በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ዕውቅና ካላቸው የውድድር መድረኮች መካከል የወዳጅነት ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ለረዥም ዓመታት በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታ መርሐ ግብር መሳተፍ ሳይችል የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፕሮግራሙ አካል ሆኖ የወዳጅነት ጨዋታዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሆነው እንዲቀጥሉ የሁለት ዓመት ኮንትራት ከፌዴሬሽኑ ጋር በቅርቡ የተፈራረሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ፊፋ ወቅቱን ጠብቆ በሚያከናውናቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ለመሳተፍ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በፊፋ የውድድር ፕሮግራም መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ መስከረም 13 እና 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለወዳጅነት ጨዋታዎቹ ከመረጧቸው 23 ተጫዋቾች መካከል በደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ እየተጫወተ የሚገኘው የዋልያዎቹ ወሳኝ አጥቂ አቡበከር ናስር አልተካተተም።
ያም ሆኖ ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ ለሰባት ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ያረጋገጡበት ውጤት ከትናንት በስቲያ አስመዝግበዋል። ዋልያዎቹ ከሱዳን አቻቸው ጋር በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም በቀናት ልዩነት ያደረጉትን የወዳጅነት ጨዋታ ሁለት ለሁለት በማጠናቀቅ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ አድርገዋል።
በአቋም መለኪያ ጨዋታው ዋልያዎቹ በመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥሩ ዳዋ ሆጤሳ አሁንም የቡድኑ የግብ አዳኝ መሆኑን ያስመሰከረበትን አስደናቂ ግብ ከመረብ አሳርፏል። ሌላኛዋን ግብ የመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ቸርነት ጉግሳ ማስቆጠር ችሏል። ከቀናት በፊት በመጀመሪያው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ዋልያዎቹ ከሱዳን ጋር አንድ ለአንድ ሲለያዩ ሽመልስ በቀለ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግብጽን 2ለ0 ካሸነፉ በኋላ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ በሌሎች ውድድሮች ሰባት ጨዋታዎችን አድርገው አንድም አልተሸነፉም። ከነዚህ ሰባት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፉም አራቱን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግብጽን ያሸነፉበት ጨዋታ በጉልህ የሚጠቀስ ሲሆን ደቡብ ሱዳንን እንዲሁም ሩዋንዳን በቻን ማጣሪያ 5ለ0 እንዲሁም 1ለ0 ማሸነፋቸው ይታወቃል። በአቻ ውጤት ካጠናቀቋቸው አራት ጨዋታዎች መካከል በዚሁ የቻን ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከደቡብ ሱዳንና ከሩዋንዳ ጋር 0ለ0 የተለያዩበትና ሰሞኑን ከሱዳን ጋር በሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች 1 ለ 1 እና 2 ለ 2 ያጠናቀቁበት ተጠቃሽ ናቸው።
ዋልያዎቹ ባለፉት አምስት ወራት ያለመሸነፍ ክብረወሰናቸው ጥሩ የሚባል ነው። ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ዋልያዎቹ በ2022 የውድድር ዓመት በተለይም በወዳጅነት ጨዋታዎች(የሱዳኑን ሳይጨምር) አፈጻጸማቸው መካከለኛ ደረጃ የሚሰጠው ነው። በዚህ ረገድ ሁለት ጨዋታ በማሸነፍ፣ አራት አቻ በማጠናቀቅና አራት በመሸነፍ አጠናቀዋል። ይህም የዋልያዎቹን የወዳጅነት ጨዋታዎች የማሸነፍ አፈጻጸም ሃያ በመቶ እንደሆነ ያመላክታል። በነዚህ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ በሜዳቸውም ከሜዳቸው ውጪም በሚያደርጉት ጨዋታ ያለመሸነፍ ክብረወሰናቸው ጥሩ ሊባል የሚችል ነው። ለዚህም በሜዳቸው አንድ ጨዋታ ሲያሸንፉ አንድ ብቻ ተሸንፈው ሶስት ጨዋታ አቻ የተለያዩበት ቁጥራዊ መረጃ ማሳያ ነው። ከሜዳቸው ውጪም አንድ በማሸነፍ፣ አንድ አቻ በማጠናቀቅና ሶስት በመሸነፍ አጠናቀዋል።
ዋልያዎቹ በውድድር ዓመቱ ከሱዳን ጋር ያደረጉትን ሳይጨምር በአስራ አንድ የወዳጅነት ጨዋታዎች አስራ አንድ ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፉ አስራ አራት ግቦችን ደግሞ አስተናግደዋል። በነዚህ ጨዋታዎችም በአማካኝ በስልሳ አራት ደቂቃዎች በአማካኝ አንድ ግብ ያስተናግዳሉ ማለት ነው። በእያንዳንዱ ጨዋታም በአማካኝ 1.4 ግብ ያስተናግዳሉ እንደማለት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015