ቀደም ባሉ ዘመናት የፕሮፓጋንዳ መልእክቶችን ለማስተላለፍ የዜና ዘገባዎች፣ የመንግስት ሪፖርቶች፣ መጽሐፍት፣ በራሪ ጽሑፎች፣ ፊልሞች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ፖስተሮች ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበር። ዛሬ ግን የፕሮፓጋንዳ ስራዎች እላይ በተጠቀሱት የፕሮፓጋንዳ መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያዎች ብቻ የታጠረ አይደለም። የዲጂታል ዘመን ፕሮፓጋንዳ ሳቢ በሆነ አዲስ የጥበብ አገላለጽ የሚገለጽበት ዘመን አምጥቷል። እሱም ሜም ይባላል።
ሜም የሚለው ቃል ከግሪክ ‘’ሚሜማ’’ ከሚል ቃል የመጠ ሲሆን፤ ትርጉሙ “የተመሰለ” ማለት ነው:: ሜም ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በ1976 በብሪቲሽ የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት ሪቻርድ ዳውኪንስ ነው። ባዮሎጂስቱ ሜምን ያስተዋወቀው ‘’ዘ ሰልፊሽ ጂን’’ በተባለው ስራው ውስጥ ነው። ሜሞች በውጭ ሀገራት ከተለመደ የቆየ ቢሆንም በሀገራችን የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።
ሜሞች መጀመሪያ ላይ ሰዎችን ለማሳቅ እና ለማዝናናት ዓላማ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበረ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ ሜሞች የበይነመረብ ምህዳር መቆጣጠር ጀምረዋል። ከዲጂታል ዘመን ቀደም ብለው ይሰሩ እንደነበሩት የፕሮፓጋንዳ ፖስተሮች፤ ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ ሜሞች አስደናቂ እይታዎችን ከውጤታማ ተግባቦት ጋር በማጣመር የተመልካቹን አስተሳሰብ ወይም ንቃተ ህሊና የመለወጥ ዓላማ አንግበው እየተሰሩ ነው። ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ አብዛኛዎቹ ሜሞች ተቃዋሚዎችን ሰብአዊነት ለማሳጣት እና ፖለቲከኞች ያነገቧቸውን የፖለቲካ ዓላማ ግላዊ አድርገው በማቅረብ ተቀባይነት እንዳይኖረው ማድረግን ዓላማ አድርገው እየተሰራ ይገኛል።
ከዲጂታል ዘመን በፊት የተለያዩ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎችን በመጠቀም ፕሮፓጋንዳ በሚሰራበት ወቅት ትልቅ ሚና ይጫወቱ የነበሩት አብዛኛዎቹ መርሆዎች ግን ዛሬም እንደ መጠቀሚያ ዘዴዎች ለዲጂታል ዘመን በሚመጥን መልኩ ተሻሽለው ቀጥለዋል። ቀደም ባሉት ዘመናት በፕሮፓጋንዳ ውስጥ የነበሩ መርሆዎችን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፕሮፓጋንዳ በረቀቀ መንገድ እየተሰራ ነው። ስሜት መኮርኮር፣ “እኛ” ከ “ጠላት” ጋር በሚል በጎራ መክፈል፣ ቡድኖችን እንዲሁም ግለሰቦችን በስፋት መድረስ እና ፕሮፓጋንዳ መሆኑ እንዳይታወቅ በተቻለ መጠን ድብቅ ማድረግ የሚሉ መርሆዎች ዛሬም ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ህዝቦች የሚያቀራርብ እና ፍቅርን የሚሰብኩ ሜሞች ቢለመዱ የሚበረታታ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሜሞች የህዝብን ጥቅም ለማራመድ የተነደፉ እና የተቀነባበሩ የማይሆኑበት አጋጣሚ አለ። በአንጻሩ አፍራሽ ዓላማ ያነገቡ በርካታ ሜሞች ማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት እየታየ ነው።
ጽንፍ የረገጡ እና ሌሎችን አስተሳሰቦችን የመጨፍለቅ ዓላማ ያነገቡ አካላት ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተሳሳተ መረጃን ለማሰራጨት የሜም ፎርማትን እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል። ሜሞችን ለዘረኛ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ለመረዳት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ሜሞችን መመልከት ብቻ በቂ ነው።
ሀይማኖቶችን እና ብሄሮችን የሚያጠለሹ ሜሞችን መመልከት እየተለመደ ከመጠ ሰነባብቷል። ሌሎች አካላት ላይ ጥላቻ ከመስበክ ባሻገር ለዘረኛ ንቅናቄያቸው ድጋፍ ለማሰባሰብም እየተጠቀሙበት ነው። የሀገር መሪዎችን እና የህዝብ አገልጋይ ተሷሚዎችን መልካም ስብዕና ለማጠልሸት ብሎም በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት በትኩረት ይሰራል።
በጣም የሚያስፈረው ደግሞ አዲሱ የፖለቲካ ጥበብ የሜም ፎርማት ከዲጂታል ዘመን በፊት ከነበሩት የፕሮፓጋንዳ ፖስተሮች እጅግ የላቀ የመሰራጨት አቅም ያለው መሆኑ ነው። ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በፍጥነት እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው። ከዲጂታል ዘመን በፊት ፕሮፓጋንዳዎች በዋናነት በመንግስት ነበር የሚሰራው።
ዛሬ ግን በመንግስት በተለያዩ መንገዶች ከሚሰሩ ፕሮፓጋንዳዎች ይልቅ፣ ማንኛውም ሰው፣ የሀገር ውስጥም ይሁን አለማቀፋዊ፣ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች እና ግለሰቦች ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ ምልክቶችን፣ ምስሎችን እና ዲጂታል ጥበብን ተጠቅመው የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ ብዙ ተመልካቾች ጋር ማድረስ እየቻሉ ነው።
የፕሮፓጋንዳ ፖስተሮች ስለ ፖለቲካ ነክ ስነ- ጥበባት በስነ-ልቦና ላይ ስለሚያሳድሩት ተፅእኖዎች ብዙ ያስተምሩናል። ሜሞች የኢንተርኔት ባሕል የፈጠረው የሞኝ የተዝረከረከ ጨዋታ ቢመስሉም በማስታወቂያ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እና መረጃዎችን ወስደን በምናይበት ጊዜ ሜሞች የሰዎችን ንቃተ ህሊና ሊለውጡ እንደሚችሉ ያሳያሉ። አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሰዎች ከፕሮፓጋንዳ ነፃ አይደሉም። አንዴ የተሰራ ፕሮፓጋንዳ የሰዎች ህሊና ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አላቸው። ከብዙ ዓመታት በፊት የተሰሩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ አይጠፉም።
በይነመረብ የፈጠረውን እድል በመጠቀም አፍራሽ ዓላማ ያነገቡ ሜሞችን በተመሳሳይ ሰዓት ማንኛውም ሰው በጅምላ ሊያባዘው ይችላል። በደቂቃዎች ውስጥ ሚሊየኖች ጋር የመድረስ እድል አላቸው። በሜሞች አማካኝነት ከሚተላለፉ መልዕክቶች ውስጥ እውነተኛውን እና ልቦለድ ለመለየት ከባድ ነው። በተለይም ተራው ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በሜሞች አማካኝነት የሚተላለፉ መልዕክቶችን ሳያስበው የመቀበል እድሉ ከፍ ያለ ነው።
በአሁኑ ወቅት የበይነ መረብ ምህዳሩ ላይ እየተለመዱ ያሉት የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ ሜሞች የፖለቲካ ታሪካችን ቋሚ አካል ሆነው ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም የሚለውን ጊዜ የሚመልስ ይሆናል። ለጊዜው ግን የሜሞችን ያልተገመቱ ተጽዕኖዎች በግልጽ እያየን ነው። በመሆኑም መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል። በተለይም ሀይማኖት ነክ እና ብሄር ነክ ሜሞች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ ሊበጅ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም