉት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመደበኛነት ከሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች በተጨማሪ በዘመቻ በርካታ ሥራዎችን ለረጅም ጊዜ ሲያከናውን የቆየ ሕዝብ መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቢዝማርክ ጀርመን አሜሪካንን ጨምሮ ስምንት ሀገሮች አፍሪካን ለመከፋፈል ያደረጉትን ስምምነት በዘመቻ እራሱን በመከላከል ወረራውን ያመከነ ብቸኛ ሕዝብ ነው። በምስራቅና በሰሜን በተደጋጋሚ የገጠሙንን ጦርነቶች በአሸናፊነት የተወጣናቸውም ሕዝብ ባደረገው በርካታ የዘመቻ ትብብር ነው።
ሀገርን ከመከላከል በተጨማሪ በርካታ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘመቻዎችን በጋራ ሲያከናውን ዘመናትን ያሳለፈ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጠኑ ይነስና ይለያይ እንጂ በዘመቻ መሥራት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ልማዱ ነው። በመሆኑም ሀገራዊ የኩሬ ምስረታ ጥሪና ዘመቻ ቢደረግ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የኩሬ ምሥረታ ሥራ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሊሠራ ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ አሸዋማና ውሃን መያዝ ለማይችል መሬት አካባቢ፣ በዘመቻ የሃገር ጥሪ ነውና የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ መሰሎችንና ተመሳሳይ ምርቶችን ማምረት ለሚችሉ ባለፋብሪካዎችና ተባባሪዎች ሁሉ መንግሥት የትብብር ጥሪ ቢያደርግ፣ ቢያቀነባብርና አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርግ ውሃ ለመቋጠር ችግር ያለበት አካባቢ በአብዛኛው በዝናብ ጊዜ ከሚገኝ ውሃ አነስተኛ ኩሬ በመሥራት ተጠቃሚና ባለቤት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ።
ኢትዮጵያ በዓለም በሕዝብ ቁጥር 12ኛ ስትሆን በመሬት ስፋት ደግሞ 27ኛ ነች። የሕዝቧ ብዛትም በፍጥነት እያደገ ያለችም ሃገር ናት፡፡ ስለዚህ ሕዝቧን ለመመገብ በዝናብ ብቻ የሚመረተው ምርት (ከ95% በላይ) በቂ ስለማይሆን ገበሬው በመስኖ የማምረት ጥረትን በመጨመር አጠቃላይ ምርቱንም ማሳደግ አለበት፡፡በመጪዎቹ 25 እና 50 ዓመታት ሕዝቧ በጣም ስለሚያድግ ለረጅም ጊዜ ስንከተል የቆየነውን አሠራርና አመራረት መቀየርና ማሻሻል አለብን።
ስለሆነም በመስኖና በተጠራቀመ ውሃ የእራሳችንን ምርት ማምረትና የመደጎም ልምዱን በተፋጠነ ሁኔታ በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም ጭምር ማሳደግ አለብን። የዚህን አይነት ልምድ ያላቸው አካባቢዎች በኢትዮጵያ ስለአሉን የእነሱን ተሞክሮ ሃገራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረግም ያለብን ይመስለኛል፡፡
በዓለም ካሉ ሃገሮች ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ባላት የእርሻ ወኪሎች ቁጥር ቻይና ካላት 910,000 የእርሻ ወኪሎች በመቀጠል በ108,576 የእርሻ ሠራተኞች ቁጥር ሁለተኛ ነች ( GFRAS: Global Forum for Rural Advisory Services)። በሦስተኝነት ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ሕንድ ናት፣ 90,000 የእርሻ ወኪሎች አላት። ስለዚህ በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ የተሠማራ በርካታ ሙያተኛ አለ ማለት ነው። ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ከሚመለከታቻው ጋር በመተባበር የኩሬ ዘመቻ ቢደረግና እያንዳንዱ የግብርና ሠራተኛ ከአምስት እስከ ሰባት ኩሬዎችን ቢያስተባብር ከአምስት መቶ ሺህ እስከ ሰባት መቶ ሺህ (500,000 እስከ 700,000) ኩሬዎችንና የተገደበ የውሃ ምንጮችን ወይም ክምችቶችን በዓመት ልንሠራ ወይም ልንፈጥር እንችላለን ማለት ነው።
ይህ ሊሆን አይችልም የሚል ካለ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የእርሻ ወኪሎችና ገብሬው ከተባበሩ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ ልምድና ግንዛቤ የሌለው ሰው ብቻ ነው። ምክንያቱም በበጋው ወራት የእርሻ ሠራተኞች በቂ ጊዜ አላቸውና ነው። ፍላጎት፣መሠረታዊ እቃዎች፣ተጨማሪ በጀት፣የማስተባበር፣ የማነሳሳት፣ኃላፊነትን መቀበልና ከሥራ መደብ ጋር የተቆራኘ የዘመቻ ግዴታ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆንና ክትትል በማድረግ ይህን ግብ ለሟሟላት ምንም አዳጋች ሊሆን አይችልም ብል በፍጹም ማጋነን አይሆንም።
ከላይ ለጠቀስኩት የይቻላል ድምዳሜ ያደረሰኝ በልጅነቴ የማውቃቸው የተለያዩ የአራት ሰዎች ሥራና እኔም በእርሻ ወኪልነት ሠርቼ ስለነበረ ነው። አባ ወልደየስ ፊደል ያስቆጠሩኝ መምህሬ ሲሆኑ ትንሽ 2 ሜትር ጥልቀት በ3 ሜትር ስፋት ገደማ ካለው በጓሮአቸው ከሚገኝ ኩሬ በበጋ ወራት በምንም መልኩ ጎመንና ሌላ አትክልት አይጠፋም ነበር። ወይዘሮ ሎሚ የሚባሉ የጉራጌ አገር ሴት ደግሞ በጓሮአቸው በነበራቸው በሁለት ሰባራ ጋን ከሚጠራቀም ውሃ በበጋ ወራት በምንም መልኩ ጎመንና ቃሪያ እሳቸውም አያጡም ነበር።
ሌላው አቶ ሸበላው ሲሆን እሱ ደግሞ ሁል ጊዜ ውሃ ከወንዝ በመሸከምና በማጠራቀም በበጋው ወራት ከራሱ ተርፎት በገንዘብ የሚሸጠውን ጎመን ያመርት እንደነበር አውቃለሁ። ሌላው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር በነበሩት በአቶ ታደሰ ኃይለመስቀል አስተባባሪነት የተዘረጋውና በተማሪዎችና በአካባቢ ገበሬዎች የተቆፈረው ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ እርዝመት የነበረው የቦይ ውሃ ነው። ይህ ቦይ ለአካባቢው ገበሬዎች የጓሮ አትክልት ለማምረትና ለከብቶች የውሃ መጠጫነት በጣም ይጠቅም እንደነበረና በትምህርት ቤታችንም በርካታ የአትክልት አይነቶችን እናመርትበት እንደነበረ ስለማውቅና ስለማስታውስ ነው። ከነዚህ ሁሉ ልምዶቼ በተጨማሪ በግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ወኪልነት ለአጭር ጊዜም ቢሆን የአገለገልኩ ስለነበረም ነው ይቻላል የምለው።
ኩሬዎች በየወንዙ የሚፈሰውን ውሃ በከፊል በማቆምና የጎርፍ ውሃን በማጠራቀም የሚፈጠሩ ሲሆን ትነትን በመጨመር የጠፋ ደናችንን በመተካት ለዝናብ መኖር ሊረዱ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት የመሬት ጥበትን ፈጥራል። ጥበቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው የሚሄደው። ስለዚህ ወንዞችንና ለእርሻ የማይውሉ ሸለቆዎችን ለውሃ መቋጠሪያ ብንጠቀም በርካታ ኩሬዎች በየአካባቢው ሊኖሩ ይችላሉ። ከነዚሁ በርካታ ኩሬዎች የሚተነው ውሃም እርጥበት በመፍጠር ዝናብ ለማግኘት የራሱ ሚና ሊኖረው ይችላል።
ከደን ተከላው ጎን ለእርሻ የማይውሉ ቦታዎች ላይ ውሃ ቢተኛ ከፍተኛ የሆነ ትነት ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል። የኩሬዎች በየአካባቢው መኖር ከእርሻ ምርትና ዝናብ ለማግኘት ከመጥቀም ሌላ ለዓሳ ምርት ማምረቻና ለተጨማሪ ምግብ ምንጭ ሊያገለግሉ ይችላል። ከነዚህም በላይና በተጨማሪ የበርካታ ኩሬዎች መኖር የሃገራችን ጸጋ የሆነውን የከብት እርባታን በመኖ ምርት በመደገፍ ከእንስሳት የሚገኝ ተዋጽዖን ለማሳደግ በከፍተኛ ደረጃ ሊረዳ ይችላል።
በአጠቃላይ በኩሬ የተከማቸ ውሃን የመጠቀም ልምድ የእርሻ ሰብል ምርትን ይጨምራል፣የምግብ እጥረትን ይቀንሳል፣በድርቅ ጊዜ ያለውን የምግብ ምርት ማነስ ይደጉማል፣ ለከብት መኖ ምርት ማደግ ይረዳል፣ ለአካባቢ የአየር ሁኔታም ይጠቅማል። በመሆኑም የኩሬ ዘመቻ በመጀመሪያ የሚረዳው በምግብ እራስን መደጎምን ይሆንና ከጊዜ በኋላ ደግሞ በምግብ እራስን የመቻል አቅምን ሊያጎናጽፈን ይችላል። ሰለሆነም የኩሬ ዘመቻን እውን ለማድረግ መንግሥት ፕላን አውጥቶ፣ ዘርዘር ያለ ፕሮግራም ሠርቶ፣በጀትም መድቦለት፣ የተቀናጀ የሥራ አፈጻጸምና የግምገማ ሥርዓት አውጥቶ ክትትል የተሞላበት ጥረትና ድጋፍ ያለው ሥራ ቢሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ምንም አያጠራጥርም።
ከዚህም በተጨማሪ በግልም ሆነ በጋራ ለሚሠሩ ኩሬዎች ሁሉ የየአካባቢው የእርሻ ወኪሎችና የወረዳው የአስተዳደር ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና የማስተባበር ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ጥረት ለተከታታይ ዓመታት ከተከናወነ በኢትዮጵያ የእርሻ ምርትን ማሳደግና በምግብ እራስን መቻልን ብዙም አስቸጋሪና አጠራጣሪ አይሆንም ማለት የሚቻል ይመስለኛል።
{ጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር) ከጂማ እርሻ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ፣ከኦክለሆማ እስቴት ዩኒቨርስቲ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ በእርሻ ምጣኔ ሲኖረኝ በግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ወኪልነት፣ በጂማ እርሻ ኮሌጅ በአስተማሪነት፣በክፍል ኃላፊነት፣በተማሪዎች ዲንነትና በኮሌጅ ዲንነት አገልግያለሁ። በአሜሪካን ሀገር ደግሞ በአርከንሳስ እስቴት ዩኒቨርሲቲ በአስተማሪነት ሰርቻለሁ፤}
ጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር)
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም